በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ቢኖሩም ጸንቷል

ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ቢኖሩም ጸንቷል

በእምነታቸው ምሰሏቸው

ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ቢኖሩም ጸንቷል

ሳሙኤል በሴሎ በነበረው ለቅሶ ልቡ አዝኗል። ከተማይቱ በእንባ የምትታጠብ ትመስል ነበር። አባታቸው፣ የትዳር ጓደኛቸው፣ ልጃቸው ወይም ወንድማቸው ከቤት እንደወጣ በመቅረቱ ምክንያት የማያለቅሱ ሴቶችና ልጆች አልነበሩም ማለት ይቻላል። ሕዝቡ የሚያለቅሰው ከፍልስጥኤማውያን ጋር ባደረጉት ጦርነት ክፉኛ ተሸንፈው ወደ 30,000 የሚጠጉ ወታደሮቻቸውን በማጣታቸው ነው፤ ይህ እልቂት የደረሰው በቅርቡ ተደርጎ በነበረ ሌላ ጦርነት 4,000 ወታደሮች መገደላቸው ያስከተለው ሐዘን ሳይረሳ ነው።—1 ሳሙኤል 4:1, 2, 10

ይህ እስራኤላውያን በተከታታይ ካጋጠሟቸው አሳዛኝ ክስተቶች አንዱ ብቻ ነበር። ሊቀ ካህኑ ዔሊ፣ አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉ ሁለት መጥፎ ልጆች የነበሩት ሲሆን እነዚህ ልጆች ቅዱስ የነበረው የኪዳኑ ታቦት ከሴሉ በተወሰደ ጊዜ አብረው ሄደው ነበር። ለወትሮው በመገናኛው ድንኳን ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ይቀመጥ የነበረው ይህ ክቡር ታቦት አምላክ በመካከላቸው እንዳለ የሚያመለክት ነበር። ሕዝቡ ምትሃታዊ ኃይል ያለው ይመስል ይህ ታቦት ድል ያስገኝልናል በሚል የተሳሳተ አመለካከት ወደ ጦርነቱ ስፍራ ይዘውት ሄዱ። ሆኖም ፍልስጥኤማውያን አፍኒንንና ፊንሐስን ገድለው ታቦቱን ማርከው ወሰዱ።—1 ሳሙኤል 4:3-11

ታቦቱ ለብዙ መቶ ዓመታት ሴሎ በሚገኘው የማደሪያ ድንኳን ውስጥ መቀመጡ ማደሪያውን ክብር አጎናጽፎት ነበር። አሁን ግን ታቦቱ ተማረከ። የ98 ዓመቱ ዔሊ ይህን ዜና ሲሰማ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ ወደኋላ ወድቆ ሞተ። በዚያኑ ዕለት ባሏን በሞት ያጣችው የልጁ ሚስትም በወሊድ ላይ እያለች አረፈች። ከመሞቷ በፊት እያጣጣረች “ክብር ከእስራኤል ተለይቶአል” በማለት ተናግራ ነበር። በእርግጥም፣ ከዚያ በኋላ ሴሎ ፈጽሞ እንደቀድሞዋ ልትሆን አልቻለችም።—1 ሳሙኤል 4:12-22

ታዲያ ሳሙኤል እነዚህን ሁሉ አሳዛኝ ሁኔታዎች እንዴት ይቋቋም ይሆን? እምነቱ፣ የይሖዋን ጥበቃና ሞገስ ያጣውን ሕዝብ የመርዳቱን ተፈታታኝ ሥራ እንዲወጣ ያስችለው ይሆን? በዛሬው ጊዜ፣ ሁላችንም እምነታችንን የሚፈታተን መከራ ብሎም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ያጋጥመን ይሆናል፤ ከሳሙኤል ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።

“ጽድቅ እንዲፈጸም የሚያደርግ ተግባር” አከናውኗል

አሁን ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ የሳሙኤልን ታሪክ ተወት ያደርግና ፍልስጥኤማውያን ቅዱሱን ታቦት በመውሰዳቸው ምን ችግር እንደደረሰባቸውና ታቦቱን ለመመለስ እንዴት እንደተገደዱ መተረኩን ይቀጥላል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሳሙኤል እንደገና መተረክ የሚጀምረው 20 ዓመታት ገደማ ካለፉ በኋላ ስለተፈጸሙ ነገሮች በመናገር ነው። (1 ሳሙኤል 7:2) ሳሙኤል በእነዚያ 20 ዓመታት ምን ሲያደርግ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሳሙኤል ይህን ጊዜ እንዴት እንዳለፈው ስለሚነግረን መገመት አያስፈልገንም።

መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የ20 ዓመት ጊዜ ከመጀመሩ በፊት የሆነውን አስመልክቶ ሲናገር “የሳሙኤልም ቃል ወደ እስራኤል ሁሉ ደረሰ [“መምጣቱን ቀጠለ፣” NW]” ይላል። (1 ሳሙኤል 4:1) ይህ የ20 ዓመት ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ሳሙኤል አለመግባባቶችን ለመዳኘትና ጥያቄዎችን ለመፍታት በየዓመቱ በሦስት የእስራኤል ከተሞች ውስጥ እየተዘዋወረ ይሠራ እንደነበረ ዘገባው ይናገራል። ከዚያም ወደ ትውልድ ከተማው ወደ አርማቴም ይመለስ ነበር። (1 ሳሙኤል 7:15-17) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደምንችለው ሳሙኤል በእነዚያ 20 ዓመታት ውስጥ በርካታ ሥራ ስለነበረው ምንጊዜም በሥራ የተጠመደ ሰው ነበር።

የዔሊ ልጆች በነበራቸው የተበላሸ ሥነ ምግባር ምክንያት የሕዝቡ እምነት ተሸርሽሮ ነበር። እንዲያውም ብዙዎች በዚህ ምክንያት ወደ ጣዖት አምልኮ ፊታቸውን ሳያዞሩ አልቀሩም። ሳሙኤል ለሁለት አሥርተ ዓመታት ጠንክሮ ከሠራ በኋላ ለሕዝቡ እንዲህ የሚል መልእክት አስተላለፈ፦ “በፍጹም ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትመለሱ ከሆነ፣ ሌሎችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለእግዚአብሔር አሳልፋችሁ ስጡ፤ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ እርሱም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋችኋል።”—1 ሳሙኤል 7:3

‘የፍልስጥኤማውያን እጅ’ በሕዝቡ ላይ በርትቶ ነበር። ፍልስጥኤማውያን፣ የእስራኤልን ጦር ድል ስላደረጉ እነዚህን የአምላክ ሕዝቦች በማንአለብኝነት ይጨቁኑ ነበር። ይሁንና ሳሙኤል፣ ሕዝቡ ወደ ይሖዋ ቢመለስ ነገሮች እንደሚለወጡ ማረጋገጫ ሰጣቸው። ታዲያ ሕዝቡ ፈቃደኛ ነበር? ሕዝቡ ጣዖቶቻቸውን አስወግደው ይሖዋን ብቻ ማምለክ ጀመሩ፤ ይህ ሁኔታ ሳሙኤልን በጣም አስደስቶታል። ከዚያ በኋላ ሳሙኤል ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን በሚገኘው ተራራማ አካባቢ በነበረችው ምጽጳ በተባለች ከተማ ሕዝቡን ሰበሰበ። ሕዝቡም ተሰብስቦ ከጾመ በኋላ ከጣዖት አምልኮ ጋር በተያያዘ ለፈጸመው በርካታ ኃጢአት ንስሐ ገባ።—1 ሳሙኤል 7:4-6

ይሁንና ፍልስጥኤማውያን ሕዝቡ በአንድነት እንደተሰበሰበ ሲያውቁ ይህን አጋጣሚ ሊጠቀሙበት አሰቡ። በዚያ የተሰበሰበውን የአምላክ ሕዝብ ለማጥፋት ሠራዊታቸውን ወደ ምጽጳ ላኩ። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን አደጋ እንዳንዣበበባቸው አወቁ። ሕዝቡ በጣም ከመሸበሩ የተነሳ ሳሙኤልን እንዲጸልይላቸው ጠየቁት። ሳሙኤል መጸለይ ብቻ ሳይሆን መሥዋዕት ጭምር አቀረበ። ይህ ቅዱስ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ እያለ የፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ወደ ምጽጳ ተቃረበ። ይሖዋ በዚህ ጊዜ የሳሙኤልን ጸሎት ሰማ። ይሖዋ በፍልስጥኤማውያን ላይ እጅግ ከመቆጣቱ የተነሳ “ከባድ የነጐድጓድ ድምፅ [አንጐደጐደባቸው።]”—1 ሳሙኤል 7:7-10

