በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኤደን ገነት በእውን የነበረ ቦታ ነው?

ኤደን ገነት በእውን የነበረ ቦታ ነው?

ኤደን ገነት በእውን የነበረ ቦታ ነው?

ስለ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ስለ ኤደን የአትክልት ስፍራ የሚናገረውን ታሪክ ታውቀዋለህ? በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ሰዎች ያውቁታል። ለምን መጽሐፍ ቅዱስህን ገልጠህ ታሪኩን አታነበውም? ዘገባው የሚገኘው ከዘፍጥረት 1:26 እስከ 3:24 ላይ ነው። ታሪኩ ባጭሩ ይህን ይመስላል፦

ይሖዋ አምላክ * ሰውን ከምድር አፈር ከሠራው በኋላ ስሙን አዳም ብሎ ጠራው፤ ከዚያም ኤደን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ባለ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እንዲኖር አደረገ። ይህን የአትክልት ስፍራ ያዘጋጀው አምላክ ራሱ ነው። ስፍራው እንደ ልብ ውኃ የሚያገኝ ከመሆኑም ሌላ ፍሬ የሚሰጡ የሚያማምሩ ዛፎች የሞሉበት ነበር። በመካከሉም “መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ” ይገኝ ነበር። አምላክ፣ ሰዎች ከዚህ ዛፍ እንዳይበሉ አዘዛቸው፤ ታዛዥ ሳይሆኑ ቀርተው ቢበሉ ግን እንደሚሞቱ ነገራቸው። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ ከአዳም የጎድን አጥንቶች አንዱን ወስዶ አጋር የምትሆነውን ሴት ማለትም ሔዋንን ፈጠረለት። አምላክ ለአዳምና ሔዋን የአትክልት ስፍራውን የመንከባከብ ሥራ የሰጣቸው ሲሆን እየተባዙ ምድርን እንዲሞሏትም ነገራቸው።

ሔዋን ብቻዋን ሳለች አንድ እባብ አነጋገራት፤ እባቡ አምላክ እንደዋሻትና አንድ መልካም ነገር ማለትም እንደ አምላክ እንድትሆን ሊያደርጋት የሚችል ነገር እንደነፈጋት በመናገር ከተከለከለው ፍሬ እንድትበላ አግባባት። እሷም በማባበያው ተታልላ ከተከለከለው ፍሬ በላች። በኋላም አዳም ከእሷ ጋር በመተባበር የአምላክን ትእዛዝ ጣሰ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ በአዳም፣ በሔዋንና በእባቡ ላይ የፍርድ ብይን አስተላለፈ። ከዚያም ሰዎቹን ከኤደን የአትክልት ስፍራ ያባረራቸው ሲሆን ወደ ገነት የሚያስገባውን በር ለመጠበቅም መላእክት አቆመ።

ምሑራን፣ ጠበብትና የታሪክ ባለሙያዎች በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን ክንውን በመመርመር እውነተኛና በእርግጥ የተፈጸመ ታሪክ ስለመሆኑ የምሥክርነት ቃል መስጠታቸው የተለመደ ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን እንዲህ ስላሉት ጉዳዮች ተጠራጣሪ መሆን ፋሽን እየሆነ መጥቷል። ይሁን እንጂ ስለ አዳም፣ ስለ ሔዋንና ስለ ኤደን የአትክልት ስፍራ የሚተርከውን የዘፍጥረት ዘገባ ለመጠራጠር ምክንያት የሆናቸው ምንድን ነው? እስቲ ብዙ ጊዜ የሚጠቅሷቸውን አራት ምክንያቶች እንመርምር።

1. የኤደን የአትክልት ስፍራ በእውን የነበረ ቦታ ነው?

