በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁሉም ሰው የሚያስፈልገው ምሥራች

ሁሉም ሰው የሚያስፈልገው ምሥራች

ሁሉም ሰው የሚያስፈልገው ምሥራች

“ምሥራቹ . . . መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል ነው።”​—ሮም 1:16

1, 2. ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ የምትሰብከው ለምንድን ነው? በስብከትህ ላይ ጎላ አድርገህ የምትገልጸው የትኞቹን የምሥራቹ ገጽታዎች ነው?

‘ምሥራቹን⁠ በየዕለቱ መስበክ ያስደስተኛል።’ ብዙ ጊዜ እንዲህ ብለህ ታስብ ወይም ትናገር ይሆናል። እንደ አንድ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር መጠን ‘ይህን የመንግሥት ምሥራች’ መስበክ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ትገነዘባለህ። እንዲያውም ኢየሱስ ይህን ሥራ እንደምናከናውን የተናገረውን ትንቢት በቃልህ ታውቀው ይሆናል።​—ማቴ. 24:14

2 ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ ስትሰብክ ኢየሱስ የጀመረው ሥራ እንዲቀጥል እያደረግህ ነው። (ሉቃስ 4:43ን አንብብ።) ምሥራቹን ስትሰብክ ጎላ አድርገህ ከምትገልጻቸው ሐሳቦች አንዱ አምላክ በቅርቡ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ነው። ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት አምላክ የሐሰት ሃይማኖትንና በምድር ላይ ያለውን ክፋት በሙሉ ያስወግዳል። (ማቴ. 24:21) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ መንግሥት ምድርን እንደገና ወደ ገነትነት በመለወጥ ሰላምና ደስታ እንዲሰፍን እንደሚያደርግ ጎላ አድርገህ ትገልጽ ይሆናል። “የመንግሥቱ ምሥራች” ለአብርሃም “ሕዝቦች ሁሉ በአንተ አማካኝነት ይባረካሉ” በማለት አምላክ አስቀድሞ ያስታወቀው ‘ምሥራች’ ክፍል ነው።​—ገላ. 3:8

3. ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም መጽሐፍ ላይ ምሥራቹን ጎላ አድርጎ ገልጾታል የምንለው ለምንድን ነው?

3 ይሁንና ሰዎች ለሚያስፈልጋቸው የምሥራቹ ቁልፍ ገጽታ እምብዛም ትኩረት አንሰጥ ይሆን? ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “መንግሥት” የሚለውን ቃል የጠቀሰው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን “ምሥራች” የሚለውን ቃል ግን ከ10 ጊዜ በላይ ተጠቅሞበታል። (ሮም 14:17ን አንብብ።) ጳውሎስ በሮም መጽሐፍ ላይ ደጋግሞ የገለጸው የትኛውን የምሥራቹን ገጽታ ነው? ይህኛው የምሥራቹ ገጽታ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? “የአምላክን ምሥራች” በክልላችን ውስጥ ለምናገኛቸው ሰዎች ስንሰብክ ይህንን የምሥራቹን ገጽታ በአእምሯችን መያዝ የሚኖርብን ለምንድን ነው?​—ማር. 1:14፤ ሮም 15:16፤ 1 ተሰ. 2:2

የሮም ክርስቲያኖች የሚያስፈልጋቸው ነገር

4. ጳውሎስ በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ በታሰረበት ወቅት ስለ ምን ነገር ሰብኳል?

4 ጳውሎስ በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ በታሰረበት ወቅት ስለ የትኞቹ ጉዳዮች እንደሰበከ ማወቃችን ጠቃሚ ነው። በርከት ያሉ አይሁዳውያን ሊጠይቁት በመጡበት ወቅት (1) ‘ስለ አምላክ መንግሥት እና (2) ስለ ኢየሱስ የተሟላ ምሥክርነት በመስጠትና አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ ጉዳዩን አብራራላቸው።’ ታዲያ ሕዝቡ ምን ምላሽ ሰጡ? “አንዳንዶቹ የተናገረውን ነገር ሲያምኑ ሌሎቹ ግን አላመኑም።” ከዚያ በኋላም ጳውሎስ “ወደ እሱ የሚመጡትንም ሁሉ በደግነት ይቀበላቸው ነበር።” እንዲሁም (1) “ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክላቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ” (2) “ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምራቸው ነበር።” (ሥራ 28:17, 23-31) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ ለአምላክ መንግሥት ትኩረት ሰጥቷል። ይሁንና ሌላስ ምን ነጥብ አጉልቷል? በአምላክ መንግሥት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለውን ነገር ይኸውም ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ጎላ አድርጎ ገልጿል።

