በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ዘፍጥረት 6:3 “ሰው ሟች ስለ ሆነ መንፈሴ እያዘነ ከእርሱ ጋር ለዘላለም አይኖርም፤ ዕድሜው 120 ዓመት ይሆናል” ይላል። ይሖዋ ይህን ሲናገር የሰው ዕድሜ ከ120 ዓመት እንዳይበልጥ መገደቡ ነበር? ወይስ ኖኅ ለ120 ዓመት ስለ መጪው የጥፋት ውኃ እንደሚሰብክ መናገሩ ነበር?

የሁለቱም ጥያቄዎች መልስ አይደለም የሚል ነው።

ከጥፋት ውኃ በፊት ብዙ ሰዎች ለበርካታ መቶ ዓመታት ኖረዋል። የጥፋት ውኃው በመጣ ጊዜ ኖኅ ዕድሜው 600 ዓመት የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ ለ950 ዓመት ኖሯል። (ዘፍ. 7:6፤ 9:29) ከጥፋት ውኃው በኋላ የተወለዱ አንዳንድ ሰዎችም ቢሆኑ ከ120 ዓመት በላይ ኖረዋል፤ ለምሳሌ ያህል፣ አርፋክስድ የሞተው በ438 ዓመቱ ሲሆን ሳላ የሞተው ደግሞ በ433 ዓመቱ ነበር። (ዘፍ. 11:10-15) ሆኖም በሙሴ ዘመን የሰዎች ዕድሜ ወደ 70 ወይም 80 ዓመት ወርዶ ነበር። (መዝ. 90:10) በመሆኑም ዘፍጥረት 6:3 የሰዎች የዕድሜ ጣሪያ 120 ዓመት ብቻ እንዲሆን መወሰኑን የሚያሳይ አይደለም።

ታዲያ ይህ ጥቅስ የጥፋት ውኃው ከ120 ዓመት በኋላ እንደሚመጣ ኖኅ ለሰዎች እንዲያስጠነቅቅ አምላክ እያሳሰበው እንደሆነ የሚያመለክት ነው? አይደለም። አምላክ በተለያዩ አጋጣሚዎች ኖኅን አነጋግሮታል። ከአሥር ቁጥሮች በኋላ እንዲህ የሚል ሐሳብ እናገኛለን፦ “እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፦ ‘ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ ምድር በሰው ዐመፅ ስለ ተሞላች።’” በቀጣዮቹ ዓመታት ኖኅ መርከብ የመሥራቱን ከባድ ሥራ አጠናቀቀ፤ በዚህ ጊዜ “እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፤ . . . ‘ቤተ ሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ።’” (ዘፍ. 6:13፤ 7:1) ይሖዋ አንዳንድ ነገሮችን በተመለከተ ለኖኅ እንደተናገረ የሚገልጹ ሌሎች ጥቅሶችም አሉ።—ዘፍ. 8:15፤ 9:1, 8, 17

ይሁንና በ⁠ዘፍጥረት 6:3 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ከዚህ የተለየ ነው፤ እዚህ ጥቅስ ላይ ኖኅ ያልተጠቀሰ ከመሆኑም በላይ አምላክ ለኖኅ እየተናገረ አልነበረም። እዚህ ጥቅስ ላይ አምላክ ዓላማውን ወይም ሊያደርገው የፈለገውን ነገር እየተናገረ ነበር። (ከ⁠ዘፍጥረት 8:21 ጋር አወዳድር።) አዳም ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ በሚናገረው ታሪካዊ ዘገባ ላይ “እግዚአብሔር . . . አለ” የሚሉ አገላለጾችን እንደምናገኝ ልብ ማለታችን አስፈላጊ ነው። (ዘፍ. 1:6, 9, 14, 20, 24) በዚህ ወቅት የሰው ዘር ገና ስላልተፈጠረ ይሖዋ ሰዎችን እያነጋገረ እንዳልነበረ ግልጽ ነው።

