በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት በቁም ነገር ተመልከቱት

ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት በቁም ነገር ተመልከቱት

ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት በቁም ነገር ተመልከቱት

ቁም ነገር ያለበትን ነገር ሁሉ . . . ማሰባችሁን አታቋርጡ።ፊልጵ. 4:8

1, 2. በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ነገሮችን እንደዋዛ እንዲመለከቱ ያደረጋቸው ምንድን ነው? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?

የምንኖረው⁠ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ በሆነና አሳዛኝ ሁኔታዎች በሞሉበት ጊዜ ላይ ነው። ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ለሌላቸው ሰዎች “በዓይነቱ ልዩ” የሆነውን ይህን ዘመን መቋቋም የማይታሰብ ነገር ነው። (2 ጢሞ. 3:1-5) ያላቸው አማራጭ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በራሳቸው መወጣት ብቻ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ብዙም ስኬት አያስገኝላቸውም። ብዙዎች በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመርሳት ሲሉ የመዝናኛው ዓለም በየጊዜው የሚያቀርባቸውን አዳዲስ ነገሮች ያሳድዳሉ።

2 ብዙውን ጊዜ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ውጥረቶች ለመቋቋም ሲሉ ተድላን ማሳደድ ይጀምራሉ። ክርስቲያኖችም ካልተጠነቀቁ እንዲህ ባለው ወጥመድ በቀላሉ ሊወድቁ ይችላሉ። ታዲያ ከዚህ ወጥመድ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ወጥመድ ላለመውደቅ ስንል ጨርሶ ደስታ የራቀን ልንሆን ይገባል ማለት ነው? ደስታ ለማግኘት መጣርንና ኃላፊነትን መወጣትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስኬድ የምንችለው እንዴት ነው? በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ልንሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ከፍ ያለ ግምት ብንሰጥም ወደ አንድ ጽንፍ በመሄድ መፈናፈኛ የሌለው ሕይወት እንዳንመራ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመሪያ ሊሆኑን ይገባል?

ተድላን በሚወድ ዓለም እየኖሩ ቁም ነገረኛ መሆን

3, 4. ቅዱሳን መጻሕፍት ቁም ነገረኛ የመሆንን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ የሚረዱን እንዴት ነው?

3 ይህ ዓለም ‘ለሥጋዊ ደስታ’ ከልክ ያለፈ ቦታ ይሰጣል ቢባል ማጋነን አይሆንም። (2 ጢሞ. 3:4) ዓለም ለመዝናኛ ትልቅ ቦታ የሚሰጥ መሆኑ ተጽዕኖ ሊያሳድርብንና መንፈሳዊነታችንን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። (ምሳሌ 21:17) በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለጢሞቴዎስና ለቲቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ቁም ነገረኝነትን የተመለከተ ምክርም ማካተቱ የተገባ ነው። ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን በዓለም ላይ የሚታየው ነገሮችን እንደዋዛ የመመልከት ዝንባሌ እንዳይጋባብን ይረዳናል።—1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2ን እና ቲቶ 2:2-8ን አንብብ።

4 ሰለሞን፣ አንዳንድ ጊዜ መዝናናትን ተወት አድርገን በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዙ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ማሰብ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ጽፎ ነበር። (መክ. 3:4፤ 7:2-4) በእርግጥም ሕይወት አጭር በመሆኑ መዳን ለማግኘት ‘ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ’ ያስፈልገናል። (ሉቃስ 13:24) መዳን ለማግኘት “ቁም ነገር” ለሆኑ ነገሮች ሁሉ ምንጊዜም ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። (ፊልጵ. 4:8, 9) በሌላ አባባል ከክርስቲያናዊ ሕይወታችን ጋር ተያያዥነት ላላቸው ነገሮች በሙሉ ትልቅ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል ማለት ነው።

5. በቁም ነገር ልንመለከተው የሚገባው አንዱ የሕይወታችን ዘርፍ ምንድን ነው?

