በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ስኬታማ’ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

‘ስኬታማ’ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

‘ስኬታማ’ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

“ስኬት”​—ትኩረት የሚስብ ቃል ነው! አንዳንዶች ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ ችለዋል፤ ሀብታምና ስመ ጥር በመሆን ረገድም በጣም ተሳክቶላቸዋል። ሌሎች ግን ስኬታማ ለመሆን ቢያልሙም አልተሳካላቸውም።

ስኬት ማግኘትህ በአብዛኛው የተመካው በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ በምትሰጠው ነገር ላይ ነው። ለስኬት አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ሌሎች ሁለት ወሳኝ ነገሮች ደግሞ ጊዜህንና ጉልበትህን የምትጠቀምበት መንገድ እንዲሁም አንድን ነገር ለማከናወን ያለህ ተነሳሽነት ናቸው።

በርካታ ክርስቲያኖች በአገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ ማድረጋቸው ከፍተኛ እርካታ አስገኝቶላቸዋል። ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሰማራታቸው በሕይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ይሁንና አንዳንዶች አገልግሎት አሰልቺ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል፤ ሌሎች ግቦችን ለመከታተል ሲሉ ለአገልግሎታቸው ሁለተኛ ቦታ ሊሰጡት ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚፈጠረው ለምን ሊሆን ይችላል? ትልቅ ቦታ ልትሰጠው የሚገባውን ነገር ቸል እንዳትል ምን ማድረግ ትችላለህ? በሕይወትህ ውስጥ ‘ስኬታማ’ መሆን የምትችለውስ እንዴት ነው?​—ኢያሱ 1:8

ከትምህርት ሰዓት ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች

ክርስቲያን ወጣቶች ለእውነተኛው አምላክ የሚያቀርቡትን አምልኮና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማስኬድ መጣር ይኖርባቸዋል። እንዲህ የሚያደርጉ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ ስኬታማ የሚያደርጋቸውን ጎዳና እየተከተሉ ነው፤ ለዚህም በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል።

አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች ግን ከትምህርት ሰዓት ውጪ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች በጣም ተጠላልፈዋል። እንደነዚህ ያሉት እንቅስቃሴዎች በራሳቸው መጥፎ ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ክርስቲያን ወጣቶች እንደሚከተለው እያሉ ራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል፦ ‘እነዚህ እንቅስቃሴዎች ጊዜዬን ምን ያህል ይሻሙብኛል? ከእነማን ጋር እንድውል ያደርጉኛል? በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ስካፈል ጊዜዬን የማሳልፈው ምን ዓይነት አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ነው? ሕይወቴስ በምን ላይ ያተኮረ ይሆናል?’ አንድ ሰው እንደነዚህ ባሉት እንቅስቃሴዎች ከመጠን በላይ መጠላለፉ ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ይዞ ለመቀጠል የሚያስፈልገውን ጊዜም ሆነ ጉልበት ሊያሳጣው እንደሚችል ሳትገነዘብ አትቀርም። እንግዲያው ቅድሚያ ሊሰጠው ለሚገባው ነገር ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ከዚህ መረዳት ትችላለህ።​—ኤፌ. 5:15-17

የቪክቶርን * ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “የ12 ዓመት ልጅ እያለሁ አንድ የመረብ ኳስ ቡድን ውስጥ ገብቼ መጫወት ጀመርኩ። ከጊዜ በኋላ በጣም ብዙ ሽልማቶችን ለማግኘት በቃሁ። በዚህ ስፖርት ታዋቂ የመሆን አጋጣሚ ነበረኝ።” ውሎ አድሮ ግን ቪክቶር በዚህ ስፖርት የሚያደርገው ተሳትፎ በመንፈሳዊነቱ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑ ይረብሸው ጀመር። አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ ሳለ እንቅልፍ ወሰደው። ከዚህም በተጨማሪ በመስክ አገልግሎት ሲካፈል የሚያገኘው ደስታ እየቀነሰ እንደሆነ አስተዋለ። እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ ስፖርት መካፈሌ ጉልበቴን እያሟጠጠብኝ ነበር፤ እንዲሁም ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለኝ ቅንዓት እንዲቀዘቅዝ እያደረገ እንደሆነ ተገነዘብኩ። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ እያደረግሁ እንዳልሆነ ተሰማኝ።”

