በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ፈጽሞ ችላ አትበሉ

የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ፈጽሞ ችላ አትበሉ

የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ፈጽሞ ችላ አትበሉ

“ለአሥር ዓመታት ያህል በንግዱ ዓለም ውስጥ ተጠላልፈን የነበረ ከመሆኑም ሌላ የናጠጥን ሀብታሞች ሆነን ነበር። ሁለታችንም ያደግነው በእውነት ውስጥ ቢሆንም ቀስ በቀስ ከይሖዋ በጣም ርቀን በመሄዳችን ለመመለስ መንፈሳዊ ጥንካሬ አልነበረንም” በማለት ያሮስዋቭ እና ባለቤቱ ቤአታ ተናግረዋል። *

ማሬክ የተባለ ሌላ ወንድም ያለፈውን ሕይወቱን ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፦ “በፖላንድ በተካሄደው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥ የተነሳ በተደጋጋሚ ጊዜ ከሥራ ተቀንሻለሁ። ይህ ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖብኝ ነበር። የራሴን ንግድ እንዳልጀምር ደግሞ የንግድ ሰው እንዳልሆንኩ ስለማስብ እፈራ ነበር። በመጨረሻ ግን በዚህ መስክ መሰማራት እንዳለብኝ ተሰማኝ፤ የራሴ ንግድ ቢኖረኝ መንፈሳዊነቴ ሳይጎዳ የቤተሰቤን ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላት እንደምችል አስቤ ነበር። ምን ያህል ተሳስቼ እንደነበር የገባኝ ከጊዜ በኋላ ነው።”

ኑሮ በጣም እየተወደደና ሥራ አጥነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ባለበት በዚህ ዓለም ውስጥ አንዳንዶች ነገሮች ተስፋ አስቆራጭ ስለሚሆኑባቸው ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ያደርጋሉ። በርካታ ወንድሞች ትርፍ ሰዓት ለመሥራት፣ ተጨማሪ ሥራ ለመያዝ ወይም ልምዱ ባይኖራቸውም እንኳ የራሳቸውን ሥራ ለመጀመር ወስነዋል። በዚህ መንገድ የሚያገኙት ተጨማሪ ገቢ ቤተሰባቸውን ለመደጎም እንደሚያስችላቸው የሚሰማቸው ሲሆን በመንፈሳዊም ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያጋጥማቸው ያስባሉ። አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት ውሳኔ የሚያደርገው በሚገባ አስቦበት ቢሆንም እንኳ ባልተጠበቁ ክስተቶችና በኢኮኖሚ አለመረጋጋት የተነሳ ነገሮች እንዳሰበው ሳይሆኑ በመቅረታቸው መንፈሳዊነቱ ሊነካበት ይችላል። በዚህም ምክንያት አንዳንዶች በስግብግብነት ወጥመድ ውስጥ የወደቁ ከመሆኑም ሌላ ቁሳዊ ነገሮችን ሲያሳድዱ መንፈሳዊነታቸውን መሥዋዕት አድርገዋል።​—መክ. 9:11, 12

አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች በሥጋዊ ነገሮች በጣም ከመጠላለፋቸው የተነሳ ለግል ጥናት፣ ለስብሰባዎችና ለአገልግሎት የሚሆን ጊዜ አጥተዋል። እነዚህን ነገሮች ችላ ማለታቸው መንፈሳዊነታቸውንና ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት እንደሚጎዳው ምንም ጥያቄ የለውም። ከዚህም በተጨማሪ ‘በእምነት ከሚዛመዷቸው ሰዎች’ ጋር ያላቸውን ውድ ዝምድና ችላ ሊሉ ይችላሉ። (ገላ. 6:10) አንዳንዶች ከክርስቲያናዊው የወንድማማች ማኅበር ቀስ በቀስ እየራቁ ይሄዳሉ። በመሆኑም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ያለን ዝምድና በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