5. በሮም መጽሐፍ ላይ ጳውሎስ በጣም አስፈላጊ ስለሆነው ስለ የትኛው ነገር ጠቅሷል?

5 ሁሉም ሰው ስለ ኢየሱስ ማወቅ እንዲሁም በእሱ ላይ እምነት ማሳደር ያስፈልገዋል። ጳውሎስ በሮም መጽሐፍ ላይ ስለዚህ አስፈላጊ ጉዳይ ጽፏል። በደብዳቤው መጀመሪያ ላይ ‘ስለ ልጁ የሚገልጸውን ምሥራች በማወጅ በሙሉ ልቡ ቅዱስ አገልግሎት ስለሚያቀርብለት አምላክ’ ጽፎ ነበር። አክሎም “እኔ በምሥራቹ አላፍርም፤ እንዲያውም ምሥራቹ ለሚያምን ሁሉ . . . መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል ነው” ብሏል። ቀጥሎም ‘እሱ በሚያውጀው ምሥራች መሠረት አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ስለሚፈርድበት ቀን’ ጽፏል። በተጨማሪም “ከኢየሩሳሌም አንስቶ ዙሪያውን እስከ እልዋሪቆን ድረስ ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ ሰብኬያለሁ” በማለት ተናግሯል። * (ሮም 1:9, 16፤ 2:16፤ 15:19) ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች ሲጽፍ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ትኩረት ያደረገው ለምን ይመስልሃል?

6, 7. ስለ ሮም ጉባኤ አመሠራረትና ስለ አባላቱ ምን ማለት ይቻላል?

6 የሮም ጉባኤ የተቋቋመው እንዴት እንደሆነ አናውቅም። በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት የነበሩ አይሁዳውያን ወይም ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ክርስቲያን ሆነው ወደ ሮም ተመልሰው ይሆን? (ሥራ 2:10) ወይስ ክርስቲያን የሆኑ ነጋዴዎችና መንገደኞች እውነትን በሮም አሰራጭተው ይሆን? ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ጳውሎስ በ56 ዓ.ም. ለሮም ክርስቲያኖች ደብዳቤውን ሲጽፍ ጉባኤው ከተመሠረተ ረዘም ያለ ጊዜ አልፎ ነበር። (ሮም 1:8) የሮም ጉባኤ አባላት ምን ዓይነት ሰዎች ነበሩ?

7 አንዳንዶቹ አይሁዳውያን ነበሩ። ጳውሎስ፣ ሰላምታ የላከላቸውን አንድሮኒኮስንና ዩኒያስን “ዘመዶቼ” ብሎ ጠርቷቸዋል፤ እነዚህ ሰዎች አይሁዳውያን ዘመዶቹ ሳይሆኑ አይቀሩም። በተጨማሪም በሮም ይኖር የነበረው ድንኳን ሰፊው አቂላና ሚስቱ ጵርስቅላ አይሁዳውያን ነበሩ። (ሮም 4:1፤ 9:3, 4፤ 16:3, 7፤ ሥራ 18:2) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ሰላምታ የላከላቸው አብዛኞቹ ወንድሞችና እህቶች አሕዛብ ሳይሆኑ አይቀሩም። አንዳንዶቹ “ከቄሳር ቤተሰብ” የነበሩ ሲሆን ይህ አገላለጽ የቄሳር ባሮችና አነስተኛ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ የተሾሙ ባለሥልጣናት እንደሆኑ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።​—ፊልጵ. 4:22፤ ሮም 1:6፤ 11:13

8. በሮም የነበሩት ክርስቲያኖች ምን አስቸጋሪ ሁኔታ ተጋርጦባቸው ነበር?

