በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለይሖዋ ዘምሩ!

ለይሖዋ ዘምሩ!

ለይሖዋ ዘምሩ!

“በሕይወትም እስካለሁ ለአምላኬ እዘምራለሁ።”—መዝ. 146:2

1. ወጣቱ ዳዊት አንዳንድ መዝሙሮቹን እንዲያቀናብር ያነሳሳው ምንድን ነው?

ዳዊት ወጣት ሳለ በቤተልሔም አቅራቢያ ባሉ መስኮች ላይ የአባቱን መንጎች በመጠበቅ በርካታ ሰዓታት ያሳልፍ ነበር። ዳዊት በጎቹን በሚጠብቅበት ጊዜ የይሖዋን አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የመመልከት አጋጣሚ ነበረው፤ ለምሳሌ በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ፣ “የዱር አራዊትን” እንዲሁም “የሰማይ ወፎችን” ማየት ይችል ነበር። ዳዊት በተመለከተው ነገር ልቡ እጅግ ስለተነካ እነዚህን አስደናቂ ፍጥረታት የሠራውን ፈጣሪ ለማወደስ ስሜት ቀስቃሽ መዝሙሮችን ለማቀናበር ተነሳስቷል። ዳዊት ያቀናበራቸው አብዛኞቹ መዝሙሮች በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ። *መዝሙር 8:3, 4, 7-9ን አንብብ።

2. (ሀ) ሙዚቃ በአንድ ሰው ስሜት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል? ምሳሌ ስጥ። (ለ) ዳዊት ከይሖዋ ጋር ስለመሠረተው ዝምድና ከመዝሙር 34:7, 8 እንዲሁም ከመዝሙር 139:2-8 ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

2 ዳዊት የሙዚቃ ክህሎቱን ያዳበረው በእነዚህ ወቅቶች ሳይሆን አይቀርም። እንዲያውም ዳዊት የተዋጣለት ሙዚቀኛ ከመሆኑ የተነሳ ለንጉሥ ሳኦል በገና እንዲጫወት ተጋብዞ ነበር። (ምሳሌ 22:29) በዛሬው ጊዜ ግሩም ሙዚቃ በሰዎች ላይ ጥሩ ስሜት እንደሚፈጥረው ሁሉ ዳዊት ይጫወት የነበረው ሙዚቃም መንፈሱ የተጨነቀውን ንጉሥ ያረጋጋ ነበር። ዳዊት የሙዚቃ መሣሪያውን አንስቶ በተጫወተ ቁጥር ‘ሳኦል ይሻለው ነበር።’ (1 ሳሙ. 16:23) ፈሪሃ አምላክ ያለው ይህ ሙዚቀኛና ገጣሚ ያቀናበራቸው ሙዚቃዎች አሁንም ድረስ ተወዳጅ ናቸው። እስቲ አስበው! በዛሬው ጊዜ ማለትም ዳዊት ከሞተ 3,000 ዓመታት ካለፉ በኋላም በምድር ዙሪያ የሚኖሩና በተለያየ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽናኛና ተስፋ ለማግኘት የዳዊትን መዝሙር አዘውትረው ያነባሉ።—2 ዜና 7:6፤ መዝሙር 34:7, 8ን እና መዝሙር 139:2-8ን አንብብ፤ አሞጽ 6:5

ሙዚቃ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ያለው ከፍተኛ ቦታ

3, 4. በዳዊት ዘመን ሙዚቃ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ቦታ እንዲኖረው ምን ዝግጅት ተደረገ?

3 ዳዊት ልዩ ተሰጥኦ የነበረው ሲሆን ይህን ተሰጥኦውንም ከሁሉ በተሻለ መንገድ ማለትም ይሖዋን ለማወደስ ተጠቅሞበታል። ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ በኋላ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከሚቀርቡ አገልግሎቶች መካከል በግሩም ሁኔታ የተቀናበረ ሙዚቃ እንዲካተት አድርጎ ነበር። በቤተ መቅደስ ውስጥ ከሚያገለግሉት ሌዋውያን መካከል አንድ አሥረኛ የሚሆኑት ይኸውም ወደ 4,000 የሚጠጉት ‘ምስጋና’ እንዲያቀርቡ የተመደቡ መዘምራን ሲሆኑ ከእነሱ መካከል 288ቱ ‘ወደ ይሖዋ በሚቀርበው ዜማ የሠለጠኑና የተካኑ’ ነበሩ።—1 ዜና 23:3, 5፤ 25:7

