በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁ ሰው አክባሪ እንዲሆኑ አሠልጥኗቸው

ልጆቻችሁ ሰው አክባሪ እንዲሆኑ አሠልጥኗቸው

ልጆቻችሁ ሰው አክባሪ እንዲሆኑ አሠልጥኗቸው

“ባርኔጣን ማንሳት መንገድን ቀና ያደርጋል” የሚል የጀርመን አባባል አለ። በብዙ ባሕሎች አንድ ሰው ወደ ቤት ሲገባ ወይም ሰዎችን ሰላም ሲል ባርኔጣውን ማውለቁ የአክብሮት መግለጫ እንደሆነ ተደርጎ የሚታይ ሲሆን ለሰውየውም አክብሮት ያተርፍለታል። በመሆኑም ከላይ ያለው አባባል፣ ሰዎች ጥሩ ምግባር ላላቸው ግለሰቦች ደግነት እንደሚያሳዩአቸውና ጥሩ አመለካከት እንደሚኖራቸው ይጠቁማል።

ጥሩ ምግባር ያላቸውን ልጆች ማየት ምንኛ ያስደስታል! በሆንዱራስ ያለ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በተለያየ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ አስፋፊዎች ጋር ከቤት ወደ ቤት የሚያገለግል ሲሆን እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ እኔ ከምናገረው ሐሳብ ይልቅ ጥሩ ሥልጠና ያገኘና ሥርዓታማ የሆነ ልጅ የሰዎችን ትኩረት ይበልጥ እንደሚስብ አስተውያለሁ።”

ለሰዎች አክብሮት ማሳየት እየቀረ ባለበት በዚህ ዘመን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት እንደሚገባን ማወቅ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ነገር ነው። ከዚህም በላይ ቅዱሳን መጻሕፍት “አኗኗራችሁ ስለ ክርስቶስ ከሚገልጸው ምሥራች ጋር የሚስማማ ይሁን” በማለት ይመክሩናል። (ፊልጵ. 1:27፤ 2 ጢሞ. 3:1-5) በመሆኑም ልጆቻችንን ሰው አክባሪ እንዲሆኑ ማሠልጠናችን በጣም አስፈላጊ ነው። ልጆቻችሁ ከአንገት በላይ የሆነ ትሕትና እንዲያሳዩ ሳይሆን ከልብ የመነጨ አክብሮት ማሳየትን እንዲማሩ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? *

ጥሩ ምግባርን በምሳሌ ማስተማር

ልጆች ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር በማየት ይማራሉ። በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸው ሥርዓታማ እንዲሆኑ ማሠልጠን የሚችሉበት ዋነኛው መንገድ እነሱ ራሳቸው ጥሩ ምግባር በማሳየት ነው። (ዘዳግም 6:6, 7) ልጆቻችሁ ትሑት እንዲሆኑ ማስተማር አስፈላጊ ቢሆንም ይህ ብቻ በቂ አይደለም። ሥልጠና ከመስጠት በተጨማሪ እናንተ ራሳችሁ ጥሩ ምሳሌ መሆናችሁ በጣም አስፈላጊ ነው።

በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ በነጠላ ወላጅ ያደገችውን የፖላን * ሁኔታ እንመልከት። ፖላ፣ እገሌ ከገሌ ሳትል ሰውን ሁሉ ታከብራለች። እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ለማዳበር የረዳት ምንድን ነው? “እማዬ ጥሩ ምሳሌ መሆኗ እኛም ሰዎችን ማክበር ቀላል እንዲሆንልን አድርጓል” በማለት ተናግራለች። ዎልተር የተባለ አንድ ክርስቲያን፣ ልጆቹ እናታቸው የይሖዋ ምሥክር ባትሆንም እንዲያከብሯት አሠልጥኗቸዋል። “ልጆቼ እናታቸውን እንዲያከብሯት እኔ ራሴ ምሳሌ ለመሆን ጥረት አደርጋለሁ፤ ባለቤቴን መቼም ቢሆን መጥፎ ነገር አልናገራትም” ብሏል። ዎልተር ልጆቹን ሁልጊዜ በአምላክ ቃል መሠረት የሚያሠለጥን ከመሆኑም በላይ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ይጸልይ ነበር። ከልጆቹ አንዱ በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አቅኚ ነው። ልጆቹ አባታቸውንም ሆነ እናታቸውን ይወዷቸዋል እንዲሁም ያከብሯቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” ይላል። (1 ቆሮ. 14:33) ይሖዋ ሁሉን ነገር የሚያደርገው በሥርዓት ነው። ክርስቲያኖች ይህን አምላካዊ ባሕርይ በማንጸባረቅ ቤታቸው ያልተዝረከረከ እንዲሆን ጥረት ማድረግ አለባቸው። አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት በየቀኑ አልጋቸውን እንዲያነጥፉ፣ ልብሳቸውን በቦታው እንዲያስቀምጡና አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ አሠልጥነዋቸዋል። በቤታችሁ ውስጥ ሁሉ ነገር ሥርዓታማና ንጹሕ ከሆነ ልጆቻችሁም ክፍላቸውንና የራሳቸውን ዕቃ በንጽሕና ለመያዝ ይነሳሳሉ።

