በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሞቱ ሰዎች ተስፋ አላቸው?

የሞቱ ሰዎች ተስፋ አላቸው?

ከአምላክ ቃል ተማር

የሞቱ ሰዎች ተስፋ አላቸው?

ይህ ርዕሰ ትምህርት በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን የሚያነሳ ሲሆን መልሶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችልም ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ቢወያዩ ደስ ይላቸዋል።

1. ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?

ኢየሱስ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ወደምትገኘው የቢታንያ መንደር ሲደርስ ወዳጁ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን አልፎት ነበር። ኢየሱስ ከሟቹ እህቶች ከማርታና ከማርያም ጋር ወደ መቃብሩ ስፍራ ሄደ። ወዲያው በርካታ ሰዎች ተሰበሰቡ። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሳው ማርታና ማርያም ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ?​—ዮሐንስ 11:20-24, 38-44ን አንብብ።

ማርታ ሙታን እንደሚነሱ እምነት ነበራት። ታማኝ የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች አምላክ እንደገና በምድር ላይ መኖር እንዲችሉ ሲል ወደፊት የሞቱ ሰዎችን እንደሚያስነሳ ከድሮ ጀምሮ ያውቁ ነበር።​—ኢዮብ 14:14, 15ን አንብብ።

2. ሙታን የሚገኙት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው?

የሕይወት ኃይል ወይም “መንፈስ” ሰዎችንም ሆነ እንስሳትን ሕያው አድርጎ የሚያቆም ቢሆንም እኛ የሰው ልጆች ሥጋዊ አካል የለበስን መንፈሳዊ ፍጥረታት አይደለንም። (መክብብ 3:19፤ ዘፍጥረት 7:21, 22) እኛ ከአፈር የተሠራን ፍጥረታት ነን። (ዘፍጥረት 2:7፤ 3:19) አንጎላችን ሥራውን ሲያቆም የማሰብ ችሎታችን ይጠፋል። ሙታን ምንም ስለማያውቁ አልዓዛር ከሞት ከተነሳ በኋላ ሞቶ እያለ ስለነበረው ሁኔታ ምንም የተናገረው ነገር አልነበረም።​—መዝሙር 146:4ን እና መክብብ 9:5, 10ን አንብብ።

ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው የሞቱ ሰዎች አይሠቃዩም። በመሆኑም አምላክ የሞቱ ሰዎችን ያሠቃያል የሚለው ትምህርት ሐሰት ነው። ይህ አምላክን እንደ መሳደብ ነው። አምላክ፣ ሰዎችን በእሳት የማቃጠልን ሐሳብ እንኳ ይጸየፋል።​—ኤርምያስ 7:31ን አንብብ።

3. ከሙታን ጋር መነጋገር እንችላለን?

የሞቱ ሰዎች መናገር አይችሉም። (መዝሙር 115:17) ይሁንና ክፉ መላእክት የሞተው ሰው መንፈስ መስለው በመቅረብ ከሰዎች ጋር ሊነጋገሩ ይችላሉ። (2 ጴጥሮስ 2:4) ይሖዋ ከሞቱ ሰዎች ጋር ለመነጋገር መሞከር እንደሌለብን አስጠንቅቋል።​—ዘዳግም 18:10, 11ን አንብብ።

4. ትንሣኤ የሚያገኙት እነማን ናቸው?

በሚመጣው አዲስ ዓለም በመቃብር ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ይነሳሉ። ይሖዋን ሳያውቁ መጥፎ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የነበሩ ሰዎች እንኳ ይነሳሉ።​—ሉቃስ 23:43ን እና የሐዋርያት ሥራ 24:15ን አንብብ።

ከሞት የተነሱ ሰዎች አምላክን በተመለከተ እውነቱ ምን እንደሆነና ኢየሱስን በመታዘዝ በእሱ ላይ እምነት እንዳላቸው ማሳየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይማራሉ። (ራእይ 20:11-13) ከሞት ተነስተው መልካም ሥራዎችን መሥራታቸውን የቀጠሉ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ። ይሁንና ትንሣኤ ካገኙት መካከል አንዳንዶቹ መጥፎ ድርጊት መፈጸማቸውን ይቀጥላሉ። ይህም ያገኙት ትንሣኤ ‘የፍርድ ትንሣኤ’ እንዲሆንባቸው ያደርጋል።​—ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብ።

5. ትንሣኤ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

የትንሣኤ ተስፋ እውን ሊሆን የቻለው አምላክ ልጁን ለእኛ ሲል እንዲሞት በመላኩ ነው። በመሆኑም ትንሣኤ የይሖዋ ፍቅርና ጸጋ መገለጫ ነው።​—ዮሐንስ 3:16ን እና ሮም 6:23ን አንብብ።

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 6 እና 7ን ተመልከት።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳም የተፈጠረው ከአፈር ነው