እነዚህን ፍልስጥኤማውያን፣ የነጐድጓድ ድምፅ ሲሰማ በጣም ከመፍራቱ የተነሳ እናቱ ሥር እንደሚሸጎጥ ትንሽ ልጅ አድርገን ልናስባቸው ይገባል? በፍጹም፣ እነዚህ ሰዎች ጦርነት ምንም የማይመስላቸው ኃይለኛ ተዋጊዎች ነበሩ። ይሁንና ይህ የነጐድጓድ ድምፅ ፈጽሞ ሰምተውት የማያውቁት ነገር ሳይሆንባቸው አልቀረም። ምናልባት ይህ የሆነው የድምፁ መጠን “ከባድ” ስለነበረ ይሆን? ወይስ ድምፁ ጥርት ካለው ሰማይ ላይ ስለመጣ? አሊያም እንግዳ የሆነ ድምፅ በተራራዎቹ መሃል ስላስተጋባ ይሆን? ምንም ይሁን ምን ድምፁ እነዚህን ፍልስጥኤማውያን እንዲርበተበቱ አድርጓቸዋል። እንዲያውም ፍልስጥኤማውያን በጣም ግራ ስለተጋቡ ኃያል ተዋጊዎች መሆናቸው ቀርቶ እነሱ ራሳቸው የጥቃት ዒላማ ሆኑ። እስራኤላውያን ከምጽጳ ወጥተው ጥቃት በመሰንዘር ድል ያደረጓቸው ከመሆኑም በላይ እስከ ደቡብ ምዕራብ ኢየሩሳሌም ድረስ ረጅም ርቀት አሳደዷቸው።—1 ሳሙኤል 7:11

ይህ ጦርነት ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። ፍልስጥኤማውያን፣ ሳሙኤል መስፍን ሆኖ ባስተዳደረባቸው ዓመታት ዳግመኛ እስራኤልን ለመውረር አልሞከሩም። የአምላክ ሕዝቦች ተወስደውባቸው የነበሩትን ከተሞች ቀስ በቀስ በቁጥጥራቸው ሥር አደረጉ።—1 ሳሙኤል 7:13, 14

ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “ጽድቅ እንዲፈጸም የሚያደርግ ተግባር ፈጽመዋል” ካላቸው ታማኝ መሳፍንትና ነቢያት መካከል ሳሙኤልን ጠቅሶታል። (ዕብራውያን 11:32, 33) በእርግጥም ሳሙኤል እስራኤላውያን በአምላክ ዓይን መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ለመርዳት ጥረት አድርጓል። ሳሙኤል ውጤታማ ሊሆን የቻለው ይሖዋን በትዕግሥት ስለተጠባበቀና ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ቢኖሩም ሥራውን በታማኝነት ማከናወኑን ስለቀጠለ ነው። እንዲሁም ሳሙኤል የአመስጋኝነት መንፈስ አሳይቷል። በምጽጳ ድል ከተገኘ በኋላ ሳሙኤል ይሖዋ ለሕዝቡ ላደረገው እርዳታ መታሰቢያ እንዲሆን አንድ ሐውልት አቁሟል።—1 ሳሙኤል 7:12

አንተስ ‘ጽድቅ እንዲፈጸም የሚያደርግ ተግባር የመፈጸም’ ፍላጎት አለህ? ከሆነ ሳሙኤል ካሳየው ትዕግሥትና ትሕትና እንዲሁም የአመስጋኝነት መንፈስ መማር ይኖርብሃል። ከመካከላችን እነዚህ ባሕርያት የማያስፈልጉት ማን አለ? ሳሙኤል በኋለኞቹ ዓመታት ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ስላጋጠሙት ልጅ ሳለ እነዚህን ባሕርያት ማዳበሩና ማንጸባረቁ በጣም ረድቶታል።

“ልጆችህ ያንተን ፈለግ አይከተሉም”

መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በኋላ ስለ ሳሙኤል የሚተርከው ‘ከሸመገለ’ በኋላ ስላከናወነው ነገር በመናገር ነው። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ኢዮኤል እና አብያ የተባሉ ሁለት ትልልቅ ልጆች ያደረሰ ሲሆን ፈራጆች ሆነው እንዲረዱት ኃላፊነት ሰጥቷቸው ነበር። የሚያሳዝነው ግን ልጆቹ እሱ እንደሚጠብቅባቸው ሆነው አልተገኙም። ሳሙኤል ሐቀኛና ጻድቅ ሰው ቢሆንም ልጆቹ ፍትሕ በማጣመምና ጉቦ በመቀበል ሥልጣናቸውን የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድ ተጠቅመውበታል።—1 ሳሙኤል 8:1-3

አንድ ቀን የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ አረጋዊው ነቢይ ቀርበው “ልጆችህ ያንተን ፈለግ አይከተሉም” በማለት ምሬታቸውን ገለጹ። (1 ሳሙኤል 8:4, 5) ሳሙኤል ይህን ችግር ያውቅ ነበር? ዘገባው ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚናገረው ነገር የለም። ይሁንና ሳሙኤል እንደ ዔሊ ቸልተኛ አባት እንዳልነበረ እርግጠኞች ነን። ዔሊ ከአምላክ ይልቅ ልጆቹን በማክበር ለፈጸሙት ኃጢአት ተግሣጽ ሳይሰጣቸው በመቅረቱ ይሖዋ ገሥጾታል እንዲሁም ቀጥቶታል። (1 ሳሙኤል 2:27-29) ይሖዋ በሳሙኤል ላይ እንዲህ ያለ ስህተት አላገኘበትም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሳሙኤል ልጆቹ መጥፎ ተግባር እንደሚፈጽሙ ሲሰማ በሃፍረት ስለመሸማቀቁ፣ ስለመጨነቁ ወይም ተስፋ ስለመቁረጡ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም በርካታ ወላጆች፣ በዚያ ጊዜ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መረዳት አይከብዳቸውም። በዚህ የጨለማ ዘመን በወላጆች ሥልጣን ላይ ማመጽና እነሱ የሚሰጡትን ተግሣጽ አለመቀበል እንደወረርሽኝ እየተስፋፋ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጠማቸው ወላጆች ሳሙኤል የተወውን ምሳሌ በመከተል መጽናኛና መመሪያ ማግኘት ይችላሉ። ሳሙኤል ልጆቹ የተከተሉት እምነት የለሽ አካሄድ እርምጃውን በጥቂቱ እንኳ እንዲያዛባበት አልፈቀደም። ወላጆች የሚናገሩት ሐሳብና የሚሰጡት ተግሣጽ ለጊዜው ተቀባይነት ባያገኝ እንኳ ምንጊዜም ለልጆቻቸው ምሳሌ መሆናቸው ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። እንዲሁም ወላጆች ልክ እንደ ሳሙኤል፣ የአባታቸውን የይሖዋ አምላክን ልብ ደስ የማሰኘት አጋጣሚ አላቸው።

“የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን”

የሳሙኤል ልጆች ስግብግብና ራስ ወዳድ መሆናቸው ምን ያህል መጥፎ ውጤት እንዳስከተለ ሊረዱት አይችሉም። የእስራኤል ሽማግሌዎች በመቀጠል “ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” አሉት። ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ከዚያ በኋላ ሳሙኤልን እንደማይቀበሉ ለማሳየት ነው? ለነገሩ ሳሙኤል፣ ለብዙ አሥርተ ዓመታት በሕዝቡ ላይ ሲፈርድ የነበረው ይሖዋን ወክሎ ነው። አሁን ግን እስራኤላውያን እንደ ሳሙኤል ያለ ሌላ ተራ ነቢይ ሳይሆን ንጉሥ እንዲያስተዳድራቸው ተመኙ። በዙሪያቸው እንደነበሩት አሕዛብ እነሱም ንጉሥ እንዲኖራቸው ፈለጉ! ታዲያ ሳሙኤል ምን ተሰማው? ዘገባው ይህ ሐሳብ ሳሙኤልን ‘እንዳላስደሰተው’ ይናገራል።—1 ሳሙኤል 8:5, 6

