በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በበጋ ወቅት በሩሲያ የሚካሄዱ የአውራጃ ስብሰባዎች በረከት ያመጣሉ

በበጋ ወቅት በሩሲያ የሚካሄዱ የአውራጃ ስብሰባዎች በረከት ያመጣሉ

በበጋ ወቅት በሩሲያ የሚካሄዱ የአውራጃ ስብሰባዎች በረከት ያመጣሉ

ተፈጥሮን ማድነቅ የሚወዱ ሩሲያውያን በከተማ ያለውን መኖሪያ ቤታቸውን ትተው ዳቻ ተብለው በሚጠሩ የበጋ ጎጆዎች ጊዜያቸውን ለማሳለፍ በየዓመቱ በጋ ላይ ወደ ገጠር ይጎርፋሉ። ይህ ወቅት ለእነሱ ወከባ ከሞላበት የከተማ ሕይወት ፋታ የሚያገኙበት ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሩሲያ ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችም በበጋ ወቅት ላይ ገጠራማ ወደሆኑ አካባቢዎች ሲጎርፉ ቆይተዋል፤ ይሁን እንጂ የእነሱ ዓላማ የተለየ ነው።

በሩሲያ ባሉ አንዳንድ ከተሞች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራ ቢታገድም በአገሪቱ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታቸውን በነፃነት የማራመድ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም ለአምልኮ በይፋ መሰብሰባቸውን ቀጥለዋል። አንዳንድ ጊዜ ግን የተሳሳተ መረጃ የደረሳቸው ባለሥልጣናትም ሆኑ በአካባቢው ያሉ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቀሳውስት በሚያደርሱባቸው ተቃውሞና ጫና የተነሳ በየዓመቱ በበጋ ወራት ለሚያካሂዷቸው ትልልቅ ስብሰባዎች የሚሆኑ ተስማሚ መሰብሰቢያዎችን መከራየት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በጫካ ውስጥ ወይም ሜዳ ላይ ስብሰባዎችን አዘጋጅተዋል። ከ2007 እስከ 2009 ባሉት ዓመታት ውስጥ በመላው ሩሲያ በሚገኙ 25 ቦታዎች ላይ እነዚህን የመሰሉ 40 መንፈሳዊ “ሽርሽሮች” ተደርገዋል።

በሩሲያ በተደረጉ ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ለብዙ ዓመታት የተገኘ አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ባለፉት ዓመታት በትልልቅ ከተሞች የሚገኙ ስታዲየሞችንና ሕንፃዎችን ስንከራይ ብዙ ቅን ሰዎች ብሎም የአካባቢው ባለሥልጣናት ንጽሕናችንን እና ሥርዓታማነታችንን በመመልከት ስለ ድርጅታችን የራሳቸው ድምዳሜ ላይ መድረስ ይችሉ ነበር። አሁን ግን ከሰው ተነጥለን ጫካ ውስጥ ለመሰብሰብ ተገደናል። ሕዝቡ ከተለያየ የኑሮ ደረጃ፣ ዘርና ሃይማኖት የመጡ ሰዎች የሚገኙባቸውን እነዚህን ድንቅ ስብሰባዎች ለማየት አለመቻሉ የሚያሳዝን ነው።”

እንደነዚህ ያሉት ስብሰባዎች አስደሳች ወቅቶች ቢሆኑም ሁኔታው አንድ የይሖዋ ምሥክር እንደተናገረው ነው፦ “የእምነት አጋሮቻችን አስቸጋሪ ሁኔታ ሳይበግራቸው የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ሲያደርጉና በታማኝነት ሲያገለግሉ መመልከት የሚያስደስት ነገር ነው። እውነቱን ለመናገር ግን ባለሥልጣናቱ ትልልቅ ስብሰባዎችን እንዳናደርግ እንቅፋት ሲፈጥሩብን በአካልም ሆነ በስሜት ላይ ከፍተኛ ውጥረት ማስከተሉ አይቀርም። በተጨማሪም ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ፣ ክብር ባለው መንገድ በነፃነት እንዳናመልክ ጋሬጣ ይሆንብናል።” ታዲያ በሩሲያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ የተጋፈጡት እንዴት ነው?

በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በጫካ ውስጥ የተደረጉ ትልልቅ ስብሰባዎች

ብዙ ጊዜ ባለቀ ሰዓት ላይ የኪራይ ውሎች ይሰረዙ ነበር፤ ይህም የስብሰባው አደራጆች በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ታዳሚዎች የሚበቃ ሌላ መሰብሰቢያ ለማዘጋጀት የሚኖሯቸው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ እንዲሆን ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል፣ ቹቫሽ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ቸባክሳሪ ከተማ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በ2008 ስብሰባቸውን በዛፎች በተከበበና የቮልጋን ወንዝ ቁልቁል ለማየት በሚያስችልና በጣም ሰፊ በሆነ የማረፊያ ሰፈር (ካምፕሳይት) ላይ ለማድረግ ተገደው ነበር። ቦታውን ለስብሰባው ለማዘጋጀት ብዙ ልፋት ጠይቆባቸዋል። ስብሰባው ላይ እንደሚገኙ ከሚጠበቁት 1,930 ታዳሚዎች መካከል 1,700 ለሚያህሉት በሜዳው ላይ ማደሪያ ማዘጋጀት አስፈልጎ ነበር። በተጨማሪም ተሰብሳቢዎቹ ሙቅና ቀዝቃዛ ውኃ ያላቸው መታጠቢያ ቤቶች እንዲሁም መጸዳጃ ቤቶችና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ያስፈልጋቸው ነበር። ከዚህም በላይ ለሁሉም ተሰብሳቢ ምግብ መቅረብ ነበረበት።

ወንድሞች ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት በትጋት ሠርተዋል። አናጺዎች፣ የኤሌክትሪክ ባለሙያዎችና የቧንቧ ሠራተኞች በቦታው ተገኝተው ነበር። ወደ 350 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፈ አንድ ቡድን በሥራው ለመካፈል ራሱን በፈቃደኝነት ያቀረበ ሲሆን ከቡድኑ ውስጥ 14ቱ በቦታው ላይ አሥር ቀናት አሳልፈዋል። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ጣውላዎችን እንደ መቁረጥ፣ ጭድ እንደ ማጋዝ፣ ድንኳን እንደ መትከል እንዲሁም መታጠቢያ ቤቶችንና መጸዳጃ ቤቶችን እንደ ማዘጋጀት ያሉ ሥራዎችን አከናውነዋል። ሌላው ቡድን ደግሞ ቁሳቁሶችን ለመግዛት ለበርካታ ጊዜያት ወደ ከተማ መሄድ አስፈልጎታል። የተዘጋጁ ምግቦችን ለማስቀመጥ የሚበቃ ማቀዝቀዣ ስላልነበር ወንድሞች በቀን ሦስት ጊዜ እዚያው የተዘጋጀ ትኩስ ምግብ ለማቅረብ ወሰኑ። የማረፊያ ሰፈሩ አስተዳደርም ለተሰብሳቢዎቹ ምግብ የሚያዘጋጁ ጥቂት ሠራተኞችን በመቅጠር ተባበረ። ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ 500ዎቹ የራሳቸውን ድንኳን ይዘው መጥተዋል፤ 150ዎቹ በማረፊያ ሰፈሩ አቅራቢያ ቤት ተከራይተዋል፤ 15ቱ ምንም ቅር ሳይላቸው ጋጣ ውስጥ ሣር ጎዝጉዘው ተኝተዋል፤ የተቀሩት ደግሞ ወንድሞች በተከሏቸው ድንኳኖች ውስጥ አርፈዋል።