8 የኋላ ታሪካቸው ምንም ይሁን ምን በሮም የነበሩት ክርስቲያኖች በሙሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ተጋርጦባቸዋል፤ እኛም ያለንበት ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ጳውሎስ ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል።” (ሮም 3:23) ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈላቸው ሰዎች በሙሉ ኃጢአተኞች መሆናቸውን መገንዘብና አምላክ ይህንን ሁኔታ ለማስተካከል ባደረገው ዝግጅት ላይ እምነት ማሳደር እንደነበረባቸው ግልጽ ነው።

ኃጢአተኛ መሆናቸውን መገንዘብ

9. ጳውሎስ ምሥራቹ ምን እንደሚያስገኝ ተናግሯል?

9 ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ መጀመሪያ አካባቢ፣ በደብዳቤው ውስጥ ደጋግሞ የጠቀሰው ምሥራች ስለሚያመጣው አስደናቂ ነገር ገልጿል፤ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እኔ በምሥራቹ አላፍርም፤ እንዲያውም ምሥራቹ ለሚያምን ሁሉ ይኸውም በመጀመሪያ ለአይሁዳዊ ከዚያም ለግሪካዊ መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል ነው።” አዎን፣ መዳን ማግኘት ይቻላል። ይሁንና በ⁠ዕንባቆም 2:4 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ እውነት እንደሚጠቁመው ለመዳን እምነት አስፈላጊ ነው፤ ጥቅሱ “ጻድቅ . . . በእምነት ይኖራል” ይላል። (ሮም 1:16, 17፤ ገላ. 3:11፤ ዕብ. 10:38) ይሁን እንጂ ወደ መዳን የሚመራው ምሥራች “ሁሉም ኃጢአት [ከመሥራታቸው]” ጋር ምን ግንኙነት አለው?

10, 11. በ⁠ሮም 3:23 ላይ የተጠቀሰው ነጥብ ለአንዳንዶች እንግዳ ባይሆንባቸውም ለሌሎች ግን አዲስ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው?

10 አንድ ሰው ለመዳን የሚያስፈልገውን እምነት ከማዳበሩ በፊት ኃጢአተኛ መሆኑን አምኖ መቀበል ያስፈልገዋል። ከልጅነታቸው ጀምሮ በአምላክ መኖር የሚያምኑና በተወሰነ መጠን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቁ ሰዎች ኃጢአተኛ መሆናቸውን ማመን ብዙም ላይከብዳቸው ይችላል። (መክብብ 7:20ን አንብብ።) እነዚህ ሰዎች ኃጢአተኛ መሆናቸውን አመኑም አላመኑ ቢያንስ ጳውሎስ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ይገባቸዋል። (ሮም 3:23) ይሁንና አገልግሎታችንን ስናከናውን ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ መረዳት የሚከብዳቸው ብዙ ሰዎች እናገኝ ይሆናል።

11 በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች፣ የሰው ልጆች ሲወለዱ ጀምሮ ኃጢአተኞች እንደሆኑና ከአዳም ኃጢአትን እንደወረሱ አያውቁም። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ባሉ አገሮች ውስጥ ያደገ አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ስህተት እንደሚሠራና ጥሩ ያልሆኑ ባሕርያት እንዳሉት ማስተዋሉ አይቀርም፤ እንዲሁም አንዳንድ መጥፎ ድርጊቶችን ፈጽሞ ይሆናል። በተጨማሪም ሌሎች ሰዎችም እንደ እሱ ዓይነት ችግር እንዳለባቸው ሊያስተውል ይችላል። ያም ሆኖ ግን ከአዳም የወረሰው ኃጢአት እንዳለበት ስለማያውቅ እሱም ሆነ ሌሎች ሰዎች እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ለምን እንደሆነ መረዳት ይከብደዋል። እንዲያውም በአንዳንድ ቋንቋዎች አንድ ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ ከተናገርክ ይህን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ ግለሰቡ ወንጀለኛ እንደሆነ ወይም ሕግ እንደጣሰ እየገለጽክ እንደሆነ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። በእንደዚህ ዓይነት ማኅበረሰብ ውስጥ ያደገ ሰው፣ ጳውሎስ የገለጸው ዓይነት ኃጢአት እንዳለበት በቀላሉ ላይመጣለት ይችላል።

12. ብዙዎች፣ ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ የማያምኑት ለምንድን ነው?