4 ሌዋውያን የዘመሯቸውን በርካታ መዝሙሮች ያቀናበረው ዳዊት ራሱ ነው። የዳዊት መዝሙሮች ሲዘመሩ በቦታው የመገኘት አጋጣሚ የነበረው ማንኛውም እስራኤላዊ በሰማው ነገር ልቡ እንደሚነካ ምንም ጥርጥር የለውም። ከጊዜ በኋላ የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ዳዊት “በዜማ መሣሪያ ማለትም በመሰንቆ፣ በበገናና በጸናጽል እየታጀቡ የደስታ ዜማዎችን የሚያዜሙ መዘምራንን ከወንድሞቻቸው መካከል እንዲሾሙ ለሌዋውያኑ መሪዎች ነገራቸው።”—1 ዜና 15:16

5, 6. (ሀ) በዳዊት ዘመነ መንግሥት ለሙዚቃ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ለምን ነበር? (ለ) በጥንቷ እስራኤል ሙዚቃ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ይሰጠው እንደነበር እንዴት እናውቃለን?

5 በዳዊት ዘመን ለሙዚቃ ይህን ያህል ትኩረት የተሰጠው ለምን ነበር? ንጉሥ ዳዊት የተዋጣለት ሙዚቀኛ ስለነበረ ይሆን? ይህ ብቻ አልነበረም፣ ሌላም ምክንያት ነበር። ይህ ግልጽ የሆነው ጻድቅ የነበረው ንጉሥ ሕዝቅያስ ከተወሰኑ መቶ ዓመታት በኋላ በቤተ መቅደስ ውስጥ ይሰጡ የነበሩት አገልግሎቶች እንደገና እንዲከናወኑ ባደረገበት ጊዜ ነበር። ሁለተኛ 2 ዜና መዋዕል 29:25 እንዲህ ይላል፦ “ንጉሥ ሕዝቅያስም በዳዊት፣ በንጉሡ ባለ ራእይ በጋድና በነቢዩ በናታን በተሰጠው መመሪያ መሠረት ሌዋውያኑን ጸናጽል፣ በገናና መሰንቆ አስይዞ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መደባቸው፤ ይህም በነቢያት አማካይነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ነበር።”

6 አዎ፣ ይሖዋ አገልጋዮቹ በመዝሙር እንዲያወድሱት በነቢያቱ በኩል ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። እንዲያውም መዘምራኑ ሙዚቃ ለማቀናበር በተለይ ደግሞ ልምምድ ለማድረግ በቂ ጊዜ እንዲያገኙ ሲባል ሌሎች ሌዋውያን ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች ነፃ እንዲሆኑ ተደርገው ነበር።—1 ዜና 9:33

7, 8. የመንግሥቱን መዝሙሮች በምንዘምርበት ጊዜ ከችሎታ የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ምንድን ነው?

7 “የመዝሙር ነገር ከተነሳ፣ እኔ በዚያ ዘመን ብኖር ኖሮ በመገናኛው ድንኳን እንዲዘምሩ ከተመረጡት የተካኑ መዘምራን መካከል ልሆን እንደማልችል የታወቀ ነው” ትል ይሆናል። ይሁንና የተካኑ የነበሩት ሁሉም ሌዋዊ ሙዚቀኞች አይደሉም። አንደኛ 1 ዜና መዋዕል 25:8 (የ1954 ትርጉም) በቡድኑ ውስጥ ‘ተማሪዎች’ እንደነበሩም ይናገራል። በተጨማሪም ከሌሎቹ የእስራኤል ነገዶች መካከል ከሌዋውያኑ በተሻለ የመዘመር ችሎታ የነበራቸው ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሰባችን የተገባ ነው፤ ሆኖም ይሖዋ መዘምራን እንዲሆኑ የመረጠው ሌዋውያንን ነበር። ታማኝ የሆኑ ሌዋውያን በሙሉ፣ ‘የተካኑም’ ሆኑ ‘ተማሪዎች’ ከልብ በመነጨ ስሜት ለአምላካቸው ዝማሬ እንዳቀረቡ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