ለእምነት ባልንጀሮቻችን ያለብን ኃላፊነት

ወንድማማችና እህትማማች እንደመሆናችን መጠን አንዳችን ለሌላው ጥልቅ ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉን። (ሮም 13:8) በጉባኤያችሁ ውስጥ ‘ለእርዳታ የሚጮኹ ችግረኞች’ መኖራቸውን አስተውላችሁ ይሆናል። (ኢዮብ 29:12) አንዳንዶች መሠረታዊ ነገሮችን እንኳ አጥተው ይቸገራሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ ይህ ምን ለማድረግ አጋጣሚ እንደሚከፍትልን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ለኑሮ የሚያስፈልጉ ቁሳዊ ነገሮች ያሉት ሰው ወንድሙ ሲቸገር ተመልክቶ ሳይራራለት ቢቀር የአምላክ ፍቅር በእሱ ውስጥ እንዴት ሊኖር ይችላል?”​—1 ዮሐ. 3:17

አንተም እንዲህ ያሉ ችግረኞችን በመርዳት ልግስና አሳይተህ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ለወንድሞቻችን አሳቢነት የምናሳየው ቁሳዊ እርዳታ በማድረግ ብቻ አይደለም። አንዳንዶች ለእርዳታ የሚጮኹት የብቸኝነት ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ስለሚሰማቸው ሊሆን ይችላል። ይሖዋን ለማገልገል እንደማይበቁ ይሰማቸው፣ በከባድ የጤና እክል ይሠቃዩ ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው ምክንያት በሐዘን ይደቆሱ ይሆናል። እነዚህን ግለሰቦች ማበረታታት የምንችልበት አንዱ መንገድ ሲናገሩ ጆሮ ሰጥተን ማዳመጥና ማዋራት ነው፤ በዚህ መንገድ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ልንረዳቸውና መንፈሳዊነታቸውን ልናጠናክርላቸው እንችላለን። (1 ተሰ. 5:14) እንዲህ ማድረጋችን ከወንድሞቻችን ጋር ያስተሳሰረንን ፍቅር ያጠናክረዋል።

በተለይ መንፈሳዊ እረኞች የሌሎችን ስሜት እንደሚጋሩ በሚጠቁም መንገድ ለማዳመጥ፣ ችግራቸውን እንደተረዱላቸው ለማሳየት እንዲሁም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ አላቸው። (ሥራ 20:28) የበላይ ተመልካቾች እንዲህ ሲያደርጉ ለመንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶቹ “ጥልቅ ፍቅር” የነበረውን ሐዋርያው ጳውሎስን ይመስላሉ።​—1 ተሰ. 2:7, 8

ይሁንና አንድ ክርስቲያን ከመንጋው ርቆ ከሄደ ለእምነት ባልንጀሮቹ ያለበትን ኃላፊነት መወጣት እንዴት ይችላል? የበላይ ተመልካቾችም እንኳ በፍቅረ ንዋይ ወጥመድ ሊወድቁ ይችላሉ። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ባለው ፈተና ቢወድቅስ?

በኑሮ ጭንቀቶች መዳከም

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የቤተሰባችንን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የምናደርገው ሩጫ ብዙውን ጊዜ ጭንቀት ሊያስከትልብንና ይህም ለመንፈሳዊ ነገሮች የምንሰጠው ቦታ እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል። (ማቴ. 13:22) ከላይ የተጠቀሰው ማሬክ እንዲህ ብሏል፦ “ንግዱ አልሳካ ሲለኝ ወደ ሌላ አገር በመሄድ ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ ለመፈለግ ወሰንኩ። መጀመሪያ ስሄድ ለሦስት ወራት ብቻ ለመቆየት አስቤ የነበረ ቢሆንም ሌላ ሦስት ወር ጨመርኩ፤ በመሃሉ ለአጭር ጊዜ ያህል ወደ ቤት የምመጣባቸው ጊዜያት ቢኖሩም እንዲህ እያልኩ ለብዙ ጊዜ ቆየሁ። ይህ ሁኔታ የይሖዋ ምሥክር ባልሆነችው ሚስቴ ላይ ስሜታዊ ጫና ፈጥሮባት ነበር።”

