በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምንም ያህል ጥረት ቢደረግለት አያስቆጭም!

ምንም ያህል ጥረት ቢደረግለት አያስቆጭም!

ምንም ያህል ጥረት ቢደረግለት አያስቆጭም!

ልጆችን “በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው [ቀርጾ]” ለማሳደግ የቤተሰብ አምልኮና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። (ኤፌ. 6:4) ይሁንና ወላጆች ከሆናችሁ ልጆች በቀላሉ እንደሚሰላቹ ሳታስተውሉ አትቀሩም። ታዲያ በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ልጆች እንዳይሰለቻቸው ምን ማድረግ ትችላላችሁ? አንዳንድ ወላጆች ምን እንዳደረጉ እስቲ እንመልከት።

በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ጆርጅ እንዲህ ይላል፦ “ልጆቻችን ትንንሽ በነበሩበት ጊዜ እኔና ባለቤቴ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን አስደሳችና የማይሰለች እንዲሆን ለማድረግ እንጥር ነበር። አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የሚለውን መጽሐፍ ስናነብ ሁላችንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጹት ባለ ታሪኮች በመልበስ ታሪኩን በድራማ መልክ እንሠራዋለን። ለድራማው የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ለምሳሌ ሰይፍ፣ የንጉሥ ዘንግ፣ ቅርጫቶችና ሌሎች ነገሮች እናዘጋጃለን። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን አዘጋጅተን ‘እኔ ማን ነኝ?’ እንደሚሉት ያሉ ጨዋታዎችን እንጫወት ነበር፤ እንዲሁም ቀላልና ከባድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን የሚያካትት ጨዋታ አዘጋጅተን ነበር። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ የቤተሰብ አምልኳችን አንድ ላይ ሆነን ምርምር ማድረግን ወይም የሆነ ነገር መሥራትን የሚያካትት እንዲሆን እናደርግ ነበር፤ ለምሳሌ የኖኅን መርከብ እንሠራለን ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ክንውኖችን በቅደም ተከተል እናስቀምጣለን። አንዳንድ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሰው የምናገኛቸውን ሰዎች ወይም ታሪኮች በሥዕል ለማስቀመጥ እንሞክራለን። አሁን በ⁠ኤፌሶን 6:11-17 ላይ ያለውን መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ እየሣልን ሲሆን እያንዳንዱ የጦር ትጥቅ ምን እንደሚያመለክት ሁላችንም በየተራ እናብራራለን። እነዚህ ዘዴዎች የቤተሰብ ጥናታችን አስደሳች እንዲሆን ለማድረግ ረድተውናል።”

በሚሺገን፣ ዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ዴቢ የተባለች አንዲት እናት እንዲህ ትላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ልጃችን ዕድሜዋ ሦስት ዓመት አካባቢ በነበረበት ወቅት ትምህርቱን በትኩረት እንድትከታተል ማድረግ በጣም ቸግሮን ነበር። አንድ ቀን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ ከሚለው መጽሐፍ ስለ ይስሐቅና ስለ ርብቃ የሚናገረውን ታሪክ እያነበብኩላት ሳለ በሁለት አሻንጉሊቶች በመጠቀም እነሱ እንደሚናገሩ እያስመሰልኩ ታሪኩን መተረክ ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ ልጃችን ታሪኩን በትኩረት ትከታተል ጀመር! በቀጣዮቹ ወራት በእነዚህ ሁለት አሻንጉሊቶች በመጠቀም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ለልጃችን እንተርክላት ነበር። አንድን ዘገባ ካነበብን በኋላ ልጃችን ታሪኩን በድራማ መልክ ለመሥራት የሚያገለግሉ አሻንጉሊቶችን ወይም ሌሎች ዕቃዎችን መፈለግ ትጀምራለች። እነዚህን ነገሮች ለማግኘት የምታደርገው ጥረት እንደ ጨዋታ ሆኖላት ነበር! የረዓብን ቤት ለመሥራት በጫማ ካርቶን የተጠቀምን ሲሆን ከዚያም ቀይ ሪባን አንጠለጠልንበት። በ⁠ዘኍልቍ 21:4-9 ላይ ያለውን ስለ ነሐስ እባብ የሚናገረውን ታሪክ ስናነብላት ደግሞ አምስት ጫማ [1.5 ሜትር] ርዝመት ያለውን በእባብ መልክ የተሠራ አሻንጉሊት በመጥረጊያ እንጨት ላይ ጠመጠምነው። ታሪኮቹን ስናነብላት የምንጠቀምባቸውን ቁሳቁሶች በአንድ ትልቅ የሸራ ቦርሳ ውስጥ አስቀመጥናቸው። ልጃችን ብዙውን ጊዜ ሳሎን ቤት ቁጭ ብላ ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ቦርሳዋን’ ስትበረብር ስናያት በጣም ደስ ይለናል። በልጅ አፏ እየተኮላተፈች ታሪኮቹን ለመሥራት ስትሞክር መመልከት ምን ያህል እንደሚያስደስተን መገመት ትችላላችሁ!”

ልጆችን ማሳደግ ቀላል ነገር አይደለም፤ ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለመርዳትም በየሳምንቱ የሚደረግ ጥናት ብቻ በቂ አይደለም። ያም ሆኖ የቤተሰብ አምልኮና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጨማሪ መንፈሳዊ መመሪያዎችን ለመስጠት እንደ መሠረት ሊሆን ይችላል። በእርግጥም ልጆችን ለማሠልጠን ምንም ያህል ጥረት ቢደረግ አያስቆጭም!