8 ዳዊት ሙዚቃ ይወድ የነበረ ከመሆኑም በላይ የተዋጣለት ሙዚቀኛም ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰዎች ላላቸው ችሎታ ብቻ ነው? ጳውሎስ በ⁠ቆላስይስ 3:23 ላይ “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ እንደምታደርጉት በማሰብ በሙሉ ነፍሳችሁ አድርጉት” በማለት ጽፏል። ነጥቡ ግልጽ ነው፦ ይሖዋን በምናወድስበት ጊዜ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ‘በሙሉ ነፍሳችን’ መዘመራችን ነው።

ከዳዊት ዘመን በኋላ ሙዚቃ የነበረው ቦታ

9. በሰለሞን የግዛት ዘመን ቤተ መቅደሱ በተመረቀበት ወቅት በቦታው ብትኖር ኖሮ ምን ልታይና ልትሰማ እንደምትችል ግለጽ።

9 በሰለሞን የግዛት ዘመን ሙዚቃ በንጹሕ አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። ቤተ መቅደሱ በተመረቀበት ጊዜ የመዘምራን ጓድ የተዘጋጀ ሲሆን በትንፋሽ በሚሠሩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ክፍል ውስጥ መለከት የሚነፉ 120 ሌዋውያን ተመድበው ነበር! (2 ዜና መዋዕል 5:12ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “መለከት ነፊዎችና [ሁሉም ካህናት ናቸው] ዘማሪዎችም በአንድነት አንድ ድምፅ ሆነው ለእግዚአብሔር ውዳሴና ምስጋና አቀረቡ፤ . . . ‘እርሱ ቸር ነው፣ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።’ እያሉ ዘመሩ።” ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይሖዋን በደስታ ባመሰገኑ ጊዜ “ደመናው [የይሖዋን] ቤት ሞላው።” ይህም ይሖዋ የቀረበለትን ውዳሴ እንደተቀበለ የሚያመለክት ነበር። እነዚህ ሁሉ መለከቶችና በሺህ የሚቆጠሩት ዘማሪዎች በአንድነት የሚያሰሙትን ድምፅ መስማት ምንኛ የሚያስደስት ነበር!—2 ዜና 5:13

10, 11. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሙዚቃን ለአምልኮ ይጠቀሙ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?

10 ሙዚቃ በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድም የአምልኮ ክፍል ነበር። እርግጥ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች የሚሰበሰቡት በመገናኛ ድንኳን ወይም በቤተ መቅደሶች ውስጥ ሳይሆን በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነበር። በወቅቱ በነበረው ስደትና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ የሚሰበሰቡበት ሁኔታ ያን ያህል አመቺ አልነበረም። ያም ሆኖ ክርስቲያኖች አምላክን በመዝሙር ያወድሱ ነበር።

11 ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ የሚገኙትን ክርስቲያን ወንድሞቹን “በመዝሙራት፣ ለአምላክ በሚቀርብ ውዳሴና ለዛ ባላቸው መንፈሳዊ ዝማሬዎች . . . መምከራችሁን ቀጥሉ” በማለት አሳስቧቸው ነበር። (ቆላ. 3:16) ጳውሎስና ሲላስ እስር ቤት ከገቡ በኋላ ‘መጸለይ’ የጀመሩ ሲሆን የመዝሙር መጽሐፍ ባይኖራቸውም ‘አምላክን በመዝሙር ያወድሱ’ ነበር። (ሥራ 16:25) አንተ እስር ቤት ብትገባ ኖሮ ከመንግሥቱ መዝሙሮች ውስጥ ስንቶቹን በቃልህ መዘመር ትችል ነበር?

12. ለመንግሥቱ መዝሙሮች አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

12 ሙዚቃ በአምልኳችን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው እንደመሆኑ መጠን እንደሚከተለው ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘ለመዝሙር ተገቢው አድናቆት አለኝ? በጉባኤ፣ በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ከወንድሞቼና እህቶቼ ጋር በመሆን የመክፈቻውን መዝሙር መዘመር እንድችል በጊዜ ለመገኘት የተቻለኝን ያህል እጥራለሁ? ከልብ በመነጨ ስሜትስ እዘምራለሁ? ልጆቼ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና በአገልግሎት ስብሰባ እንዲሁም በሕዝብ ንግግርና በመጠበቂያ ግንብ ጥናት መካከል የሚዘመረውን መዝሙር እግራቸውን እንደሚያፍታቱበት የእረፍት ጊዜ አይተውት ሳያስፈልግ ቦታቸውን ለቀው እንዳይሄዱ አሳስባቸዋለሁ?’ መዝሙር የአምልኮታችን ክፍል ነው። አዎ፣ መዝሙር በመዘመር ረገድ ‘የተካንም’ እንሁን ‘ተማሪዎች’ ሁላችንም ድምፃችንን አስተባብረን ይሖዋን ማወደስ እንችላለን፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ይገባናል።—ከ⁠2 ቆሮንቶስ 8:12 ጋር አወዳድር።

ጊዜው ሲለወጥ ለውጥ አስፈለገ

13, 14. በጉባኤ ስብሰባዎች ወቅት በሙሉ ልብ መዘመራችን ምን ጥቅም አለው? በምሳሌ አስረዳ።

13 ከመቶ ዓመታት በፊት የጽዮን መጠበቂያ ግንብ የመንግሥቱ መዝሙሮች በጣም አስፈላጊ የሆኑበትን አንደኛውን ምክንያት ሲገልጽ “ስለ እውነት መዘመር፣ እውነት በአምላክ ሕዝቦች አእምሮና ልብ ውስጥ እንዲሰርጽ ለማድረግ የሚያስችል ጥሩ መሣሪያ ነው” ብሏል። የአብዛኞቹ መዝሙሮቻችን ግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ቢያንስ የተወሰኑትን መዝሙሮች በቃላችን መያዛችን እውነት በልባችን ውስጥ እንዲሰርጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባዎቻችን ላይ ተገኝተው የጉባኤው አባላት ከልብ በመነጨ ስሜት የሚያቀርቡትን መዝሙር ሲሰሙ አብዛኛውን ጊዜ ልባቸው ይነካል።

14 በ1869 አንድ ምሽት ላይ ቻርልስ ቴዝ ራስል ከሥራ ወደ ቤት እየተመለሰ ሳለ በአንድ ሕንፃ ምድር ቤት ውስጥ መዝሙር ሲዘመር ሰማ። በዚያን ወቅት ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅ ፈጽሞ እንደማይቻል ተሰምቶት ተስፋ ቆርጦ ነበር። በመሆኑም ለንግድ ሥራው የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ ለማግኘት ወስኖ ነበር፤ ሰዎችን በመንፈሳዊ መርዳት ባይችልም እንኳ ገንዘብ ማግኘቱ ቢያንስ በቁሳዊ ነገሮች ለመርዳት እንደሚያስችለው ተሰምቶት ነበር። ወንድም ራስል ድምፁን ወደሰማበት ቆሻሻ ወደሆነውና ጭልምልም ወዳለው አዳራሽ ውስጥ ሲገባ ሰዎች በዚያ ሃይማኖታዊ ስብሰባ እያደረጉ ነበር። ከዚያም ቁጭ ብሎ ማዳመጥ ጀመረ። ከጊዜ በኋላ በዚያ ምሽት የሰማውን ነገር አስመልክቶ ሲጽፍ “መጽሐፍ ቅዱስ በመለኮታዊ መሪነት የተጻፈ ስለመሆኑ የነበረኝን ደካማ እምነት በአምላክ እርዳታ ለማጠናከር በቂ ነበር” ብሏል። ወንድም ራስል ወደዚያ ስብሰባ እንዲገባ ያነሳሳው መዝሙር እንደሆነ ልብ በል።

15. በመዝሙር መጽሐፋችን ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው?

