በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሩሲያ የሚኖሩ ሰላማዊ ሕዝቦች ለስማቸው ጥብቅና ቆሙ

በሩሲያ የሚኖሩ ሰላማዊ ሕዝቦች ለስማቸው ጥብቅና ቆሙ

ይድረስ ለሩሲያ ሕዝብ፦ ይህ ዘገባ በቀረበበት በዚህ መጽሔት አማካኝነት ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሩሲያ ውስጥ የአምልኮ ነፃነት አግባብ ባልሆነ መንገድ እየታፈነ መሆኑን እንዲያውቁ ይደረጋል። የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በስርጭቱም ሆነ በሚተረጎምባቸው ቋንቋዎች ብዛት በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሔት ነው። በዚህ መጽሔት ላይ የቀረበው ይህ ዘገባ በ188 ቋንቋዎች ታትሞ ይወጣል፤ እንዲሁም ከ40 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች ይታተማል። አንዳንድ ባለሥልጣናት በሩሲያ ባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ እየደረሰ ያለውን ነገር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያውቀው አይፈልጉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “የተሰወረ መገለጡ፣ ሚስጥር የሆነም መታወቁ አይቀርም” በማለት የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸው ይረጋገጣል።​—ሉቃስ 12:2

በታኅሣሥ 2009 እና በጥር 2010 በሩሲያ ያሉ ሁለት ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት ጽንፈኛ እንደሆነ የሚገልጽ ውሳኔ አስተላልፈዋል። ታሪክ ራሱን እየደገመ ያለ ይመስላል። በሶቪየት አገዛዝ ወቅት በሩሲያ የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች የአገሪቱ ጠላት እንደሆኑ ተደርገው በመቆጠር በሐሰት ተከሰው ነበር። የይሖዋ ምሥክሮቹ በግዞት የተወሰዱ ከመሆኑም በላይ በወኅኒ ቤቶች ይታሰሩና በካምፖች ውስጥ የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ ይደረጉ ነበር። የሶቪየት አገዛዝ ከተገረሰሰ በኋላ ግን የይሖዋ ምሥክሮች ከተከሰሱበት ወንጀል ነፃ እንደሆኑ መረጋገጥ ችሎ ነበር። አዲሱ መንግሥት ይፋ በሆነ መንገድ ስማቸው እንዲታደስ አድርጎ ነበር። * በዛሬው ጊዜ ግን አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ስም እንደገና ለማጉደፍ ቆርጠው የተነሱ ይመስላል።

በ2009 መጀመሪያ ላይ ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ነፃነት ላይ ጥቃት ሰነዘሩ። በየካቲት ወር ብቻ አቃቤ ሕጎች በመላው አገሪቱ 500 ምርመራዎችን አካሂደዋል። የዚህ ዘመቻ ዓላማ ምን ነበር? የይሖዋ ምሥክሮች ሕግ ጥሰዋል የተባለውን ነገር ለማረጋገጥ ነበር። በቀጣዮቹ ወራት ደግሞ ፖሊሶች በመንግሥት አዳራሾችና በግል ቤቶች ውስጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስብሰባ እየተካሄደ ሳለ በኃይል ገብተው ፍተሻ አካሄዱ። ከዚያም ጽሑፎችንና የግል ንብረቶችን ወረሱ። ባለሥልጣናቱ የይሖዋ ምሥክሮችን ደግፈው የሚከራከሩ የውጭ አገር ጠበቆችን ከአገር ያስወጡ ከመሆኑም በላይ ወደ አገሪቱ ተመልሰው እንዳይገቡም ከልክለዋል።

ጥቅምት 5, 2009 የጉምሩክ ባለሥልጣናት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን የያዘው ጭነት በሴንት ፒተርስበርግ አቅራቢያ ባለ ድንበር ላይ እንዲታገድ አደረጉ። ጽሑፎቹ የታተሙት በጀርመን ሲሆን የተዘጋጁትም በሩሲያ ለሚገኙ በርካታ ጉባኤዎች ነበር። በሩሲያ ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር የሚገኝ አደገኛ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን የሚፈትሽ አንድ ልዩ ግብረ ኃይል ጭነቱን መረመረ። ለምን? የጉምሩክ ባለሥልጣን የጻፈው አንድ ሰነድ ጭነቱ “ሃይማኖታዊ ብጥብጥ ለማስነሳት ታስበው የተዘጋጁ ጽሑፎችን ይዞ ሊሆን ይችላል” በማለት ገልጿል።

ብዙም ሳይቆይ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚፈጸመው እንግልት እየተባባሰ መጥቶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደረሰ። የሩሲያ ፌዴሬሽንና የአልታይ ሪፑብሊክ (የሩሲያ ክፍል ናት) ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች አሁን እያነበብከው ያለኸውን መጽሔት ጨምሮ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸውን የተለያዩ ጽሑፎች ጽንፈኝነትን የሚያንጸባርቁ እንደሆኑ የሚገልጽ ውሳኔ አስተላልፈዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ በሆነ መንገድ ይግባኝ ቢጠይቁም እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጉዳዩ እንዳሳሰበው ቢገልጽም ሰሚ ጆሮ አልተገኘም! ፍርድ ቤቶቹ ያሳለፏቸው ብያኔዎች አሁንም እንደጸኑ ሲሆን በዚህም የተነሳ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ወደ አገሪቱ ማስገባትም ሆነ ማሰራጨት ሕገ ወጥ እንደሆነ ቀጥሏል።

ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ስማቸውን የሚያጎድፍና እንቅስቃሴያቸውን የሚገድብ ነገር ሲፈጸምባቸው ምን ምላሽ ሰጡ? ደግሞስ ፍርድ ቤቶቹ ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ሁሉም የሩሲያ ዜጎች ያላቸውን ሃይማኖታዊ ነፃነት የሚነካው እንዴት ነው?

ሁኔታው እየተባባሰ ሲመጣ የተሰጠ ፈጣን ምላሽ

ቭላዲሚር ሌትቪን (ዕድሜ 81) የ14 ዓመት ልጅ ሳሉ በግዞት ወደ ክራስነያርስኪ ክሬይ ተወስደው ነበር። ዘመቻው ከተካሄደባቸው ቀናት በአንዱ ማለትም ዓርብ ዕለት ጠዋት ልዩ ትራክቱን ለማሰራጨት የተሰማራን አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን መርተዋል

ዓርብ፣ የካቲት 26, 2010 ላይ በመላው ሩሲያ የሚገኙ 160,000 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች እንደገና ሊመጣ ይሆን? ለሩሲያ ዜጎች የቀረበ ጥያቄ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ አንድ ልዩ ትራክት 12 ሚሊዮን ቅጂ ማሰራጨት ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ኡሶልየ ሲቢርስከየ በምትባለው የሳይቤሪያ ከተማ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ትራክቱን ለማሰራጨት ከማለዳው 11:30 በተለያዩ ጎዳናዎች ላይ ተሰብስበው ነበር። ከእነሱም መካከል አንዳንዶቹ በ1951 በእምነታቸው ምክንያት በግዞት ወደ ሳይቤሪያ የተወሰዱ ነበሩ። በከተማዋ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ከዜሮ በታች 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሆነውን ቅዝቃዜ ተቋቁመው ለእነሱ የተመደበላቸውን 20,000 ትራክት አሰራጭተዋል።

ኒኮላይ ያሲንስኪ (ዕድሜ 73) ቅንዓት በተሞላበት ስሜት በዘመቻው ተሳትፈዋል። ቭላዲሚር “አሁን እውነት እንደገና ሊያሳድዱንና ይሖዋን የማምለክ መብታችንን ሊቀሙን ነው?” በማለት ጠይቀዋል

የይሖዋ ምሥክሮች የሦስቱን ቀን ዘመቻ ለማስታወቅ የሩሲያ ዋና ከተማ በሆነችው በሞስኮ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ንግግር እንዲያቀርቡ ከተጋበዙት መካከል ከሰብዓዊ መብት ተቋም የመጡት ሚስተር ልየፍ ሌቪንሶን የተባሉ ኤክስፐርት ይገኙበታል። እሳቸውም በናዚ ጀርመንና በሶቪየት ኅብረት አገዛዝ ወቅት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የደረሰውን አግባብ ያልሆነ እንግልትና ስደት በአጭሩ ከገለጹ በኋላ ከዚያ ወዲህ መንግሥት ከተከሰሱበት ወንጀል ነፃ አድርጓቸው እንደነበር ተናገሩ። በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል፦ “በሶቪየት የግዛት ዘመን ስደት የደረሰባቸው ሁሉም ሃይማኖታዊ እምነቶች በፕሬዚዳንት የልሲን ትእዛዝ ስማቸው ታድሶላቸዋል። እንዲሁም የተወሰደባቸው ነገር በሙሉ እንዲመለስላቸው ተደርጓል። የይሖዋ ምሥክሮች በሶቪየት ኅብረት መንግሥት የተወሰደባቸው ምንም ዓይነት ንብረት ባይኖርም መልካም ስማቸው ግን ተመልሶላቸዋል።”

የሚያሳዝነው ይህ መልካም ስማቸው እንደገና ስጋት ላይ ወድቋል። ሚስተር ሌቪንሶን እንደገለጹት መንግሥት “በተፈጸመው በደል ማዘኑን በገለጸበት በዚያው አገር እነዚህ ሰዎች እንደገና አግባብ ያልሆነ ስደት እየደረሰባቸው ነው።”

ዘመቻው የሕዝቡን ልብ ነክቷል

ታዲያ የትራክቱ ዘመቻ የታለመለትን ግብ መትቷል? ሚስተር ሌቪንሰን እንዲህ ብለዋል፦ “ወደዚህ እየመጣሁ ሳለ [ጋዜጣዊ መግለጫ ወደሚሰጥበት ስፍራ ማለታቸው ነው] ሰዎች በባቡር ጣቢያው ውስጥ ቁጭ ብለው የይሖዋ ምሥክሮች ዛሬ በመላው ሩሲያ እያሰራጩ ያሉትን በራሪ ወረቀት ሲያነቡ አየኋቸው። . . . ሰዎች ቁጭ ብለው እያነበቡት ነው፤ ደግሞም የሚያነቡት በትኩረት ነው።” * ለምሳሌ ቀጥሎ የቀረቡትን ተሞክሮዎች ተመልከት።