ከፍተኛ ትምህርት

አንድ ክርስቲያን ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር የማቅረብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ ያለበት ሲሆን ይህም ቁሳዊ ነገሮችን ይጨምራል። (1 ጢሞ. 5:8) ታዲያ ይህን ለማድረግ የግድ የኮሌጅ ወይም የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ያስፈልጋል?

አንድ ሰው ከፍተኛ ትምህርት መከታተሉ ከይሖዋ ጋር ባለው ዝምድና ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ማጤን ያስፈልገዋል። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንመልከት።

ባሮክ የነቢዩ ኤርምያስ ጸሐፊ ነበር። በአንድ ወቅት ባሮክ ይሖዋን ለማገልገል ባገኘው መብት ላይ ከማተኮር ይልቅ ትልቅ ቦታ ላይ የመድረስ ምኞት አድሮበት ነበር። ይሖዋ ይህንን ስላስተዋለ በኤርምያስ በኩል ለባሮክ እንዲህ የሚል ምክር ሰጠው፦ “ለራስህ ታላቅ ነገር ትሻለህን? . . . አትፈልገው።”​—ኤር. 45:5

ባሮክ ይፈልገው የነበረው “ታላቅ ነገር” ምንድን ነው? በአይሁድ ማኅበረሰብ ውስጥ ትልቅ ቦታ የማግኘት ፍላጎት አድሮበት ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ቁሳዊ ብልጽግና ማግኘት ፈልጎ ይሆናል። ባሮክ የተመኘው ነገር ምንም ይሁን ምን ይህ የአምላክ አገልጋይ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ይኸውም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት ተስኖት ነበር። (ፊልጵ. 1:10) ደስ የሚለው ግን ባሮክ ይሖዋ በኤርምያስ በኩል የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምቷል፤ በዚህም ምክንያት ሕይወቱ ከጥፋት ተርፏል።​—ኤር. 43:6

ከዚህ ዘገባ ምን እንማራለን? ይሖዋ ለባሮክ ከሰጠው ምክር መረዳት እንደምንችለው ይህ የአምላክ አገልጋይ የተሳሳተ ጎዳና ተከትሎ ነበር። ለራሱ ታላቅ ነገር መሻት ጀምሮ ነበር። አንተስ ራስህን የምታስተዳድርበት ገቢ ካለህ፣ ስኬታማ እንደሆንክ እንዲሰማህ ስትል አሊያም ወላጆችህ ወይም ሌሎች ዘመዶችህ ስለሚጠብቁብህ ብቻ ተጨማሪ ትምህርት ለመማር ጊዜህን፣ ገንዘብህንና ጉልበትህን ማባከን ይኖርብሃል?

የኮምፒውተር ፕሮግራም የሚሠራውን የግዤጎሽን ሁኔታ እንመልከት። ግዤጎሽ፣ የሥራ ባልደረቦቹ ልዩ የሆነ ተጨማሪ ሥልጠና እንዲወስድ ስለገፋፉት መማር ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ጊዜ ማግኘት አቃተው። እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “ብዙ ጊዜ በውጥረት ልፈነዳ እንደደረስኩ ይሰማኝ ነበር። ያወጣኋቸው መንፈሳዊ ግቦች ላይ መድረስ ባለመቻሌ ሕሊናዬ ይረብሸኝ ጀመር።”