በዚህ ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ የተፈጠረው ለምንድን ነው? ፍልስፍና የራሱ ድርሻ ሳይኖረው አይቀርም። ለብዙ መቶ ዓመታት የሃይማኖት ምሑራን አምላክ የተከላት ገነት የሆነ ቦታ ላይ ትገኛለች የሚል ግምት ነበራቸው። ይሁን እንጂ፣ ‘ሰማይ ላይ ካልሆነ በስተቀር በምድር ላይ ፍጹም የሆነ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም’ የሚል አመለካከት የነበራቸው እንደ ፕላቶና አርስቶትል ያሉ የግሪክ ፈላስፎች በቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ አሳድረው ነበር። በመሆኑም የሃይማኖት ምሑራን፣ የመጀመሪያዋ ገነት ለሰማይ ቀረብ ብላ የምትገኝ መሆን አለባት ብለው አሰቡ። * አንዳንዶች ገነትን የሚያስቧት ከዚህች የረከሰች ምድር ጋር እንዳትነካካ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ተራራ አናት ላይ እንደተቀመጠች አድርገው ነው፤ ሌሎች በሰሜን ወይም በደቡብ ዋልታ ላይ እንደምትገኝ ሲያስቡ አንዳንዶች ደግሞ ጨረቃ ላይ ወይም ለጨረቃ ቅርብ በሆነ አካባቢ እንደምትገኝ ይሰማቸዋል። ከዚህ አንጻር ስለ ኤደን የሚናገረው ታሪክ ቅዠት መስሎ መታየቱ ምንም አያስገርምም። አንዳንድ የዘመናችን ምሑራን ኤደን የሚባል ስፍራ ኖሮ አያውቅም የሚል ጠንካራ እምነት ስላላቸው ኤደንን ከካርታ ላይ ለማግኘት መሞከር ሞኝነት እንደሆነ ይሰማቸዋል።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አዳምና ሔዋን ስለኖሩበት የአትክልት ስፍራ የሚሰጠው መግለጫ ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው። በዘፍጥረት 2:8-14 ላይ ስለዚህ ስፍራ በርካታ ዝርዝር ነገሮች ተገልጸው እናገኛለን። ይህ ስፍራ የሚገኘው ኤደን በሚባል ቦታ ምሥራቃዊ ክፍል ነበር። መነሻው ኤደን ከሆነ አንድ ትልቅ ወንዝ ተከፍለው የሚወጡ አራት ወንዞች የአትክልት ስፍራውን ያጠጡ ነበር። የአራቱም ወንዞች ስም የተጠቀሰ ከመሆኑም በላይ ወዴት አቅጣጫ እንደሚፈሱም በአጭሩ ተገልጿል። እነዚህ ዝርዝር መረጃዎች፣ ምሑራን ይህን ስፍራ ለማግኘት ጉጉት እንዲያድርባቸው አድርገዋል፤ አብዛኞቹ ምሑራንም ይህ ጥንታዊ ስፍራ በአሁኑ ጊዜ የት እንደሚገኝ የሚጠቁም ፍንጭ ለማግኘት በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይሁንና የምርምራቸውን ውጤት አስመልክተው የሰጧቸው አያሌ አስተያየቶች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ናቸው። ይህ መሆኑ ታዲያ ስለ ኤደን፣ በዚያ ስለነበረው የአትክልት ስፍራና ስለ ወንዞቿ የተሰጠው መግለጫ ሐሰት ወይም ተረት ነው ለማለት ያስችላል?

እስቲ አስበው፦ በኤደን የአትክልት ስፍራ የተከናወኑት ነገሮች የተፈጸሙት ከ6,000 ዓመታት በፊት ነው። እነዚህን ክንውኖች በጽሑፍ እንዳሰፈረ የሚገመተው ሙሴ ሲሆን ዘገባዎቹን ያጠናቀረው በቃል የተላለፉ ታሪኮችን ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል የተጻፉ ሰነዶችን በመጠቀም ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ሙሴ ዘገባውን የጻፈው በኤደን ገነት የተከናወኑት ነገሮች ከተፈጸሙ ከ2,500 ዓመታት ገደማ በኋላ ነበር። ስለ ኤደን ገነት የሚገልጸው ታሪክ ሙሴ ለኖረበት ዘመን ጭምር ጥንታዊ ነበር። ታዲያ ወንዞችን ጨምሮ የኤደን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በበርካታ መቶ ዘመናት ውስጥ ሊለወጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ይሆን? የመሬት ገጽ ባለበት የማይቀጥልና ምንጊዜም የሚለዋወጥ ነው። ኤደን የምትገኝበት ስፍራ እንደነበር የሚገመተው አካባቢ የመሬት መናወጥ የሚያጠቃው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ከደረሱት ታላላቅ የመሬት ነውጦች ውስጥ 17 በመቶ የሚሆኑት የተከሰቱት በዚህ ቦታ ነው። እንዲህ ባሉ አካባቢዎች ለውጥ መከሰቱ የማይቀር ነገር ነው። ሌላስ ምክንያት ይኖር ይሆን? የኖኅ የጥፋት ውኃ የመሬትን ገጽ በዛሬው ጊዜ ፈጽሞ ልናውቀው በማንችል ሁኔታ ለውጦት ሊሆን ይችላል። *