12 ክርስቲያን ነን በሚሉ አንዳንድ አገሮች እንኳ ብዙ ሰዎች ኃጢአተኛ እንደሆኑ አይገነዘቡም። ለምን? አልፎ አልፎ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ቢሆንም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ስለ አዳምና ስለ ሔዋን የሚናገረውን ዘገባ ተረት ወይም አፈ ታሪክ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ሌሎች ደግሞ ያደጉት አምላክ የለሽ በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። እነዚህ ሰዎች አምላክ መኖሩን ስለሚጠራጠሩ ከሁሉ በላይ የሆነ አንድ አካል የሰው ልጆች የሚመሩባቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን እንዳወጣና ከእነዚህ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ አለመኖር እንደ ኃጢአት እንደሚቆጠር መቀበል ይከብዳቸዋል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በአንደኛው መቶ ዘመን ከነበሩትና ጳውሎስ “በዓለም ውስጥ ያለ ተስፋና ያለ አምላክ” እንደሆኑ ከገለጻቸው ሰዎች ጋር ይመሳሰላሉ ማለት ይቻላል።​—ኤፌ. 2:12

13, 14. (ሀ) በአምላክ መኖር የማያምኑና ኃጢአተኞች እንደሆኑ የማይሰማቸው ሰዎች የሚያመካኙበት ነገር የላቸውም የምንልበት አንደኛው ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) ብዙዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት መያዛቸው ወደ ምን መርቷቸዋል?

13 ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ በዚያን ጊዜም ሆነ ዛሬ አንድ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን ላለመቀበል ያደገበት ማኅበረሰብ ሰበብ ሊሆን እንደማይችል የሚጠቁሙ ሁለት ምክንያቶች አቅርቧል። የመጀመሪያው ምክንያት ፈጣሪ መኖሩን ፍጥረት ራሱ የሚመሠክር መሆኑ ነው። (ሮም 1:19, 20ን አንብብ።) ይህም ጳውሎስ በሮም ሆኖ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ካቀረበው ሐሳብ ጋር ይስማማል፤ ሐዋርያው “እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው” ብሎ ነበር። (ዕብ. 3:4) ሐዋርያው ያቀረበው የመከራከሪያ ሐሳብ መላውን ጽንፈ ዓለም የሠራ ወይም ወደ ሕልውና ያመጣ ፈጣሪ እንዳለ ይጠቁማል።

14 በመሆኑም ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በላከው ደብዳቤ ላይ የጥንቶቹን እስራኤላውያን ጨምሮ ሕይወት አልባ ለሆኑ ምስሎች አምልኮ የሚያቀርቡ ሁሉ “የሚያመካኙበት ነገር” እንደሌላቸው ለመጻፍ የሚያበቃ ጠንካራ መሠረት ነበረው። ሰውነታቸውን ተፈጥሯዊ ባልሆነ መንገድ በመጠቀም የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ወንዶችና ሴቶችን በተመለከተም ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል። (ሮም 1:22-27) በእርግጥም ጳውሎስ “አይሁዳውያንም ሆኑ ግሪካውያን ሁሉም የኃጢአት ተገዥዎች እንደሆኑ” መናገሩ ተገቢ ነው።​—ሮም 3:9

‘ይመሠክርባቸዋል’

15. ሁሉም ሰው ምን ዓይነት ስጦታ ተሰጥቶታል? ይህ ስጦታስ ምን ያከናውናል?

15 ሰዎች ኃጢአተኞች መሆናቸውንና ከዚህ ሁኔታ መላቀቅ እንደሚያሻቸው እንዲገነዘቡ የሚያደርጋቸውን ሌላኛውን ምክንያት የሮም መጽሐፍ ይነግረናል። ጳውሎስ፣ አምላክ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰጣቸውን ሕግጋት አስመልክቶ “ሕግ እያላቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ . . . በሕግ ይፈረድባቸዋል” ሲል ጽፏል። (ሮም 2:12) በመቀጠልም ይህን መለኮታዊ ሕግ የማያውቁ ሕዝቦች ወይም ጎሣዎች አብዛኛውን ጊዜ “በተፈጥሮ በሕጉ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሲያደርጉ” እንደሚታዩ ተናግሯል። በእነዚህ ሕዝቦች ዘንድ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚደረግ የፆታ ግንኙነት፣ ነፍስ ማጥፋትና ስርቆት በአብዛኛው የተከለከለ ድርጊት የሆነው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ይህ የሆነው ሕሊና ስላላቸው መሆኑን ገልጿል።​—ሮም 2:14, 15ን አንብብ።

