በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ አድርጉ

አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ አድርጉ

አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ አድርጉ

“አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል።”—ምሳሌ 14:15

1, 2. (ሀ) ማንኛውንም ውሳኔ ስናደርግ በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ምን መሆን አለበት? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

በየዕለቱ⁠ የምናደርገው ነገር ነው ማለት ይቻላል። አብዛኛውን ጊዜ በሕይወታችን ላይ ያን ያህል ለውጥ አያመጣም። አንዳንድ ጊዜ ግን ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ይህ ነገር ምንድን ነው? ውሳኔ ነው። ትልቅም ይሁን ትንሽ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ በዋነኝነት የሚያሳስበን አምላክን ማስከበር ነው።—1 ቆሮንቶስ 10:31ን አንብብ።

2 ውሳኔ ማድረግ ይከብድሃል ወይስ ያን ያህል አያስቸግርህም? ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ለማደግ የምንፈልግ ከሆነ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየትን መማር እንዲሁም በሌሎች ተመርተን ሳይሆን እኛ ራሳችን ያመንንበትን ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። (ሮም 12:1, 2፤ ዕብ. 5:14) ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታ ለማዳበር እንድንነሳሳ የሚያደርጉን ሌሎች ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ውሳኔ ማድረግ አንዳንድ ጊዜ ከባድ የሚሆንብን ለምንድን ነው? የምናደርገው ውሳኔ አምላክን የሚያስከብር እንዲሆን የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን?

ውሳኔ ማድረግ ለምን አስፈለገ?

3. ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ምን ነገሮች ተጽዕኖ እንዲያደርጉብን መፍቀድ አይኖርብንም?

3 የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የምንወላውል ከሆነ አብረውን የሚማሩ ወይም የሚሠሩ ሰዎች እነዚህን ትምህርቶች ከልብ እንደማናምንባቸውና በቀላሉ በእነሱ ተጽዕኖ እንደምንሸነፍ ሊሰማቸው ይችላል። እነዚህ ሰዎች ሊዋሹ፣ ሊያጭበረብሩ ወይም ሊሰርቁ ይችላሉ፤ እኛም ‘ብዙዎችን በመከተል’ ቢያንስ ድርጊታቸውን እንድንሸፍንላቸው ከተቻለ ደግሞ ከእነሱ ጋር እንድንተባበር ጫና ሊያሳድሩብን ይሞክራሉ። (ዘፀ. 23:2) ያም ሆኖ አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ እንዴት ማድረግ እንደሚችል የሚያውቅ ግለሰብ በፍርሃት ተሸንፎ ወይም በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል በመጽሐፍ ቅዱስ ከሠለጠነ ሕሊናው ጋር የሚጋጭ ጎዳና አይከተልም።—ሮም 13:5

4. ሌሎች ሰዎች በእኛ ቦታ ሆነው ውሳኔ ሊያደርጉልን የሚፈልጉት ለምን ሊሆን ይችላል?

4 በእኛ ቦታ ሆነው ውሳኔ ሊያደርጉልን የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ይህን የሚያደርጉት እኛን ለመጉዳት ብለው ነው ማለት አይቻልም። አንዳንድ ጓደኞቻችን በቅን ልቦና ተነሳስተው የእነሱን ምክር እንድንከተል ይጫኑን ይሆናል። ከቤተሰብ ተለይተን ራሳችንን ችለን የምንኖር ቢሆንም ቤተሰቦቻችን የእኛ ደኅንነት በጥልቅ ስለሚያሳስባቸው አሁንም አንዳንድ አስፈላጊ ውሳኔዎችን በተመለከተ ጣልቃ መግባት እንደሚኖርባቸው ይሰማቸው ይሆናል። ከሕክምና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንደ ምሳሌ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ደምን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀምን በግልጽ ያወግዛል። (ሥራ 15:28, 29) ይሁንና ከጤና ጋር የተያያዙ ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ በግልጽ የተቀመጠ መመሪያ ስለሌለ የትኛውን ሕክምና መቀበል እንዳለብን ወይም እንደሌለብን እያንዳንዳችን የራሳችንን ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። * ቤተሰቦቻችን በዚህ ረገድ የራሳቸው የሆነ አመለካከት ይኖራቸው ይሆናል። ያም ሆኖ ከሕክምና ጋር የተያያዙ ውሳኔዎች ማድረግን በተመለከተ እያንዳንዱ የተጠመቀ ክርስቲያን “የራሱን የኃላፊነት ሸክም” መሸከም ይኖርበታል። (ገላ. 6:4, 5) በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ነገር በሰው ፊት ሳይሆን በአምላክ ዘንድ ጥሩ ሕሊና ይዞ መኖር ነው።—1 ጢሞ. 1:5

5. አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነታችን እንዳይጠፋ መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?

5 ውሳኔ ለማድረግ መወላወል ትልቅ አደጋ ሊያስከትልብን ይችላል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ፣ የሚወላውል ሰው “በሁለት ሐሳብ የሚዋልል” መሆኑን ጽፏል። (ያዕ. 1:8) በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ላይ መሪ በሌለው ጀልባ እንደሚጓዝ ሰው እንዲህ ዓይነቱ ግለሰብም ተለዋዋጭ በሆነው ሰብዓዊ አመለካከት እየተመራ ወዲያና ወዲህ ይንገዋለላል። ይህ ሰው አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ በቀላሉ እምነቱ ሊጠፋ ይችላል፤ ከዚያም ለደረሰበት አሳዛኝ ሁኔታ ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግ ይጀምራል። (1 ጢሞ. 1:19) ታዲያ እንዲህ ያለውን መዘዝ ማስቀረት የምንችለው እንዴት ነው? ‘በእምነት ጸንተን በመኖር’ ነው። (ቆላስይስ 2:6, 7ን አንብብ።) ጸንተን መኖር እንድንችል ደግሞ በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ላይ እምነት እንዳለን የሚያንጸባርቅ ውሳኔ ማድረግን መማር ይኖርብናል። (2 ጢሞ. 3:14-17) ይሁንና ጥሩ ውሳኔ እንዳናደርግ እንቅፋት የሚሆንብን ምን ሊሆን ይችላል?

ውሳኔ ማድረግ አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው?

6. ፍርሃት ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል?

6 ፍርሃት ውሳኔ እንዳናደርግ ሊያሽመደምደን ይችላል፤ ለምሳሌ የተሳሳተ ውሳኔ ባደርግስ ወይም ባይሳካልኝስ አሊያም የሰው መሳቂያ ብሆንስ የሚል ፍርሃት ያድርብን ይሆናል። እንዲህ ብለን ማሰባችን የሚያስገርም አይደለም። ማንም ሰው ቢሆን ለችግር ምናልባትም ለኀፍረት የሚዳርግ የተሳሳተ ውሳኔ ማድረግ አይፈልግም። ያም ቢሆን ለአምላክና ለቃሉ ያለን ፍቅር ፍርሃታችን እንዲቀንስ ሊረዳን ይችላል። እንዴት? ለአምላክ ያለን ፍቅር አስፈላጊ ውሳኔዎችን ከማድረጋችን በፊት ምንጊዜም ቃሉንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን እንድንመረምር ይገፋፋናል። እንዲህ ማድረጋችን ልንሠራቸው የምንችላቸውን ስህተቶች ለመቀነስ ይረዳናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአምላክ ቃል “ብስለት ለሌላቸው አስተዋይነትን፣ በዕድሜ ለጋ ለሆኑት ዕውቀትንና ልባምነትን” ይሰጣል።—ምሳሌ 1:4