ተሰብሰቢዎቹ በቦታው ሲደርሱ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ፕላስቲክ ወንበሮች በሥርዓት ተደርድረው ተመለከቱ። ከፊት ለፊት በሩሲያኛና በቹቫሽኛ ቋንቋ ለሚካሄዱ ፕሮግራሞች የተዘጋጁ በአበባ ያጌጡ ሁለት ቀለል ያሉ መድረኮች ነበሩ። ሁሉም ሰው በመንፈሳዊ ፕሮግራሙ የተደሰተ ሲሆን የፈቃደኛ ሠራተኞቹንም ትጋት የተሞላበት ጥረት አድንቋል። ምግብ ሲያዘጋጁ ከነበሩት አንዱ “በገዛ ዓይኖቼ ባላይ ኖሮ ሥራውን በብቃት የሚወጣና ሥርዓታማ የሆነ እንዲህ ያለ ድርጅት ይኖራል ብዬ አላምንም ነበር!” በማለት በአድናቆት ተናግሯል። አንዳንዶች የስብሰባ ዝግጅቱን የጥንቶቹ እስራኤላውያን ያከብሩት ከነበረው የዳስ በዓል ጋር አመሳስለውታል።

በሌሎች ከተሞች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ ስብሰባውን ለመጀመር አንድ ቀን ብቻ ሲቀራቸው የኪራይ ውሉ ይሰረዝባቸዋል፤ በመሆኑም በአንድ ቀን ውስጥ ሌላ የመሰብሰቢያ ስፍራ ፈልገው ማዘጋጀት ነበረባቸው። እንዲህ ያለ ሁኔታ በኒዥኒ ኖቭገረት አጋጥሟል፤ በአካባቢው ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የግለሰብ ይዞታ የሆነን አንድ ቦታ ለስብሰባ ለማዘጋጀት ቀን ከሌት በፈረቃ ሠርተዋል። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ዛፎችን መቁረጥ፣ ቁጥቋጦዎችን መመንጠር፣ ሣር ማጨድ እንዲሁም አካባቢውን ከተባይና ከጉንዳን ማጽዳት ነበረባቸው። ተሰብሳቢዎቹ ዓርብ ዕለት ጠዋት ወደ ቦታው ሲደርሱ ፈቃደኛ ሠራተኞቹ 2,000 የፕላስቲክ መቀመጫዎችንና አሥር ተንቀሳቃሽ መጸዳጃ ቤቶችን አምጥተው፣ የእጅ መታጠቢያዎችን ተክለው፣ መድረክ ሠርተው እንዲሁም ጀነሬተርና የድምፅ መሣሪያ አዘጋጅተው ነበር። አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በጣም የሚያስደንቀው ነገር ቀን ከሌት በፈረቃ የሠሩት ወንድሞች ጀብዱ እንደሠራ ሰው መታየት አልፈለጉም። ስብሰባው በሚካሄድበት ሰዓትም ሌሎችን በትሕትና ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ምቾታቸው ተጠብቆ መንፈሳዊ ትምህርቱን መከታተል እንዲችሉ ሁለመናቸውን ሰጥተዋል።”

አንድ ሌላ ወንድም ደግሞ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እውነተኛ የትብብር መንፈስ ይታይ ነበር። ወንድሞች ሜዳ ላይ ትልቅ ስብሰባ ሲያዘጋጁ ይህ የመጀመሪያቸው ከመሆኑም በላይ የነበራቸው ጊዜ በጣም አጭር ነበር፤ እንደዚያም ሆኖ ፕሮግራሙ በሚካሄድበት ሰዓት በተቻለ መጠን ምንም የሚረብሽ ነገር እንዳይኖር ለማድረግ እያንዳንዱን ነገር አስቀድመው አስበውበታል። ይህን ሁሉ ሥራ ብናከናውንም ድካም አልተሰማንም። ይሖዋ ጉልበት ሆኖን ነበር!”