16. አንድ ሰው ሕሊና ስላለው ብቻ ኃጢአት ከመሥራት ይቆጠባል ማለት የማይቻለው ለምንድን ነው?

16 ያም ሆኖ አንድ ሰው በውስጡ የሚመሠክር ሕሊና ስላለው ብቻ ሕሊናው የሚሰጠውን መመሪያ ይከተላል ማለት እንዳልሆነ አስተውለህ ይሆናል። የጥንቶቹ እስራኤላውያን ታሪክ ይህን ያሳያል። አምላክ ለእስራኤላውያን ሕሊና የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ስርቆትንና ምንዝርን የሚከለክሉ ቀጥተኛ ሕግጋት ሰጥቷቸው ነበር፤ ሆኖም ሕዝቡ በተደጋጋሚ ጊዜያት ከሕሊናቸውም ሆነ ከይሖዋ ሕግጋት ጋር የሚጋጩ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር። (ሮም 2:21-23) በዚህም የተነሳ ድርብ ጥፋት ሠርተዋል፤ ኃጢአተኞች እንደሆኑና ከአምላክ ፈቃድም ሆነ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው መኖር እንደተሳናቸው ግልጽ ነበር። ይህም ከፈጣሪያቸው ጋር ያላቸው ዝምድና እንዲሻክር አድርጓል።​—ዘሌ. 19:11፤ 20:10፤ ሮም 3:20

17. በሮም መጽሐፍ ውስጥ ምን የሚያጽናና ሐሳብ እናገኛለን?

17 ከሮም መጽሐፍ ላይ እስከ አሁን ከመረመርናቸው ነጥቦች አንጻር እኛን ጨምሮ የሰው ልጆች በአጠቃላይ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ዘንድ በመልካም እንደማይታዩ እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ኃጢአተኞች መሆናችንን በመግለጽ ብቻ ከመወሰን ይልቅ በ⁠መዝሙር 32:1, 2 ላይ የሚገኘውን ዳዊት የተናገረውን ሐሳብ በመጥቀስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የዓመፅ ሥራቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኃጢአታቸውም የተሸፈነላቸው ደስተኞች ናቸው፤ ይሖዋ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ደስተኛ ነው።” (ሮም 4:7, 8) አዎን፣ አምላክ ኃጢአትን ይቅር ለማለት የሚያስችል ሕጋዊ ዝግጅት አድርጓል።

በኢየሱስ ላይ ያተኮረ ምሥራች

18, 19. (ሀ) ጳውሎስ በሮም መጽሐፍ ላይ ያተኮረው በየትኛው የምሥራቹ ገጽታ ላይ ነው? (ለ) የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን በረከቶች ለማግኘት የትኞቹን ነገሮች መገንዘብ ይኖርብናል?

18 “ይህማ ታላቅ የምሥራች ነው!” ትል ይሆናል። በእርግጥም የምሥራች ነው፤ ይህ ደግሞ ጳውሎስ በሮም መጽሐፍ ላይ ጎላ አድርጎ የገለጸውን የምሥራቹን ገጽታ እንድናስብ ያደርገናል። ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ጳውሎስ “እኔ በምሥራቹ አላፍርም፤ እንዲያውም ምሥራቹ . . . መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል ነው” ሲል ጽፏል።​—ሮም 1:15, 16

