በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ይሖዋ እረኛዬ ነው”

“ይሖዋ እረኛዬ ነው”

ወደ አምላክ ቅረብ

“ይሖዋ እረኛዬ ነው”

እስቲ በዚህ ገጽ ላይ ያለውን ሥዕል ለአንድ አፍታ ተመልከተው። ግልገሏ በእረኛዋ እቅፍ ውስጥ መሆኗ ምን ያህል የመተማመን ስሜት እንደፈጠረባት መገመት ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለውን ጥልቅ አሳቢነት ለማሳየት በመዝሙር 23 ላይ አንድ እረኛ ከበጎቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ምሳሌ አድርጎ ይጠቀማል። ይሖዋ በእሱ እንድንተማመንና እኛም እንደ ዳዊት “ይሖዋ እረኛዬ ነው” ብለን አፋችንን ሞልተን እንድንናገር ይፈልጋል። *​—ቁጥር 1 NW

የዚህ መዝሙር ጸሐፊ የሆነው ዳዊት ወጣት እያለ እረኛ ነበር። በጎች ምን እንደሚያስፈልጋቸውና የእረኛ ኃላፊነት ምን እንደሆነ በሚገባ ያውቃል። የአምላክን እንክብካቤ በሕይወቱ የተመለከተው ዳዊት “የማረጋገጫ ወይም የመተማመኛ መዝሙር” ተብሎ የሚጠራውን መዝሙር ጽፏል። ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በመዝሙሩ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ ተገልጿል። (ቁጥር 16 NW) በሁለቱ ቁጥሮች መካከል ያለው ሐሳብ ደግሞ አንድ እረኛ ለበጎቹ ከሚያደርገው እንክብካቤ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ይሖዋ ሕዝቡን የሚንከባከብበትን ሦስት መንገዶች ይገልጻል።​—መዝሙር 100:3

ይሖዋ በጎቹን ይመራል። በጎች እረኛቸው ከሌለ ባዝነው ይጠፋሉ። እኛም በተመሳሳይ ትክክለኛውን የሕይወት ጎዳና ለማግኘት እርዳታ ያስፈልገናል። (ኤርምያስ 10:23) ዳዊት እንደገለጸው ይሖዋ ሕዝቡን ወደ ‘ለመለመ መስክ’ እና ወደ ‘ዕረፍት ውኃ’ ይመራቸዋል። በተጨማሪም “በጽድቅ መንገድ” እየመራ ይወስዳቸዋል። (ቁጥር 23) ውብ ስለሆነው የመሰማሪያ ስፍራ የሚናገረው ይህ መግለጫ በይሖዋ መታመን እንደምንችል ማረጋገጫ ይሰጠናል። አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በገለጸው መሠረት የመንፈሱን አመራር የምንከተል ከሆነ ሕይወታችን እርካታ ያለው ይሆናል፤ እንዲሁም እፎይታና ደኅንነት ይሰማናል።

ይሖዋ በጎቹን ይጠብቃል። በጎች ድንጉጦችና አቅመ ቢስ ስለሆኑ የግድ እረኛ ያስፈልጋቸዋል። ይሖዋ ፈጽሞ መፍራት እንደሌለባቸው ለሕዝቡ ነግሯቸዋል፤ ሌላው ቀርቶ “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ” ቢሄዱም በሌላ አማርኛ ሕይወታቸው ምንም ተስፋ የሌለው ጨለማ መስሎ በሚታያቸው ጊዜም እንኳ መፍራት አንደማይገባቸው ገልጾላቸዋል። (ቁጥር 4) ይሖዋ ሁልጊዜም እነሱን ለመርዳት ዝግጁ ስለሆነ በዓይኑ ይከታተላቸዋል። አገልጋዮቹ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ለመወጣት የሚያስችላቸውን ጥበብና ጥንካሬ ሊሰጣቸው ይችላል።​—ፊልጵስዩስ 4:13፤ ያዕቆብ 1:2-5

ይሖዋ በጎቹን ይመግባቸዋል። በጎች በራሳቸው ምግብ ወዳለበት ስፍራ መሄድ ስለማይችሉ የግድ የእረኛቸውን እጅ ይጠብቃሉ። እኛም መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካት የምንችለው አምላክ በሚሰጠን እርዳታ አማካኝነት ብቻ ነው። (ማቴዎስ 5:3) የሚያስደስተው ነገር ይሖዋ ለጋስ አምላክ በመሆኑ ለአገልጋዮቹ የተትረፈረፈ ማዕድ አዘጋጅቶላቸዋል። (ቁጥር 5) መጽሐፍ ቅዱስና አሁን እያነበብከው እንዳለኸው ያሉ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች፣ የሕይወትን ትርጉምና አምላክ ለእኛ ያለውን ዓላማ ለማወቅ የሚያስችለንን መንፈሳዊ ምግብ ያቀርቡልናል።

ዳዊት በሰማይ ከሚኖረው እረኛው ጋር ተቀራርቦ እስከ ኖረ ድረስ ‘በሕይወቱ ዘመን ሁሉ’ የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደሚያገኝ ስለተረዳ በውስጡ የመተማመን ስሜት ተሰምቶት ነበር። (ቁጥር 6) አንተስ እንዲህ ያለው የመተማመን ስሜት እንዲኖርህ ትመኛለህ? ከሆነ ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ መማር ይኖርብሃል። እንዲህ ካደረግህ ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ እንደሆኑ የሚያሳዩትን አገልጋዮቹን በሚመራው፣ በሚጠብቀውና በሚመግበው ታላቁ እረኛ እቅፍ ውስጥ ስለምትሆን የመተማመን ስሜት ይኖርሃል።​—ኢሳይያስ 40:11

በግንቦት ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ከ⁠ኢዮብ 38 እስከ መዝሙር 25

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ብዙ ሰዎች የሚያውቁት “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው” የሚለውን ነው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊውን ስም ያልተጠቀሙት ለምን እንደሆነ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 195-197 ተመልከት።