በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ጊዜ አሁን ነው”

“ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ጊዜ አሁን ነው”

ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ጊዜ አሁን ነው”

“እነሆ፣ ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ጊዜ አሁን ነው። እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።”—2 ቆሮ. 6:2

1. በማንኛውም ጊዜ ልናከናውነው የሚገባው ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ሥራ የትኛው እንደሆነ ማስተዋል ያለብን ለምንድን ነው?

“ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው።” (መክ. 3:1) ሰለሞን ይህን ሲል ግብርናን፣ ጉዞን፣ ንግድን ወይም ከሌሎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግን ጨምሮ ለማንኛውም ጠቃሚ የሆነ ተግባር ይበልጥ አመቺ የሆነውን ጊዜ የመምረጥን አስፈላጊነት መግለጹ ነበር። እንደዚያም ሆኖ በማንኛውም ጊዜ ልናከናውነው የሚገባው ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ሥራ የትኛው እንደሆነ ማስተዋል አለብን። በሌላ አባባል ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡት ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ለይተን ማወቅ ይኖርብናል።

2. ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ በሚያከናውንበት ወቅት በየትኛው ጊዜ ላይ እንዳለ በሚገባ ተገንዝቦ እንደነበረ እንዴት እናውቃለን?

2 ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት በየትኛው ጊዜ ላይ እንዳለና ምን ማከናወን እንዳለበት የተሟላ ግንዛቤ ነበረው። ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡት ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ በሚገባ ያውቅ የነበረ ሲሆን ፍጻሜያቸው ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበሩት ስለ መሲሑ የተነገሩ በርካታ ትንቢቶች የሚፈጸሙበት ወቅት እንደደረሰም ተረድቶ ነበር። (1 ጴጥ. 1:11፤ ራእይ 19:10) ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን ለሰዎች ለማሳወቅ ሊያከናውነው የሚገባ ሥራ ነበረው። የመንግሥቱን እውነት በተሟላ ሁኔታ መመሥከርና በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከእሱ ጋር ተባባሪ ወራሾች የሚሆኑትን መሰብሰብ ነበረበት። በተጨማሪም እስከ ምድር ዳር ድረስ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ለሚያከናውነው የክርስቲያን ጉባኤ መሠረት መጣል ነበረበት።—ማር. 1:15

3. ኢየሱስ የጊዜውን አጣዳፊነት መገንዘቡ ምን እንዲያደርግ አነሳስቶታል?

3 ኢየሱስ የጊዜውን አጣዳፊነት መገንዘቡ የአባቱን ፈቃድ በቅንዓት ለመፈጸም እንዲነሳሳ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በእርግጥም አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ ሥራ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።” (ሉቃስ 10:2፤ ሚል. 4:5, 6) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል መጀመሪያ ላይ 12 በኋላም 70 ሰዎችን ከመረጠ በኋላ ግልጽ መመሪያዎችን በመስጠት “መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል” የሚለውን አስደሳች መልእክት እንዲሰብኩ ላካቸው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ራሱ ምን ያደርግ እንደነበር ሲገልጽ “ለአሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርቱ መመሪያ ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ በሌሎች ከተሞች ለማስተማርና ለመስበክ ሄደ” ይላል።—ማቴ. 10:5-7፤ 11:1፤ ሉቃስ 10:1

4. ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ የተከተለው በምን መንገድ ነበር?