ከሚገባው በላይ በሥራ መጠመድ

እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ሠራተኞችም ሆኑ አሠሪዎች ትጉህና ኃላፊነት የሚሰማቸው ሊሆኑ እንደሚገባ የአምላክ ቃል ይገልጻል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ እንደምታደርጉት በማሰብ በሙሉ ነፍሳችሁ አድርጉት” በማለት ጽፏል። (ቆላ. 3:22, 23) ትጉህ ሠራተኛ መሆን የሚያስመሰግን ቢሆንም ከዚያ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ከፈጣሪያችን ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረታችን ነው። (መክ. 12:13) አንድ ክርስቲያን በሰብዓዊ ሥራው ከልክ በላይ ከተጠመደ ብዙም ሳይቆይ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቹ ሁለተኛ ቦታ መስጠት ይጀምራል።

አንድ ክርስቲያን ከልክ በላይ በሥራ መጠመዱ መንፈሳዊ ሚዛኑን ለመጠበቅም ሆነ ቤተሰቡን በመንፈሳዊ ለመርዳት ኃይል እንዲያጣ ሊያደርገው ይችላል። ንጉሥ ሰለሞን ‘በድካም የሚገኝ ሁለት ዕፍኝ’ ብዙውን ጊዜ ውጤቱ ‘ነፋስን እንደ መከተል’ መሆኑን ተናግሯል። አንድ ክርስቲያን ከልክ በላይ በሥራ የሚጠመድ ከሆነ የኋላ ኋላ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ከባድ ውጥረት ሊያጋጥመው ይችላል። እንዲህ ያለው ሰው ከሚገባው በላይ በሥራው ከመጠመዱ የተነሳ ከፍተኛ ድካምና የመዛል ስሜት ሊሰማው ይችላል። ይህ ከሆነ ታዲያ ‘ደስ መሰኘት’ እንዲሁም “በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን [ማግኘት]” ይችላል? (መክ. 3:12, 13፤ 4:6) ከሁሉ በላይ ደግሞ የቤተሰብ ኃላፊነቱን ለመወጣትና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል የሚያስችል ኃይልና ውስጣዊ ጥንካሬ ይኖረዋል?

በምሥራቅ አውሮፓ የሚኖረው ያኑሽ አትክልት በመንከባከብ ሥራው ከሚገባው በላይ ተጠምዶ ነበር። እንዲህ ይላል፦ “ከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት ስለነበረኝና የተሰጠኝን እያንዳንዱን ሥራ በብቃት ስለማጠናቅቅ ሰዎች በጣም ያደንቁኝ ነበር። ይሁንና መንፈሳዊነቴ የተጎዳ ሲሆን በመስክ አገልግሎት መካፈሌንም አቆምኩ። ብዙም ሳይቆይ ከስብሰባ ቀረሁ። ኩራት ስለተጠናወተኝ ሽማግሌዎች የሚሰጡኝን ምክር ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበርኩም፤ ቀስ በቀስ ከጉባኤው እየራቅሁ ሄድኩ።”

ሕይወትህን ስኬታማ ማድረግ ትችላለህ

አንድ ክርስቲያን እስከ አሁን በተመለከትናቸው ሦስት ነገሮች ከሚገባው በላይ መጠላለፉ መንፈሳዊነቱን ሊጎዳበት ይችላል። አንተስ እንደ እነዚህ ባሉት ነገሮች ተጠላልፈሃል? ከሆነ ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት ጥያቄዎች፣ ጥቅሶችና ሐሳቦች ወደ ስኬት በሚያመራው ጎዳና ላይ መሆን አለመሆንህን ለማወቅ ሊረዱህ ይችላሉ።

ከትምህርት ሰዓት ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች፦ እንዲህ ባሉ እንቅስቃሴዎች ምን ያህል ተጠላልፈሃል? ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ታውለው የነበረውን ጊዜ እየተሻሙብህ ነው? ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር መሆን ብዙም አያስደስትህም? ከሆነ የንጉሥ ዳዊትን ምሳሌ ለምን አትከተልም? ዳዊት “የምሄድበትን መንገድ አሳየኝ” በማለት ይሖዋን ለምኖት ነበር።​—መዝ. 143:8

ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ቪክቶርን አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ረዳው። ይህ ወንድም በጨዋታቸው መሃል ቪክቶርን “ስለ መረብ ኳስ የምታወራው በስሜት ተውጠህ ነው” አለው። ቪክቶር እንደሚከተለው ብሏል፦ “እንዲህ ሲለኝ በጣም ደነገጥሁ። ሚዛኔን እንደሳትኩ ገባኝ። ብዙም ሳይቆይ በስፖርት ቡድኑ ውስጥ ከነበሩት ዓለማዊ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋረጥኩ፤ ከዚያም በጉባኤ ውስጥ ጓደኞች ለማፍራት ጥረት ማድረግ ጀመርኩ።” በአሁኑ ጊዜ ቪክቶር በጉባኤው ውስጥ ይሖዋን በቅንዓት እያገለገለ ነው። እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል፦ “በትምህርት ቤት የምታደርጉት እንቅስቃሴ ወደ ይሖዋ እንድትቀርቡ እያደረጋችሁ አሊያም ከይሖዋ እያራቃችሁ እንደሆነ ለማወቅ ጓደኞቻችሁ፣ ወላጆቻችሁ አሊያም የጉባኤያችሁ ሽማግሌዎች ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚሰማቸው ጠይቋቸው።”

ተጨማሪ መብቶች በማግኘት አምላክን ማገልገል እንደምትፈልግ በጉባኤህ ውስጥ ላሉ ሽማግሌዎች ለምን አትነግራቸውም? ጓደኛ ወይም እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች መደገፍ ትችላለህ? ምናልባትም ገበያ በመውጣት ወይም በቤት ውስጥ አንዳንድ ሥራዎችን በማከናወን ልትረዳቸው ትችል ይሆን? በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ብትሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመሳተፍ ለደስታህ ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ለሌሎች ማካፈል ትችላለህ።

ከፍተኛ ትምህርት፦ ኢየሱስ ‘ለራሳችን ክብር ከመፈለግ’ እንድንርቅ አስጠንቅቆናል። (ዮሐ. 7:18) በዓለማዊ ትምህርት ረገድ እስከ ምን ድረስ መሄድ እንዳለብህ የምታደርገው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች’ የትኞቹ እንደሆኑ ለይተህ አውቀሃል?​—ፊልጵ. 1:9, 10

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ግዤጎሽ በሕይወቱ ውስጥ አንዳንድ ማስተካከያዎችን አደረገ። እንዲህ ብሏል፦ “ሽማግሌዎች የሰጡኝን ምክር በመከተል ሕይወቴን ቀላል አደረግሁ። ተጨማሪ ትምህርት መከታተል እንደማያስፈልገኝ ተገንዝቤ ነበር። እንዲህ ያለው ትምህርት ጊዜዬንና ጉልበቴን ከማሟጠጥ ውጪ የሚያተርፍልኝ ነገር የለም።” ግዤጎሽ በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ተሳትፎ ማድረግ ጀመረ። ከጊዜ በኋላም ለነጠላ ወንድሞች ከተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት (ቀደም ሲል የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ይባል ነበር) ተመረቀ። በእርግጥም ተጨማሪ መለኮታዊ ትምህርት ለመቅሰም የሚሆን ‘ጊዜ ገዝቷል።’​—ኤፌ. 5:16

ሰብዓዊ ሥራ፦ በሰብዓዊ ሥራህ በጣም ከመጠመድህ የተነሳ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሁለተኛ ቦታ መስጠት ጀምረሃል? ከቤተሰብህ ጋር የሐሳብ ልውውጥ የምታደርግበት በቂ ጊዜ አለህ? በጉባኤ ውስጥ የሚሰጡህን ክፍሎች የምታቀርብበትን መንገድ እያሻሻልክ ነው? ከሌሎች ጋር የሚያንጽ ጭውውት በማድረግ ረገድስ እንዴት ነህ? እውነተኛውን አምላክ ‘የምትፈራና ትእዛዛቱን የምትጠብቅ’ ከሆነ ከይሖዋ የተትረፈረፈ በረከት የምታገኝ ከመሆኑም ሌላ ‘በሥራህ ትረካለህ።’​—መክ. 2:24፤ 12:13