5 ለምሳሌ ክርስቲያኖች የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ጠንክሮ የመሥራት ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር ይመለከቱታል። (ዮሐ. 5:17) በዚህም የተነሳ በታታሪነታቸውና እምነት የሚጣልባቸው በመሆናቸው ብዙ ጊዜ በሌሎች ዘንድ አድናቆትን አትርፈዋል። በተለይ የቤተሰብ ራሶች ቤተሰባቸውን ለመደገፍ ተግተው መሥራት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። ደግሞም አንድ ሰው ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር የማያሟላ ከሆነ “እምነትን የካደ” እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል፤ ይህ ደግሞ ይሖዋን ከመካድ ተለይቶ አይታይም።—1 ጢሞ. 5:8

አምልኳችንበቁም ነገር የሚታይ ሆኖም አስደሳች

6. ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው እንደሆነ እንዴት እናውቃለን?

6 ይሖዋ እውነተኛውን አምልኮ ምንጊዜም የሚመለከተው በቁም ነገር ነው። ይህን በአንድ ምሳሌ ማየት ይቻላል፤ በሙሴ ሕግ ሥር የነበሩት እስራኤላውያን ይሖዋን ከማምለክ ዘወር ባሉበት ወቅት ከባድ ቅጣት ደርሶባቸዋል። (ኢያሱ 23:12, 13) በአንደኛው መቶ ዘመን የነበሩ የክርስቶስ ተከታዮች፣ እውነተኛው አምልኮ ጉባኤውን ከሚበክሉ ትምህርቶችና አስተሳሰቦች የጸዳ እንዲሆን ለማድረግ ብርቱ ትግል ማድረግ አስፈልጓቸዋል። (2 ዮሐ. 7-11፤ ራእይ 2:14-16) ዛሬም እውነተኛ ክርስቲያኖች አምልኳቸውን በቁም ነገር መመልከታቸውን ቀጥለዋል።—1 ጢሞ. 6:20

7. ጳውሎስ ለአገልግሎቱ ይዘጋጅ የነበረው እንዴት ነው?

7 የመስክ አገልግሎታችን ለደስታችን ምክንያት ከሚሆኑት ነገሮች አንዱ ነው። ይሁንና በአገልግሎት ደስተኞች ሆነን መቀጠል ከፈለግን ስለ አገልግሎታችን በቁም ነገር ልናስብና አስቀድመን ልንዘጋጅ ይገባል። ጳውሎስ ለሚያስተምራቸው ሰዎች ያስብ እንደነበር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በተቻለ መጠን የተወሰኑ ሰዎችን አድን ዘንድ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር ሆንኩ። ምሥራቹን ከሌሎች ጋር እካፈል ዘንድ ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ።” (1 ቆሮ. 9:22, 23) ጳውሎስ ሰዎችን በመንፈሳዊ መርዳት ያስደስተው ነበር፤ እንዲሁም የአድማጮቹን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት እያንዳንዱ ግለሰብ የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት የሚችለው እንዴት እንደሆነ በቁም ነገር ያስብ ነበር። በመሆኑም ሰዎች ይሖዋን እንዲያመልኩ ማበረታታትና ማነሳሳት ችሏል።

8. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን ስለምናስተምራቸው ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ልናዳብር ይገባል? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት በአገልግሎታችን ደስተኛ እንድንሆን አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?

8 ጳውሎስ አገልግሎቱን ምን ያህል በቁም ነገር ይመለከተው ነበር? ለይሖዋም ሆነ የእውነትን መልእክት ለሚቀበሉ ሰዎች ራሱን “ባሪያ” ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። (ሮም 12:11፤ 1 ቆሮ. 9:19) የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራም ይሁን በክርስቲያናዊ ስብሰባ ወቅት አሊያም በቤተሰብ አምልኮ ክፍለ ጊዜ ላይ የአምላክን ቃል የማስተማር ኃላፊነት ሲኖረን ለምናስተምራቸው ሰዎች ኃላፊነት እንዳለብን እንገነዘባለን? ምናልባት አንድን ሰው በየጊዜው መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጫና እንደሚፈጥርብን ይሰማን ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ጥናት ለመምራት ለግል ጉዳዮቻችን ከምናውለው ጊዜ ቆርሰን ሌሎችን ለመርዳት ማዋል እንደሚያስፈልገን አይካድም። ይሁንና እንዲህ ማድረጋችን ኢየሱስ የተናገረውን “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” የሚለውን ሐሳብ የሚያንጸባርቅ አይሆንም? (ሥራ 20:35) ሰዎች መዳን እንዲያገኙ በግለሰብ ደረጃ ማስተማር ከምንም ነገር ጋር ሊወዳደር የማይችል ደስታ ያስገኝልናል።

9, 10. (ሀ) ቁም ነገረኞች መሆን አለብን ሲባል ከሌሎች ጋር ዘና ያለና አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ አንችልም ማለት ነው? አብራራ። (ለ) አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ሌሎችን የሚያበረታታና በቀላሉ የሚቀረብ እንዲሆን ምን ሊረዳው ይችላል?

