በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አብርሃም በእርግጥ ግመሎች ነበሩት?

አብርሃም በእርግጥ ግመሎች ነበሩት?

አብርሃም በእርግጥ ግመሎች ነበሩት?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ፈርዖን ለአብርሃም ከሰጠው የቤት እንስሳት መካከል ግመሎች ይገኙበት ነበር። (ዘፍ. 12:16) የአብርሃም አገልጋይ ሩቅ ወደ ሆነው ወደ መስጴጦምያ ለመሄድ ሲነሳ “ከጌታው ግመሎች መካከል ዐሥሩን [ወስዷል]።” ስለዚህ በሁለተኛው ሺህ ዓ.ዓ. መጀመሪያ አካባቢ አብርሃም ግመሎች እንደነበሩት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።—ዘፍ. 24:10

ይሁንና አንዳንዶች ይህንን አይቀበሉም። ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን አርኪኦሎጂካል ስተዲ ባይብል እንዲህ ይላል፦ “ምሑራን፣ ስለ ግመሎች የሚናገረው ሐሳብ ከታሪክ አንጻር ትክክል ስለመሆኑ ጥያቄ ያነሳሉ፤ ምክንያቱም ብዙ ምሑራን፣ እነዚህ እንስሳት እስከ 1200 ዓ.ዓ. አካባቢ ድረስ (አብርሃም ከኖረበት ዘመን ከረጅም ጊዜ በኋላ ማለት ነው) ከሰዎች ጋር ተላምደው የቤት እንስሳት ሆነው ማገልገላቸው ያን ያህል የተለመደ እንዳልነበረ ያምናሉ።” ምሑራን በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ በተጠቀሰው ዘመን ግመሎች እንደ ቤት እንስሳት ተደርገው እንደማይታዩ ስለሚያምኑ ከላይ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክል እንዳልሆነ ይሰማቸዋል።

ሌሎች ምሑራን ግን ግመሎች እንደ ቤት እንስሳት ተደርገው መቆጠራቸው ይበልጥ እየተለመደ የመጣው በሁለተኛው ሺህ ዓ.ዓ. መገባደጃ አካባቢ ቢሆንም ሰዎች ከዚያ በፊት በግመሎች አይጠቀሙም ማለት እንዳልሆነ ይናገራሉ። ሲቪላይዜሽንስ ኦቭ ዚ ኤንሸንት ኒር ኢስት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በስተ ደቡብ ምሥራቅ በሚገኙት የዓረብ አገሮች በሦስተኛው ሺህ [ዓ.ዓ.] አካባቢ ግመሎች እንደ ቤት እንስሳት ሆነው ያገልግሉ ነበር። መጀመሪያ ላይ ሰዎች ግመሎችን የሚያረቡት ለወተታቸው፣ ለፀጉራቸው፣ ለቆዳቸውና ለምግብነት ሊሆን ይችላል፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ለጭነት እንስሳነት ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ሳይገነዘቡ አልቀሩም።” ግመሎች ከአብርሃም ዘመን በፊት እንደ ቤት እንስሳት ሆነው ያገለግሉ እንደነበር የሚጠቁመው ይህ ጥናት ትክክል መሆኑን በአርኪኦሎጂ የተገኙ የአጥንት ስብርባሪዎችና ሌሎች ነገሮች ያረጋግጣሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በጽሑፍ የሰፈረ ማስረጃ ተገኝቷል። ከላይ የተጠቀሰው የማመሳከሪያ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በመስጴጦሚያ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች ተጽፎ የተገኘ ዝርዝር ይህን እንስሳ [ግመልን] የሚጠቅስ ሲሆን በርካታ ማኅተሞች ላይም ቅርጹ ተገኝቷል፤ ይህም በሁለተኛው ሺህ ዓ.ዓ. መጀመሪያ አካባቢ [አብርሃም በኖረበት ዘመን ማለት ነው] ይህ እንስሳ በመስጴጦምያ ሊገኝ እንደሚችል ይጠቁማል።”

አንዳንድ ምሑራን፣ በዕጣን ንግድ ላይ የተሰማሩ የደቡብ ዓረብ ነጋዴዎች በረሃውን አቋርጠው ጭነታቸውን ወደ ሰሜን ለማጓጓዝ በግመሎች ይጠቀሙ እንደነበር ያምናሉ፤ እነዚህ ነጋዴዎች እንደ ግብፅና ሶሪያ ወዳሉት አካባቢዎች ሲሄዱ ግመል በእነዚህ አካባቢዎች እንዲታወቅ አድርገዋል። እንዲህ ያለው ንግድ በ2000 ዓ.ዓ. መጀመሪያ አካባቢ እንኳ የተለመደ ሳይሆን አይቀርም። ዘፍጥረት 37:25-28 በግመሎቻቸው ላይ ዕጣን ጭነው ወደ ግብፅ ስለሚሄዱ እስማኤላውያን ነጋዴዎች የሚገልጽ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ይህ የሆነው ከአብርሃም ዘመን ከመቶ ዓመት ገደማ በኋላ ነው።

በሁለተኛው ሺህ ዓ.ዓ. መጀመሪያ ላይ በጥንቱ የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ በግመሎች መጠቀም ያን ያህል አልተለመደ ይሆናል፤ ይሁንና ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት እነዚህ እንስሳት ጨርሶ አይታወቁም ማለት አይደለም። ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “ግመሎች [ከአብርሃም ዘመን] በፊት እንደ ቤት እንስሳት ያገለግሉ እንደነበር የሚያሳዩ በርካታ የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች ስላሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፈሩት የመጀመሪያዎቹ ዘገባዎች ላይ የሚገኘውን ስለ ግመሎች የሚናገረውን ሐሳብ ትክክል እንዳልሆነ አድርጎ መመልከቱ ተገቢ አይደለም።”