7. ከንጉሥ ዳዊት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 ሁልጊዜ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን? አንችልም። ምክንያቱም ሁላችንም ስህተት እንሠራለን። (ሮም 3:23) ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ዳዊት ጥበበኛና ታማኝ ሰው ነበር። ይሁንና በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ መከራ ያስከተለ የተሳሳተ ውሳኔ ያደረገበት ጊዜ ነበር። (2 ሳሙ. 12:9-12) ይህ መሆኑ ግን አምላክን የሚያስደስቱ ውሳኔዎች ማድረግ እንደማይችል በመፍራት ውሳኔ ከማድረግ ወደኋላ እንዲል አላደረገውም። (1 ነገ. 15:4, 5) እኛም እንደ ዳዊት፣ ይሖዋ የፈጸምነውን ስህተት እንደሚያልፍልንና ኃጢአታችንን ይቅር እንደሚለን ካስታወስን ቀደም ሲል ተሳስተን የምናውቅ ቢሆንም እንኳ ውሳኔ ከማድረግ ወደኋላ አንልም። ይሖዋ የሚወዱትንና የሚታዘዙትን ምንጊዜም ይደግፋቸዋል።—መዝ. 51:1-4, 7-10

8. ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ትዳር ከሰጠው ሐሳብ ምን እንማራለን?

8 ውሳኔ ማድረግ የሚያስከትልብንን ጭንቀት ማቅለል እንችላለን። እንዴት? አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛ የሆኑ በርካታ አማራጮች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገንዘብ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ትዳር ያቀረበውን ሐሳብ እንመልከት። በመንፈስ መሪነት እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አንድ ሰው ከድንግልናው ጋር በሚስማማ ሁኔታ በአግባቡ መኖር ካልቻለ፣ በተለይ ደግሞ አፍላ የጉርምስና ዕድሜን ያለፈ ከሆነና ማግባቱ የሚመረጥ ከሆነ የፈለገውን ያድርግ፤ ኃጢአት አይሆንበትም። እንዲህ ያሉ ሰዎች ያግቡ። ሆኖም አንድ ሰው ማግባት እንደማያስፈልገውና ራሱን መግዛት እንደሚችል ተሰምቶት ድንግልናውን ጠብቆ ለመኖር በልቡ ከወሰነና በዚህ ውሳኔው ለመጽናት በልቡ ከቆረጠ መልካም ያደርጋል።” (1 ቆሮ. 7:36-38) ጳውሎስ ሳያገቡ መኖር የተሻለ እንደሆነ ሐሳብ ያቀረበ ቢሆንም ትክክለኛው አካሄድ ይህ ብቻ እንደሆነ አልተናገረም።

9. ሌሎች ስለ ውሳኔያችን ምን እንደሚሰማቸው ሊያሳስበን ይገባል? አብራራ።

9 ሌሎች ስለ ውሳኔያችን ምን እንደሚሰማቸው ሊያሳስበን ይገባል? አዎን፣ በተወሰነ መጠን ሊያሳስበን ይገባል። ጳውሎስ ምናልባት ለጣዖታት የተሠዉ ሊሆኑ የሚችሉ ምግቦችን ስለ መብላት ምን እንደተናገረ ልብ በል። አንድ ሰው የሚያደርገው ውሳኔ በራሱ ስህተት ላይሆን ቢችልም ደካማ ሕሊና ያለውን ሰው ግን ሊጎዳ እንደሚችል ሐዋርያው ተናግሯል። ታዲያ ጳውሎስ ምን ውሳኔ ላይ ደረሰ? “ምግብ ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከእንግዲህ ፈጽሞ ሥጋ አልበላም” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 8:4-13) እኛም የምናደርገው ውሳኔ የሌሎችን ሕሊና የሚነካው እንዴት እንደሆነ ማሰብ አለብን። እርግጥ ነው፣ በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው የምናደርገው ምርጫ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት የሚነካው እንዴት ነው የሚለው ነው። (ሮም 14:1-4ን አንብብ።) ታዲያ አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?

ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ ስድስት እርምጃዎች

10, 11. (ሀ) በቤተሰብ ውስጥ ቦታችንን እንደምናውቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ጉባኤውን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ሲያደርጉ በአእምሯቸው ሊይዙት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

10 ቦታህን የምታውቅ ሁን። አንድ እርምጃ ለመውሰድ ከመወሰናችን በፊት ‘ይህን ውሳኔ ማድረግ የእኔ ቦታ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። ንጉሥ ሰለሞን “ትዕቢት ስትመጣ ውርደትም ትከተላለች፤ በትሑት ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” በማለት ጽፏል።—ምሳሌ 11:2

11 ወላጆች ልጆቻቸው አንዳንድ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ ሊፈቅዱላቸው ይችላሉ፤ ያም ሆኖ ልጆች በራሳቸው ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላቸው አድርገው ማሰብ የለባቸውም። (ቆላ. 3:20) ሚስቶችና እናቶች በቤተሰብ ውስጥ የተወሰነ ሥልጣን ያላቸው ቢሆንም የቤተሰቡ ራስ ባል መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም። (ምሳሌ 1:8፤ 31:10-18፤ ኤፌ. 5:23) በተመሳሳይም ባሎች ያላቸው ሥልጣን ውስን መሆኑንና በክርስቶስ ራስነት ሥር መሆናቸውን ማስታወስ አለባቸው። (1 ቆሮ. 11:3) ሽማግሌዎች ጉባኤውን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን ያደርጋሉ። ይሁንና በአምላክ ቃል ውስጥ ‘ከተጻፈው ላለማለፍ’ ይጠነቀቃሉ። (1 ቆሮ. 4:6) በተጨማሪም ከታማኙ ባሪያ የሚያገኙትን መመሪያ በጥብቅ ይከተላሉ። (ማቴ. 24:45-47) ቦታችንን የምናውቅና ውሳኔ የማድረግ መብት ሲኖረን ብቻ የምንወስን ከሆነ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ለጭንቀትና ለሐዘን አንዳርግም።

12. (ሀ) ምርምር ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ሰው እንዴት ምርምር ማድረግ እንደሚችል አብራራ።

12 ምርምር አድርግ። ሰለሞን “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 21:5) ለምሳሌ አንድ ዓይነት ንግድ ውስጥ ለመግባት እያሰብክ ነው? እንግዲያው በስሜት የምትነዳ አትሁን። እውነታውን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ መረጃዎችን በሙሉ ለማግኘት ሞክር፣ ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ ሰዎችን አማክር፤ እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት ምርምር አድርግ። (ምሳሌ 20:18) የምርምርህን ውጤት መልክ ለማስያዝ ሁለት ዝርዝሮችን አዘጋጅ፤ በአንደኛው ላይ ምን ጥቅሞች እንደምታገኝ በሌላው ላይ ደግሞ ምን ጉዳቶች ሊያስከትልብህ እንደሚችል ማስፈር ትችላለህ። ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ‘ወጪህን አስላ።’ (ሉቃስ 14:28) የምታደርገው ውሳኔ በገንዘብ ረገድ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊነትህም ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ አስብ። እርግጥ ነው፣ ምርምር ለማድረግ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ይሁንና እንዲህ ማድረግህ አስፈላጊ ላልሆነ ጭንቀት የሚዳርጉ የችኮላ ውሳኔዎችን ከማድረግ ይጠብቅሃል።

13. (ሀ) በ⁠ያዕቆብ 1:5 ላይ ምን ማረጋገጫ እናገኛለን? (ለ) ጥበብ ለማግኘት መጸለያችን የሚረዳን እንዴት ነው?

13 ጥበብ ለማግኘት ጸልይ። ውሳኔያችን አምላክን የሚያስከብር የሚሆነው በምናደርገው ውሳኔ የእሱን እርዳታ ለማግኘት ከጠየቅነው ብቻ ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ ምክንያቱም አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣል፤ ለእሱም ይሰጠዋል።” (ያዕ. 1:5) ውሳኔ ስናደርግ የአምላክ ጥበብ እንደሚያስፈልገን አምኖ መቀበሉ ሊያሳፍረን አይገባም። (ምሳሌ 3:5, 6) ደግሞም በራሳችን ማስተዋል ብቻ የምንመራ ከሆነ በቀላሉ ልንሳሳት እንችላለን። ጥበብ ለማግኘት ስንጸልይና በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ስንመረምር አንድን እርምጃ ለመውሰድ ያነሳሳን እውነተኛ ዝንባሌ ምን እንደሆነ እንድናስተውል መንፈስ ቅዱስ ይረዳናል።—ዕብ. 4:12፤ ያዕቆብ 1:22-25ን አንብብ።

14. ዛሬ ነገ ማለትን ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?