ማሬክ የቤተሰብ ሕይወቱ ከመጎዳቱም በተጨማሪ ሌሎች ችግሮች አጋጥመውት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ጭንቅ የሚል ሙቀት ባለበት አካባቢ ለረጅም ሰዓት መሥራቴ ሳያንስ ሌሎችን መጠቀሚያ ለማድረግ ከሚሯሯጡ ጋጠወጥ ሰዎች ጋር መዋል ግድ ሆኖብኝ ነበር። ነገረ ሥራቸው ሁሉ እንደ ተራ ወሮበሎች ነበር። በዚህም ምክንያት ደስታ የራቀኝ ሲሆን ባሪያ የሆንኩ ያህል ተሰማኝ። ለራሴ የሚሆን ጊዜ እንኳ ማግኘት ሳልችል ሌሎችን መርዳት መቻሌ የማይመስል ነገር ሆነብኝ።”

ማሬክ ያደረገው ውሳኔ ያስከተለበት አሳዛኝ ውጤት እኛም ቆም ብለን እንድናስብ ሊያነሳሳን ይገባል። ወደ ሌላ አገር መሄድ የገንዘብ ችግራችንን የሚፈታልን ቢመስልም ሌላ ጣጣ ያስከትልብን ይሆን? ለምሳሌ ስለ ቤተሰባችን ብናስብ፣ በመንፈሳዊነታቸውና በስሜታቸው ላይ ጫና ይፈጥር ይሆን? ሌላ አገር መሄዳችን ከጉባኤ ጋር ያለን ግንኙነት እንዲቋረጥ ያደርግ ይሆን? የእምነት ባልንጀሮቻችንን የማገልገል መብት እንዳይኖረን እንቅፋት አይሆንብንም?​—1 ጢሞ. 3:2-5

አንድ ሰው ሰብዓዊ ሥራው ወጥመድ የሚሆንበት ወደ ሌላ አገር ሲሄድ ብቻ እንዳልሆነ ሳታስተውል አልቀረህም። ያሮስዋቭን እና ቤአታን እንመልከት። ያሮስዋቭ እንዲህ ብሏል፦ “ሥራውን ስንጀምረው ምንም ጉዳት የሚያስከትል አይመልስም ነበር። እንደተጋባን ጥሩ ገበያ በሚገኝበት አንድ ቦታ ላይ የቋሊማ ሳንድዊች መሸጥ ጀመርን። ገበያው እየደራ ሲሄድ ሥራችንን ለማስፋት አሰብን። ሆኖም ሥራው ፋታ የሚባል ነገር ስላሳጣን ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መቅረት ጀመርን። ብዙም ሳይቆይ በጉባኤ አገልጋይነትና በአቅኚነት ማገልገሌን አቆምኩ። የምናገኘው ትርፍ እየጣመን ሲሄድ ትልቅ ሱቅ ከፈትን፤ እንዲሁም ከአንድ የማያምን ሰው ጋር በሽርክና መሥራት ጀመርን። ከዚያም በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያስገኙ ውሎችን ለመፈራረም ወደ ሌሎች አገሮች መጓዝ ጀመርኩ። ቤት የምሆነው ከስንት አንዴ በመሆኑ ከባለቤቴና ከሴት ልጄ ጋር ያለን ቤተሰባዊ ቅርርብ እየጠፋ ሄደ። በንግዱ ዓለም ያገኘነው ስኬት ቀስ በቀስ በመንፈሳዊ እንድናንቀላፋ አደረገን። ከጉባኤው ጋር ስለተቆራረጥን ስለ ወንድሞቻችን የምናስብበት ጊዜም አልነበረን።”

ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? አንድ ክርስቲያን እንደ “ንጉሥ” ያለ ሕይወት ለመምራት ያለው ፍላጎት ወጥመድ ሊሆንበትና ግዴለሽ እንዲሆን ሊያደርገው አልፎ ተርፎም “መደረቢያውን” ማለትም ክርስቲያናዊ መለያውን እስከ ማጣት ሊያደርሰው ይችላል። (ራእይ 16:15) ይህም ልንረዳቸው እንችል ከነበሩት ወንድሞቻችን ጋር እንድንራራቅ ሊያደርገን ይችላል።

ራስህን በሐቀኝነት መርምር

‘ይህ በእኔ ላይ አይደርስም’ ብለን እናስብ ይሆናል። ይሁንና ሁላችንም ብንሆን በሕይወት ውስጥ መሠረታዊ የሚባለው ነገር ምን እንደሆነ በቁም ነገር ልናስብበት ይገባል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለም፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም። ስለዚህ ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።” (1 ጢሞ. 6:7, 8) እርግጥ ነው፣ የኑሮ ደረጃ ከአገር ወደ አገር የተለያየ ነው። ባደጉ አገሮች ውስጥ ማንኛውም ሰው ሊኖረው የሚችለው ተራ ነገር በሌሎች አገሮች እንደ ቅንጦት ሊታይ ይችላል።

ያለንበት አገር የኑሮ ደረጃ ምንም ይሁን ምን ጳውሎስ ቀጥሎ የተናገረውን ሐሳብ ልብ ልንለው ይገባል፦ “ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ፈተናና ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም ሰዎችን ጥፋትና ብልሽት ውስጥ በሚዘፍቁ ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ።” (1 ጢሞ. 6:9) ወጥመድ የሚቀመጠው በቀላሉ እንዳይታይ ተደርጎ ነው። ዓላማውም ሊያዝ የተፈለገውን ነገር በድንገት ሳያስበው መያዝ ነው። ታዲያ ‘ጎጂ የሆኑ ምኞቶች’ ወጥመድ እንዳይሆኑብን መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?

ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ለይተን ማወቃችን የግል ጥናትን ጨምሮ ለአምልኳችን የበለጠ ጊዜ እንድንሰጥ ሊያነሳሳን ይችላል። አንድ ክርስቲያን ጸሎት የታከለበት የግል ጥናት ማድረጉ ሌሎችን ለመርዳት “በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ” ያስችለዋል።​—2 ጢሞ. 2:15፤ 3:17

አፍቃሪ የሆኑ ሽማግሌዎች የያሮስዋቭን መንፈሳዊነት ለማጠናከርና እሱን ለማበረታታት ለተወሰኑ ዓመታት ያህል ጥረት ያደርጉ ነበር። ይህም ከፍተኛ ለውጥ እንዲያደርግ አነሳሳው። እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ወቅት ከሽማግሌዎቹ ጋር ስንወያይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ቢፈልግም ቁሳዊ ንብረቶቹን ለመተው ፈቃደኛ ስላልነበረው ሀብታም ወጣት የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደ ምሳሌ ጠቀሱልኝ። ከዚያም ይህ ታሪክ በእኔ ሕይወት ውስጥ ይሠራ እንደሆነ በዘዴ ጠየቁኝ። ይህ ጠቃሚ ውይይት ነገሮችን እንዳስተውል ዓይኔን ከፈተልኝ!”​—ምሳሌ 11:28፤ ማር. 10:17-22