ሙስሊሞች በሚበዙበት በማዕከላዊ ሩሲያ የሚኖሩ አንዲት አረጋዊት ሴት ትራክቱን ከተቀበሉ በኋላ ስለ ምን ጉዳይ እንደሚናገር ጠየቁ። ትራክቱ የሚገልጸው በሩሲያ ስላለው ሰብዓዊ መብትና ነፃነት እንደሆነ ሲነገራቸው “በመጨረሻ፣ ይህን ጉዳይ የሚያነሳ ሰው ተገኘ ማለት ነው! በዚህ ረገድ ሩሲያ ወደ ሶቪየት ኅብረት ዘመን እየተመለሰች ነው። በጣም አመሰግናችኋለሁ። ጥሩ ሥራ ነው!” በማለት በአድናቆት ተናግረዋል።

በቼልያቢንስክ የምትኖር አንዲት ሴት ደግሞ ትራክቱን እንድትቀበል ግብዣ ሲቀርብላት እንዲህ ብላለች፦ “ትራክቱ ደርሶኝ አንብቤዋለሁ። ሙሉ በሙሉ ከጎናችሁ ነኝ። እንዲህ በመሰለ የተደራጀ መንገድ ለእምነቱ ጥብቅና የሚቆም ሌላ ሃይማኖት አይቼ አላውቅም። አለባበሳችሁን እወደዋለሁ፤ ደግሞም ምንጊዜም ዘዴኞች ናችሁ። ስለምታምኑበት ነገር በጣም እርግጠኞች እንደሆናችሁ በግልጽ ይታያል። አምላክ ከእናንተ ጋር እንደሆነ ይሰማኛል።”

በሴንት ፒተርስበርግ የሚኖር ቀደም ብሎ ትራክቱ የደረሰው አንድ ሰው ያነበበውን ነገር ወዶት እንደሆነ ተጠይቆ ነበር። እሱም “አዎን” በማለት መልስ ከሰጠ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እያነበብኩት ሳለ ስሜቴ በጥልቅ ተነካ፤ እንዲያውም አልቅሼ ነበር። ሴት አያቴ [በሶቪየት የግዛት ዘመን] ጭቆና ደርሶባት ነበር፤ ከእሷ ጋር ታስረው ስለነበሩት ሰዎችም ብዙ ነግራኛለች። አብረዋት ከታሰሩት ውስጥ ብዙ ወንጀለኞች የነበሩ ቢሆንም ያለ ምንም ጥፋት በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩም ነበሩ። ሁሉም ሰው በዚያን ዘመን ስለተፈጸመው ነገር ማወቅ ያለበት ይመስለኛል፤ ስለዚህ እያደረጋችሁ ያላችሁት ነገር ትክክል ነው።”

ወደፊትስ በሩሲያ ምን ይመጣ ይሆን?

ስቴፓን ሌቪትስኪ (ዕድሜ 85) እና ባለቤታቸው ዬሌና። ስቴፓን አንድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ይዘው በመገኘታቸው ለአሥር ዓመት ታስረዋል

የይሖዋ ምሥክሮች ላለፉት 20 ዓመታት በሩሲያ ውስጥ ያገኙትን መጠነኛ ነፃነት ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ ያገኙትን ነፃነት በቀላሉ ሊያጡት እንደሚችሉም አሳምረው ያውቃሉ። በቅርቡ የተሰነዘረባቸው የስም ማጥፋት ዘመቻ ሩሲያ ወደ ጭቆናው ዘመን እየተመለሰች መሆኗን የሚጠቁም ይሁን አይሁን ጊዜ ያሳየናል።

ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ምንም ይምጣ ምን ሰላምና ተስፋ ያዘለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለሰዎች መስበካቸውን ለመቀጠል ቆርጠዋል። የተዘጋጀው ልዩ ትራክት ቁርጠኝነታቸውን እንደሚከተለው በማለት በአጭሩ ገልጾታል፦ “ጭቆና የተሳካ ውጤት ያስገኛል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ቃሉ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ዘዴ በታከለበትና አክብሮት በተሞላበት መንገድ መናገራችንን አናቆምም። (1 ጴጥሮስ 3:15) በናዚ ጀርመን ግዛት ብዙ ማስፈራሪያዎች ቢደርሱብንም አላቆምንም፤ አገራችን በነበረችበት የጨለማ ዘመን ጭቆና ቢደርስብንም አላቆምንም፤ አሁንም ቢሆን አናቆምም።​—የሐዋርያት ሥራ 4:18-20

^ አን.13 ጋዜጣዊ መግለጫው ከመቅረቡ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በሞስኮ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ትራክቱን ማሰራጨት ጀምረው ነበር።