በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር አሰልቺ አይሆንም?

በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር አሰልቺ አይሆንም?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር አሰልቺ አይሆንም?

▪ መጽሐፍ ቅዱስ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንደምንችል የሚናገር ተስፋ ይዟል። (መዝሙር 37:29፤ ሉቃስ 23:43) ታዲያ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ሥር ማለቂያ ለሌለው ጊዜ መኖር አሰልቺ አይሆንም?

ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው። ተመራማሪዎች አሰልቺ በሆነ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ መቆየት ውጥረትና ጭንቀት ሊያስከትል እንዲሁም ራስን ለአደጋ የማጋለጥ አጋጣሚን ሊጨምር እንደሚችል ደርሰውበታል። በሕይወታቸው ውስጥ ዓላማ የሌላቸው ሰዎች ወይም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ማከናወን የመረራቸው ሰዎች ሕይወት አሰልቺ ሊሆንባቸው ይችላል። ታዲያ በገነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሕይወታቸው ዓላማ ቢስ ይሆናል? በዚያ የሚደረገው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴስ አሰልቺ ይሆናል?

በመጀመሪያ ደረጃ የዘላለም ሕይወት ተስፋን የሰጠን የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነው ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። (ዮሐንስ 3:16፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ ደግሞ ፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር ጥልቅ ከመሆኑም በላይ አሁን ያሉንን መልካም ነገሮች በሙሉ የሰጠን እሱ ነው።​—ያዕቆብ 1:17

ደስተኛ እንድንሆን ከተፈለገ ዓላማ ያለው ሥራ መሥራት እንዳለብን የፈጠረን አምላክ ያውቃል። (መዝሙር 139:14-16፤ መክብብ 3:12) በገነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሮቦት የሆኑ ይመስል ሥራቸው እርካታ የሌለውና ትርጉም የለሽ እንደሆነ አይሰማቸውም። ከዚህ ይልቅ የሚያከናውኑት ሥራ ለራሳቸውም ሆነ ለሚወዷቸው ሰዎች ጥቅም የሚያመጣ ይሆናል። (ኢሳይያስ 65:22-24) ደስ ብሎህ ሙሉ ቀን በትኩረት የምትሠራው ሥራ ቢኖርህ ሕይወት አሰልቺ የሚሆንብህ ይመስልሃል?

በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ ማንኛውም ሰው በገነት ውስጥ እንዲኖር የማይፈቅድ መሆኑን ልብ በል። የዘላለም ሕይወት ስጦታን የዘረጋው ልጁን ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ለሚያደርጉ ሰዎች ብቻ ነው። (ዮሐንስ 17:3) ኢየሱስ በምድር ሳለ የአባቱን ፈቃድ ማድረግ ያስደስተው ነበር። ዘላቂ ደስታ ሊገኝ የሚችለው ከመቀበል ይልቅ በመስጠት እንደሆነ በቃልም ሆነ ምሳሌ በመሆን ተከታዮቹን አስተምሯቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ዳግመኛ በምትቋቋመው ገነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ሕይወታቸውን የሚመሩት በሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት ይኸውም አምላክንና ሰዎችን እንዲወዱ በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት ነው። (ማቴዎስ 22:36-40) ራስ ወዳድ ባልሆኑና አንተንም ሆነ ሥራቸውን በሚወዱ ሰዎች መካከል መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስበው! እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር መኖር አሰልቺ የሚሆን ይመስልሃል?

በገነት ውስጥ የምናከናውነው ሌላስ ምን ነገር አለ? በየዕለቱ ስለ ፈጣሪያችን አዲስ ነገር እንማራለን። በአሁኑ ጊዜም እንኳ ተመራማሪዎች ስለ ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ብዙ አስደናቂ ነገሮችን አግኝተዋል። (ሮም 1:20) ሆኖም ስለ እነዚህ ነገሮች ያለን እውቀት ከባሕር ላይ በጭልፋ የተቀዳ ያህል ነው። ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ይኖር የነበረው ታማኙ ኢዮብ ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች የሚያውቃቸውን ነገሮች መለስ ብሎ ካሰበ በኋላ የደረሰበት መደምደሚያ ዛሬም ድረስ እውነት ነው። እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህ የሥራው ዳር ዳር ናቸው፤ ስለ እርሱ የሰማነው ምንኛ አነስተኛ ነው! የኀይሉንስ ነጐድጓድ ማን ሊያስተውል ይችላል?”​—ኢዮብ 26:14

ምንም ያህል ዘመን ብንኖር ስለ ይሖዋ አምላክም ሆነ ስለ ሥራዎቹ ማወቅ የምንፈልገውን ሁሉ መርምረን ልንጨርስ አንችልም። አምላክ በልባችን ውስጥ ለዘላለም የመኖር ፍላጎት እንዳስቀመጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይሁን እንጂ አክሎ “እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም” በማለት ይናገራል። (መክብብ 3:10, 11) በየጊዜው ስለ ፈጣሪህ አዲስ ነገር ብታውቅ ሕይወት አሰልቺ የሚሆንብህ ይመስልሃል?

በዛሬው ጊዜም እንኳ ለሰዎች የሚጠቅምና ለአምላክ ክብር የሚያመጣ ሥራ በመሥራት የተጠመዱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሕይወት አሰልቺ አይሆንባቸውም። እንዲህ ባለው ሥራ የምንጠመድ ከሆነ ምንጊዜም ሌላው ቀርቶ ለዘላለም ብንኖር እንኳ ሕይወት አሰልቺ እንደማይሆንብን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Earth: Image Science and Analysis Laboratory, NASA-Johnson Space Center; Galaxy: The Hubble Heritage Team (AURA/STScI/NASA)