በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

“ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . .”—ማቴዎስ 24:14

ኢየሱስ ዝነኛ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ውስጥ “መንግሥትህ ይምጣ” የሚለውን ልመና አካትቷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ጸሎት የሸመደዱት ሲሆን በየጊዜው ይደግሙታል። አንድ መዝገበ ቃላት ይህን ጸሎት “ሁሉም የክርስትና ሃይማኖቶች ምንጊዜም በአምልኮ ልማዳቸው ውስጥ የሚያካትቱት ዓብይ ጸሎት” በማለት ፈትቶታል። ይሁን እንጂ ጸሎቱን የሚደግሙት አብዛኞቹ ሰዎች ይህ መንግሥት ምን እንደሆነ ወይም በሚመጣበት ጊዜ ምን እንደሚያደርግ አያውቁም።—ማቴዎስ 6:9, 10

ይህ መሆኑ ምንም አያስደንቅም። የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ስለ አምላክ መንግሥት ምንነት የሚሰጡት ማብራሪያ እርስ በርሱ የሚጋጭ፣ ግራ የሚያጋባና ለመረዳት የሚያስቸግር ነው። አንድ ጸሐፊ ስለ አምላክ መንግሥት እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ከሰው በላይ የሆነ ኃይል ነው። . . . ሕያው ከሆነው አምላክ ጋር በመንፈስ የምንገናኝበት መስመር ነው። . . . ወንዶችና ሴቶች መዳን ለማግኘት የሚያስችላቸው ከአምላክ ጋር የሚፈጥሩት ዝምድና ነው።” ሌላ ጸሐፊ ደግሞ የመንግሥቱን ወንጌል “ስለ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መመሪያ” በማለት ገልጸውታል። ካቴኪዝም ኦቭ ዘ ካቶሊክ ቸርች የተባለው መጽሐፍ ደግሞ “የአምላክ መንግሥት ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ጽድቅ፣ ሰላምና ደስታ ነው” በማለት ይናገራል።

በዚህ መጽሔት ገጽ 2 ላይ የአምላክን መንግሥት በተመለከተ ግልጽ ማብራሪያ ማግኘት ትችላለህ። እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ መንግሥት ማለትም በሰማይ ያለው እውን መስተዳድር በቅርቡ ክፋትን ሁሉ በማጥፋት ምድርን ወደ ገነትነት [ይለውጣል]።” እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሐሳብ የሚደግፈው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ወደፊት መላውን ምድር የሚያስተዳድሩ ገዥዎች

የአምላክ መንግሥት በንጉሥ የሚመራ መስተዳድር ሲሆን ንጉሡም ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ በሰማይ ንጉሣዊ ሥልጣን ሲቀበል በራእይ የተመለከተው ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሌሊት ባየሁት ራእይ፣ የሰውን ልጅ የሚመስል [ኢየሱስ] ከሰማይ ደመና ጋር ሲመጣ አየሁ፤ ወደ ጥንታዌ ጥንቱ [ይሖዋ አምላክ] መጣ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና [“ብሔራትና፣” NW] ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።”—ዳንኤል 7:13, 14

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዳንኤል መጽሐፍ፣ ይህ መንግሥት የተቋቋመው በአምላክ እንደሆነ፣ ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት እንደሚያጠፋና ለዘላለም እንደሚኖር ጭምር ይገልጻል። ዳንኤል ምዕራፍ 2 አምላክ ለባቢሎን ንጉሥ ሕልም እንዳሳየው ይናገራል፤ ንጉሡ በተከታታይ የሚነሱትን ኃያላን የዓለም መንግሥታት የሚወክል አንድ ግዙፍ ምስል በሕልሙ ተመልክቷል። ነቢዩ ዳንኤል ደግሞ ለንጉሡ ሕልሙን ፈትቶለታል። ዳንኤል እንደጻፈው “በሚመጡት ዘመናት” ማለትም በመጨረሻዎቹ ቀናት “የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳንኤል 2:28, 44

የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ምድርን የሚያስተዳድረው ብቻውን አይደለም። በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያቱና ሌሎች ታማኝ ሰዎች ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ እንደሚሄዱና በዙፋን ላይ እንደሚቀመጡ ቃል ገብቷል። (ሉቃስ 22:28-30) ኢየሱስ እንደተናገረው መንግሥቱ የሚቋቋመው በሰማይ ላይ ስለሆነ ዙፋኑ ቃል በቃል ዙፋንን አያመለክትም። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ተባባሪ ገዥዎች “ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ” የመጡ እንደሆኑ ይገልጻል። እነዚህ ሰዎች “ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት [ይሆናሉ]፤ በምድርም ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።”—ራእይ 5:9, 10

ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው መልእክት ምሥራች የሆነው ለምንድን ነው?

ክርስቶስ ኢየሱስ ‘በልዩ ልዩ ቋንቋ በሚናገሩ ሰዎች፣ ብሔራትና ሕዝቦች’ ላይ እንዲገዛ ሥልጣን እንደተሰጠውና አብረውት የሚሆኑትም ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው’ እንደሚገዙ ልብ በል። ታዲያ የዚህ መንግሥት ተገዥዎች የሚሆኑት እነማን ናቸው? ዛሬ እየተሰበከ ላለው ምሥራች አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች የመንግሥቱ ተገዥዎች ይሆናሉ። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ከሞት ተነስተው ለዘላለም የመኖር ተስፋ የሚያገኙ ሰዎችም ከተገዥዎቹ መካከል ይሆናሉ።

እነዚህ ሰዎች በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የሚያገኟቸው በረከቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልብ በሚነካ መንገድ ተገልጸዋል። ከበረከቶቹ መካከል ጥቂቶቹን ተመልከት፦

“ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል፤ ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል።”መዝሙር 46:9

“ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም።”ኢሳይያስ 65:21, 22

“[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”ራእይ 21:3, 4

“በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል።”ኢሳይያስ 35:5, 6

“በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ [የኢየሱስን ድምፅ] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ [ይወጣሉ]።”—ዮሐንስ 5:28, 29

“ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”መዝሙር 37:11

በእርግጥም ይህ የምሥራች ነው! ከዚህም በተጨማሪ ፍጻሜያቸውን ያገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የአምላክ መንግሥት በመላዋ ምድር ላይ የጽድቅ አገዛዙን የሚጀምርበት ጊዜ ቅርብ እንደሆነ ይጠቁማሉ።