ሳሙኤል ጉዳዩን በጸሎት ለይሖዋ ባቀረበ ጊዜ ይሖዋ ምን እንደተናገረ ልብ በል፦ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና ሕዝቡ የሚሉህን ሁሉ አድምጥ።” ይህ አባባል ሳሙኤልን ምን ያህል ያጽናናው ይሆን? ይሁንና ሕዝቡ የተናገረው ይህ ሐሳብ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ እንደመሳደብ ይቆጠር ነበር። ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ ማንገሣቸው ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው በመንገር ሕዝቡን እንዲያስጠነቅቅ ለነቢዩ ነገረው። ሳሙኤል የይሖዋን ሐሳብ ሲነግራቸው ሕዝቡ “አይሆንም፤ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን” በማለት አሻፈረኝ አሉ። ምንጊዜም ለአምላኩ ታዛዥ የነበረው ሳሙኤል ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ይሖዋ የመረጠላቸውን ንጉሥ አነገሠላቸው።—1 ሳሙኤል 8:7-19

ሆኖም ሳሙኤል የታዘዘው በምን ዓይነት መንፈስ ነበር? በንዴትና ከአንገት በላይ በሆነ ስሜት ነበር? ያጋጠመው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ልቡን እንዲመርዘውና ምሬት በውስጡ ሥር እንዲሰድ ፈቅዷል? ብዙ ሰዎች እንዲህ ያደርጉ ይሆናል፤ ሳሙኤል ግን እንዲህ አላደረገም። ሳኦልን ንጉሥ አድርጎ ከቀባው በኋላ ይሖዋ የመረጠው ሰው ለመሆኑ እውቅና ሰጥቶታል። ሳሙኤል ሳኦልን ስሞታል፤ ይህም አዲሱን ንጉሥ እንደተቀበለና ለእሱ ለመገዛት ፈቃደኛ እንደሆነ የሚያሳይ ድርጊት ነበር። ከዚያም ለሕዝቡ “እግዚአብሔር የመረጠውን ሰው አያችሁን? ከሕዝቡ ሁሉ የሚስተካከለው ማንም የለም” በማለት ተናግሯል።—1 ሳሙኤል 10:1, 24

ሳሙኤል ሕዝቡ በሠራው ስህተት ላይ ሳይሆን ይሖዋ የመረጠው ሰው ባሉት መልካም ጎኖች ላይ ትኩረት አድርጓል። ከራሱ ጋር በተያያዘ ግን እንደ እስስት በሚለዋወጠው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት በማጣቱ ላይ ሳይሆን ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ ባስመዘገበው ታሪክ ላይ አተኩሯል። (1 ሳሙኤል 12:1-4) በተጨማሪም የአምላክ ሕዝብ ወደፊት ሊያጋጥመው ስለሚችለው መንፈሳዊ አደጋ ምክር በመስጠትና ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት እንዲጠብቁ በማበረታታት ኃላፊነቱን በታማኝነት ተወጥቷል። ሕዝቡም በሳሙኤል ምክር ልባቸው ስለተነካ ወደ ይሖዋ እንዲጸልይላቸው ተማጸኑት። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል “ለእናንተ ከመጸለይ ወደ ኋላ በማለት እግዚአብሔርን መበደል ከእኔ ይራቅ፤ እኔ መልካምና ቅን የሆነውን መንገድ አስተምራችኋለሁ” የሚል ግሩም መልስ ሰጥቷቸዋል።—1 ሳሙኤል 12:21-24

ለአንድ የኃላፊነት ቦታ ወይም መብት ከአንተ ይልቅ ሌላ ሰው በመመረጡ ያዘንክበት ጊዜ አለ? ሳሙኤል የተወልን ምሳሌ ቅናት ወይም ምሬት በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ መፍቀድ እንደማይኖርብን ግሩም ማሳሰቢያ ይሆነናል። አምላክ ለሁሉም ታማኝ አገልጋዮቹ የሚሆን እርካታ የሚያስገኝ ሥራ አለው።

“ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው?”

