በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

ኤደን ገነት በእውን የነበረ ቦታ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ኤደን ገነትን በእውን የነበረ ቦታ እንደሆነ አድርጎ የሚገልጸው ሲሆን ይህ የአትክልት ስፍራ የነበረበትን ቦታ አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎችን ይሰጠናል። በዘፍጥረት ዘገባ ላይ ከተጠቀሱት ወንዞች መካከል ሁለቱ ዛሬም ድረስ አሉ። ዘገባው የፈጠራ ታሪክ ወይም ተረት ቢሆን ኖሮ በዚህ መልክ አይቀርብም ነበር። ከሁሉ የላቀ አስተማማኝ ምሥክር የሆነው ኢየሱስ ስለ አዳምና ሔዋን የተናገረው በእውን እንደነበሩ ሰዎች አድርጎ ነው።—1/1 ገጽ 5-6, 9

አዳምና ሔዋን እንደሚሳሳቱ አምላክ ያውቅ ነበር?

አያውቅም። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥራቸው የማሰብ ችሎታና ነፃ ምርጫ የሰጣቸው ሲሆን ይህም ለመታዘዝም ሆነ ላለመታዘዝ ምርጫ እንዲያደርጉ ያስችላቸው ነበር። አምላክ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ ቢኖረውም ይህን ችሎታውን የሚጠቀምበት ሲፈልግ ብቻ ነው።—1/1 ገጽ 13-15

እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክ ስም ምትሃታዊ ኃይል እንዳለው አድርገው ማሰብ ይኖርባቸዋል?

አንዳንድ ሰዎች፣ አንድን ዕቃ ወይም ምልክት ጥበቃ የሚያስገኝ ምትሃታዊ ኃይል እንዳለው አድርገው በማሰብ እንደ ክታብ ይጠቀሙበታል፤ የአምላክ ሕዝቦች ግን የይሖዋን ስም እንዲህ አድርገው አይመለከቱትም። ስሙን መጠጊያ የሚያደርጉት በአምላክ ላይ እምነት በማሳደርና ፈቃዱን ለመፈጸም ጥረት በማድረግ ነው። (ሶፎ. 3:12, 13)—1/15 ገጽ 5-6

በእስራኤል ከሚኖሩት መካከል ከቃርሚያ ዝግጅት ተጠቃሚ የነበሩት እነማን ናቸው?

ሁሉም ሰው ተጠቃሚ ነበር። የቃርሚያ ዝግጅት፣ ይህን ሥራ የሚያከናውኑትን ድሆች ታታሪ ሠራተኞች እንዲሆኑ ያበረታታቸው ነበር። ሌሎች ደግሞ ለጋሶች እንዲሆኑና በይሖዋ በረከት እንዲተማመኑ ስለሚያደርጋቸው ጥቅም ያገኛሉ።—2/1 ገጽ 15

ይሖዋ ንጉሥ ሳኦልን የናቀው ለምን ነበር?

ሳኦል፣ የአምላክ ነቢይ መሥዋዕቱን ለማቅረብ እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ ነበረበት፤ ነገር ግን ንጉሡ የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ መሥዋዕቱን ራሱ አቀረበ። ቆየት ብሎም ጠላቶቹን ጨርሶ እንዲያጠፋ የተሰጠውን ትእዛዝ ሳይፈጽም ቀርቷል።—2/15 ገጽ 22-23

ዓመፅን እንደምንጠላ እንዴት ማሳየት እንችላለን?

የአልኮል ባሪያዎች ባለመሆን፣ ከመናፍስት ድርጊቶች በመራቅና ኢየሱስ ስለ ሥነ ምግባር ብልግና የሰጠውን ማሳሰቢያ ልብ በማለት ነው። ለምሳሌ፣ ከብልግና ምስሎችና ጽሑፎች መራቅ እንዲሁም ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የቅዠት ሐሳቦችን ማስወገድ ይኖርብናል። (ማቴ. 5:27, 28) በተጨማሪም ከተወገዱ ሰዎች ጋር ጊዜ አናሳልፍም።—2/15 ገጽ 29-32

የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በዘመናዊቷ እስራኤል ውስጥ በርካታ ጥንታዊ የንብ ቀፎዎችን ማግኘታቸው ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ከ30 የሚበልጡ የንብ ቀፎዎችን ያገኙ ሲሆን ምሑራን እንደገመቱት ከሆነ ከእነዚህ ቀፎዎች በየዓመቱ እስከ 500 ኪሎ ግራም የሚመዝን ማር ይመረት ነበር። ይህም አምላክ ‘ማርና ወተት የምታፈስ’ እንደሆነች በተናገረላት አገር ውስጥ ንብ የማነብ ሥራ ይካሄድ እንደነበር ይጠቁማል። (ዘፀ. 3:8)—3/1 ገጽ 15

ኤርምያስ “በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣ ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ” የሆነው በምን መንገድ ነው? (ኤር. 17:7, 8)

ኤርምያስ ፈጽሞ ፍሬ ማፍራቱን አላቋረጠም፤ እንዲሁም ፌዘኛ የሆኑ ሰዎች ተጽዕኖ እንዲያሳድሩበት አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ ሕይወት ሰጪ የሆነው ውኃ ምንጭ ከሆነው አምላክ ጋር በመጣበቅ እሱ የነገረውን ነገር ሁሉ ተግባራዊ አድርጓል።—3/15 ገጽ 14

ኢየሱስ ለማርታ የሚያስፈልገው ጥቂት ወይም አንድ ነገር እንደሆነ ሲናገር ሊያስተላልፍ የፈለገው ነጥብ ምን ነበር? (ሉቃስ 10:41, 42)

ማርታ የተለያዩ ምግቦችን በማዘጋጀቷ ሥጋዊ ለሆኑ ነገሮች ከልክ በላይ እንደምትጨነቅ መናገሩ አልነበረም፤ አሊያም ልፋቷን ከምንም አልቆጠረውም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቅድሚያ ልትሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ማጉላቱ ነበር። ማርታ እምነቷን ለማጠናከር የሚያስችላትን ልዩ አጋጣሚ አልተጠቀመችበትም ነበር።—4/1 ገጽ 12, 13

የኢየሱስን ጉዳይ ያየው ችሎት ከፈጸማቸው የሕግ ጥሰቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

ፍርድ ቤቱ ኢየሱስ ንጹሕ ሰው ለመሆኑ የሚቀርቡ የመከራከሪያ ነጥቦችን አላዳመጠም። ከሳሾቹ የሐሰት ምሥክሮችን ያፈላልጉ ነበር። የፍርድ ሂደቱ የተከናወነው በሌሊት ነበር። ችሎቱ ተጀምሮ ያለቀው በአንድ ቀን ነበር።—4/1 ገጽ 20