በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ሕንዳውያን ሆነንም እንኳ ይሖዋ ይወደናል?”

“ሕንዳውያን ሆነንም እንኳ ይሖዋ ይወደናል?”

ከሜክሲኮ የተላከ ደብዳቤ

“ሕንዳውያን ሆነንም እንኳ ይሖዋ ይወደናል?”

የኦዳም ቋንቋ ተናጋሪ የሆነው ሜለሲዮ ሥራ ፍለጋ አልፎ አልፎ ከሚኖርበት ተራራማ አካባቢ ወደታች ይወርዳል። በዚህ ጊዜ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን ለአካባቢው ሕዝብ የሚሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ይዞ ይመለሳል። ሜለሲዮ አንድ ሰው እነሱ ወደሚኖሩበት አካባቢ መጥቶ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስተምራቸው ሁልጊዜ ይለምን ነበር።

የኦዳም ጎሳ አባላት በሰሜን ማዕከላዊ ሜክሲኮ በሚገኝ ተራራማ የሆነ ገለልተኛ ክልል ይኖራሉ፤ ይህ ቦታ በጣም ቅርብ ከሚባለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ 240 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ያም ቢሆን የተወሰንን ወንድሞች ሄደን ልንጠይቃቸው ወሰንን።

አንዲት አነስተኛ የጭነት መኪና ስላገኘን ድንኳኖችን፣ መተኛ ከረጢቶችን እንዲሁም ለሦስት ቀን የሚበቃ ምግብና ነዳጅ ይዘን ከዱራንጎ ከተማ በመነሳት ጉዞ ጀመርን። ከዱራንጎ የተነሳነው ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ሲሆን አቀበታማ በሆነ ጥርጊያ መንገድ ላይ ለስምንት ሰዓታት ነድተን የኦዳም ጎሳ የሚኖርበት ክልል ገባን። ያሰብንበት ቦታ ለመድረስ አንድ ጥልቅ ሸለቆ ማለፍና ሌላ ተራራ መውጣት ይኖርብን ነበር።

መኪናችንን ራንቺቶ በሚባል መንደር ካቆምን በኋላ ዕቃዎቻችንን ተሸክመን ወደ ሸለቆው ታችኛ ክፍል ለመድረስ ሦስት ሰዓት በእግራችን ተጓዝን። እዚያም ድንኳኖቻችንን ተከልንና የዱር አራዊት እንዳይቀርቡን ለማድረግ እሳት የምናነድበት በቂ እንጨት ሰበሰብን፤ ከዚያም ሌሊቱን በየሦስት ሰዓቱ እየተፈራረቅን እሳቱን ለመጠበቅ በቡድን በቡድን ተከፋፈልን።

በማግስቱ ማለዳ ላይ ተራራውን መውጣት ጀመርን። በተራራው ላይ ብዙ መንገዶች ስለነበሩ በተደጋጋሚ ጊዜ መንገድ ስተን ነበር። ከቡድናችን ውስጥ የኦዳም ቋንቋ በትንሹ መናገር የሚችል አንድ ወንድም ስለነበረ በመንገዳችን ላይ በምናገኛቸው ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በአጭሩ እንናገር ነበር። የሚገርመው ነገር፣ አንዳንድ ሰዎች ልንሄድበት ባሰብነው በሎስ አሬናሌስ ራሳቸውን የይሖዋ ምሥክሮች ብለው የሚጠሩ ሰዎች እንዳሉና የመጽሐፍ ቅዱስ ስብሰባዎችን እንደሚያካሂዱ ነገሩን። ይህ የሚያስደንቅ ብሎም የሚያበረታታ ዜና ነበር።

ሎስ አሬናሌስ ስንደርስ እግሮቻችን ውኃ ቋጥረው ነበር። ማኅበረሰቡ ከጡብ በተሠሩና የካርቶን ክዳን ባላቸው ቤቶች ውስጥ የሚኖር ሲሆን ትምህርት ቤትም ሆነ የኤሌክትሪክ መብራት አልነበረውም። ከሌላው ዓለም ሙሉ በሙሉ ተገልለው የሚኖሩት እነዚህ ሕዝቦች እጅግ በከፋ ድህነት ውስጥ ይኖራሉ፤ ሕይወታቸውን ለማቆየት ቶርቲያ የሚባለውን የበቆሎ ቂጣና ሌላ ትንሽ ነገር ይበላሉ። መለሎ ቁመና ካለው ከሜለሲዮ ጋር ተገናኘን፤ እሱም ሲያየን እጅግ ተደሰተ። ሜለሲዮ ቅልብጭ ወዳለችው ቤቱ እንድንገባ የጋበዘን ሲሆን ቤተሰቡንም ሆነ ወገኖቹን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸው የይሖዋ ምሥክር እንዲልክላቸው ወደ ይሖዋ በየቀኑ ይጸልይ እንደነበረ ነገረን። ሕዝቡ ለሚያቀርበው ጥያቄ በሙሉ መልስ መስጠት እንዳልቻለ እንደሚሰማው ገለጸልን።

