በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ ማን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ ማን ነው?

“ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ‘ይህ ሰው ማን ነው?’ በማለት መላ ከተማዋ ተናወጠች። ሕዝቡም ‘ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው!’ እያለ ይናገር ነበር።”—ማቴዎስ 21:10, 11

በ33 ዓ.ም. በጸደይ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ * ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ከተማዋ ይህን ያህል የተናወጠችው ለምንድን ነው? በከተማዋ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ስለ ኢየሱስም ሆነ እሱ ስላከናወናቸው አስደናቂ ነገሮች ሰምተው ነበር። እነሱም ይህን ነገር ለሌሎች ሰዎች መናገራቸውን ቀጥለው ነበር። (ዮሐንስ 12:17-19) ሆኖም ሕዝቡ በመካከላቸው ያለው ይህ ሰው በዓለም ላይ እስከ ዘመናችን ድረስ የሚዘልቅ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ያን ያህል አልተገነዘበም ነበር!

ኢየሱስ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረ የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

  • በዓለም ዙሪያ በብዙ አገሮች የሚሠራበት የቀን መቁጠሪያ የተመሠረተው ኢየሱስ ተወልዷል ተብሎ በሚታሰብበት ዓመት ነው።

  • ከዓለም ሕዝብ መካከል ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጋው ማለትም የዓለም ሕዝብ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የክርስትና እምነት ተከታይ እንደሆነ ይናገራል።

  • በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታይ ያለው የእስልምና ሃይማኖትም ኢየሱስ “ከአብርሃም፣ ከኖኅ እና ከሙሴ” የሚበልጥ ነቢይ እንደሆነ ያስተምራል።

  • ኢየሱስ የተናገራቸው ጥበብ የታከለባቸው ብዙ አባባሎች የዕለት ተዕለት የንግግር ክፍል ሆነዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

    ‘ሌላኛውን ጉንጭህን አዙርለት።’ማቴዎስ 5:39

    ‘አንኳኩ ይከፈትላችኋል።’ማቴዎስ 7:7

    ‘አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም።’ማቴዎስ 6:24

    ‘የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ።’ማቴዎስ 7:6

    ‘ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።’ማቴዎስ 7:12

    ‘ስጡ ይሰጣችኋል።’ሉቃስ 6:38

ኢየሱስ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ሰዎች ስለ እሱ ያላቸው አመለካከትና እምነት በጣም የተለያየ ነው። በዚህ ምክንያት ‘በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ኢየሱስ ከየት እንደመጣ፣ ሕይወቱ ምን ይመስል እንደነበረና የሞተው ለምን እንደሆነ ሊነግረን የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ስለ እሱ እነዚህን እውነታዎች ማወቅህ በሕይወትህ ላይ አሁንም ሆነ ወደፊት ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።

^ አን.3 የናዝሬት ሰው የሆነው የዚህ ነቢይ ስም “ኢየሱስ” ሲሆን ትርጉምም “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ነው። “ቅቡዕ” የሚል ትርጉም ያለው “ክርስቶስ” የሚለው የማዕረግ ስም ኢየሱስ የተቀባ ወይም ለአንድ የተለየ ዓላማ በአምላክ የተሾመ መሆኑን ያመለክታል።