በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በጥንታዊ የሸክላ ማኅተሞች ላይ ያሉት ስሞች ከመጽሐፍ ቅዱስ ስሞች ጋር ሲመሣከሩ ምን ውጤት ተገኘ?

በጥንት ጊዜ ሕጋዊ ሰነዶችን የሚይዙ ሰዎች ሰነዱን ከጠቀለሉት በኋላ በሲባጎ ያስሩታል፤ ከዚያም ቋጠሮው ላይ የሸክላ ጭቃ ያደርጉና በማኅተም ተጭነው ይቀርጹታል። ሰዎቹ በሸክላው ላይ የማኅተም ቅርጽ ማኖራቸው እንደፈረሙበት፣ ምሥክር እንደሆኑ እንዲሁም ሰነዱ ትክክለኛ መሆኑን እንዳረጋገጡ ተደርጎ ይታይ ነበር።

አንዳንድ ጊዜ ማኅተሞች በቀለበት መልክ የሚዘጋጁ ሲሆን በወቅቱ እንደ ውድ ነገር ይታዩ ነበር። (ዘፍጥረት 38:18፤ አስቴር 8:8፤ ኤርምያስ 32:44 የታረመው የ1980 ትርጉም) በአብዛኛው አንድ ማኅተም የባለቤቱን ስም፣ የማዕረግ ስሙንና የአባቱን ስም ይይዛል።

ተመራማሪዎች የማኅተም ምልክት ያረፈባቸው በመቶ የሚቆጠሩ ነገሮችን አግኝተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎችን ስም ይዘዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አርኪኦሎጂስቶች በሁለት አይሁዳውያን ነገሥታት የግል ማኅተም እንደታተሙ የሚገመቱ የማኅተም ምልክቶች አግኝተዋል። አንደኛው እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዟል፦ ‘ንብረትነቱ የይሁዳ ንጉሥ የየሆታም [ኢዮአታም] ልጅ የአካዝ ነው።’ ሌላኛው ደግሞ ‘ንብረትነቱ የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ የሕዝቅያስ ነው’ ይላል። (2 ነገሥት 16:1, 20) አካዝና ሕዝቅያስ የነገሡት በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነበር።

ምሑራን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ንብረት እንደሆኑ የሚታመኑ ማኅተሞች ባረፉባቸው በርካታ የማኅተም ምልክቶች ላይ ምርምር አድርገዋል። ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል በኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች ለምሳሌ ባሮክ (የኤርምያስ ጸሐፊ)፣ ገማርያ (‘የሳፋን ልጅ’)፣ ይረምሕኤል (‘የንጉሡ ልጅ’)፣ ዮካል (“የሰሌምያ ልጅ”) እና ሠራያ (የባሮክ ወንድም) ይገኙበታል።​—ኤርምያስ 32:12፤ 36:4, 10, 26፤ 38:1፤ 51:59

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ጊዜያት የሚከፋፈሉት እንዴት ነበር?

▪ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ‘ጠዋት፣’ “ቀትር፣” “እኩለ ቀን” እና “ምሽት” የሚሉትን የጊዜ መግለጫዎች ይጠቀማሉ። (ዘፍጥረት 24:​63፤ ዘፍጥረት 43:16፤ 1 ነገሥት 18:26) ዕብራውያን ሌሊቱን እያንዳንዳቸው አራት ሰዓት ገደማ በሚሆኑ ሦስት ክፍለ ጊዜያት ይከፋፍሉት ነበር፤ በኋላ ግን የግሪካውያንን እና የሮማውያንን ዘዴ በመከተል ሌሊቱን በአራት ክፍለ ጊዜ መከፋፈል ጀመሩ። ኢየሱስ ቀጥሎ ያለውን ሐሳብ ሲናገር አይሁዳውያን በኋላ ላይ የተከተሉትን የጊዜ አከፋፈል ዘዴ እንደተጠቀመ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፦ “የቤቱ ባለቤት፣ በምሽት ይሁን በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ይሁን ንጋት ላይ፣ መቼ እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።” (ማርቆስ 13:35) “ምሽት” የተባለው የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ ፀሐይ ከጠለቀችበት አንስቶ እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ድረስ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። ቀጥሎ ያለው ክፍለ ጊዜ እስከ እኩለ ሌሊት የሚቆይ ሲሆን “ዶሮ ሲጮኽ” የተባለው ሦስተኛው ክፍለ ጊዜ ደግሞ እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ድረስ ይዘልቃል። “ንጋት” የሚባለው የመጨረሻው ክፍለ ጊዜ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ ያለውን ሰዓት ይሸፍናል። ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ላይ እየተራመደ የሄደው “በአራተኛው ክፍለ ሌሊት” ነበር።​—⁠ማቴዎስ 14:23-26

በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ሰዓት” የሚለው ቃል ፀሐይ ወጥታ እስክትጠልቅ ያለውን የቀን ክፍለ ጊዜ አንድ አሥራ ሁለተኛ ክፋይን የሚያመለክት ነው። (ዮሐንስ 11:9) ፀሐይ የምትወጣበትና የምትጠልቅበት ጊዜ ከወቅት ወቅት ስለሚለያይ ግምታዊ አጠራሮችን መጠቀም የተለመደ ነበር፤ “ስድስት ሰዓት ገደማ” የሚለውን ጥቅስ እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል።​—⁠የሐዋርያት ሥራ 10:9

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሸክላ ማኅተሞች፤ የፊተኛው የሕዝቅያስን እና የአካዝን ስም የያዘ ነው፤ የኋለኛው ደግሞ የባሮክን ስም እንደያዘ ይገመታል

[የሥዕሉ ምንጭ]

Back: Courtesy of Israel Museum, Jerusalem

Front: www.BibleLandPictures.com/Alamy

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥላ የሚቆጥር ሰዓት፣ በሮማውያን ሥርወ መንግሥት (ከ27 ዓ.ዓ.–476 ዓ.ም.)

[የሥዕሉ ምንጭ]

© Gerard Degeorge / The Bridgeman Art Library International