4 ኢየሱስ ቀናተኛና ለአምላክ ያደረ በመሆን ረገድ ለተከታዮቹ በሙሉ ፍጹም ምሳሌ ትቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት አጋሮቹን “እኔ የክርስቶስን አርዓያ እንደምከተል እናንተም የእኔን አርዓያ ተከተሉ” በማለት ያሳሰባቸው ለዚህ ነው። (1 ቆሮ. 11:1) ጳውሎስ የክርስቶስን አርዓያ የተከተለው በምን መንገድ ነበር? ይህን ያደረገበት ዋነኛ መንገድ ምሥራቹን በመስበክ ረገድ አቅሙ የፈቀደለትን ሁሉ በማድረግ ነው። ጳውሎስ ለተለያዩ ጉባኤዎች በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ እንደሚከተሉት ያሉ አገላለጾችን እናገኛለን፦ “በሥራችሁ አትለግሙ፣” “ይሖዋን እንደ ባሪያ አገልግሉ፣” “ሁልጊዜ የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ” እንዲሁም “የምታደርጉትን ሁሉ . . . ለይሖዋ እንደምታደርጉት በማሰብ በሙሉ ነፍሳችሁ አድርጉት።” (ሮም 12:11፤ 1 ቆሮ. 15:58፤ ቆላ. 3:23) ጳውሎስ ወደ ደማስቆ ሲሄድ መንገድ ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተገለጠለት ወቅት የነበረውን ሁኔታ እንዲሁም ኢየሱስ በደቀ መዝሙሩ ሐናንያ አማካኝነት የተናገረውን ነገር ፈጽሞ አልረሳውም። ኢየሱስ፣ እሱን በተመለከተ “ይህ ሰው በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት ስሜን እንዲሸከም ለእኔ የተመረጠ ዕቃ [ነው]” ማለቱን ጳውሎስ ከሐናንያ ሰምቶ መሆን አለበት።—ሥራ 9:15፤ ሮም 1:1, 5፤ ገላ. 1:16

“ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ጊዜ”

5. ጳውሎስ አገልግሎቱን በቅንዓት እንዲያከናውን ያነሳሳው ምን ነበር?

5 የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ስናነብ ጳውሎስ አገልግሎቱን በድፍረትና በቅንዓት እንዳከናወነ በግልጽ እንመለከታለን። (ሥራ 13:9, 10፤ 17:16, 17፤ 18:5) ጳውሎስ የሚኖረው ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እነሆ፣ ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ጊዜ አሁን ነው። እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።” (2 ቆሮ. 6:2) ወደ ባቢሎን በግዞት ተወስደው ለነበሩት አይሁዳውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ተቀባይነት ያለው ጊዜ 537 ዓ.ዓ. ነበር። (ኢሳ. 49:8, 9) ይሁንና ጳውሎስ ከላይ ባለው ጥቅስ ላይ ስለ የትኛው ወቅት እየተናገረ ነበር? በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ጳውሎስ ምን ማለቱ እንደሆነ ለመገንዘብ ይረዳናል።

6, 7. በዘመናችን ላሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ትልቅ መብት ተሰጥቷቸዋል? ከቅቡዓኑ ጋር አብረው እየሠሩ ያሉት እነማን ናቸው?

6 ጳውሎስ ለእሱም ሆነ ለሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለተሰጣቸው ታላቅ መብት በደብዳቤው ላይ ቀደም ብሎ ገልጾ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 5:18-20ን አንብብ።) አምላክ እነዚህን ክርስቲያኖች የጠራቸው ለአንድ የተለየ ዓላማ ይኸውም ሰዎችን “ከአምላክ ጋር ታረቁ” ብለው በመለመን “የማስታረቅ አገልግሎት” እንዲፈጽሙ መሆኑን ጳውሎስ ገልጿል። ከአምላክ ጋር ማስታረቅ ሲባል ሰዎች ከእሱ ጋር የነበራቸውን ዝምድና እንዲያድሱ ወይም እርቅ እንዲፈጥሩ መርዳት ማለት ነው።

7 በኤደን ዓመፅ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ የሰው ዘር በሙሉ ከይሖዋ ርቋል ወይም ተለይቷል። (ሮም 3:10, 23) ይህ ደግሞ የሰው ልጆች በአጠቃላይ በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እንዲኖሩ በማድረግ ለሥቃይና ለሞት ዳርጓቸዋል። ጳውሎስ “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ በአንድነት ሆኖ በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን” በማለት ጽፏል። (ሮም 8:22) ይሁንና አምላክ፣ ሰዎች ወደ እሱ እንዲመለሱ ወይም ከእሱ ጋር እንዲታረቁ እያበረታታ እንዲያውም ‘እየለመነ’ ነው። ለጳውሎስም ሆነ በዚያ ዘመን ለነበሩት ቅቡዓን የእምነት አጋሮቹ በአደራ የተሰጣቸው አገልግሎት ይህ ነበር። ይህ “ተቀባይነት ያለው ጊዜ” በኢየሱስ ለሚያምኑ “የመዳን ቀን” ሊሆንላቸው ይችላል። ሁሉም የተቀቡ ክርስቲያኖች እንዲሁም ከእነሱ ጋር አብረው የሚሠሩት “ሌሎች በጎች” ሰዎች ‘ተቀባይነት ባለው ጊዜ’ እንዲጠቀሙ መጋበዛቸውን ቀጥለዋል።—ዮሐ. 10:16

8. ሰዎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ የቀረበውን ግብዣ አስገራሚ የሚያደርገው ምንድን ነው?

8 ሰዎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ የቀረበውን ግብዣ ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ የሰው ልጆች በኤደን በተነሳው ዓመፅ ምክንያት ከአምላክ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ለመበላሸቱ ተጠያቂዎቹ ራሳቸው ቢሆኑም የተፈጠረውን ሁኔታ ለማስተካከል ቅድሚያውን የወሰደው አምላክ መሆኑ ነው። (1 ዮሐ. 4:10, 19) አምላክ ሁኔታውን ለማስተካከል ምን አድርጓል? ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት መልስ ሰጥቷል፦ “አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ዓለምን ከራሱ ጋር ከማስታረቁም በላይ በደላቸውን አልቆጠረባቸውም፤ ለእኛ ደግሞ የእርቁን ቃል ሰጥቶናል።”—2 ቆሮ. 5:19፤ ኢሳ. 55:6

9. ጳውሎስ፣ አምላክ ላሳየው ምሕረት አድናቆቱን ለመግለጽ ምን አድርጓል?

9 ይሖዋ፣ ክርስቶስ ቤዛ እንዲሆን ዝግጅት በማድረግ በቤዛው ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች በደላቸው ይቅር እንዲባልላቸውና ከእሱ ጋር የነበራቸው ዝምድና እንዲታደስ ወይም እርቅ መፍጠር እንዲችሉ አጋጣሚ ከፍቷል። ከዚህም በላይ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ሰዎች አጋጣሚው ሳያመልጣቸው ከእሱ ጋር ሰላም እንዲፈጥሩ ለማሳሰብ መልእክተኞቹን ልኳል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3-6ን አንብብ።) ጳውሎስ የአምላክን ፈቃድ ስለተገነዘበና የጊዜውን አጣዳፊነት ስላስተዋለ ‘በማስታረቁ አገልግሎት’ ራሱን ሳይቆጥብ በትጋት ተካፍሏል። የይሖዋ ፈቃድ አሁንም አልተለወጠም። ዛሬም ቢሆን ሰዎች ከእሱ ጋር እንዲታረቁ እጁን ዘርግቶላቸዋል። ጳውሎስ “ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ጊዜ አሁን ነው” እንዲሁም “የመዳን ቀን አሁን ነው” በማለት የተናገረው ሐሳብ በዘመናችንም ይሠራል። ይሖዋ እንዴት ያለ መሐሪና ርኅሩኅ አምላክ ነው!—ዘፀ. 34:6, 7

“ዓላማውን እንዳትስቱ”

10. ጥንት ለኖሩትም ሆነ በዛሬው ጊዜ ላሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች “የመዳን ቀን” ምን ትርጉም አለው?