19 ይህ ምሥራች ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ በሚጫወተው ሚና ላይ ያተኮረ ነው። ጳውሎስ፣ እሱ ‘በሚያውጀው ምሥራች መሠረት አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ሰዎች በስውር በሚያስቧቸውና በሚያደርጓቸው ነገሮች ላይ የሚፈርድበትን ቀን’ በጉጉት እንደሚጠባበቅ ገልጿል። (ሮም 2:16) ሐዋርያው ‘የክርስቶስንና የአምላክን መንግሥት’ ወይም አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት የሚያከናውነውን ነገር አቅልሎ አልተመለከተውም። (ኤፌ. 5:5) ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ፣ በአምላክ መንግሥት ሥር ለመኖርና በዚያ ከሚኖረው በረከት ለመቋደስ እንድንችል (1) በአምላክ ፊት ኃጢአተኞች መሆናችንን እንዲሁም (2) ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት ማሳደር የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ መገንዘብ እንዳለብን ጠቁሟል። አንድ ሰው ከአምላክ ዓላማ ጋር የተያያዙትን እነዚህን ነገሮች ሲያውቅና አምኖ ሲቀበል እንዲሁም ይህን ማድረጉ ተስፋ እንደሚሰጠው ሲገነዘብ “በእርግጥም ይህ ታላቅ የምሥራች ነው!” ለማለት ይገፋፋል።

20, 21. አገልግሎታችንን ስናከናውን በሮም መጽሐፍ ላይ ጎላ ተደርጎ የተገለጸውን የምሥራቹን ገጽታ በአእምሯችን መያዝ የሚኖርብን ለምንድን ነው? ይህስ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

20 እኛም ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ስናከናውን ይህን የምሥራቹን ገጽታ በአእምሯችን መያዝ እንዳለብን ምንም ጥያቄ የለውም። ጳውሎስ፣ ስለ ኢየሱስ ሲናገር በኢሳይያስ ላይ የሚገኘውን ትንቢት በመጥቀስ “እምነቱን በእሱ ላይ የሚጥል ሁሉ አያፍርም” ብሏል። (ሮም 10:11፤ ኢሳ. 28:16) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኃጢአት የሚናገረውን ሐሳብ የሚያውቁ ሰዎች ስለ ኢየሱስ የሚገልጸው መልእክት መሠረታዊ ሐሳብ አዲስ ላይሆንባቸው ይችላል። ለሌሎች ግን ይህ መልእክት በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ የማይታወቅ ወይም ብዙዎች የማያምኑበት አዲስ ሐሳብ ሊሆንባቸው ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች በአምላክ መኖር ሲያምኑና በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እምነት ሲያሳድሩ የኢየሱስን ሚና ልናብራራላቸው ይገባል። ይህ የምሥራቹ ገጽታ በሮም ምዕራፍ 5 ላይ እንዴት እንደሚብራራ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን። በዚያ የጥናት ርዕስ ላይ በአገልግሎትህ የምትጠቀምባቸውን ሐሳቦች ልታገኝ ትችላለህ።

21 ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በሮም መጽሐፍ ላይ በተደጋጋሚ የተገለጸውን ምሥራች ይኸውም “ለሚያምን ሁሉ . . . መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል” የሆነውን ምሥራች እንዲያውቁ መርዳት እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ነው! (ሮም 1:16) ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ በ⁠ሮም 10:15 ላይ የጠቀሰውን “የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ምሥራች የሚናገሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው!” የሚለውን ሐሳብ ሌሎችም ሲያስተጋቡ በመመልከት እንደሰታለን።​—ኢሳ. 52:7

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 እንዲህ ዓይነት አገላለጾች በመንፈስ መሪነት በተጻፉ ሌሎች መጻሕፍት ውስጥም ይገኛሉ።​—ማር. 1:1፤ ሥራ 5:42፤ 1 ቆሮ. 9:12፤ ፊልጵ. 1:27

ታስታውሳለህ?

• በሮም መጽሐፍ ውስጥ ጎላ ተደርጎ የተገለጸው የምሥራቹ ገጽታ የትኛው ነው?

• ሌሎች የትኛውን እውነት እንዲገነዘቡ መርዳት ይኖርብናል?

• “ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች” ማወቃችን ለእኛም ሆነ ለሌሎች በረከት የሚሆነው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሮም መጽሐፍ ውስጥ ጎላ ተደርጎ የተገለጸው ምሥራች ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና የሚገልጽ ነው

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ ለሞት የሚዳርግ እንከን ይኸውም ኃጢአት ወርሰናል!