በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወት በእርግጥ ትርጉም አለው?

ሕይወት በእርግጥ ትርጉም አለው?

ሕይወት በእርግጥ ትርጉም አለው?

“ሕይወት በእርግጥ ትርጉም አለው?” ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ይህን ጥያቄ ሲጠይቁ ኖረዋል። የሚያሳዝነው ግን ሰዎች ለሕይወት ያላቸው አመለካከት ምንም ይሁን ምን አብዛኞቹ ሰዎች ቪክቶር ፍራንክል የተባሉ ኦስትሪያዊ የነርቭ ሐኪም እንደገለጹት “ትርጉም የለሽና ባዶ” ሕይወት ከመምራት ማምለጥ አልቻሉም።

በርካታ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሕይወት የሚመሩት ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት፣ በመላው ዓለም የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለማመን በሚያዳግት መልኩ በሰቆቃና ቅስም በሚሰብር ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸው ነው። ለእነዚህ ሰዎች ድህነት፣ በሽታ፣ ዘግናኝ ዓመፅና ጭቆና የሕይወታቸው ክፍል ሆነዋል። በእርግጥም በጥንት ዘመን የኖረው ኢዮብ በሰው ዘር ላይ የሚደርሰውን ሥቃይን አስመልክቶ እንደተናገረው የእነዚህ ሰዎች ሕይወት “በመከራ የተሞላ ነው።” (ኢዮብ 14:1) እነዚህ ሰዎች በእያንዳንዱ ቀን በሕይወት ለመቀጠል ከባድ ትግል ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በቁሳዊ ነገሮች የበለጸጉ ናቸው። እንዲሁም በሕይወት ውስጥ እውነተኛ እርካታ ለማግኘት የሚያስችሉ ነገሮች በሙሉ የተሟሉላቸው ይመስላል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ እርካታ ያለው ሕይወት እየመሩ አይደለም። ለምን? ምክንያቱም በተደጋጋሚ ጊዜ እንደታየው እነዚህ ሰዎች ‘መከራና ሐዘን’ ሲመጣባቸው ማለትም ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ያልተጠበቀ ችግር ሲያጋጥማቸው ወይም የልጅ ሞትን የመሰለ መሪር ሐዘን ሲደርስባቸው የነበራቸው ተስፋና ምኞት ሁሉ በንኖ ይጠፋል።​—መዝሙር 90:10 1980 ትርጉም

ብዙ ