በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን ለማገልገል ጊዜው አላለፈም

አምላክን ለማገልገል ጊዜው አላለፈም

አምላክን ለማገልገል ጊዜው አላለፈም

በማላጋ፣ ደቡባዊ ስፔን የሚኖሩት ሁለቱም አና ተብለው የሚጠሩ እናትና ልጅ ታኅሣሥ 19, 2009 ተጠመቁ። በ2009 በስፔን 2,352 ሰዎች የተጠመቁ ቢሆንም እነዚህን እናትና ልጅ ልዩ የሚያደርጋቸው አንድ ነገር ነበር፤ የእናትየው ዕድሜ 107 ዓመት ሲሆን ልጅየው ደግሞ 83 ዓመታቸው ነበር!

እነኚህ እናትና ልጅ ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የትንሿ አና ጎረቤት የሆነች አንዲት የይሖዋ ምሥክር በቤቷ በሚከናወነው የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ እንዲገኙ አናን ትጋብዛቸው ነበር። አና በስብሰባው ላይ አልፎ አልፎ ይገኙ የነበረ ቢሆንም በሥራቸው ምክንያት መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አልቻሉም።

ወደ አሥር ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ የአና ልጆች መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመሩ ሲሆን በኋላ ላይም የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። ማሪ ካርመን የተባለች ልጃቸው፣ አና ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የነበራቸው ፍቅር እንዲቀጣጠል በመርዳት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንዲጀምሩ አደረገች። ከዚያም የማሪ ካርመን አያት የሆኑት ትልቋ አና ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት አሳዩ። ከጊዜ በኋላ የዚህ ቤተሰብ አሥር አባላት ራሳቸውን ወስነው ተጠምቀዋል።

ሁለቱም አናዎች በተጠመቁ ጊዜ በጣም ተደስተው ነበር። የ107 ዓመቷ አና “ይሖዋ ለእኔ በጣም ጥሩ ነገር አድርጎልኛል፤ ምክንያቱም እሱን እንዳውቀው ፈቅዶልኛል” በማለት ተናግረዋል። ልጃቸው አና ደግሞ “አዲሱ ሥርዓት ከመምጣቱ በፊት በተቻለኝ መጠን የይሖዋን ፈቃድ በማድረግና ምሥራቹን በመስበክ እሱን ማገልገል እፈልጋለሁ” ብለዋል።

ባሎቻቸው የሞቱባቸውን እነኚህን እናትና ልጅ በጣም የሚያስደስታቸው ነገር ቢኖር በስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው። በጉባኤያቸው የሚያገለግል አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “አንዲት ቀን እንኳ ከስብሰባ ቀርተው አያውቁም። በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ሐሳብ ለመስጠት ምንጊዜም ዝግጁ ናቸው።”

እነኚህ እናትና ልጅ የተዉት የታማኝነት ምሳሌ “ሌትና ቀንም በጾምና በምልጃ ቅዱስ አገልግሎት እያቀረበች ከቤተ መቅደስ ፈጽሞ አትጠፋም ነበር” የተባለላትን ሐና የተባለችውን መበለት ያስታውሰናል። ሐና እንዲህ ማድረጓ ሕፃኑን ኢየሱስን የማየት መብት አስገኝቶላታል። (ሉቃስ 2:36-38) የ84 ዓመቷ ሐናም ሆነች ከእሷ ጋ ተመሳሳይ ስም ያላቸው እነ አና ይሖዋን ለማገልገል ዕድሜ አልገደባቸውም።

አንተስ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ የሆኑ ዘመዶች አሉህ? ወይስ ቤታቸው ሄደህ ስታነጋግራቸው ሊያዳምጡህ ፈቃደኛ የሆኑ አረጋዊ ሰው አግኝተሃል? እነዚህ ሰዎች በዚህ ተሞክሮ ላይ እንዳየናቸው እንደ ሁለቱ አናዎች መሆን ይችላሉ፤ እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ለማገልገል ጊዜው አላለፈባቸውም።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ይሖዋ ለእኔ በጣም ጥሩ ነገር አድርጎልኛል”

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘አዲሱ ሥርዓት ከመምጣቱ በፊት ይሖዋን ማገልገል እፈልጋለሁ’