9 ቁም ነገረኞች መሆን አለብን ሲባል ከሌሎች ጋር ዘና ያለና አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ አንችልም ማለት አይደለም። ኢየሱስ ጊዜውን ለማስተማር ብቻ ሳይሆን ዘና ለማለትና ከሌሎች ጋር አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍ በማዋል ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። (ሉቃስ 5:27-29፤ ዮሐ. 12:1, 2) በተጨማሪም ቁም ነገረኞች መሆን አለብን ሲባል ሁልጊዜ ኮስታራ መሆን አለብን ማለት አይደለም። ኢየሱስ ኮስተር ያለና ምንጊዜም ፊቱ የማይፈታ ቢሆን ኖሮ ሰዎች ወደ እሱ አይሳቡም ነበር። ልጆች እንኳ ሳይቀሩ ከእሱ ጋር መሆን ደስ ይላቸው ነበር። (ማር. 10:13-16) በዚህ ረገድ ሚዛናዊ አመለካከት በመያዝ ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

10 አንድ ወንድም ስለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ሲናገር “ከራሱ ብዙ የሚጠብቅ ቢሆንም ከሌሎች ግን ጨርሶ ፍጽምናን አይጠብቅም” ብሏል። ስለ አንተስ እንዲህ ሊባል ይችላል? ምክንያታዊ በሆነ መልኩ አንዳንድ ነገሮችን ከሌሎች መጠበቃችን ተገቢ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ምክንያታዊ የሆኑ ግቦችን የሚያወጡላቸውና እዚያ ላይ እንዲደርሱ የሚረዷቸው ከሆነ ልጆቹ ደስ እያላቸው ግቦቹ ላይ ለመድረስ ይጥራሉ። በተመሳሳይም ሽማግሌዎች የጉባኤውን አባላት በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ በግለሰብ ደረጃ ሊያበረታቷቸውና ይህን ለማድረግ የሚረዷቸውን ሐሳቦች ለይተው ሊጠቁሟቸው ይችላሉ። ከዚህም በላይ አንድ ሽማግሌ ለራሱ ሚዛናዊ አመለካከት የሚኖረው ከሆነ ሌሎችን የሚያበረታታና በቀላሉ የሚቀረብ ሰው ይሆናል። (ሮም 12:3) አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ሽማግሌ ሁሉንም ነገር እንደ ቀልድ የሚመለከት እንዲሆን አልፈልግም። በሌላ በኩል ደግሞ ሁልጊዜ ኮስተር ያለ ከሆነ እሱን መቅረብ አስቸጋሪ ይሆናል።” ሌላ እህት ደግሞ አንዳንድ ሽማግሌዎች “ከሚገባው በላይ ኮስታራ በመሆናቸው ለመቅረብ በጣም እንደሚከብዱ” የሚሰማት መሆኑን ተናግራለች። ሁሉም ክርስቲያኖች “ደስተኛ አምላክ” የሆነውን ይሖዋን ማምለክ አስደሳች ነገር እንደሆነ አድርገው ሊያስቡ ይገባል፤ በመሆኑም ሽማግሌዎች፣ የጉባኤው አባላት እንዲህ ያለ ደስታ እንዳይኖራቸው እንቅፋት የሚሆን ነገር በፍጹም ማድረግ የለባቸውም።—1 ጢሞ. 1:11

በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነትን መቀበል

11. አንድ ወንድ በጉባኤ ውስጥ ለኃላፊነት ለመብቃት ‘መጣጣር’ አለበት ሲባል ምን ማለት ነው?