10 የአምላክ ጸጋ መገለጫ ከሆነው ከዚህ ዝግጅት በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠቀሙት “ከክርስቶስ ጋር አንድ” የሆኑት ናቸው። (2 ቆሮ. 5:17, 18) ለእነዚህ ክርስቲያኖች “የመዳን ቀን” የጀመረው በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ነው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ እነዚህ ክርስቲያኖች “የእርቁን ቃል” የማወጅ ሥራ በአደራ ተሰጥቷቸዋል። በአሁኑ ጊዜም ቅቡዓን ቀሪዎች ‘የማስታረቁን አገልግሎት’ እያከናወኑ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በተመለከተው ትንቢታዊ ራእይ ላይ የተጠቀሱት አራት መላእክት “በምድር . . . ላይ ምንም ነፋስ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት አጥብቀው” እንደያዙ እነዚህ ክርስቲያኖች ተገንዝበዋል። በመሆኑም አሁን ያለንበት ጊዜም “የመዳን ቀን” እንዲሁም “ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ጊዜ” ነው። (ራእይ 7:1-3) በዚህም የተነሳ ከ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ጀምሮ ቅቡዓን ቀሪዎች ‘የማስታረቁን አገልግሎት’ እስከ ምድር ዳር ድረስ በቅንዓት እያከናወኑ ነው።

11, 12. በ20ኛው መቶ ዘመን መግቢያ አካባቢ የነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመከሩ ወቅት እንደሚኖሩ መገንዘባቸውን ያሳዩት እንዴት ነበር? (በገጽ 15 ላይ የሚገኘውን ሥዕል ተመልከት።)

11 ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው በ20ኛው መቶ ዘመን መግቢያ አካባቢ “ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስልና የሥራ ባልደረቦቹ፣ የሚኖሩት በመከር ወቅት እንደሆነና ሰዎች ነፃነት የሚያስገኘውን ይህን እውነት መስማት እንደሚያስፈልጋቸው በጥብቅ ያምኑ ነበር።” ታዲያ ምን አደረጉ? እነዚህ ወንድሞች በመከሩ ወቅት ይኸውም ‘ይበልጥ ተቀባይነት ባለው ጊዜ’ ላይ መሆናቸውን ስለተገነዘቡ ሰዎችን ወደ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶቻቸው በመጋበዝ ብቻ ረክተው አልተቀመጡም። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ለረጅም ጊዜ እንዲህ ሲያደርጉ ቆይተዋል። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ግን ምሥራቹን የሚያሰራጩባቸው ሌሎች መንገዶችን መፈለግ ጀመሩ። ሥራቸውን ለማስፋፋት ከተጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል በወቅቱ ዘመናዊ የሚባሉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይገኙበታል።

12 አነስተኛ ቁጥር የነበራቸው እነዚህ ቀናተኛ አገልጋዮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማሰራጨት በትራክቶች፣ በበራሪ ወረቀቶች፣ በመጽሔቶችና በመጻሕፍት ይጠቀሙ ነበር። በተጨማሪም በሺዎች በሚቆጠሩ ጋዜጦች ላይ የሚታተሙ ስብከቶችንና አምዶችን ያዘጋጁ ነበር። ቅዱስ ጽሑፋዊ ፕሮግራሞችን በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ የሬዲዮ ጣቢያዎች ያስተላልፉ ነበር። የፊልም ኢንዱስትሪው ከድምፅ ጋር የተቀናጀ ተንቀሳቃሽ ምስል ለሕዝብ ማሳየት ከመጀመሩ በፊት እንኳ እነዚህ ክርስቲያኖች ከድምፅ ጋር የተቀዱ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ማዘጋጀት ጀምረው ነበር። እንዲህ ያለ የማይበርድ ቅንዓት ማሳየታቸው ምን ውጤት አስገኘ? በዛሬው ጊዜ ሰባት ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ለመልእክቱ ምላሽ የሰጡ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ከቅቡዓኑ ጋር በመተባበር “ከአምላክ ጋር ታረቁ” የሚለውን መልእክት እያወጁ ነው። በእርግጥም ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩት እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች እንቅፋት የሚሆኑባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም በቅንዓት በማገልገል ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተዋል።

13. የትኛውን የአምላክ ዓላማ ልብ ማለት ይገባናል?