ይሁንና ስለ ኤደን ገነት የምናውቃቸው ጥቂት እውነታዎች አሉ፦ የዘፍጥረት ዘገባ ስለዚህ ስፍራ የሚናገረው በእውን የነበረ ቦታ እንደሆነ አድርጎ ነው። በዘገባው ላይ ከተጠቀሱት አራት ወንዞች ውስጥ ሁለቱ ማለትም ኤፍራጥስና ጤግሮስ ወይም ሂዲኬል ዛሬም ድረስ እየፈሰሱ ሲሆን የእነዚህ ወንዞች መነሻ ከሆኑት የውኃ አካላት አንዳንዶቹ የሚገኙት ቅርብ ለቅርብ ነው። ሌላው ቀርቶ ዘገባው አራቱ ወንዞች አቋርጠው የሚያልፉባቸውን አገሮች ስም ጭምር የሚጠቅስ ሲሆን በአካባቢው የሚታወቁትን የተፈጥሮ ሀብቶች ለይቶ ይጠቅሳል። ስለ ኤደን በሚገልጸው ዘገባ ውስጥ የቀረቡት ዝርዝር ጉዳዮች የዘፍጥረትን መጽሐፍ ለማንበብ የመጀመሪያ ለሆኑት የጥንቶቹ እስራኤላውያን በቂ መረጃ የሚሰጡ ነበሩ።

ዘገባው የፈጠራ ታሪክ ወይም ተረት ቢሆን ኖሮ በዚህ መልክ ይቀርብ ነበር? እውነት መሆን አለመሆናቸው በቀላሉ ሊረጋገጡ የሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ተረቶች ውስጥ ማግኘት እንችላለን? ተረቶች የሚጀምሩት “ከዕለታት አንድ ቀን በጣም ሩቅ በሆነ አገር” በማለት ነው። እውነተኛ ታሪክ ግን ስለ ኤደን በሚገልጸው ዘገባ ላይ እንዳሉት ያሉ አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር መረጃዎችን አካቶ ይይዛል።

2. አምላክ አዳምን ከምድር አፈር እንደሠራውና ሔዋንን ደግሞ ከአዳም የጎድን አጥንቶች አንዱን ወስዶ እንደሠራት የሚናገረው ታሪክ በእርግጥ ተአማኒ ነው?

ዘመናዊው ሳይንስ የሰው አካል እንደ ሃይድሮጅን፣ ኦክሲጅንና ካርቦን ካሉት የተለያዩ ንጥረ ነገሮች እንደተሠራ ያረጋገጠ ሲሆን እነዚህ ንጥረ ነገሮች በሙሉ የሚገኙት በምድር አፈር ውስጥ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ንጥረ ነገሮች ተሰባስበው አንድ ሕያው ፍጡር ያስገኙት እንዴት ነው?

ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት ሕይወት ያላቸው ነገሮች የመጡት በራሳቸው ነው የሚል መላ ምት አላቸው፤ እንደነሱ አነጋገር ሕይወት የጀመረው ውስብስብ ካልሆነ የሴል ዓይነት ሲሆን በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ ይበልጥ ውስብስብ ወደሆኑ ሕያዋን ነገሮች ተለውጧል። ይሁን እንጂ “ውስብስብ ያልሆነ” የሚለው አገላለጽ አሳሳች ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም በዓይን የማይታዩ ረቂቅ ሴሎችን ጨምሮ ሕያዋን ነገሮች በሙሉ እጅግ ውስብስብ ናቸው። የትኛውም ዓይነት ሕይወት በአጋጣሚ እንደተገኘ ወይም ሊገኝ እንደሚችል የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ የለም። ከዚህ ይልቅ በሁሉም ሕያዋን ነገሮች ላይ የሚታየው ንድፍ ከእኛ እጅግ የላቀ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ለመኖሩ የማያሻማ ማስረጃ ይሰጣል። *ሮም 1:20