ሳሙኤል የሳኦልን መልካም ጎን መመልከቱ ተገቢ ነበር፤ ምክንያቱም ሳኦል ልዩ ባሕርያት ያሉት ሰው ነበር። ረጅምና ጥሩ ቁመና የነበረው ከመሆኑም ሌላ ደፋርና ብልህ ነበር። በኋላ ላይ ተለወጠ እንጂ ልኩን የሚያውቅና ልታይ ልታይ የማይልም ሰው ነበር። (1 ሳሙኤል 10:22, 23, 27) ሳኦል ከእነዚህ ባሕርያት በተጨማሪ ሌላ ውድ መብት ነበረው፤ ይህም የፈለገውን የሕይወት ጎዳና የመምረጥና የራሱን ውሳኔ የማድረግ ነፃ ምርጫ ነው። (ዘዳግም 30:19) ታዲያ ይህን መብቱን በጥሩ ሁኔታ ተጠቅሞበታል?

የሚያሳዝነው ነገር፣ አንድ ሰው ሥልጣን አግኝቶ ከፍ ከፍ ሲል እንደ ጉም በንኖ የሚጠፋው የመጀመሪያው ባሕርይ ልክን ማወቅ ነው። ሳኦልም ብዙ ሳይቆይ ትዕቢተኛ መሆን ጀመረ። በሳሙኤል በኩል የተሰጠውን የይሖዋን ትእዛዝ ለመፈጸም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። እንዲያውም በአንድ ወቅት ትዕግሥት አጥቶ ሳሙኤል ብቻ ሊያቀርበው የሚገባውን መሥዋዕት እስከ ማቅረብ ደርሷል። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ጠንከር ያለ ተግሣጽ ለመስጠት የተገደደ ሲሆን የሳኦል ቤተሰብ ከዚያ በኋላ የንግሥና መብት እንደማይኖረው ትንቢት ተናግሯል። ሳኦል የተሰጠውን ተግሣጽ ተቀብሎ መስተካከል ሲገባው መታዘዝ እንደማይፈልግ የሚያሳዩ የከፉ ድርጊቶችን መፈጸሙን ቀጠለ።—1 ሳሙኤል 13:8, 9, 13, 14

በአንድ ወቅት ይሖዋ፣ ሳኦል አማሌቃውያንን እንዲወጋ በሳሙኤል በኩል ነገረው። ይሖዋ ከሰጠው ትእዛዝ መካከል የአማሌቃውያንን ክፉ ንጉሥ አጋግን መግደል ይገኝበታል። ይሁን እንጂ ሳኦል፣ አጋግን ሳይገድል የቀረ ከመሆኑም በላይ መጥፋት ከሚገባቸው ነገሮች መካከል ምርጥ ምርጡን አስቀረ። ሳሙኤል ሊገሥጸው በመጣ ጊዜ ሳኦል ባሕርይው ፈጽሞ እንደተለወጠ የሚያሳዩ ነገሮችን አድርጓል። የተሰጠውን ተግሣጽ በትሕትና ከመቀበል ይልቅ ሰበብ አስባብ ለማቅረብ፣ ያደረገው ነገር ትክክል እንደሆነ ለማስመሰል፣ ጥፋቱ ያን ያህል ከባድ እንዳልሆነ ለማሳመን እንዲያውም ጥፋቱን በሕዝቡ ላይ ለማላከክ ሞከረ። ሳኦል በምርኮ የያዛቸውን አንዳንድ እንስሳት ሳያጠፋ የቀረው ለይሖዋ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ አስቦ እንደሆነ በመናገር የፈጸመው ስህተት ያን ያህል ከባድ እንዳልሆነ ለማስተባበል በሞከረ ጊዜ ሳሙኤል “እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት . . . ይበልጣል” የሚለውን በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀውን ሐሳብ ተናገረ። ሳሙኤል ሳኦልን በድፍረት ከገሠጸው በኋላ ይሖዋ ያሳለፈውን ውሳኔ ይኸውም መንግሥት ከሳኦል እንደተቀደደና ከእሱ ለተሻለ ሌላ ሰው እንደተሰጠ ነገረው።—1 ሳሙኤል 15:1-33

