በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጄ ለመጠመቅ ደርሷል?

ልጄ ለመጠመቅ ደርሷል?

ልጄ ለመጠመቅ ደርሷል?

“ልጄ የይሖዋ አገልጋይ በመሆኗ በጣም ደስተኛ ነኝ። እሷም ብትሆን እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በማድረጓ ተደስታለች” በማለት በፊሊፒንስ የሚኖር ካርሎስ * የተባለ አንድ ክርስቲያን አባት ተናግሯል። በግሪክ የሚኖር አንድ አባት ደግሞ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እኔና ባለቤቴ፣ ሦስቱም ልጆቻችን በጉርምስና ዕድሜ ላይ በነበሩበት ወቅት ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናቸው ደስተኞች ነን። በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ እድገት እያደረጉ ሲሆን ይሖዋን በደስታ ያገለግላሉ።”

ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ሲጠመቁ ልባቸው በሐሴት የሚሞላ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ስጋት ያድርባቸዋል። አንዲት እናት “በአንድ በኩል በጣም ብደሰትም በሌላ በኩል ግን ጭንቀት አድሮብኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። ይህች እናት እንዲህ ያለ የተደበላለቀ ስሜት የተሰማት ለምን ነበር? “ልጄ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ እንደሚሆን ስለተገነዘብኩ ነው” ብላለች።

ሁሉም ልጆች የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው አምላክን የማገልገል ግብ ሊኖራቸው ይገባል። ይሁንና አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው ወላጆች እንደሚከተለው ብለው ያስቡ ይሆናል፦ ‘ልጄ ጥሩ እድገት እያደረገ እንደሆነ ይሰማኛል፤ ሆኖም ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽም የሚደርስበትን ግፊት በመቋቋም በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ ለመኖር የሚያስችል ጥንካሬ አለው?’ ሌሎች ወላጆች ደግሞ ‘ልጄ ከፍቅረ ንዋይ ጋር የተያያዘ ፈተና ሲያጋጥመው አምላክን በደስታና በቅንዓት ማገልገሉን ይቀጥል ይሆን?’ ብለው ራሳቸውን ይጠይቁ ይሆናል። ታዲያ ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ለመጠመቅ ዝግጁ መሆናቸውን ለማወቅ የሚረዷችሁ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ናቸው?

ደቀ መዝሙር መሆን​ዋነኛው ብቃት

የአምላክ ቃል አንድ ሰው በስንት ዓመቱ መጠመቅ እንዳለበት አይገልጽም፤ ከዚህ ይልቅ ይህን እርምጃ ለመውሰድ ብቁ የሚሆኑ ሰዎች ሊኖራቸው ስለሚገባው መንፈሳዊ አቋም ይናገራል። ኢየሱስ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ተከታዮቹን አዝዟቸዋል። (ማቴ. 28:19) በመሆኑም ለመጠመቅ ብቁ የሚሆኑት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ ሰዎች ናቸው።

ደቀ መዝሙር የሚባለው ማን ነው? ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ቃል በዋነኝነት የሚሠራበት በክርስቶስ ትምህርቶች በማመን ብቻ ሳይወሰኑ ትምህርቶቹን በጥብቅ የሚከተሉ ሰዎችን በሙሉ ለማመልከት ነው።” ታዲያ ልጆች እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆን ይችላሉ? ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በላቲን አሜሪካ ሚስዮናዊ ሆና ያገለገለች አንዲት እህት ስለ ራሷና ስለ ሁለት እህቶቿ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ልጆች ብንሆንም ይሖዋን ማገልገልና በገነት መኖር እንደምንፈልግ ተገንዝበን ነበር። ራሳችንን መወሰናችን ከወጣትነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ጠንካሮች እንድንሆን ረድቶናል። በልጅነታችን ራሳችንን ለአምላክ በመወሰናችን አንቆጭም።”

ልጃችሁ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆኑን እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ ከአድራጎቱ ይታወቃል” ይላል። (ምሳሌ 20:11) ልጃችሁ ከአንድ ደቀ መዝሙር የሚጠበቀውን በማድረግ ‘እድገቱን በግልጽ ማሳየት’ የሚችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።​—1 ጢሞ. 4:15

ደቀ መዝሙር መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ

ልጃችሁ ይታዘዛችኋል? (ቆላ. 3:20) በቤት ውስጥ የምትሰጡትን ሥራ ያከናውናል? ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ በነበረበት ጊዜ ወላጆቹን ‘እንደ ወትሮው ይታዘዛቸው እንደነበር’ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ሉቃስ 2:51) እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ወላጆቹን ፍጹም በሆነ መንገድ መታዘዝ የሚችል ልጅ የለም። ያም ቢሆን እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስን “ፈለግ በጥብቅ [እንዲከተሉ]” ታዝዘዋል። ስለዚህ የመጠመቅ ፍላጎት ያላቸው ልጆች ወላጆቻቸውን የሚታዘዙ መሆን አለባቸው።​—1 ጴጥ. 2:21

እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስቡባቸው፦ ልጃችሁ በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ በማድረግ ‘ከሁሉ አስቀድሞ መንግሥቱን እንደሚፈልግ’ ያሳያል? (ማቴ. 6:33) በራሱ ተነሳስቶ ምሥራቹን ለሰዎች ይናገራል? ወይስ አገልግሎት ለመውጣትና ሰዎችን ለማነጋገር የእናንተ ጉትጎታ ያስፈልገዋል? ያልተጠመቀ አስፋፊ መሆኑ የሚያስከትልበትን ኃላፊነት በሚገባ ተገንዝቧል? በአገልግሎት ላይ ያገኛቸውን ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ተመልሶ ለማነጋገር ይጓጓል? አብረውት ለሚማሩት ልጆችና ለአስተማሪዎቹ የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ይነግራቸዋል?

በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል? (መዝ. 122:1) በመጠበቂያ ግንብ ጥናት እና በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ሐሳብ መስጠት ያስደስተዋል? በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተመዝግቧል? እንዲሁም በዚህ ትምህርት ቤት የሚካፈለው ደስ እያለው ነው?​—ዕብ. 10:24, 25

ልጃችሁ በትምህርት ቤትም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ከመጥፎ ጓደኞች በመራቅ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናውን ጠብቆ ለመኖር ጥረት ያደርጋል? (ምሳሌ 13:20) በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና በቪዲዮ ጨዋታዎች ረገድ ምርጫው ምን ይመስላል? የኢንተርኔት አጠቃቀሙስ ምን ያሳያል? ንግግሩና ድርጊቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር እንደሚፈልግ ያሳያል?

ልጃችሁ መጽሐፍ ቅዱስን ምን ያህል ያውቀዋል? በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ወቅት ያገኘውን ትምህርት በራሱ አባባል መግለጽ ይችላል? መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ማብራራት ይችላል? (ምሳሌ 2:6-9) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ታማኝና ልባም ባሪያ የሚያወጣቸውን ጽሑፎች ማጥናት ያስደስተዋል? (ማቴ. 24:45) የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችንና ጥቅሶችን በተመለከተ ጥያቄ ይጠይቃል?

እነዚህ ጥያቄዎች የልጃችሁን መንፈሳዊ እድገት ለመለካት ያስችሏችኋል። በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ካሰባችሁባቸው በኋላ ልጃችሁ ከመጠመቁ በፊት አንዳንድ ነገሮችን ማሻሻል እንዳለበት ሊሰማችሁ ይችላል። ይሁንና አኗኗሩ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆኑን የሚያረጋግጥ ከሆነና ሕይወቱን ለይሖዋ ከወሰነ እንዲጠመቅ ልትፈቅዱለት እንደምትችሉ ይሰማችሁ ይሆናል።

ልጆች ይሖዋን ማወደስ ይችላሉ

በርካታ የአምላክ አገልጋዮች ገና ትንንሽ ልጆች እያሉም ሆነ በጉርምስና ዕድሜ ላይ በነበሩበት ወቅት ለአምላክ ታማኝ መሆናቸውን አሳይተዋል። ዮሴፍን፣ ሳሙኤልን፣ ኢዮስያስንና ኢየሱስን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። (ዘፍ. 37:2፤ 39:1-3፤ 1 ሳሙ. 1:24-28፤ 2:18-20፤ 2 ዜና 34:1-3፤ ሉቃስ 2:42-49) ትንቢት ይናገሩ የነበሩት የፊልጶስ አራት ሴቶች ልጆችም ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ጥሩ ሥልጠና አግኝተው መሆን አለበት።​—ሥራ 21:8, 9