የአምላክ መንፈስ እገዛ

ትልልቅ ስብሰባዎችን ከማዘጋጀት ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የተደረገው ጥረት፣ በብዙ መንገድ የአካባቢውን የይሖዋ ምሥክሮች ይበልጥ እንዲቀራረቡ ያደረገ ከመሆኑም በላይ የአምላክ መንፈስ እገዛ እንዳልተለያቸው አሳይቷል። በስሞሌንስክ ከተማ አስቀድመው ከተያዙት ማረፊያ ክፍሎች ውስጥ ብዙዎቹ በስብሰባው ዋዜማ ተሰረዙ። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “ተሰብሳቢዎቹ የተሳፈሩባቸው በርካታ አውቶቡሶች ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት በቦታው ሲደርሱ እነሱን የምናሳርፍበት ቤት አልነበረንም። ምንም ላደርግላቸው ስላልቻልኩ ማልቀስ ጀመርኩ። ወደ ይሖዋ በመጸለይ ለችግሩ መላ እንዲሰጠን ለመንኩት። በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ለሁሉም የሚሆን ሌላ ማረፊያ ቦታ ስናገኝ ደስታዬ ወደር አልነበረውም! ሁኔታው ተአምር ነበር! ከዚህም በላይ ይሖዋ ጻድቁ ያለ ረዳት ተጥሎ እንዲቀር እንደማያደርግ የሚያረጋግጥ ነበር።” በጫካ ውስጥ በተደረገ ሌላ ትልቅ ስብሰባ ላይ ወንድሞች ማረፊያ እንዲሰጧቸው የመንደሩን ነዋሪዎች እርዳታ ጠይቀው ነበር፤ የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢው ባስመዘገቡት መልካም ስም የተነሳ የመንደሩ ነዋሪዎች ስብሰባው እስኪያልቅ ድረስ 2,000 ተሰብሳቢዎችን በፈቃደኝነት ተቀብለው በቤታቸው አሳርፈዋል።

“ስብሰባው መካሄድ መቻሉ ብቻ እንኳ በማንኛውም ሁኔታ በይሖዋ መታመን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ነው” በማለት አንድ የይሖዋ ምሥክር ተናግሯል። በተለይም ያልተጠበቁ “እንግዶች” ስብሰባውን ለመረበሽ በመጡበት ወቅት ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል። ኖቫሻክቲንስክ ውስጥ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቀሳውስትና ተቃዋሚዎች የተናጋሪው ድምፅ እንዳይሰማ ለማድረግ በድምፅ ማጉያ ተጠቅመው መዘመርና ቅዳሴ ማሰማት ጀመሩ። ፖሊሶች ግን ሰዎቹ ፕሮግራሙን እንዳይረብሹ አስቆሟቸው። የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ የሆነች አንዲት ተቃዋሚ በሙቀቱ ሳቢያ ራሷን ስታ ስትወድቅ ወንድሞች በስብሰባው ወቅት የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና እርዳታ ለመስጠት ወደተቋቋመው ክፍል ወስደው ተገቢውን እርዳታ ሰጧት። ይህም ሴትዮዋን በጣም አስገረማት።

ባዩት ነገር ተገረሙ

ሽብርተኝነት የፈጠረው ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ ብዙ ጊዜ በሩሲያ ትልልቅ ስብሰባዎች ሲደረጉ የሕግ አስከባሪዎችንና ሁኔታዎችን በጥርጣሬ ዓይን የሚመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎችን ትኩረት ይስባል። ለምሳሌ ያህል፣ በቮልዥስኪ በጫካ ውስጥ በተካሄደ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ የፀረ ሽብርተኛ ፖሊስ ኃይል ጥበቃ እንዲያደርግ ተመድቦ ነበር። ፕሮግራሙ በሚካሄድበት ሰዓት ከፖሊሶቹ አንዱ ሞባይል ስልኩ ጠፍቶበት ስለነበር ወንድሞች ጠፍተው የተገኙ ዕቃዎች ከሚቀመጡበት ክፍል ሄዶ እንዲወስድ ረዱት። ሞባይሉን ከወሰደ ብዙም ሳይቆይ አለቃው በስብሰባው ላይ የዓመፅ እንቅስቃሴ ወይም የአክራሪነት መንፈስ መኖሩን የሚጠቁም ነገር እንዳለ ለማጣራት ደወለለት። ፖሊሱም እንዲህ በማለት መልስ ሰጠ፦ “ሁሉ ነገር በጣም ጥሩ ነው፤ ወደ 5,000 የሚጠጉ ሰዎች ቢኖሩም ምንም ዓይነት ዓመፅ የለም። ደግሞ የምን አክራሪነት? ብታየው አንተ ራስህ ትገረማለህ። ስልኬ ጠፍቶብኝ ነበር፤ እነሱ ግን አግኝተው መለሱልኝ!”