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ያኑሽ፣ በሥራው ስኬታማ አልሆነም፤ እንዲያውም ለኪሳራ ተዳረገ። የገቢ ምንጭ የሌለው ከመሆኑም ሌላ በዕዳ ተዘፍቆ ነበር። ያኑሽ ወደ ይሖዋ ዘወር በማለት ሕይወቱን ያስተካከለ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የዘወትር አቅኚና የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች መርካቴ እንዲሁም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መጠመዴ የአእምሮ ሰላምና ውስጣዊ መረጋጋት እንዳገኝ አስችሎኛል።”​—ፊልጵ. 4:6, 7

ጊዜ ወስደህ ውስጣዊ ዝንባሌህንና ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች በሐቀኝነት መርምር። ይሖዋን ማገልገል በሕይወትህ ሁሉ ስኬታማ እንድትሆን ያስችልሃል። እንግዲያው በሕይወትህ ውስጥ ለይሖዋ አምልኮ ትልቅ ስፍራ ስጠው።

“ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ” መርምረህ ማረጋገጥ እንድትችል አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ሌላው ቀርቶ አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከናካቴው ማስወገድ ይኖርብህ ይሆናል። (ሮም 12:2) ያም ቢሆን ይሖዋን በሙሉ ነፍስህ በማገልገል ስኬታማ መሆን ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ስኬታማ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

ትኩረትህን የሚሰርቁ በርካታ ነገሮች እያሉም ትልቅ ቦታ ልትሰጠው የሚገባውን ነገር ቸል እንዳትል ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በሚከተሉት ጥያቄዎች በመጠቀም ጊዜ ወስደህ ውስጣዊ ዝንባሌህንና ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች መርምር፦

ከትምህርት ሰዓት ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች

▪ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ስትካፈል ጊዜህን የምታሳልፈው ምን ዓይነት አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ነው?

▪ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ጊዜህን ምን ያህል ይሻሙብሃል?

▪ በሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ ይይዙ ይሆን?

▪ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ታውለው የነበረውን ጊዜ እየተሻሙብህ ነው?

▪ ከእነማን ጋር እንድትውል ያደርጉሃል?

▪ ከእነዚህ ሰዎች ጋር መሆን ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር ከመሆን ይበልጥ ያስደስትሃል?

ከፍተኛ ትምህርት

▪ ራስህን የምታስተዳድርበት ገቢ ካለህ ተጨማሪ ትምህርት ለመማር ጊዜህን፣ ገንዘብህንና ጉልበትህን ማባከን ይኖርብሃል?

▪ ራስህን ለማስተዳደር የግድ የኮሌጅ ወይም የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ያስፈልግሃል?

▪ ከፍተኛ ትምህርት መከታተልህ ከጉባኤ ስብሰባዎች እንድትቀር ያደርግሃል?

▪ ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተህ አውቀሃል?’

▪ ይሖዋ የሚያስፈልጉህን ነገሮች ማሟላት እንደሚችል ያለህን እምነት ማጠናከር ያስፈልግህ ይሆን?

ሥራ

▪ የሥራ ምርጫህ ‘ደስ ለመሰኘትና በምትደክምበት ሁሉ እርካታ ለማግኘት’ ያስችልሃል?

▪ የቤተሰብ ኃላፊነትህን ለመወጣትና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል የሚያስችል ኃይልና ውስጣዊ ጥንካሬ ይኖርሃል?

▪ ከቤተሰብህ ጋር የሐሳብ ልውውጥ የምታደርግበት በቂ ጊዜ አለህ?

▪ በሰብዓዊ ሥራህ በጣም ከመጠመድህ የተነሳ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሁለተኛ ቦታ መስጠት ጀምረሃል?

▪ ሥራህ በጉባኤ ውስጥ የሚሰጡህን ክፍሎች በምታቀርብበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው?

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ባሮክን ታላቅ ነገር እንዳይሻ አስጠንቅቆታል