በግሪክ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሏል፦ “የተጠመቅሁት በ12 ዓመቴ ነበር። ባደረግሁት ውሳኔ ፈጽሞ ተቆጭቼ አላውቅም። ከተጠመቅሁ 24 ዓመታት ያለፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 23ቱን ያሳለፍኩት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ነው። ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር በወጣትነት ጊዜ ያጋጠሙኝን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሙሉ ለመወጣት ረድቶኛል። የ12 ዓመት ልጅ እያለሁ አሁን ያለኝን ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አልነበረኝም። ያም ቢሆን ይሖዋን እንደምወድና እሱን ለዘላለም ማገልገል እንደምፈልግ አውቅ ነበር። ይሖዋም እሱን ማገልገሌን እንድቀጥል ስለረዳኝ ደስተኛ ነኝ።”

አንድ ሰው የክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዝሙር መሆኑን እስካሳየ ድረስ ልጅም ሆነ አዋቂ መጠመቅ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፤ በአፉ ደግሞ እምነቱን በይፋ ተናግሮ ይድናል” ሲል ጽፏል። (ሮም 10:10) የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ልጅ፣ ራሱን ወስኖ በመጠመቅ ወሳኝ የሆነውን ይህን እርምጃ መውሰዱ በእሱም ሆነ በወላጆቹ ሕይወት ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ክንውን ነው። እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ ይህ እርምጃ የሚያስገኘውን ታላቅ ደስታ እንዳታጣጥሙ ምንም ነገር እንዲያግዳችሁ አትፍቀዱ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለጥምቀት ተገቢውን አመለካከት መያዝ

አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆቻቸው መጠመቃቸው ልክ የመንጃ ፈቃድ እንደማውጣት ጠቃሚ እርምጃ ቢሆንም የሚያስከትለው ችግር ሊኖር እንደሚችል ይሰማቸዋል። ይሁንና አንድ ሰው መጠመቁና ቅዱስ አገልግሎት ማቅረቡ በሕይወቱ ስኬታማ እንዳይሆን ይገድበዋል? መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚህ አይልም። ምሳሌ 10:22 “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” ይላል። ጳውሎስም ለወጣቱ ጢሞቴዎስ ሲጽፍ “ባለው ነገር ለሚረካ ሰው ለአምላክ ማደር ትልቅ ትርፍ ያስገኛል” ብሏል።​—1 ጢሞ. 6:6

ይሖዋን ማገልገል ቀላል ላይሆን እንደሚችል አይካድም። ኤርምያስ የአምላክ ነቢይ ሆኖ ባገለገለበት ወቅት በርካታ ችግሮች አጋጥመውታል። ያም ሆኖ ለእውነተኛው አምላክ የሚያቀርበውን አገልግሎት በተመለከተ ሲጽፍ “የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በስምህ ተጠርቻለሁና፣ ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነልኝ” ብሏል። (ኤር. 15:16) ኤርምያስ ደስታ ያገኘው አምላክን በማገልገሉ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ችግሮችን የሚያመጣው የሰይጣን ዓለም ነው። ወላጆች፣ ልጆቻቸው ይህንን እውነታ ለይተው እንዲያውቁ ሊረዷቸው ይገባል።​—ኤር. 1:19

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ልጄ ለመጠመቅ ትንሽ ቢቆይ ይሻል ይሆን?

አንዳንድ ጊዜ ልጆች ለጥምቀት ብቁ ቢሆኑም እንኳ ወላጆቻቸው ትንሽ ቢቆዩ እንደሚሻል ይወስኑ ይሆናል። ወላጆች እንዲህ የሚያደርጉበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?