ልጆቻችሁ በትምህርት ቤት ለሚሰጣቸው ትምህርት ምን አመለካከት አላቸው? አስተማሪዎቻቸው ለሚያደርጉላቸው ነገር አድናቆታቸውን ይገልጻሉ? እናንተስ ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ለአስተማሪዎቻቸው አድናቆታችሁን ትገልጻላችሁ? ልጆቻችሁ ለሚሰጣቸው የትምህርት ቤት ሥራም ሆነ ለአስተማሪዎቻቸው እናንተ ያላችሁ አመለካከት በልጆቻችሁ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። አስተማሪዎቻቸውን የማመስገን ልማድ እንዲያዳብሩ ለምን አታበረታቷቸውም? አስተማሪም ሆነ የሕክምና ባለሙያ ወይም ሱቅ ውስጥ የሚሠራ ሰው አሊያም ሌላ ማንኛውም ግለሰብ ለሰጠን አገልግሎት ምስጋናችንን መግለጽ አክብሮት ለማሳየት የሚያስችል ግሩም መንገድ ነው። (ሉቃስ 17:15, 16) በትሕትናቸውና በመልካም ምግባራቸው አብረዋቸው ከሚማሩት ልጆች የሚለዩ ክርስቲያን ልጆች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።

የክርስቲያን ጉባኤ አባላት መልካም ሥነ ምግባር በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን አለባቸው። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ልጆች “እባክህ” እና “አመሰግናለሁ” እንደሚሉት ያሉ አክብሮትን የሚያንጸባርቁ ቃላትን ሲጠቀሙ መስማት እንዴት ያስደስታል! አዋቂዎች በስብሰባዎች ወቅት ለሚሰጡ መመሪያዎች ትኩረት በመስጠት ለይሖዋ አክብሮት ሲያሳዩ ልጆችም የእነሱን ምሳሌ ለመከተል ይነሳሳሉ። ልጆች በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ወንድሞች የሚያሳዩትን መልካም ምግባር በመመልከት ለሰዎች አክብሮት ማሳየትን መማር ይችላሉ። ለምሳሌ አንድሩ የተባለው የአራት ዓመት ልጅ በትልልቅ ሰዎች መሃል አቋርጦ በሚያልፍበት ጊዜ “ይቅርታ” ማለትን ተምሯል።

ወላጆች፣ ልጆቻቸው መልካም ምግባር እንዲኖራቸው ለማስተማር ሌላስ ምን ማድረግ ይችላሉ? በአምላክ ቃል ውስጥ የተጠቀሱት በርካታ ምሳሌዎች በያዙት ቁም ነገር ላይ ጊዜ ወስደው ከልጆቻቸው ጋር መወያየት ይችላሉ፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ አለባቸው።—ሮም 15:4

በመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች በመጠቀም አስተምሩ

የሳሙኤል እናት፣ ልጇ በሊቀ ካህኑ ዔሊ ፊት እንዲሰግድ ሳታሠለጥነው አልቀረችም። ሐና፣ ሳሙኤልን ወደ ማደሪያው ድንኳን ስትወስደው የሦስት ወይም የአራት ዓመት ልጅ ሳይሆን አይቀርም። (1 ሳሙ. 1:28) ትንንሽ ልጆቻችሁ “እንደምን አደራችሁ፣” “እንደምን ዋላችሁ፣” “እንደምን አመሻችሁ” እንደሚሉት ያሉ ወይም በአካባቢያችሁ የተለመዱ ሌሎች ሰላምታዎችን እንዲሰጡ ልታሠለጥኗቸው ትችላላችሁ? እንደ ብላቴናው ሳሙኤል ሁሉ ልጆቻችሁም “በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ሞገስ” ሊያገኙ ይችላሉ።—1 ሳሙ. 2:26 የ1954 ትርጉም

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ዘገባዎች በመጠቀም አክብሮት በማሳየትና ባለማሳየት መካከል ያለውን ልዩነት ለልጆቻችሁ ለምን አታስረዷቸውም? ለምሳሌ ያህል፣ ታማኝ ያልነበረው የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ፣ ነቢዩ ኤልያስን ወደ እሱ እንዲያመጡት “አንድ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ወታደሮቹ ጋር” ልኮ ነበር። የአምሳ አለቃው ወደ ነቢዩ በመሄድ “ንጉሡ፣ ‘ና ውረድ’ ይልሃል” የሚል ትእዛዝ አስተላለፈ። አንድን የአምላክ ወኪል ለማናገር ተገቢው መንገድ ይህ አልነበረም። በዚህ ጊዜ ኤልያስ ምን ምላሽ ሰጠ? “እኔ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንሁ፣ እሳት ከሰማይ ወርዳ፣ አንተንና አምሳውን ሰዎችህን ትብላ!” አለው። እንዳለውም ሆነ። “እሳት ከሰማይ ወርዳ የአምሳ አለቃውንና ሰዎቹን ፈጽማ በላች።”—2 ነገ. 1:9, 10

