በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቋንቋው ለጆሮዬ እንደ ውብ ሙዚቃ ነበር

ቋንቋው ለጆሮዬ እንደ ውብ ሙዚቃ ነበር

ከማዳጋስካር የተላከ ደብዳቤ

ቋንቋው ለጆሮዬ እንደ ውብ ሙዚቃ ነበር

እኔና ባለቤቴ በሚስዮናዊነት እንድናገለግል ወደተመደብንበት አዲስ ክልል ይኸውም ማዳጋስካር ወደምትባለው ደሴት ለመሄድ ተነሳን። ይሖዋ ለእኛ ተስማሚ የሆነውን የአገልግሎት ምድብ እንደመረጠልንና በዚያም ውጤታማ እንድንሆን እንደሚረዳን በመተማመን እንባችንንና ፍርሃታችንን ዋጥ አድርገን ከወዳጅ ዘመዶቻችን ጋር ተሰነባበትን።

በአዲሱ ምድባችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘንበትን የጉባኤ ስብሰባ ፈጽሞ አንረሳውም። የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የሚመራው ወንድም የኅብረ ዝማሬ ኦርኬስትራን የሚመራ ይመስል ነበር። ስለ ቋንቋው ያለን እውቀት በጣም ውስን ከመሆኑ የተነሳ የሚነገሩት ቃላት ለጆሯችን እንደ ውብ ሙዚቃ ነበሩ። የሚነገረውን ነገር ቶሎ መረዳት አንችልም ነበር።

በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ የሚቀርብን ተጨማሪ ጥያቄ ለመጀመሪያ ጊዜ መረዳት በቻልኩበት ወቅት ሳላስበው ጮክ ብዬ መልስ ሰጠሁ። አጠገቤ የተቀመጡት ሰሙኝ፤ እኔም ሳቄ እንዳያመልጠኝ አፌን በእጄ አፍኜ ያዝኩት። ኀፍረት ቢሰማኝም ምን እየተባለ እንዳለ ስለገባኝ ተደስቼ ነበር!

በአገልግሎት ለሌሎች ምሳሌ በመሆን ፈንታ እነሱ እጄን ይዘው እየመሩኝ እንዳለ ሆኖ ይሰማኝ ነበር። ወንድሞችና እህቶች በመስክ አገልግሎት ላይ ሰዎች ሊረዱት በሚችል መንገድ እንዴት መናገር እንደምችል ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ይነግሩኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ምን ማለት እንዳለብኝና የትኞቹን ጥቅሶች መጠቀም እንደምችል ያሳዩኝ ነበር።

አንድ ቀን በአገልግሎት ላይ ሳለሁ አንድ ልጅ “ቫዛ! ቫዛ!” ሲል ጮኸ። ይህም በማላጋሲ ቋንቋ “ፈረንጅ” እንደ ማለት ነው። ሌሎችም ልጆች ተሰብስበው እንዲህ እያሉ እንዳይጮኹ በማሰብ ፈጠን ፈጠን እያልን መራመድ ጀመርን። ከዚያም አንድ ልጅ ይጮኽ የነበረውን ልጅ ተቆጣው። “ፈረንጅ አይደለችም፤ ቋንቋችንን መናገር ትችላለች!” አለ። ልጆቹ የሚነጋገሩት በፍጥነት ስለነበር የሚሉትን መረዳት ተቸግሬ ነበር፤ በመሆኑም ከእኔ ጋር የነበረችው የአገሩ ተወላጅ የሆነች እህት ያሉትን ነገር ተረጎመችልኝ። ያም ሆኖ እየተሻሻልኩ እንደሆነ ስለተሰማኝ ደስ አለኝ። ከጊዜ በኋላ ማዳጋስካርን እንደ ትውልድ አገሬ አድርጌ መመልከት ጀመርኩ።