14 ውሳኔ አድርግ። ምርምር ከማድረግህና ጥበብ ለማግኘት ከመጸለይህ በፊት ይህን እርምጃ ለመውሰድ አትቸኩል። ጠቢብ ሰው ጊዜ ወስዶ “ርምጃውን ያስተውላል።” (ምሳሌ 14:15) ያም ሆኖ ዛሬ ነገ አትበል። ዛሬ ነገ የሚል ሰው እርምጃ ላለመውሰድ የማይረባ ምክንያት ይደረድር ይሆናል። (ምሳሌ 22:13) ግራም ነፈሰ ቀኝ ይህ ሰው ውሳኔ ማድረጉ አልቀረም፤ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ካቃተው በተዘዋዋሪ ሕይወቱን ሌሎች ሰዎች እንዲቆጣጠሩት ወስኗል ማለት ነው።

15, 16. አንድን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

15 ውሳኔህን ተግባራዊ አድርግ። ውሳኔያችንን ተግባራዊ ለማድረግ በሙሉ ልብ ካልሠራን ጥሩ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያደረግነው ጥረት ሁሉ ከንቱ ይሆናል። ሰለሞን “እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው” በማለት ጽፏል። (መክ. 9:10) ስኬታማ መሆን እንድንችል ውሳኔያችንን በተግባር ለማዋል አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን አለብን። ለምሳሌ አንድ የጉባኤ አስፋፊ አቅኚ ለመሆን ይወስን ይሆናል። ይሳካለት ይሆን? ሰብዓዊ ሥራውና መዝናኛ አገልግሎቱን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ኃይል እንዲያሟጥጡበት ብሎም ጊዜውን እንዲሻሙበት የማይፈቅድ ከሆነ በውሳኔው ስኬታማ ሊሆን ይችላል።

16 በጣም ጥሩ የሆኑ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ማድረግ ብዙ ጊዜ ቀላል አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም “መላው ዓለም . . . በክፉው ኃይል ሥር ነው።” (1 ዮሐ. 5:19) “ይህን ጨለማ ከሚቆጣጠሩ የዓለም ገዥዎች እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራዎች ካሉ ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር” ትግል መግጠም አለብን። (ኤፌ. 6:12) ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ፣ አምላክን ለማክበር የወሰኑ ሰዎች ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።—1 ጢሞ. 6:12፤ ይሁዳ 3

17. ከምናደርጋቸው ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ ይሖዋ ከእኛ ምን ይጠብቃል?

17 ውሳኔህን ገምግም፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ማስተካከያ አድርግ። ልክ ባቀድነው መሠረት የሚከናወኑት ሁሉም ውሳኔዎች አይደሉም። ሁላችንም “ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ያጋጥሙናል። (መክ. 9:11 NW) ይሖዋ፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም በአንዳንድ ውሳኔዎቻችን እንድንጸና ይጠብቅብናል። አንድ ሰው ሕይወቱን ለይሖዋ በሚሰጥበት ወይም በጋብቻ ቃል ኪዳን ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ያደረገው ውሳኔ ለድርድር የሚቀርብ ነገር አይደለም። አምላክ እንዲህ ያሉትን ውሳኔዎች አክብረን እንድንኖር ይጠብቅብናል። (መዝሙር 15:1, 2, 4ን አንብብ።) ይሁንና አብዛኞቹ ውሳኔዎች የዚህን ያህል ክብደት የሚሰጣቸው አይደሉም። ጠቢብ የሆነ ሰው ያደረጋቸውን ውሳኔዎች በየጊዜው መለስ ብሎ ይገመግማል። ኩራት ወይም ግትርነት ያደረገውን ውሳኔ ከማስተካከል ሌላው ቀርቶ ከመለወጥ እንዲያግደው አይፈቅድም። (ምሳሌ 16:18) በዋነኝነት የሚያሳስበው ነገር የሚከተለው የሕይወት ጎዳና ምንጊዜም አምላክን የሚያስከብር መሆኑ ነው።

ሌሎች አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ እንዲያደርጉ ማሠልጠን

18. ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርጉ እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ?