በኦርኬስትራ የተቀነባበረ ልዩ ሙዚቃ እያዳመጥክ ወይም አስደናቂ የሥዕል ሥራ እያደነቅህ አሊያም ደግሞ በአንድ የቴክኖሎጂ ግኝት እየተደመምክ ነው እንበል፤ እነዚህ ነገሮች ሠሪ የላቸውም ብለህ ድርቅ ትላለህ? እንደማትል ግልጽ ነው! ነገር ግን እነዚህ ድንቅ የፈጠራ ሥራዎች በሰው አካል ንድፍ አወጣጥ ላይ ከተንጸባረቀው ውስብስብነት፣ ውበት ወይም የፈጠራ ችሎታ ጋር ሲወዳደሩ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም። ታዲያ የሰው አካል ፈጣሪ የለውም ብለን ማሰብ የምንችለው እንዴት ነው? ከዚህም በላይ የዘፍጥረት ዘገባ በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ በአምላክ መልክ የተሠሩት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:26) ከዚህ አንጻር በዚህች ምድር ላይ የአምላክን የመፍጠር ፍላጎት የወረሱት ሰዎች ብቻ መሆናቸው ምንም አያስደንቅም፤ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች አስደናቂ የሆኑ የሙዚቃ፣ የሥነ ጥበብና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መፈልሰፋቸው ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። ታዲያ አምላክ በመፍጠር ችሎታው ከእኛ እጅግ የሚበልጥ መሆኑ ሊያስገርመን ይገባል?

አምላክ ከአዳም የጎድን አጥንቶች አንዱን ወስዶ ሴትን መፍጠሩስ ያን ያህል ለማመን አስቸጋሪ ነው? * እርግጥ ነው፣ አምላክ ሌላ ዘዴ ሊጠቀም ይችል ነበር፤ ሆኖም ሴትን በዚህ መንገድ መፍጠሩ ጥልቅ ትርጉም አለው። አዳምና ሔዋን እንዲጋቡና “አንድ ሥጋ” የሆኑ ያህል የተሳሰሩ እንዲሆኑ ፈልጎ ነበር። (ዘፍጥረት 2:24) አንድ ወንድና አንዲት ሴት ዘላቂና ለሁለቱም የሚጠቅም ትስስር በመፍጠር አንዳቸው የሌላው ማሟያ መሆን መቻላቸው ጥበበኛና አፍቃሪ ፈጣሪ ለመኖሩ ጠንካራ ማስረጃ አይሆንም?

ከዚህም በላይ በዘመናችን ያሉ የጄኔቲክ ተመራማሪዎች፣ የሰው ዘር በሙሉ የመጣው ከአንድ ወንድና ከአንዲት ሴት ሳይሆን እንደማይቀር አምነው ተቀብለዋል። እንዲህ ከሆነ ታዲያ የዘፍጥረት ዘገባ ሊታመን የማይችልበት ምን ምክንያት አለ?

3. ስለ እውቀት ዛፍና ስለ ሕይወት ዛፍ የሚገልጸው ታሪክ ልብ ወለድ ይመስላል።

እንደ እውነቱ ከሆነ የዘፍጥረት ዘገባ እነዚህ ዛፎች በራሳቸው አንዳች የተለየ ባሕርይ ወይም ኃይል እንዳላቸው አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ምሳሌያዊ ትርጉም እንዲኖራቸው አድርጎ ያበቀላቸው እውነተኛ ዛፎች ነበሩ።

ሰዎችስ አንዳንድ ጊዜ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ያደርጉ የለም? ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ዳኛ ፍርድ ቤቱን መዳፈር ወንጀል እንደሆነ በመናገር ሊያስጠነቅቅ ይችላል። ዳኛው ይህን ሲል የፍርድ ሂደት የሚካሄድበት ሕንፃ ወይም በውስጡ ያሉት ቁሳቁሶች አክብሮት ሊሰጣቸው ይገባል ማለቱ ሳይሆን በፍርድ ቤቱ የሚወከለው የፍትሕ ሥርዓት ሊከበር እንደሚገባ መናገሩ ነው። የተለያዩ ነገሥታትም በትረ መንግሥታቸውንና ዘውዳቸውን የሉዓላዊ ሥልጣናቸው መገለጫ እንደሆኑ አድርገው ሲጠቀሙባቸው ኖረዋል።

ታዲያ እነዚያ ሁለት ዛፎች የያዙት ምሳሌያዊ ትርጉም ምንድን ነው? ይህን በተመለከተ ውስብስብ የሆኑ ብዙ መላ ምቶች ቢሰነዘሩም ትክክለኛው መልስ ቀላል ሆኖም ጥልቅ ትርጉም ያለው ነው። መልካምና ክፉን የሚያሳውቀው ዛፍ ለአምላክ ብቻ የሚገባውን መብት ይኸውም መልካም ወይም ክፉ የሚባለው ምን እንደሆነ የመወሰን መብቱን የሚወክል ነው። (ኤርምያስ 10:23) በመሆኑም ከዛፉ ላይ መስረቅ ወንጀል መሆኑ ምንም አያስደንቅም! በሌላ በኩል ደግሞ የሕይወት ዛፍ አምላክ ብቻ ሊሰጥ የሚችለውን ስጦታ ማለትም የዘላለም ሕይወትን ይወክላል።—ሮም 6:23

