በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመንግሥቱ ምሥራች ምንድን ነው?

የመንግሥቱ ምሥራች ምንድን ነው?

የመንግሥቱ ምሥራች ምንድን ነው?

“ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . .”—ማቴዎስ 24:14

ክርስቲያኖች፣ ስለ አምላክ መንግሥት በመናገር ማለትም ይህ መንግሥት ወደፊት ምድርን በጽድቅ የሚያስተዳድር ዓለም አቀፋዊ አገዛዝ እንደሆነ ለሌሎች በመግለጽ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ መስበክ አለባቸው። ሆኖም “ምሥራች” የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላም መንገድ ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ‘ስለ ማዳን የሚገልጸው ምሥራች’ (መዝሙር 96:2 NW)፣ ‘የአምላክ ምሥራች’ (ሮም 15:16) እና “ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸው ምሥራች” የሚሉ አገላለጾችን እናገኛለን።—ማርቆስ 1:1

በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል ኢየሱስ የተናገረውና ደቀ መዛሙርቱ የጻፉት እውነት በሙሉ በምሥራቹ ውስጥ ይካተታል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለተከታዮቹ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።” (ማቴዎስ 28:19, 20) በመሆኑም የእውነተኛ ክርስቲያኖች ሥራ ስለ መንግሥቱ ለሌሎች በመናገር ብቻ መወሰን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ መጣርም ይኖርባቸዋል።

በዚህ ረገድ አብያተ ክርስቲያናት ምን እያደረጉ ነው? አብዛኞቹ ቀድሞውኑም የአምላክ መንግሥት ምንነት ስላልገባቸው ሌሎችን በትክክል ማስተማር አይችሉም። ይልቁንስ መስበክ የሚቀናቸው ስለ ኃጢአት ይቅርታና በኢየሱስ ስለ ማመን የሚናገሩትን ለሰዎች ጆሮ የሚጥሙ ትምህርቶችን ነው። በተጨማሪም በማኅበራዊ ጉዳዮች ረገድ አንዳንድ ተግባራትን በማከናወን ወይም ለተቸገሩ ሰዎች ሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችንና መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ሰዎችን ወደ ሃይማኖታቸው ለመሳብ ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ ያለው ጥረት የምዕመናንን ብዛት ሊጨምር ቢችልም ኢየሱስ ካስተማራቸው ትምህርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር ከልብ ጥረት የሚያደርጉ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ማፍራት አይችልም።

አንድ የሃይማኖት ምሑር እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ኢየሱስን የሚከተሉ ደቀ መዛሙርት ወይም ተማሪዎች ማፍራትና እነዚህን ሰዎች ኢየሱስ የተናገረውን ሁሉ በተግባር እንዲያውሉ ማስተማር እንዳለብን የሚክድ የክርስትና ሃይማኖት ምሑር አሊያም መሪ ብትፈልጉ አታገኙም ማለት ይቻላል። . . . ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠው መመሪያ ምንም አያሻማም። እኛ ግን እሱ የተናገረውን እያደረግን አይደለም። በቁም ነገር ልንሠራው አልሞከርንም። እንዴት መሠራት እንዳለበት እንኳ የምናውቅ አይመስለኝም።”

በተመሳሳይም ዩናይትድ ስቴትስ በሚኖሩ ካቶሊኮች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደጠቆመው 95 በመቶ የሚሆኑት እምነታቸው ምሥራቹን መስበክ እንደሚጠብቅባቸው ይሰማቸዋል። ሆኖም ብዙዎች ይህን ለማድረግ ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ስለ መንግሥቱ መናገር ሳይሆን ሕይወታቸውን ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን በሚችል መንገድ መምራት እንደሆነ ይሰማቸዋል። በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱት አንዷ “ወንጌላዊነት ሲባል ዝም ብሎ መናገር፣ መናገር፣ መናገር ማለት አይደለም። እኛ ራሳችን ምሥራች መሆን አለብን” ብላለች። ጥናቱን የመራው ዩ ኤስ ካቶሊክ የተባለው መጽሔት፣ “ቤተ ክርስቲያኒቷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተወራ ባለው ልጆችን የማስነወር አስደንጋጭ ዜናና ችግር በሚፈጥሩት ትምህርቶቿ መጥፎ ስም በማትረፏ” ምክንያት ብዙዎች ስለ እምነታቸው ለሌሎች ከመናገር ወደኋላ እንደሚሉ ተናግሯል።

አንድ የሜቶዲስት ጳጳስ እሳቸው ያሉበት ቤተ ክርስቲያን እንደተከፋፈለ፣ ግራ መጋባት እንደነገሠበት፣ ምዕመናኑ የተሰጣቸውን ተልእኮ ለመወጣት የሚያስችል ድፍረት እንደሌላቸውና የሥነ ምግባር አቋማቸው ከሌላው ማኅበረሰብ በምንም እንደማይለይ በምሬት ተናግረዋል። እኚህ ጳጳስ በተስፋ መቁረጥ ስሜት “ታዲያ የመንግሥቱን ወንጌል የመስበክ ኃላፊነቱን የሚወስደው ማን ነው?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

እርግጥ እኚህ ጳጳስ የዚህን ጥያቄ መልስ አልተናገሩም። ይሁንና ጥያቄው መልስ አለው። መልሱን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ማግኘት ትችላለህ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ምሥራቹ ስለ አምላክ መንግሥትና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት በማሳደር ስለሚገኘው መዳን የሚገልጽ ነው