11 ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንዶችን የበለጠ ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ጥረት እንዲያደርጉ ሲያበረታታቸው ዓላማው ሥልጣን የመያዝ ጉጉት እንዲኖራቸው ማነሳሳት አልነበረም። ሐዋርያው “የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ማንኛውም ሰው መልካም ሥራን ይመኛል” ብሎ በጻፈ ጊዜ ወንዶች ኃላፊነት ለመሸከም የሚያነሳሳቸው ውስጣዊ ግፊት ምን ሊሆን እንደሚገባ ግልጽ አድርጓል። (1 ጢሞ. 3:1, 4) ክርስቲያን ወንዶች ‘መጣጣር’ አለባቸው ሲባል ወንድሞቻቸውን ለማገልገል የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ብቃቶች ለማሟላት ተግቶ የመሥራት ጠንካራ ፍላጎት ማዳበር ይኖርባቸዋል ማለት ነው። አንድ ወንድም ከተጠመቀ ቢያንስ አንድ ዓመት ከሆነውና በ⁠1 ጢሞቴዎስ 3:8-13 ላይ የተዘረዘሩትን የጉባኤ አገልጋዮች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ምክንያታዊ በሆነ መጠን ያሟላ ከሆነ ለሹመት በዕጩነት ሊቀርብ ይችላል። ቁጥር 8 “የጉባኤ አገልጋዮችም በተመሳሳይ ቁም ነገረኞች” መሆን እንዳለባቸው ለይቶ የሚጠቅስ መሆኑን ልብ በሉ።

12, 13. ወጣት ወንድሞች ለኃላፊነት ለመብቃት ሊጣጣሩ የሚችሉባቸውን አንዳንድ መንገዶች ግለጽ።

12 የተጠመቅህና ለይሖዋ የምታቀርበውን አምልኮ በቁም ነገር የምትመለከት በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የምትገኝ ወንድም ነህ? ለኃላፊነት የምትጣጣር መሆንህን የምታሳይባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። አንዱ በመስክ አገልግሎት ያለህን ተሳትፎ ማሳደግ ነው። በሁሉም የዕድሜ ክልል ላይ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ማገልገል ያስደስትሃል? መጽሐፍ ቅዱስን ልታስጠናው የምትችል ሰው ለማግኘት ጥረት እያደረግህ ነው? አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የተሰጡትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ የምትጥር ከሆነ የማስተማር ችሎታህን ታሻሽላለህ። ከዚህም ባሻገር የይሖዋን መንገዶች እያስጠናኸው ላለው ግለሰብ አሳቢነት ማሳየትን ትማራለህ። እንዲሁም የምታስጠናው ግለሰብ ለውጥ ማድረግ እንዳለበት በሚሰማው ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ እንዲያደርግ በትዕግሥትና በዘዴ መርዳት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ትማራለህ።

13 እናንት ወጣት ወንዶች፣ በጉባኤያችሁ ያሉትን አረጋውያን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ለመርዳት ራሳችሁን ማቅረብ ትችላላችሁ! በተጨማሪም የመንግሥት አዳራሹ ንጹሕና ሥርዓታማ እንዲሆን በማድረግ ለአዳራሹ ውበት እንደምትቆረቆሩ ማሳየት ትችላላችሁ። በምትችሉት ሁሉ እርዳታ ለማበርከት ራሳችሁን በፈቃደኝነት ማቅረባችሁ አገልግሎታችሁን በቁም ነገር እንደምትመለከቱ ይጠቁማል። ልክ እንደ ጢሞቴዎስ እናንተም ጉባኤውን በሚያስፈልገው ነገር የመርዳት ልባዊ ፍላጎት ማዳበር ትችላላችሁ።—ፊልጵስዩስ 2:19-22ን አንብብ።

14. ወጣት ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ለማገልገል ‘ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በቅድሚያ መፈተን’ የሚቻለው እንዴት ነው?

14 እናንት ሽማግሌዎች፣ “ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ምኞቶች” ለመሸሽ ጥረት የሚያደርጉና ሌሎች መልካም ባሕርያትን ጨምሮ “ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን” ለመከታተል የሚጥሩ ወጣት ወንድሞችን በጉባኤ ውስጥ ለመጠቀም ንቁ መሆን ይኖርባችኋል። (2 ጢሞ. 2:22) በጉባኤ ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን እንዲሠሩ በማድረግ ኃላፊነት ለመሸከም ‘ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በቅድሚያ መፈተን’ ይቻላል፤ በዚህ መንገድ ‘እድገታቸው በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ ይታያል።’—1 ጢሞ. 3:10፤ 4:15