ልጄ ከተጠመቀ፣ ከጊዜ በኋላ ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ እንዳይወገድ እፈራለሁ። ይሁንና አንድ ልጅ ስላልተጠመቀ ብቻ ለሚፈጽመው ድርጊት በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንደማይሆን ማሰብ ምክንያታዊ ነው? ሰለሞን ለወጣቶች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷቸዋል፦ “አንተ ወጣት . . . [ስለምታደርጋቸው] ነገሮች ሁሉ፣ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንደሚያመጣህ ዕወቅ።” (መክ. 11:9) ጳውሎስ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን” የሚለውን ምክር የሰጠው በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ነው።​—ሮም 14:12

የተጠመቁም ሆኑ ያልተጠመቁ የአምላክ አገልጋዮች በእሱ ዘንድ ተጠያቂ ናቸው። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ‘ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባቸው ባለመፍቀድ’ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው አትዘንጉ። (1 ቆሮ. 10:13) የአምላክ አገልጋዮች ‘የማስተዋል ስሜቶቻቸውን የሚጠብቁና’ በፈተናዎች ላለመሸነፍ ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ አምላክ እንደሚደግፋቸው መተማመን ይችላሉ። (1 ጴጥ. 5:6-9) አንዲት ክርስቲያን እናት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “የተጠመቁ ልጆች በዓለም ላይ ካሉት መጥፎ ነገሮች እንዲርቁ የሚያነሳሳቸው ተጨማሪ ምክንያት አላቸው። ልጄ የተጠመቀው በ15 ዓመቱ ሲሆን ጥምቀት ጥበቃ እንደሆነለት ይሰማዋል። ልጄ ‘ከይሖዋ ሕግ ጋር የሚጋጭ ድርጊት ለመፈጸም አናስብም’ በማለት ይናገራል። ጥምቀት፣ ጽድቅን የማድረግ ፍላጎት እንዲኖረን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።”

ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲታዘዙ በንግግራችሁና በድርጊታችሁ ካሠለጠናችኋቸው ከተጠመቁም በኋላ ይሖዋን መታዘዛቸውን እንደሚቀጥሉ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ። ምሳሌ 20:7 እንዲህ ይላል፦ “ጻድቅ ነቀፋ የሌለበት ሕይወት ይመራል፤ ከእርሱም በኋላ የሚከተሉት ልጆቹ ቡሩካን ናቸው።”

ልጄ በመጀመሪያ አንዳንድ ግቦች ላይ እንዲደርስ እፈልጋለሁ። እውነት ነው፣ ልጆች ወደፊት ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ ሥራ ለመያዝ የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠና ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይሁንና ልጆች በእውነተኛው አምልኮ ላይ ከማተኮር ይልቅ በትምህርትና ገንዘብን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት እንዲመሩ ማበረታታት አደጋ አለው። ኢየሱስ፣ ፍሬ የማያፈራውን “ዘር” (ወይም የመንግሥቱን ቃል) በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “በእሾህ መካከል የተዘራው ደግሞ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ ይሁንና የዚህ ሥርዓት ጭንቀት እንዲሁም ሀብት ያለው የማታለል ኃይል ቃሉን ያንቀዋል፤ የማያፈራም ይሆናል።” (ማቴ. 13:22) ወላጆች፣ ከመንፈሳዊነታቸው ይልቅ ለዓለማዊ ግቦች ትልቅ ቦታ እንዲሰጡ ልጆቻቸውን የሚያበረታቷቸው ከሆነ ልጆቹ አምላክን ለማገልገል ያላቸው ፍላጎት ቀስ በቀስ ሊጠፋ ይችላል።

ለመጠመቅ ብቁ ቢሆኑም ወላጆቻቸው የሚከለክሏቸውን ልጆች በተመለከተ አንድ ተሞክሮ ያካበተ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ልጅ እንዳይጠመቅ መከልከል መንፈሳዊ እድገቱን ሊገታበትና ተስፋ እንዲቆርጥ ሊያደርገው ይችላል።” አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አንድ ወጣት በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ ስለ ራሱ ጥሩ ስሜት እንዳይኖረው ወይም መንፈሳዊ አቋሙ ጥሩ እንዳልሆነ እንዲያስብ ሊያደርገው ይችላል። በራስ የመተማመን ስሜቱን ለማጎልበት ወደ ዓለም ዘወር ሊል ይችላል።”

[ሥዕል]

ልጃችን መጀመሪያ ዩኒቨርሲቲ ብትገባ ይሻል ይሆን?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ልጅ ደቀ መዝሙር መሆኑን ማሳየት ይችላል

[በገጽ 3 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ለስብሰባዎች መዘጋጀትና በስብሰባው ወቅት ተሳትፎ ማድረግ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆችን መታዘዝ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአገልግሎት መካፈል

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በግል መጸለይ