አንድ የጥበቃ ሠራተኛ በአካባቢው ንጽሕና የተደመመ ከመሆኑም ሌላ በስብሰባው ላይ ብዙ ልጆች ቢኖሩም አንዲት የከረሜላ መጠቅለያ እንኳ መሬት ላይ ባለማየቱ በጣም ተደንቋል። ሌላ ትልቅ ስብሰባ የተካሄደበት ማረፊያ ሰፈር ባለቤት የሆነ አንድ ግለሰብ ትልቅ ሃይማኖታዊ ስብሰባ እየተካሄደ መሆኑ ሪፖርት ደርሶት ከመጣ የመቶ አለቃ ጋር ተነጋግሮ ነበር። እሱም መቶ አለቃውን ወደ አንድ ሕንፃ ይዞት ከወጣ በኋላ ከሦስተኛ ፎቅ በረንዳ ላይ ሆነው ሜዳውን ቁልቁል እየተመለከቱ “እስቲ እያቸው! ምን ያህል ሥርዓታማ እንደሆኑ አንተ ራስህ መፍረድ ትችላለህ!” አለው። የማረፊያው ሰፈር ባለቤት ከይሖዋ ምሥክሮቹ መካከል የአልኮል መጠጥ የሚጠጣ ወይም ሲጋራ የሚያጨስ ሰው አለመኖሩ፣ አካባቢው ሰው ዝር ያላለበት እስኪመስል ደረስ ጽድት ያለ መሆኑ ሌላው ቀርቶ ሁሉም ሰው ቆሻሻውን ይዞ መሄዱ በጣም አስገርሞታል። “ገነት ይመስላል!” በማለት አድናቆቱን ገልጿል።

በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚታየው አንድነት

በጫካ ውስጥ ከተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ በኋላ በአቅራቢያው ያለ መንደር ኃላፊ እንደሚከተለው ብለው ለመናገር ተገፋፍተዋል፦ “ተራ ሰዎች እንደሆናችሁ አውቃለሁ፤ ነገር ግን የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል አላችሁ። እኛ በየፊናችን ስንሮጥ እናንተ ግን ሰዎችን አንድ ማድረግ ችላችኋል!” እጅግ ሰፊ በሆነችው ሩሲያ ውስጥ የሚኖሩት ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያሉ የአገሪቱ ነዋሪዎች የአምላክ ሕዝቦች በትልልቅ መንፈሳዊ ስብሰባዎቻቸው የሚያሳዩትን አንድነት በመመልከት መደነቃቸውን ይቀጥላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ያቀዱት ነገር ባልጠበቁት መንገድ ከመቅጽበት ሊቀየር ቢችልም መቼም ቢሆን የማይቀይሩት አንድ ነገር አለ፤ ይህም ለባለሥልጣናትና ለሰዎች ያላቸው አክብሮት ነው።

በሩሲያ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ያሉበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን መንፈሳዊ ትምህርት ለማግኘት በደስታ አንድ ላይ መሰብሰባቸውን ይቀጥላሉ። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች “ሙሉ በሙሉ ለአምላክ በማደርና በጥልቅ ማስተዋል በጸጥታና በተረጋጋ ሁኔታ” መኖራቸውን ይቀጥሉ ዘንድ “ነገሥታትንና በሥልጣን ላይ ያሉትን ሁሉ በተመለከተ” ይጸልያሉ።—1 ጢሞቴዎስ 2:2

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሜዳ ላይ የተደረገን አንድ ስብሰባ ለማዘጋጀት በፈቃደኝነት ከረዱት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዱ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሩሲያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ‘ሙሉ በሙሉ ለአምላክ በማደር በጸጥታና በተረጋጋ ሁኔታ’ መኖራቸውን ይቀጥላሉ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ፈቃደኛ ሠራተኞች የአውራጃ ስብሰባው ከመካሄዱ በፊት አካባቢውን ለማጽዳትና በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች ምግብ ለማቅረብ በአንድነት ሠርተዋል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሁሉም ሰው በመንፈሳዊ ፕሮግራሙ የተደሰተ ሲሆን የፈቃደኛ ሠራተኞቹንም ትጋት የተሞላበት ጥረት አድንቋል