በጉባኤም ሆነ በቤት ውስጥ ቁም ነገረኛ መሆናችንን ማሳየት

15. በ⁠1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2 መሠረት ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ቁም ነገረኛ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15 ቁም ነገረኛ መሆን ሲባል ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በአክብሮት መያዝን ይጨምራል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በሚመክርበት ጊዜ ሌሎችን በአክብሮት መመልከት አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2ን አንብብ።) በተለይ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ባለን ግንኙነት እንዲህ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ኢዮብ ሴቶችን በተለይም የትዳር ጓደኛውን በአክብሮት የያዘበት መንገድ ጥሩ አርዓያ ይሆነናል። ሌላ ሴትን በፆታ ስሜት ላለመመልከት ልባዊ ጥረት አድርጓል። (ኢዮብ 31:1) ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በተያያዘ ቁም ነገረኞች መሆን ሲባል ከማሽኮርመም መራቅን እንዲሁም አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ከእኛ ጋር መሆን እንዲጨንቃቸው የሚያደርግ ነገር አለማድረግን ይጨምራል። በተለይ ደግሞ ሁለት ሰዎች ለመጋባት በማሰብ በሚጠናኑበት ጊዜ አንዳቸው ለሌላው አክብሮት ማሳየታቸው አስፈላጊ ነው። ቁም ነገረኛ የሆነ ክርስቲያን ከተቃራኒ ፆታ ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ በሌላው ሰው ስሜት አይጫወትም።—ምሳሌ 12:22

16. ባሎችና አባቶች ካላቸው ድርሻ ጋር በተያያዘ በዓለም ላይ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሚያንጸባርቁት አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው ሐሳብ የሚለየው እንዴት ነው?

16 በተጨማሪም በቤተሰብ ውስጥ አምላክ የሰጠንን ኃላፊነት ምንጊዜም በቁም ነገር ለመመልከት ጥረት ማድረግ አለብን። የሰይጣን ዓለም ባሎች ወይም አባቶች ያላቸውን ኃላፊነት በማቃለል እነሱን መቀለጃ ማድረጉን ሥራዬ ብሎ ይዞታል። የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ሰዎችን ለማሳቅ ሲል የቤተሰብ ራሶች ሲሾፍባቸውና ሲቀለድባቸው የሚያሳዩ መዝናኛዎችን ያቀርባል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ባል “የሚስቱ ራስ” እንደሆነ በመግለጽ ከባድ ኃላፊነት እንደተጣለበት ያሳያል።—ኤፌ. 5:23፤ 1 ቆሮ. 11:3

17. በቤተሰብ አምልኮ ረገድ የምናደርገው ተሳትፎ ኃላፊነታችንን በቁም ነገር የምንመለከት ሰዎች መሆናችንን የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

17 አንድ ባል ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ያሟላ ይሆናል። ይሁንና መንፈሳዊ መመሪያ የማይሰጥ ከሆነ ማስተዋልና ጥበብ እንደጎደለው እያሳየ ነው። (ዘዳ. 6:6, 7) በመሆኑም የቤተሰብ ራስ ከሆንክና በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ መብቶችን ለማግኘት እየተጣጣርክ ከሆነ በ⁠1 ጢሞቴዎስ 3:4 ላይ እንደተጠቀሰው “ልጆቹን ታዛዥና የታረመ ጠባይ ያላቸው” ወይም ቁም ነገረኞች እንዲሆኑ አድርጎ በማሳደግ “የራሱን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድር” ዓይነት ሰው መሆን ይገባሃል። በዚህ ረገድ፣ ‘ለቤተሰብ አምልኮ የሚሆን ቋሚ ጊዜ መድቤያለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። አንዳንድ ክርስቲያን ሚስቶች፣ ባሎቻቸው ግንባር ቀደም ሆነው የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲያሟሉ ቃል በቃል መለመን አስፈልጓቸዋል ማለት ይቻላል። ሁሉም የቤተሰብ ራሶች ይህን ኃላፊነታቸውን እንዴት እንደሚመለከቱት በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል። እርግጥ ነው፣ አንዲት ክርስቲያን ሚስት የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራሙን መደገፍና ዝግጅቱ የተሳካ እንዲሆን ከባሏ ጋር መተባበር ይኖርባታል።

18. ልጆች ቁም ነገረኛ መሆንን መማር የሚችሉት እንዴት ነው?