15 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ባለን ግንዛቤ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎች ተደርገዋል። ምሳሌ 4:18 “የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣ ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን ነው” ይላል። እየጨመረ የሚመጣው ብርሃን ‘ስለ እውነት በምንዘምርበት’ መንገድ ላይ ማስተካከያ እንድናደርግ እንደሚያነሳሳን ምንም ጥርጥር የለውም። ላለፉት 25 ዓመታት በበርካታ አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ * የተባለውን የመዝሙር መጽሐፍ ይጠቀሙ ነበር። ይህ መጽሐፍ መታተም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ዓመታት ውስጥ በብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የበለጠ መንፈሳዊ ብርሃን አግኝተናል፤ በዚህም ምክንያት በመዝሙሮቹ ውስጥ በተጠቀሱት አንዳንድ ቃላትና ሐረጎች ላይ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ስም “ይቀደሳል” እንጂ “ትክክለኝነቱ መረጋገጥ” አያስፈልገውም። በግልጽ መመልከት እንደምንችለው በአንዳንድ መሠረታዊ ትምህርቶች ላይ ለውጦች ስለተደረጉ በመዝሙር መጽሐፋችን ላይ ማሻሻያ ማድረጋችን አስፈላጊ ነበር።

16. አዲሱ የመዝሙር መጽሐፋችን በኤፌሶን 5:19 ላይ የሚገኘውን የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው?

16 በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ የበላይ አካሉ ለይሖዋ ዘምሩ የተባለ አዲስ የመዝሙር መጽሐፍ እንዲወጣ ፈቃድ ሰጥቷል። በአዲሱ የእንግሊዝኛ መዝሙር መጽሐፍ ውስጥ 135 መዝሙሮች የሚገኙ ሲሆን አማርኛው ደግሞ 55 መዝሙሮችን ይዟል። አዳዲሶቹ መዝሙሮች ጥቂት ስለሆኑ ቢያንስ የተወሰኑትን መዝሙሮች ግጥም በቃል መያዝ አስቸጋሪ አይሆንብንም። እንዲህ ማድረጋችን ጳውሎስ በ⁠ኤፌሶን 5:19 ላይ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳናል።—ጥቅሱን አንብብ።

አድናቆትህን መግለጽ ትችላለህ

17. በጉባኤ ከመዘመር ጋር በተያያዘ የኀፍረት ስሜታችንን ለማሸነፍ ሊረዳን የሚችለው የትኛው ሐሳብ ነው?

17 የሚሰማን የኀፍረት ስሜት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ጮክ ብለን እንዳንዘምር ሊያደርገን ይገባል? እስቲ ሁኔታውን በዚህ መንገድ ተመልከተው፦ ከአንደበት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ‘ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንደምንሰናከል’ የታወቀ ነው። (ያዕ. 3:2) ያም ቢሆን በአንደበት አጠቃቀም ረገድ ፍጽምና የጎደለን መሆኑ ከቤት ወደ ቤት በማገልገል ይሖዋን እንዳናወድሰው አያግደንም። ታዲያ ድምፃችን ጥሩ አለመሆኑ አምላክን በመዝሙር እንዳናወድሰው ሊያደርገን ይገባል? ‘ለሰው አንደበትን የሰጠው’ ይሖዋ በድምፃችን እሱን በመዝሙር ስናወድሰው መስማት ያስደስተዋል።—ዘፀ. 4:11

18. የመዝሙሮቻችንን ግጥም እንዴት መልመድ እንደሚቻል ሐሳብ ስጥ።

18 ለይሖዋ ዘምሩ—በድምፅ የተዘመሩ መዝሙሮች የተባሉትን ሲዲዎች በተለያዩ ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል። ሲዲዎቹ በኦርኬስትራ የታጀቡ መዘምራን የዘመሯቸውን ማራኪ መዝሙሮች ይዘዋል። እነዚህን የሙዚቃ ቅንብሮች መስማት በጣም የሚመስጥ ነው። ሲዲዎቹን ደጋግመህ አዳምጣቸው፤ እንዲህ ማድረግህ ከአዲሱ መዝሙሮቻችን ውስጥ ቢያንስ የተወሰኑትን መዝሙሮች ግጥም ቶሎ እንድትለምድ ያስችልሃል። የአብዛኞቹ መዝሙሮች ግጥም የተቀናበረው የመጀመሪያውን ስንኝ ስንዘምር ሁለተኛው ምን ሊሆን እንደሚችል እንድንገምት በሚያስችለን መንገድ ነው። ሲዲዎቹን ስታዳምጥ አብረህ ለመዘመር ለምን አትሞክርም? ግጥሙንና ዜማውን ቤትህ ውስጥ በደንብ ከተለማመድከው በመንግሥት አዳራሽ ሲዘመር ከልብ በመነጨ ስሜት ለመዘመር እንደሚያስችልህ ምንም ጥርጥር የለውም።