ሳሙኤል ሳኦል በፈጸማቸው ስህተቶች በጣም ተበሳጭቶ ነበር። ጉዳዩ ስላሳሰበው ሌሊቱን በሙሉ ወደ ይሖዋ ሲያለቅስ አደረ። እንዲያውም ለሳኦል ጭምር አለቀሰለት። ሳሙኤል፣ ሳኦል በጣም ጥሩ የሆኑ ብዙ ነገሮችን ሊያከናውን እንደሚችል ተሰምቶት ነበር፤ አሁን ግን በእሱ ላይ የነበረው ተስፋ ሁሉ በንኖ ጠፋ። ከዚህ በፊት የሚያውቀው ሰው ሊሆንለት አልቻለም፤ እነዚያ ሁሉ ግሩም ባሕርያት ጠፍተው አሁን የይሖዋ ጠላት ሆኗል። በዚህ ምክንያት ሳሙኤል ከዚያ በኋላ ሳኦልን ለማየት ፈቃደኛ አልሆነም። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ደግነት በሚንጸባረቅበት ሁኔታ ለሳሙኤል እንዲህ የሚል ተግሣጽ ሰጠው፦ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? ወደ ቤተ ልሔሙ ሰው ወደ እሴይ ስለምልክህ፣ ዘይት በቀንድ ሞልተህ ሂድ፤ ከልጆቹ አንዱ ንጉሥ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ።”—1 ሳሙኤል 15:34, 35፤ 16:1

የይሖዋ ዓላማ ፍጻሜን ማግኘቱ የተመካው ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ባላቸው የሚዋዥቅ እምነት አይደለም። አንድ ሰው ታማኝነቱን ካጓደለ ይሖዋ ፈቃዱን የሚፈጽምለት ሌላ ሰው ይፈልጋል። በመሆኑም አረጋዊው ሳሙኤል በሳኦል ምክንያት ማዘኑን ማቆም አለበት። ሳሙኤል ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት በቤተልሔም ወደሚኖረው እሴይ ቤት ሄደ፤ እሴይ ግርማ ሞገስ ያላቸው በርከት ያሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት። ሆኖም ይሖዋ ገና ከጅምሩ ለሳሙኤል እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ሰጠው፦ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ . . . እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።” (1 ሳሙኤል 16:7) በመጨረሻም ሳሙኤል የሁሉም ታናሽ የሆነውን የእሴይን ልጅ አስጠራ፤ ይህ ልጅ በይሖዋ የተመረጠው ዳዊት ነበር!

ሳሙኤል በሕይወቱ የመጨረሻ ዓመታት፣ ይሖዋ በሳኦል ፋንታ ዳዊትን መተካቱ በእርግጥ ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበረ የማየት አጋጣሚ አግኝቷል። ሳኦል ቀስ በቀስ ተቀይሮ ቀናተኛ፣ ነፍሰ ገዳይና ከሃዲ ሆነ። ዳዊት ግን እንደ ድፍረት፣ እምነትና ታማኝነት ያሉ ግሩም ባሕርያት የነበሩት ሲሆን ንጹሕ አቋሙን የሚጠብቅ ሰው ነበር። ሳሙኤል በሕይወቱ መገባደጃ ላይ እምነቱ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጠንካራ ሆኖ ነበር። ሳሙኤል፣ ይሖዋ ሊፈውሰው ወይም መፍትሔ ሊያገኝለት እንዲያውም ወደ በረከት ሊለውጠው የማይችል ምንም ዓይነት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ እንደሌለ ተመልክቷል። በመጨረሻም ሳሙኤል ወደ አንድ ክፍለ ዘመን በሚጠጋ ዕድሜው አስደናቂ የሕይወት ታሪክ አስመዝግቦ አረፈ። እስራኤላውያን በሙሉ ይህን ታማኝ ሰው በሞት ሲያጡ በእጅጉ ማዘናቸው ምንም አያስደንቅም! በአሁኑ ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ‘የሳሙኤልን የእምነት ምሳሌ እየተከተልኩ ነው?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቃቸው ተገቢ ነው።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳሙኤል ሕዝቡ ያጋጠማቸውን ከፍተኛ ሐዘንና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ እንዲቋቋሙ መርዳት የሚችለው እንዴት ይሆን?

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳሙኤል ልጆቹ መጥፎ እንደሆኑ በተነገረው ጊዜ የተሰማውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት የተቋቋመው እንዴት ነበር?