4. ስለሚናገር እባብ የሚገልጸው ታሪክ ተረት ተረት ይመስላል።

በተለይ ቀሪውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከግምት ካላስገባን ስለ እባቡ የሚተርከው የዘፍጥረት ዘገባ እንቆቅልሽ ሊሆንብን እንደሚችል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍት ይህን ትኩረት የሚስብ ሚስጥር ደረጃ በደረጃ ይፈቱልናል።

እባቡን የሚናገር እንዲመስል ያደረገው ማን ነበር? የጥንቶቹ እስራኤላውያን እባቡ የነበረውን ሚና ለመረዳት የሚያስችል ፍንጭ የሚሰጡ አንዳንድ ነገሮችን ያውቁ ነበር። ለምሳሌ እንስሳት ሊናገሩ እንደማይችሉ ቢረዱም አንድ መንፈሳዊ አካል ግን አንድን እንስሳ የሚናገር እንዲመስል ሊያደርግ እንደሚችል ያውቁ ነበር። ሙሴ ስለ በለዓም የሚናገረውንም ዘገባ በጽሑፍ አስፍሯል፤ አምላክ የላከው አንድ መልአክ የበለዓም አህያ ልክ እንደ ሰው እንድትናገር ማድረጉን ዘገባው ይናገራል።—ዘኍልቍ 22:26-31፤ 2 ጴጥሮስ 2:15, 16

ታዲያ የአምላክ ጠላት የሆኑትን ጨምሮ ሌሎች መናፍስት ተአምር መሥራት ይችላሉ? ሙሴ አስማት የሚሠሩ የግብፅ ካህናት አምላክ የፈጸማቸውን አንዳንድ ተአምራትን አስመስለው ሲሠሩ ተመልክቷል፤ ለምሳሌ በትራቸውን በመለወጥ እባብ እንዲመስል ማድረግ ችለው ነበር። የግብፅ ካህናት እንዲህ ያሉ አስደናቂ ነገሮችን የማከናወን ኃይል ያገኙት በመንፈሳዊው ዓለም ከሚኖሩ የአምላክ ጠላቶች እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።—ዘፀአት 7:8-12

የኢዮብንም መጽሐፍ የጻፈው ሙሴ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ መጽሐፍ የይሖዋ አገልጋዮች ለአምላካቸው ያላቸውን ታማኝነት መጠበቅ አይችሉም የሚል የሐሰት ክስ ስላቀረበውና የአምላክ ቀንደኛ ጠላት ስለሆነው ስለ ሰይጣን ብዙ ነገር ያስተምራል። (ኢዮብ 1:6-11፤ 2:4, 5) ታዲያ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በኤደን የነበረውን እባብ የሚናገር በማስመሰል ሔዋን ለአምላክ ያላትን ታማኝነት እንድታጓድል ያሳሳታት ሰይጣን ነው ብለው አስበው ይሆን? ሳይሆን አይቀርም።

በእርግጥ ከእባቡ በስተጀርባ የነበረው ሰይጣን ነው? ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ፣ ሰይጣን “ውሸታምና የውሸት አባት” እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:44) በዚህች ምድር ላይ የተነገረውን የመጀመሪያውን ውሸት ያመነጨው ይኸው “የውሸት አባት” ነው ቢባል አትስማማም? የመጀመሪያውን ውሸት ለማወቅ እባቡ ለሔዋን የተናገራትን ነገር እንመልከት። እባቡ፣ ከተከለከለው ፍሬ መብላት ሞት እንደሚያስከትል አምላክ የተናገረውን ማስጠንቀቂያ በመቃረን “መሞት እንኳ አትሞቱም” አለ። (ዘፍጥረት 3:4) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ እባቡን መጠቀሚያ ያደረገው ሰይጣን እንደሆነ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ለሐዋርያው ዮሐንስ በሰጠው ራእይ ላይ ሰይጣን “የመጀመሪያው እባብ” ተብሎ መጠራቱ ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል።—ራእይ 1:1፤ 12:9

አንድ ኃያል መንፈሳዊ አካል እባብን የሚናገር እንዲመስል ማድረግ መቻሉ በእርግጥ ሊታመን የማይችል ነገር ነው? ከመንፈሳዊ አካላት እጅግ ያነሰ ኃይል ያላቸው ሰዎችም እንኳ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው አንድን ነገር የሚናገር እንዲመስል ማድረግ ይችላሉ።

ከሁሉ የላቀው አሳማኝ ማስረጃ

ሰዎች በዘፍጥረት ዘገባ ላይ ያላቸው ጥርጣሬ መሠረተ ቢስ ነው ቢባል አትስማማም? በሌላ በኩል ደግሞ ዘገባው እውነተኛ ታሪክ ለመሆኑ ጠንካራ ማስረጃ አለ።

ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ “የታመነውና እውነተኛው ምሥክር” ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 3:14) ኢየሱስ ፍጹም ሰው የነበረ እንደመሆኑ መጠን ፈጽሞ ዋሽቶም ሆነ በምንም መንገድ እውነትን አዛብቶ አያውቅም። ከዚህም በላይ በምድር ላይ ሰው ሆኖ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት እንዲያውም “ዓለም ከመመሥረቱ” አስቀድሞ ከአባቱ ከይሖዋ ጋር እንደኖረ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:5) በመሆኑም ሕይወት በምድር ላይ ሲጀምር ኢየሱስም ነበረ። ታዲያ ከሁሉ የላቀውና አስተማማኝ የሆነው ይህ ምሥክር ምን ብሎ ይሆን?

ኢየሱስ ስለ አዳምና ሔዋን የተናገረው በእውን የነበሩ ሰዎች አድርጎ ነው። ኢየሱስ ጋብቻን በተመለከተ የይሖዋ መሥፈርት አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት መሆኑን በገለጸበት ጊዜ የአዳምና የሔዋንን ጋብቻ ጠቅሷል። (ማቴዎስ 19:3-6) አዳምና ሔዋን በሕይወት ኖረው የማያውቁ ሰዎች ከሆኑ ብሎም የኖሩበት የአትክልት ስፍራ ተረት ከሆነ አንድም ኢየሱስ ተታልሏል አለዚያም ዋሽቷል ማለት ነው። ሁለቱም ቢሆን አያስኬድም! በኤደን ገነት የተፈጸመው አሳዛኝ ሁኔታ ሲከሰት ኢየሱስ በሰማይ ሆኖ እየተመለከተ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ከሰጠው ምሥክርነት የበለጠ አሳማኝ ማስረጃ ማግኘት ይቻላል?

እውነቱን ለመናገር አንድ ሰው በዘፍጥረት ዘገባ ላይ እምነት ማጣቱ በኢየሱስ ላይ ያለውን እምነት ያዳክምበታል። በተጨማሪም ስለ ዋና ዋናዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችና እጅግ አጽናኝ ስለሆኑት ተስፋዎች መረዳት አዳጋች እንዲሆንበት ያደርገዋል። እንዲህ የምንልበትን ምክንያት እስቲ እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።

^ አን.7 ይህ ዓይነቱ አመለካከት የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ሥራ በሙሉ ፍጹም እንደሆነና ለነገሮች መበላሸት መንስኤው እሱ እንዳልሆነ ያስተምራል። (ዘዳግም 32:4, 5) ይሖዋ በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን ፈጥሮ ሲያጠናቅቅ የሠራቸው ነገሮች በሙሉ “እጅግ መልካም” እንደሆኑ ገልጿል።—ዘፍጥረት 1:31

^ አን.9 ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው አምላክ ያመጣው የጥፋት ውኃ ኤደን ገነትን ደብዛዋ እስኪጠፋ ድረስ ጠራርጎ አጥፍቷታል። ሕዝቅኤል 31:18 እንደሚጠቁመው ‘የኤደን ዛፎች’ ሕዝቅኤል በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መጽሐፉን ከመጻፉ ከረጅም ዘመናት በፊት ጠፍተዋል። ስለዚህ ከዚያ ወዲህ ባሉት ዘመናት የኤደንን የአትክልት ስፍራ ለማግኘት ፍለጋ ያካሄዱ ሁሉ ጥረታቸው ከንቱ ሆኖባቸዋል።

^ አን.14 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የሕይወት አመጣጥመልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።

^ አን.16 የሚገርመው፣ የጎድን አጥንት ከደረሰበት ጉዳት የማገገም ልዩ ችሎታ እንዳለው ዘመናዊው የሕክምና ሳይንስ ደርሶበታል። ከሌሎች አጥንቶች በተለየ መልኩ አያያዥ ሕብረ ሕዋሶቹ እስካልተነኩ ድረስ መልሶ ሊያድግ ይችላል።