የኦዳም ሕዝብ ሻማኒዝም የሚባለውን ሃይማኖት ይከተላል። እንደ ንስር ላባና አጥንት ያሉ ነገሮችን እንደ ክታብ ይጠቀማሉ። የተፈጥሮ ኃይሎችን ያመልካሉ፤ እንዲሁም ሻማኖች የሚባሉትን የሚበዘብዟቸውንና ከመናፍስቱ ጋር የሚያገናኟቸውን ሰዎች በጣም ይፈራሉ። ሜለሲዮ ወደ ከተማ በሄደባቸው ጊዜያት እውነተኛው አምላክ ይሖዋ እንደሆነ ሲማር ለጣዖት አምልኮ የሚጠቀምባቸውን ቁሳቁሶች በሙሉ እንዳስወገደ ገለጸልን። የአካባቢው ሰዎች አማልክታቸው ሜለሲዮንን ይቀስፉታል ብለው ጠብቀው ነበር። ሆኖም ምንም እንዳልደረሰበት ሲያዩ ይሖዋ ከእነሱ አማልክት የላቀ ኃይል እንዳለው ተገነዘቡ። በዚህም የተነሳ ሜለሲዮ ጽሑፎቻችንን በመጠቀም ከቤተሰቡ ጋር በሚያደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ መገኘት ጀመሩ።

ሜለሲዮ “በመጀመሪያ ክታቦቻቸውንና ጣዖቶቻቸውን በሙሉ ማቃጠል እንዳለባቸው ነግሬያቸው ነበር” በማለት ገለጸልን። ብዙዎቹ አጉል እምነት የፈጠረባቸውን ፍርሃት ያሸነፉ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ላይ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር ከ80 በላይ ሆኗል። እኛም ይህን ስንሰማ በጣም ተገርመን በዚያኑ ዕለት ከሰዓት በኋላ ስብሰባ ለማካሄድ ወሰንን። አዘውትረው በሜለሲዮ ቤት የሚሰበሰቡትን ሰዎች እንዲጠሩልን ፈረሰኞችን ላክን። ምንም እንኳ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ድንገት የተጠሩ ቢሆንም በእግርና በአህያ ተጉዘው 25 ሰዎች መጡ።

ሜለሲዮ እያስተረጎመልን ሰዎቹ ላነሷቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች መልስ ሰጠናቸው። ከጠየቁን ጥያቄዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ “ሕንዳውያን ሆነንም እንኳ ይሖዋ ይወደናል?” “በኦዳም ቋንቋ የምናቀርበውን ጸሎት ይሰማል?” “የምንኖረው ከከተሞች በጣም ርቀን ነው፤ ታዲያ አርማጌዶን ሲመጣ ይሖዋ ያስታውሰናል?” ሰዎች የትኛውንም ዓይነት ቋንቋ ቢናገሩ ወይም የቱንም ያህል ከከተማ ርቀው ቢኖሩ ገር እስከሆኑ ድረስ ይሖዋ እንደሚያስብላቸው ለእነዚህ ትሑት ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀስን ማስረዳት በመቻላችን ደስ አለን። እነሱም ተጨማሪ ነገር የሚያስተምራቸው ሰው እንድንልክላቸው ለመኑን።

ከስብሰባው በኋላ የያዝነውን ምግብ ከአዳዲሶቹ ጓደኞቻችን ጋር ተካፍለን በላን። ምሽት ላይ ይህ ተራራማ አካባቢ በጣም ይቀዘቅዛል፤ በመሆኑም ተሠርቶ ባላለቀ አንድ ክፍል ውስጥ ማደር እንደምንችል ሲነግሩን በጣም ደስ አለን። በማግሥቱ ጠዋት በአቋራጭ መንገድ መኪናችንን ወዳቆምንበት አካባቢ ወሰዱን፤ ከዚያም ወደ ዱራንጎ ጉዞ ጀመርን፤ በወቅቱ በጣም ደክሞን የነበረ ቢሆንም ባጋጠመን ሁኔታ በጣም ረክተን ነበር።

አብዛኞቹ ስፓንኛ ማንበብ፣ መጻፍም ሆነ መናገር ባይችሉም ስለ እውነተኛው አምላክ ለመማርና እሱን ለማምለክ ከሚፈልጉት ከእነዚህ ቅን ሰዎች ጋር መገናኘታችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! እኛ ከሄድን በኋላ ስድስት የይሖዋ ምሥክሮች ወደዚያ አካባቢ ተልከው ሦስት ሳምንት ቆይተው ተመልሰዋል። እነሱም ይሖዋን ከልብ ማገልገል የሚፈልጉ 45 የሚያህሉ ሰዎችን በመንፈሳዊ ረድተዋል። ሁሉም በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ይገኛሉ።

አንድ ተጨማሪ ነገር እንንገራችሁ። በሎስ አሬናሌስ ባለው አንድ ብቸኛ ትንሽ ሱቅ ውስጥ ሲጋራ መሸጥ አቁሟል። ይህ የሆነው ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እያጠኑ ስለሆነና ማጨስ ስላቆሙ ነው። ብዙዎችም ጋብቻቸውን ሕጋዊ አድርገዋል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሜለሲዮ ከሚስቱ፣ ከአራት ሴት ልጆቹና ከአማቱ ጋር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በሎስ አሬናሌስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ክርስቲያናዊ ስብሰባ ሲደረግ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]

Servicio Postal Mexicano, Correos de Mexico