18 ወላጆች፣ ልጆቻቸው አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ ማድረግን እንዲማሩ ለመርዳት ብዙ ነገር ማድረግ ይችላሉ። ግሩም ከሆኑት የማስተማሪያ ዘዴዎች አንዱ ጥሩ ምሳሌ መሆን ነው። (ሉቃስ 6:40) ተገቢ ሆኖ ሲገኝ ወላጆች አንድን ውሳኔ ለማድረግ እነሱ ራሳቸው ምን እርምጃዎችን እንደወሰዱ ለልጆቻቸው ሊነግሯቸው ይችላሉ። በተጨማሪም ልጆቻቸው አንዳንድ ውሳኔዎችን ራሳቸው እንዲያደርጉ ሊፈቅዱላቸውና ውሳኔያቸው ጥሩ ውጤት ሲያስገኝ ሊያመሰግኗቸው ይችላሉ። ይሁንና አንድ ልጅ የተሳሳተ ውሳኔ ቢያደርግስ? ወላጆች መጀመሪያ የሚታያቸው ነገር ልጁ ውሳኔው ያስከተለውን መዘዝ እንዳይቀምስ ማድረግ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም እንዲህ ማድረጋቸው ሁልጊዜ ልጁን ይጠቅመዋል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆች ልጃቸው የመንጃ ፈቃድ እንዲያወጣ ይፈቅዱለት ይሆናል። ልጁ የትራፊክ ሕግ በመጣሱ የቅጣት ወረቀት ተሰጠው እንበል። ወላጆቹ ቅጣቱን ሊከፍሉለት ይችላሉ። ሆኖም ቅጣቱን ራሱ ሠርቶ እንዲከፍል ቢያደርጉት ለድርጊቱ ኃላፊነት መውሰድን ሊማር ይችላል።—ሮም 13:4

19. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ምን ማስተማር ይኖርብናል? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

19 ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ሌሎችን እንዲያስተምሩ መመሪያ ሰጥቷል። (ማቴ. 28:20) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ልናስተምራቸው ከሚገቡ በጣም አስፈላጊ ትምህርቶች አንዱ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ማሳየት ነው። ይህን በተሳካ ሁኔታ ማድረግ እንድንችል ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ከመንገር መቆጠብ ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተሞርኩዘው የራሳቸው ውሳኔ ላይ መድረስ እንዲችሉ ማሠልጠኑ በጣም የተሻለ ነው። ደግሞም “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።” (ሮም 14:12) እንግዲያው ሁላችንም አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ እንድናደርግ የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት አለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በኅዳር 2006 የመንግሥት አገልግሎታችን ከገጽ 3-6 ላይ የሚገኘውን “የደም ክፍልፋዮችንና የራሴን ደም በመጠቀም የሚሰጡ ሕክምናዎችን በተመለከተ ምን ውሳኔ ማድረግ ይኖርብኛል?” የሚለውን አባሪ ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ፍርሃት ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል? ፍርሃታችንን ማሸነፍ የምንችለውስ እንዴት ነው?

• የምናደርጋቸው ውሳኔዎች አምላክን የሚያስከብሩ እንዲሆኑ የትኞቹ ስድስት እርምጃዎች ይረዱናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ እርምጃዎች

1 ቦታህን የምታውቅ ሁን

2 ምርምር አድርግ

3 ጥበብ ለማግኘት ጸልይ

4 ውሳኔ አድርግ

5 ውሳኔህን ተግባራዊ አድርግ

6 ውሳኔህን ገምግም፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ማስተካከያ አድርግ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ውሳኔ ለማድረግ የሚወላውል ሰው በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ላይ መሪ በሌለው ጀልባ እንደሚጓዝ ሰው ነው