በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዲያብሎስን የፈጠረው አምላክ ነው?

ዲያብሎስን የፈጠረው አምላክ ነው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ዲያብሎስን የፈጠረው አምላክ ነው?

▪ መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉንም ነገሮች [የፈጠረው]” አምላክ እንደሆነ ስለሚናገር አንዳንዶች ዲያብሎስንም የፈጠረው አምላክ መሆን አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። (ኤፌሶን 3:9፤ ራእይ 4:11) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ይህ አመለካከት ትክክል እንዳልሆነ በግልጽ ይናገራል።

ይሖዋ በኋላ ላይ ዲያብሎስ የሆነውን አካል ፈጥሯል። በመሆኑም የአምላክ ዋነኛ ተቃዋሚ የሆነው ይህ አካል በይሖዋ ወደ ሕልውና መጥቷል የሚለው ሐሳብ ቅዱሳን መጻሕፍት ፈጣሪን ከሚገልጹበት መንገድ ጋር ሊስማማ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን አስመልክቶ “ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው” ይላል። (ዘዳግም 32:3-5) ከዚህ ጥቅስ መመልከት እንደምንችለው ሰይጣን በአንድ ወቅት ፍጹምና ጻድቅ ከሆኑት የአምላክ መላእክት መካከል አንዱ ነበር። ኢየሱስ በ⁠ዮሐንስ 8:44 ላይ ዲያብሎስ “በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም” ብሎ መናገሩ በአንድ ወቅት ሰይጣን እውነተኛና ነቀፋ የሌለበት እንደነበረ ይጠቁማል።

ይሁንና የማሰብ ችሎታ እንዳላቸው ሌሎች የይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ በኋላ ላይ ሰይጣን የሆነው መልአክም ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን የመምረጥ ነፃነት ነበረው። አምላክን በሚጻረር መንገድ ለመሄድ በመምረጥና የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ከእሱ ጎን እንዲሰለፉ በማድረግ ራሱን ሰይጣን ማለትም “ተቃዋሚ” አደረገ።—ዘፍጥረት 3:1-5

ይህ ክፉ የሆነ መንፈሳዊ ፍጥረት ራሱን ዲያብሎስ ማለትም “ስም አጥፊ” አደረገ። ከእባቡ በስተጀርባ የነበረውና ተንኮል ያዘለ ውሸት ተጠቅሞ ሔዋን ፈጣሪ የሰጠውን ግልጽ ሕግ እንድትጥስ ያደረገው በዓይን የማይታይ አስመሳይ አካል ሰይጣን ነበር። ኢየሱስ ሰይጣንን “የውሸት አባት” ብሎ የጠራው በዚህ ምክንያት ነው።—ዮሐንስ 8:44

ታዲያ የራሱ ድክመትም ሆነ የሌሎች አሉታዊ ተጽዕኖ የሌለበት ፍጹም መንፈሳዊ ፍጡር መጥፎ ዝንባሌ እንዴት ሊኖረው ቻለ? ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሰይጣን ለአምላክ ብቻ ሊሰጥ የሚገባውን አምልኮ ለማግኘት ቋምጦ የነበረ ሲሆን ሰዎች ለይሖዋ ከመገዛት ይልቅ በእሱ አገዛዝ ሥር እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚችል ተሰምቶት ነበር። ገዢ የመሆን ሕልሙን ከማስወገድ ይልቅ ያውጠነጥነው ስለነበር ያሰበውን በተግባር እስኪፈጽም ድረስ ምኞቱ ተቆጣጥሮታል። የያዕቆብ መጽሐፍ ይህንን ሂደት እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአት ደግሞ በተግባር ሲፈጸም ሞትን ያስከትላል።”—ያዕቆብ 1:14, 15፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:6

በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በሒሳብ መዝገቦች ላይ የሐሰት መረጃዎችን በማስፈር ከተቀጠረበት ድርጅት ገንዘብ አጭበርብሮ መውሰድ እንደሚችል የተሰማውን አንድ የሒሳብ ባለሙያ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ይህ ሰው እንዲህ ያለውን መጥፎ ሐሳብ ቶሎ ብሎ ከአእምሮው ማስወገድ ይችላል። እንዲህ ከማድረግ ይልቅ ባሰበው ነገር ላይ ማውጠንጠኑን ከቀጠለ ግን ምኞቱ አድጎ ለተግባር ሊያንቀሳቅሰው ይችላል። ይህ ግለሰብ ያሰበውን ከፈጸመ ራሱን ሌባ አደረገ ማለት ነው። የፈጸመውን ወንጀል ለመሸፋፈን ከዋሸ ደግሞ ውሸታም መሆኑም አይቀርም። በተመሳሳይም አምላክ የፈጠረው መልአክ መጥፎ ምኞቶችን በማውጠንጠንና እነዚህን ምኞቶች በተግባር በመፈጸም የመምረጥ ነፃነቱን ሌሎቹን ለማታለልና በአባቱ ላይ ለማመፅ ተጠቅሞበታል፤ በዚህ መንገድ ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ አደረገ።

የሚያስደስተው ነገር አምላክ እሱ በወሰነው ጊዜ ሰይጣን ዲያብሎስን ያጠፋዋል። (ሮም 16:20) እስከዚያው ድረስ ግን ይሖዋ አምላክ ለአገልጋዮቹ የሰይጣንን እቅዶች በተመለከተ መረጃ የሚሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ በዲያብሎስ መሠሪ ዘዴዎች እንዳይሸነፉ ጥበቃ ያደርግላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 2:11፤ ኤፌሶን 6:11) በመሆኑም በተቻለህ መጠን ‘ዲያብሎስን ተቃወም፤ እሱም ከአንተ ይሸሻል።’—ያዕቆብ 4:7

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ፍጹም መንፈሳዊ ፍጡር የነበረው መልአክ አምላክን በሚጻረር መንገድ ለመሄድ በመምረጥ ራሱን ሰይጣን አደረገ