ለሁለተኛ ጊዜ ሌላ የአምሳ አለቃ ወደ ኤልያስ ተላከ። ይህም ሰው ቢሆን ኤልያስ አብሮት እንዲሄድ ትእዛዝ ለመስጠት ሞከረ። በድጋሚ እሳት ከሰማይ ወርዶ ሰዎቹን በላቸው። ከዚያም ለሦስተኛ ጊዜ አንድ የአምሳ አለቃ ወደ ኤልያስ ተላከ። ይህ ሰው ለኤልያስ አክብሮት እንዳለው አሳይቷል። ለኤልያስ ትእዛዝ ከማስተላለፍ ይልቅ ተንበርክኮ እንዲህ በማለት ለመነው፦ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ እባክህ የእኔና የእነዚህ የአምሳዎቹ አገልጋዮችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን። እነሆ፤ እሳት ከሰማይ ወርዳ፣ የፊተኞቹን ሁለት አምሳ አለቆችና ሰዎቻቸውን ሁሉ በላች፤ አሁን ግን ሕይወቴ በፊትህ የከበረች ትሁን።” ይህ ሰው ኤልያስን ያናገረው አክብሮት በተሞላበት መንገድ ነው፤ ምናልባትም እንዲህ ያደረገው ፍርሃት ስላደረበት ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ግን የአምላክ ነቢይ እንዲህ ባለው ሰው ላይ እሳት እንዲወርድበት እንደማያደርግ የታወቀ ነው! እንዲያውም የይሖዋ መልአክ ኤልያስን ከዚህ የአምሳ አለቃ ጋር እንዲሄድ ነገረው። (2 ነገ. 1:11-15) ይህ ዘገባ አክብሮት ማሳየት ያለውን ጠቀሜታ ጎላ አድርጎ አያሳይም?

የሮም ወታደሮች ሐዋርያው ጳውሎስን ከቤተ መቅደሱ አውጥተው በወሰዱት ጊዜ ጳውሎስ ሐሳቡን መግለጽ መብቱ እንደሆነ በማሰብ ዝም ብሎ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ሻለቃውን “አንድ ነገር እንድነግርህ ትፈቅድልኛለህ?” በማለት በአክብሮት ጠየቀው። በዚህም የተነሳ ጳውሎስ የመከላከያ ሐሳቡን የመናገር ዕድል ተሰጠው።—ሥራ 21:37-40

ኢየሱስ ለፍርድ ቀርቦ በነበረበት ወቅት በጥፊ ተመትቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የተፈጸመበት ድርጊት ትክክል አለመሆኑን መግለጽ ያለበት እንዴት እንደሆነ እንደሚያውቅ አሳይቷል። “የተሳሳተ ነገር ተናግሬ ከሆነ ስህተት መናገሬን መሥክር፤ ትክክል ከተናገርኩ ግን ለምን ትመታኛለህ?” በማለት ተናገረ። በመሆኑም ማንም ሰው ኢየሱስ የተናገረበት መንገድ ተገቢ አይደለም ሊል አልቻለም።—ዮሐ. 18:22, 23

ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቃል ጠንከር ያለ እርማት በሚሰጠን ጊዜ ምን ምላሽ መስጠት እንደምንችል እንዲሁም ቀደም ሲል የሠራነውን ስህተት ወይም ጥፋታችንን አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ማመን የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚጠቁሙ ምሳሌዎችን ይዟል። (ዘፍ. 41:9-13፤ ሥራ 8:20-24) ለምሳሌ አቢግያ፣ ባለቤቷ ናባል ለዳዊት አክብሮት የጎደለው ምላሽ በመስጠቱ ዳዊትን ይቅርታ ጠይቃለች። ከዚህም ባሻገር ለዳዊትና አብረውት ለነበሩት ሰዎች የሚሆን ምግብ በስጦታ መልክ አምጥታለች። ዳዊት አቢግያ ባደረገችው ነገር ልቡ ስለተነካ ናባል ከሞተ በኋላ አግብቷታል።—1 ሳሙ. 25:23-41

ልጆቻችሁ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸውም ሆነ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ መልካም ምግባር ማሳየት እንዲችሉ ሰው አክባሪ እንዲሆኑ ልታሠለጥኗቸው ይገባል። በዚህ መንገድ ‘ብርሃናችን በሰው ፊት እንዲበራ’ ማድረጋችን ‘በሰማያት ያለውን አባታችንን ያስከብረዋል።’—ማቴ. 5:16

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 እርግጥ ነው፣ ልጆች አዋቂዎችን ማክበር አለባቸው ሲባል መጥፎ ዓላማ ያላቸው ሰዎች የሚሏቸውን ነገር ሁሉ ያደርጋሉ ማለት እንዳልሆነ ወላጆች ግልጽ ሊያደርጉላቸው ይገባል። የጥቅምት 2007 ንቁ! ከገጽ 3-11 ተመልከት።

^ አን.7 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።