18 ልጆችም ቢሆኑ ነገሮችን በቁም ነገር የሚመለከቱ እንዲሆኑ ተበረታተዋል። (መክ. 12:1) ልጆች እንደ ዕድሜያቸውና እንደ ችሎታቸው የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሠሩ በማድረግ ተግቶ መሥራትን እንዲማሩ ማሠልጠኑ ምንም ክፋት የለውም። (ሰቆ. 3:27) ንጉሥ ዳዊት ገና ትንሽ ልጅ እያለ ጥሩ እረኛ እንዲሆን ሥልጠና አግኝቶ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሙዚቀኛና አቀናባሪ ነበር፤ ይህ ችሎታው በእስራኤል ንጉሥ ፊት ለማገልገል አስችሎታል። (1 ሳሙ. 16:11, 12, 18-21) ዳዊት እንደ ልጅ ተጫውቶ እንዳደገ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ያም ሆኖ ጠቃሚ ክህሎቶችንም የተማረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ይሖዋን ለማወደስ ተጠቅሞባቸዋል። እረኛ ሆኖ ያካበተው ልምድ የእስራኤልን ብሔር በትዕግሥት ለመምራት አስችሎታል። እናንት ወጣቶች፣ ፈጣሪያችሁን ለማገልገልና ወደፊት ኃላፊነት ለመሸከም የሚያዘጋጇችሁን ጠቃሚ ሙያዎች እየተማራችሁ ነው?

ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

19, 20. ከራስህ በምትጠብቀውም ሆነ ለይሖዋ በምታቀርበው አምልኮ ረገድ ምን ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር ቆርጠሃል?

19 ሁላችንም ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን መጣር እንጂ ወደ አንድ ጽንፍ በመሄድ የማያፈናፍን ሕይወት መምራት አይኖርብንም። “እጅግ ጻድቅ” መሆን አንፈልግም። (መክ. 7:16) በቤት ውስጥም ሆነ በሥራ ቦታ አሊያም ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ባለን ግንኙነት በተገቢው ቦታ መቀለድ ውጥረት የሰፈነበትን ሁኔታ ለማብረድ ይረዳል። ሁሉም የቤተሰብ አባላት የማያፈናፍን ዓይነት ሰው እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፤ አለበለዚያ የቤተሰቡን ሰላም ሊያደፈርሱ ይችላሉ። በጉባኤ ውስጥም አነጋገራችንና የምናስተምርበት መንገድ የሚያንጽ ብሎም የሚገነባ እንዲሆን በማድረግ ሁሉም የጉባኤው አባላት ዘና እንዲሉና አስደሳች ጊዜ እንዲያሳልፉ ማድረግ እንችላለን።—2 ቆሮ. 13:10፤ ኤፌ. 4:29

20 የምንኖረው ይሖዋንም ሆነ ሕግጋቱን በቁም ነገር የማይመለከቱ ሰዎች ባሉበት ዓለም ውስጥ ነው። ከዚህ በተቃራኒ የይሖዋ ሕዝቦች ለአምላክ ታዛዥና ታማኝ መሆናቸው በእጅጉ ያሳስባቸዋል። ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አምልኮ ‘በቁም ነገር’ የሚመለከቱ በርካታ ሰዎችን ያቀፈ ማኅበር አባል መሆን ምንኛ የሚያስደስት ነው! ለይሖዋ ከምናቀርበው አምልኮም ሆነ ከሌሎች የሕይወታችን ዘርፎች ጋር በተያያዘ ምንጊዜም ቁም ነገረኞች ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• በዓለም ላይ የሚታየው ነገሮችን እንደዋዛ የመመልከት ዝንባሌ እንዳይጋባብን መከላከል ያለብን ለምንድን ነው?

• አገልግሎታችንን በቁም ነገር የምንመለከተው ቢሆንም አስደሳች ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

• ኃላፊነትን ስለ መቀበል ያለን አመለካከት ቁም ነገረኛ መሆን አለመሆናችንን የሚያሳየው እንዴት ነው?

• ወንድሞቻችንንና የቤተሰባችንን አባላት በአክብሮት መያዛችን በቁም ነገር ሊታይ ይገባዋል የምንለው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አንድ ባል ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ነገሮችን ለቤተሰቡ ማቅረብ ይኖርበታል