በመሆኑም ዘፍጥረት 6:3 አምላክ በምድር ላይ የነበረውን የተበላሸ ሥርዓት ለማጥፋት ስላደረገው ውሳኔ የሚናገር ነው ብለን መደምደማችን ምክንያታዊ ነው። ይሖዋ ሥርዓቱን ከ120 ዓመት በኋላ እንደሚያጠፋ የፍርድ ውሳኔ ማሳለፉ ነበር፤ እርግጥ ይሖዋ እንዲህ ያለ ውሳኔ ስለ ማሳለፉ ኖኅ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ታዲያ ይሖዋ 120 ዓመት እንዲያልፍ የወሰነው ለምንድን ነው? ይህን ያህል ጊዜ መጠበቅ ለምን አስፈለገ?

ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት አንዳንድ ምክንያቶችን ገልጿል፦ “በኖኅ ዘመን ጥቂት ሰዎች ይኸውም ስምንት ነፍሳት ከውኃው የዳኑበት መርከብ እየተሠራ በነበረበት ጊዜ አምላክ በትዕግሥት [ጠብቋል።]” (1 ጴጥ. 3:20) አዎ፣ አምላክ 120ውን ዓመት በሚመለከት ውሳኔ ባሳለፈበት ጊዜ ገና መሠራት የሚገባቸው አንዳንድ ነገሮች ነበሩ። ኖኅና ሚስቱ ልጆች መውለድ የጀመሩት ከ20 ዓመት ገደማ በኋላ ነበር። (ዘፍ. 5:32፤ 7:6) ከዚያም ሦስቱ ወንዶች ልጆቻቸው አድገው ሚስቶችን አገቡ፤ የቤተሰቡ ቁጥር “ስምንት ነፍሳት” የሆነው በዚህ ጊዜ ነው። እንዲሁም መርከቡን የመገንባት ሥራ ይጠብቃቸው ነበር፤ ከመርከቡ ግዝፈትና የኖኅ ቤተሰብ ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑ አንጻር ይህ ሥራ ቀላል አልነበረም። አዎን፣ አምላክ ለ120 ዓመት መታገሡ እነዚህ ነገሮች እንዲከናወኑ ያስቻለ ከመሆኑም በላይ ስምንት ታማኝ ሰዎች ከጥፋቱ ወይም ‘ከውኃው መዳን’ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች መንገድ ከፍቷል።

ይሖዋ የጥፋት ውኃው የሚከሰትበትን ጊዜ ለኖኅ የነገረው መቼ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። በወቅቱ ልጆቹ ተወልደው፣ አድገውና አግብተው ስለነበር ጥፋቱ ሊመጣ የቀረው 40 ወይም 50 ዓመት ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም ይሖዋ ኖኅን “ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው” አለው። አክሎም ኖኅ ግዙፍ መርከብ እንዲሠራና ከቤተሰቡ ጋር ወደ መርከቡ እንዲገባ ነገረው። (ዘፍ. 6:13-18) በቀሩት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ኖኅ በጽድቅ አኗኗሩ ግሩም ምሳሌ በመሆን ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚያ የበለጠ ነገር አድርጓል። ኖኅ፣ ይሖዋ በዚያን ጊዜ የነበረውን ፈሪሃ አምላክ የሌለውን ዓለም ለማጥፋት ቁርጥ ውሳኔ ማድረጉን የሚገልጽ ግልጽ ማስጠንቀቂያ በማወጅ “የጽድቅ ሰባኪ” ሆኖ አገልግሏል። ኖኅ ጥፋቱ መቼ እንደሚመጣ ያወቀው ያን ያክል ቀደም ብሎ ሳይሆን በተቃረበበት ጊዜ ነበረ፤ ሆኖም ጥፋቱ መምጣቱ የማይቀር ነበር። አንተም ጥፋቱ መምጣቱን እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም።—2 ጴጥ. 2:5