19. በኦርኬስትራ የተቀነባበሩት የመንግሥት መዝሙሮች የሚዘጋጁት እንዴት ነው?

19 በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የሚከፈቱትን ሙዚቃዎች ሥራዬ ብለን አናዳምጣቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሙዚቃዎች የሚዘጋጁት ብዙ ተደክሞባቸው ነው። በመጀመሪያ ሙዚቃዎቹ ከተመረጡ በኋላ 64 አባላት ያሉት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የኦርኬስትራ ቡድን ሙዚቃዎቹን እንዲጫወታቸው በሚያስችል መንገድ እንደገና በጥንቃቄ ይጻፋሉ። ሙዚቀኞቹ በርካታ ሰዓታት ፈጅተው ካጠኑና ከተለማመዱ በኋላ ሙዚቃው ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ስቱዲዮ ውስጥ ይቀረጻል። ከእነዚህ ወንድሞችና እህቶች መካከል አሥሩ የመጡት ከዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ነው። ሁሉም ወንድሞችና እህቶች፣ በቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶች ላይ የሚቀርቡትን ያማሩ ሙዚቃዎች በማዘጋጀቱ ሥራ መካፈላቸውን እንደ ትልቅ መብት ይቆጥሩታል። እነዚህ ወንድሞች በፍቅር ተነሳስተው ለሚያደርጉት ጥረት ያለንን አድናቆት በተግባር መግለጽ እንችላለን። በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎቻችን ላይ ሊቀ መንበሩ ቦታችንን እንድንይዝ ሲጋብዘን ወዲያውኑ በመቀመጥ ፍቅራዊ ዝግጅት የሆነውን ሙዚቃ ጸጥ ብለን እናዳምጥ።

20. ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?

20 ይሖዋ የምናሰማውን የምስጋና መዝሙር በትኩረት ያዳምጣል። ለእነዚህ መዝሙሮች ትልቅ ቦታ ይሰጣል። ምንጊዜም ለአምልኮ ስንሰበሰብ በሙሉ ልባችን በመዘመር የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት እንችላለን። አዎ፣ መዝሙር በመዘመር ረገድ የተካንንም እንሁን ተማሪዎች ሁላችንም ‘ለይሖዋ እንዘምር’!—መዝ. 104:33

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.1 የሚገርመው ነገር፣ ዳዊት ከሞተ ከአሥር መቶ ዓመታት በኋላ እረኞች በቤተልሔም አቅራቢያ ባሉ መስኮች ላይ መንጎቻቸውን እየጠበቁ ሳሉ በርካታ መላእክት መጥተው የመሲሑን መወለድ አብስረዋቸው ነበር።—ሉቃስ 2:4, 8, 13, 14

^ አን.15 ሁለት መቶ ሃያ አምስት መዝሙሮችን ያቀፈው የመዝሙር መጽሐፍ ከ100 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኝ ነበር።

ምን ይመስልሃል?

• ሙዚቃ በይሖዋ አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳለው የሚጠቁሙት የትኞቹ የጥንት ጊዜ ምሳሌዎች ናቸው?

በማቴዎስ 22:37 ላይ በሚገኘው የኢየሱስ ትእዛዝና የመንግሥቱን መዝሙሮች በሙሉ ልብ በመዘመር መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?

• ለመንግሥቱ መዝሙሮች ተገቢውን አድናቆት ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆችህ በመዝሙር ጊዜ ሳያስፈልግ ተነስተው እንዳይወጡ ለማድረግ ትጥራለህ?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአዲሱን መዝሙራችንን ግጥሞች በቤትህ እየተለማመድካቸው ነው?