13 “ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ጊዜ አሁን ነው” የሚለው የጳውሎስ አባባል ዛሬም ይሠራል። የይሖዋን ጸጋ የቀመስን ክርስቲያኖች የእርቁን መልእክት ለመስማትና ለመቀበል የሚያስችል አጋጣሚ ስለተሰጠን አመስጋኞች ነን። ይሁንና ይህን አጋጣሚ በማግኘታችን ረክተን ከመቀመጥ ይልቅ ጳውሎስ “የአምላክን ጸጋ ተቀብላችሁ ዓላማውን እንዳትስቱ እንለምናችኋለን” በማለት አክሎ የተናገረውን ሐሳብ ልብ ማለት ይኖርብናል። (2 ቆሮ. 6:1) የአምላክ ጸጋ ዓላማ “በክርስቶስ አማካኝነት ዓለምን ከራሱ ጋር [ማስታረቅ]” ነው።—2 ቆሮ. 5:19

14. በብዙ አገሮች ውስጥ ምን ዓይነት ለውጦች እየታዩ ነው?

14 ሰይጣን ያሳወራቸው አብዛኞቹ የሰው ልጆች አሁንም ከአምላክ ርቀው ያሉ ከመሆኑም ሌላ የአምላክ ጸጋ ዓላማ ምን እንደሆነ አያውቁም። (2 ቆሮ. 4:3, 4፤ 1 ዮሐ. 5:19) ይሁን እንጂ ብዙዎች፣ በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሱት መከራዎችና ክፉ ነገሮች መንስኤው ሰዎች ከአምላክ መራቃቸው መሆኑን ሲገነዘቡና የዓለም ሁኔታዎች ይበልጥ እየተባባሱ መሄዳቸውን ሲመለከቱ ለመልእክቱ ምላሽ መስጠት ጀምረዋል። አብዛኞቹ ሰዎች ለስብከቱ ሥራችን ግድ የለሽ በነበሩባቸው አገሮች ውስጥ እንኳ በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች ምሥራቹን እየተቀበሉ ሲሆን ከአምላክ ጋር ለመታረቅም እርምጃ እየወሰዱ ናቸው። እኛስ “ከአምላክ ጋር ታረቁ” የሚለውን ልመና ከምንጊዜውም በላይ በቅንዓት ለሰዎች የምናሰማበት ጊዜ አሁን መሆኑን ተገንዝበናል?

15. ሰዎች ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው የሚያደርግ መልእክት ብቻ ከመስበክ ይልቅ በሁሉም ቦታ የሚገኙ ሰዎች ምን እንዲያውቁ እንፈልጋለን?

15 ተልእኳችን ሰዎች ወደ አምላክ ከተመለሱ እሱ ችግሮቻቸውን ሁሉ እንደሚያስወግድላቸውና ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው እንደሚረዳቸው በመናገር ብቻ የተወሰነ አይደለም። ብዙዎች ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱበት ዓላማ ይህ ሲሆን አብያተ ክርስቲያናትም ይህን ፍላጎታቸውን ለማሟላት ዝግጁ ናቸው። (2 ጢሞ. 4:3, 4) የአገልግሎታችን ዓላማ ግን ይህ አይደለም። የምንሰብከው ምሥራች፣ ይሖዋ ለእኛ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ በደላችንን በክርስቶስ አማካኝነት ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ የሚገልጽ ነው። አምላክ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆኑ ሰዎች ከእሱ የራቁ መሆናቸው ቀርቶ ከአምላክ ጋር መታረቅ ይችላሉ። (ሮም 5:10፤ 8:32) ሆኖም “ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ጊዜ” የሚያበቃበት ወቅት በፍጥነት እየተቃረበ ነው።

“በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ”

16. ጳውሎስ ድፍረትና ቅንዓት እንዲያሳይ የረዳው ምንድን ነው?