ያሮስዋቭ ያለበትን ሁኔታ በሐቀኝነት ከመረመረ በኋላ በስፋት ያካሂድ የነበረውን የንግድ እንቅስቃሴ ለመቀነስ ወሰነ። በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እሱና ቤተሰቡ በመንፈሳዊ እንደገና አንሰራሩ። አሁን የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ወንድሞቹን እያገለገለ ነው። ያሮስዋቭ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች መንፈሳዊነታቸውን ችላ እስኪሉ ድረስ በንግድ እንቅስቃሴዎች በሚጠመዱበት ጊዜ የራሴን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ከማያምኑ ሰዎች ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ መጠመድ ምን ያህል ጥበብ የጎደለው አካሄድ እንደሆነ አስረዳቸዋለሁ። አጓጊ የሆነ ግብዣ ሲቀርብ እንቢ ማለትና ሐቀኝነት ከጎደላቸው ድርጊቶች መራቅ ቀላል አይደለም።”​—2 ቆሮ. 6:14

ማሬክም ከመከራ ተምሯል። በሌላ አገር ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ መሥራቱ ቤተሰቡን በገንዘብ ለመርዳት ቢያስችለውም ከአምላክና ከወንድሞቹ ጋር የነበረው ግንኙነት አደጋ ላይ ወድቋል። ውሎ አድሮ ማሬክ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡትን ነገሮች በድጋሚ አጤነ። እንዲህ ብሏል፦ “ባለፉት ዓመታት የነበረኝ ሕይወት ‘ለራሱ ታላቅ ነገር ይሻ ከነበረው’ በጥንት ዘመን ከኖረው ከባሮክ ጋር ይመሳሰላል። በመጨረሻም የሚያስጨንቁኝን ነገሮች በማንሳት ለይሖዋ የልቤን ግልጥልጥ አድርጌ ነገርኩት፤ አሁን እንደገና መንፈሳዊ ሚዛኔን መጠበቅ እንደቻልኩ ይሰማኛል።” (ኤር. 45:1-5) በአሁኑ ጊዜ ማሬክ “መልካም ሥራ” የሆነውን በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆኖ የማገልገል መብት ለማግኘት እየተጣጣረ ነው።​—1 ጢሞ. 3:1

ማሬክ፣ የተሻለ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ ለማግኘት ብለው ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ለሚያስቡ ሁሉ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፦ “በሌላ አገር ስትኖሩ በዚህ ክፉ ሥርዓት ወጥመድ ውስጥ በቀላሉ ልትወድቁ ትችላላችሁ። የአገሩን ቋንቋ በደንብ አለመቻላችሁ ከሌሎች ጋር እንዳትግባቡ እንቅፋት ይሆንባችኋል። ምናልባት ገንዘብ ቋጥራችሁ መመለስ ትችሉ ይሆናል፤ ያም ሆኖ በቀላሉ የማይሽር መንፈሳዊ ቁስልም ታተርፋላችሁ።”

ሰብዓዊ ሥራችንንና ለወንድሞቻችን ያለብንን ኃላፊነት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የምንወጣ ከሆነ ይሖዋን እናስደስታለን። በተጨማሪም ለሌሎች ሕያው ምሳሌ ስለምንሆን ጥበብ የታከለበት ውሳኔ እንዲያደርጉ ልናነሳሳቸው እንችላለን። በኑሮ ጭንቀቶች የተዳከሙ ክርስቲያኖች፣ የወንድሞቻቸው ድጋፍና ርኅራኄ እንዲሁም ጥሩ ምሳሌነት ያስፈልጋቸዋል። የጉባኤ ሽማግሌዎችና ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ሚዛናቸውን እንዲጠብቁና በኑሮ ጭንቀቶች እንዳይዋጡ ሊረዷቸው ይችላሉ።​—ዕብ. 13:7

እንግዲያው በሰብዓዊ ሥራችን ከሚገባ በላይ በመጠላለፍ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ፈጽሞ ችላ እንዳንል እንጠንቀቅ። (ፊልጵ. 1:10) በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን መንግሥት በማስቀደም “በአምላክ ዘንድ . . . ሀብታም” እንሁን።​—ሉቃስ 12:21

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሰብዓዊ ሥራህ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዳትገኝ እንቅፋት ይሆንብሃል?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

መንፈሳዊ ወንድሞችህንና እህቶችህን የመርዳት መብትህን ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ?