በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰይጣን ሔዋንን ለማነጋገር በእባብ የተጠቀመው ለምንድን ነው?

ሰይጣን ሔዋንን ለማነጋገር በእባብ የተጠቀመው ለምንድን ነው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ሰይጣን ሔዋንን ለማነጋገር በእባብ የተጠቀመው ለምንድን ነው?

▪ በገጽ 8 ላይ እንደተመለከትነው ሔዋንን ካነጋገራት እባብ በስተጀርባ የነበረው ሰይጣን በመሆኑ ትስማማ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚያስተምረው ይህንን ነው። ይሁንና ‘ይህ ኃይለኛ መንፈሳዊ ፍጡር እባብን መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ስልቶች “መሠሪ ዘዴዎች” በማለት የሚጠራቸው ሲሆን ይህ ደግሞ ነጥቡን ግልጽ ያደርግልናል። (ኤፌሶን 6:11) በኤደን ገነት የተከሰተው ሁኔታ፣ መናገር ስለሚችል አንድ እንስሳ የሚተርክ ተረት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሰይጣን ሰዎችን አታልሎ ከአምላክ ለማራቅ መሠሪ ዘዴዎችን እንደሚጠቀም የሚያሳይ ግልጽ የሆነ ምሳሌ ነው። ሰይጣን ሰዎችን ከአምላክ የሚያርቀው እንዴት ነው?

ሰይጣን ማንን ማነጋገር ገብቶታል። ሔዋን በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ካሉት ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታት ሁሉ በዕድሜ ለጋ ስለነበረች ብዙ ተሞክሮ አልነበራትም። ሰይጣን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም እሷን ለማታለል የሚያስችለውን የተንኮል ዘዴ ቀየሰ። ድፍረት የተሞላበት ክፉ ምኞቱን በመሰወር እንዲሁም በተፈጥሮው በጣም ጠንቃቃ ከሆነው ፍጡር ማለትም ከእባብ በስተጀርባ ሆኖ ማንነቱን በመደበቅ ወደ ሔዋን ቀረበ። (ዘፍጥረት 3:1) በተጨማሪም ዲያብሎስ እባቡን እየተናገረ እንዳለ ማስመሰሉ ምን ውጤት እንዳስገኘለት እንመልከት።

በመጀመሪያ ደረጃ ሰይጣን የሔዋንን ትኩረት ለመሳብና ልቧን ለመስረቅ ያደረገው ጥረት ተሳክቶለታል። ሔዋን እባብ እንደማይናገር ታውቃለች፤ ባልዋ አዳም ይህን እንስሳ ጨምሮ ለሁሉም እንስሳት ስም ያወጣላቸው በጥንቃቄ መርምሮ ሳይሆን አይቀርም። (ዘፍጥረት 2:19) ሔዋንም ብትሆን የዚህን ጠንቃቃ እንስሳ ባሕርይ ሳታስተውል አትቀርም። ሰይጣን የቀየሰው ዘዴ የሔዋንን የማወቅ ጉጉት ቀሰቀሰው፤ በዚህ መንገድ በአትክልቱ ስፍራ ከሚገኙት መካከል እንዳትበላ በተከለከለችው አንድ ነገር ላይ ትኩረቷ እንዲያርፍ አደረገ። ሁለተኛ፣ እባቡ የሚያናግራት በተከለከለው ዛፍ ቅርንጫፎች ላይ እየተሽሎከሎከ ከሆነ ሔዋን ምን መደምደሚያ ላይ ልትደርስ ትችላለች? መናገር የማይችለው ይህ አነስተኛ ፍጡር ከፍሬው በልቶ መናገር ቻለ ብላ እንድታስብ ሊያደርጋት አይችልም? ፍሬው እባቡን እንዲናገር ካደረገው ለእሷማ ምን ያህል ለውጥ ያመጣ ይሆን? ሔዋን ምን አስባ እንደነበረም ሆነ እባቡ ከፍሬው መቅመስ አለመቅመሱን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፤ ሆኖም ሔዋን ከፍሬው መብላቷ ‘እንደ እግዚአብሔር እንደሚያደርጋት’ እባቡ ሲነግራት እንዳመነችው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ሰይጣን የመረጣቸው ቃላትም ብዙ የሚጠቁሙን ነገሮች አሉ። ሰይጣን፣ አምላክ መልካም የሆነ አንድ ነገር እንዳስቀረባት እንዲሁም ሳያስፈልግ ነፃነቷን እንደገደበባት እንዲሰማት የሚያደርግ ሐሳብ በመናገር በሔዋን አእምሮ ውስጥ የጥርጣሬ ዘር ዘራ። ሔዋን ለግል ፍላጎቷ የምትሰጠው ቦታ ሁሉን ነገር ለሰጣት አምላክ ካላት ፍቅር ከበለጠ ሰይጣን እንደ አምላክ እንደምትሆን ቃል በመግባት የቀየሰው ዘዴ ይሳካል ማለት ነው። (ዘፍጥረት 3:4, 5) የሚያሳዝነው ሰይጣን የቀየሰው ዘዴ ተሳካ፤ ሔዋንም ሆነች አዳም ለይሖዋ ሊኖራቸው የሚገባውን ዓይነት ፍቅርና አድናቆት አላዳበሩም ነበር። በዛሬው ጊዜስ ቢሆን ሰይጣን እንዲህ ዓይነቱን የራስን ምኞት የማስቀደምና ሰበብ የመፍጠር ዝንባሌ እያስፋፋ አይደለም?

ሰይጣን እንዲህ እንዲያደርግ ስላነሳሳው ምክንያትስ ምን ማለት ይችላል? የሚፈልገው ምን ነበር? በኤደን ሳለ ማንነቱንም ሆነ ዓላማውን ለመደበቅ ሞክሮ ነበር። ይሁንና ከጊዜ በኋላ ማንነቱን ግልጽ አድርጓል። ኢየሱስን በፈተነው ጊዜ ማንነቱን መደበቁ እንደማያዋጣው ያውቅ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስን በቀጥታ “አንድ ጊዜ ተደፍተህ [አምልከኝ]” ብሎት ነበር። (ማቴዎስ 4:9) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው ሰይጣን፣ ለይሖዋ አምላክ የሚቀርበው አምልኮ ለረጅም ጊዜ ሲያስቀናው ቆይቷል። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት አምላክን እንዳያመልኩ ወይም አምልኳቸው ተቀባይነት እንዳያገኝ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ንጹሕ አቋማችንን ከማበላሸትና ከማጥፋት የበለጠ የሚያስደስተው ነገር የለም።

መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዒላማ ያደረጋቸውን ሰዎች ለማጥፋት የማይቀይሰው ዘዴ እንደሌለ በግልጽ ይናገራል። ደስ የሚለው ግን እኛ ‘የሰይጣንን ዕቅድ ስለምናውቅ’ እንደ ሔዋን አንታለልም።—2 ቆሮንቶስ 2:11