በተለያዩ ጊዜያት የብቸኝነት ስሜት ሲሰማኝ ትንንሽ ልጆች፣ ከእነሱ ጋር በደንብ ሐሳብ መለዋወጥ ባልችልም እንኳ መጥተው እጄን በመያዝ ፊታቸው በደስታ ተሞልቶ በፈገግታ ዓይን ዓይኔን ይመለከቱኛል። በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ትንንሽ ልጆች ከይሖዋ እንደተሰጡኝ በረከቶች አድርጌ እመለከታቸዋለሁ። በልጅነት ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሐሲን የምትባል እህት አስተርጓሚዬ ሆነችልኝ። ለማለት የፈለግኩትን ነገር ማንም ሰው በማይረዳልኝ ጊዜ እንኳ እሷ ትረዳልኝ ነበር። ደግሞም ብዙውን ጊዜ በጉባኤ ካሉት ወዳጆቼ ጋር ለመነጋገር ጥረት ሳደርግ ምን ለማለት እንደፈለግኩ ታስረዳልኛለች።

እኔና ባለቤቴ የምንሰበሰብበት ጉባኤ ሊከፈል ተቃርቦ ነበር። ይህ ማለት ደግሞ አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼ የሚኖሩት በአዲሱ ጉባኤ ክልል ውስጥ ስለሚሆን እነሱን ለሌሎች አስጠኚዎች መስጠት ነበረብኝ። አንዲት እህት ከጥናቶቿ መካከል አንዷን እንዳስጠና አበረታታችኝ። እኔ ፈርቼ ስለነበር ‘ገና እዚህ ደረጃ ላይ አልደረስኩም’ አልኳት፤ እሷ ግን ጥናቱን እንድመራ አደፋፈረችኝ። በይሖዋ እርዳታ ጥናቱን መምራት እንደምችል አረጋገጠችልኝ። ርኅራኄና ደግነት በተሞላበት ዓይን እያየችኝ በቅርቡ እንደምፈልገው አድርጌ ማስተማር እንደምችል በቀላል አገላለጽ ነገረችኝ። እነዚህ ቃላት በጣም አበረታቱኝ።

ከዚያ ወዲህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዋ ጥሩ ዕድገት አደረገች። አንድ ቀን ወጣ ብዬ ሳለሁ ስትጠራኝ ሰማኋት። እሷና ባለቤቷ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ለማድረግ እየሄዱ ነበር። ባለቤቷም ማጥናት የጀመረ ሲሆን ጥምቀትን ጨምሮ ያወጧቸው መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረጉ ነው። አንድን ሰው ወደ ራሱ የሚስበው ይሖዋ እንጂ እኛ እንዳልሆንን የታወቀ ቢሆንም በእነሱ ላይ ያየሁት ለውጥ ደስታ አምጥቶልኛል።

በዚህ አዲስ ክልል ስናገለግል ብዙ ነገር ተምረናል። በትውልድ አገራችን ያሉትን ወዳጆቻችንንና ቤተሰቦቻችንን የምንናፍቃቸው ቢሆንም በመንፈስ አብረውን እንዳሉ ሆኖ ይሰማናል። ብዙ ጊዜ እዚህ ላሉት ወንድሞችና እህቶች ስለ እነሱ ስለምንነግራቸው አሁን አሁን ደህንነታቸውን ይጠይቁናል። “ቤተሰቦቻችን” አንድ ላይ የሚገናኙበትንና የሚተዋወቁበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠባበቃለን።

አሁንም ድረስ ሰዎች ሲናገሩ ያው “ሙዚቃ” ይሰማኛል። ይሁን እንጂ አሁን የቃላቱ ትርጉም ይገባኛል። ቋንቋውን አጥርቼ በመናገር እኔም ከሙዚቃው ጋር የሚጣጣም ግሩም ድምፅ የማሰማበትን ቀን በናፍቆት እጠባበቃለሁ። ኢየሱስ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት” ብሏል። (ማቴዎስ 6:34) ስለዚህ በአንድ ጊዜ አንድ “የሙዚቃ ኖታ” ወይም አንድ ቃል እየያዝን መማራችንን እንቀጥላለን። ለጊዜው ግን በማዳጋስካር ከሚገኙት ታጋሽና አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ተባብሬ ለመሥራት እንድችል ጆሮዎቼን፣ አእምሮዬንና ልቤን ከሙዚቃው ስልት ጋር መቃኘቴን እቀጥላለሁ።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሐሲን ጋር ስሰብክ