16 ታዲያ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት ማዳበርና ቅንዓታችን እንዳይቀዘቅዝ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በተፈጥሯቸው ዓይናፋር ወይም ዝምተኛ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ስሜታቸውን በግልጽ መናገር ወይም ከሌሎች ጋር መግባባት ይከብዳቸው ይሆናል። ይሁንና አንድ ሰው ስሜቱን የሚገልጽ መሆኑ ብቻ ቀናተኛ እንደማያስብለው ማስታወሱ ጠቃሚ ነው፤ እንዲሁም ቅንዓት በግለሰቡ ባሕርይ ላይ የተመካ ነገር አይደለም። ጳውሎስ ለእምነት ባልደረቦቹ “በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ቅንዓት ለማዳበር ቁልፍ የሆነውን ነገር ገልጿል። (ሮም 12:11) ሐዋርያው፣ የስብከቱን ሥራ በድፍረትና በጽናት እንዲያከናውን በዋነኝነት የረዳው የይሖዋ መንፈስ ነው። ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ከጠራው ጊዜ አንስቶ ለመጨረሻ ጊዜ እስከታሰረበትና በሮም ሰማዕት ሆኖ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ይኸውም ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት ቅንዓቱ ሳይቀዘቅዝ አገልግሏል። ጳውሎስ ምንጊዜም እርዳታ የሚሻው በመንፈሱ አማካኝነት የሚያስፈልገውን ጥንካሬ ከሚሰጠው ከአምላክ ነበር። “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ” በማለት ተናግሯል። (ፊልጵ. 4:13) ከጳውሎስ ምሳሌ ትምህርት ብንወስድ በእጅጉ እንደምንጠቀም ምንም ጥርጥር የለውም!

17. ‘በመንፈስ የጋልን’ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

17 ‘መጋል’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል፣ በቀጥታ ሲተረጎም “መንተክተክ” የሚል ፍቺ አለው። (ኪንግደም ኢንተርሊንየር) ምድጃ ላይ የተጣደ ነገር እንዲንተከተክ ከተፈለገ እሳቱ መጥፋት የለበትም። በተመሳሳይም ‘በመንፈስ የጋልን’ እንድንሆን የአምላክን መንፈስ ሁልጊዜ ማግኘት ያስፈልገናል። ይህ እንዲሆን ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለማጠናከር በሚያቀርባቸው ዝግጅቶች በሙሉ መጠቀም ይኖርብናል። ይህም ሲባል የቤተሰብና የጉባኤ አምልኳችንን በቁም ነገር መመልከት ይኸውም በግልና በቤተሰብ ጥናታችን እንዲሁም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በምናደርገው ስብሰባ አዘውታሪ መሆንና ጥሩ የጸሎት ልማድ ማዳበር ማለት ነው። እንዲህ ማድረጋችን ‘በመንፈስ የጋልን’ በሌላ አባባል ‘የምንንተከተክ’ ሆነን እንድንቀጥል የሚያስፈልገንን “እሳት” ለማግኘት ያስችለናል።—የሐዋርያት ሥራ 4:20ን እና ሥራ 18:25ን አንብብ።

18. የተጠመቅን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በየትኛው ግብ ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል?

18 ሕይወቱን ለአንድ ዓላማ የወሰነ ግለሰብ ትኩረቱ ሙሉ በሙሉ ያረፈው በግቡ ላይ ነው፤ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ትኩረቱ በቀላሉ አይከፋፈልም ወይም ግቡን ከመከታተል ወደኋላ አይልም። ራሳችንን ወስነን የተጠመቅን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ግባችን ልክ እንደ ኢየሱስ፣ ይሖዋ እንድናደርግ የሚፈልገውን ማንኛውንም ነገር ማድረግ ነው። (ዕብ. 10:7) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ፈቃድ በተቻለ መጠን በጣም ብዙ ሰዎች ከእሱ ጋር እንዲታረቁ ነው። እንግዲያው የኢየሱስንና የጳውሎስን አርዓያ በመከተል በአሁኑ ወቅት ከምንም በላይ አስፈላጊ እንዲያውም አጣዳፊ የሆነውን ሥራ በቅንዓት እናከናውን!

ታስታውሳለህ?

• ለጳውሎስና ለሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአደራ የተሰጣቸው “የማስታረቅ አገልግሎት” ምንድን ነው?

• ቅቡዓን ቀሪዎች ‘ይበልጥ ተቀባይነት ያለውን ጊዜ’ በሚገባ የተጠቀሙበት እንዴት ነው?

• ክርስቲያን አገልጋዮች ‘በመንፈስ የጋሉ’ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ወደ ደማስቆ ሲሄድ ያጋጠመውን ነገር ፈጽሞ አይረሳውም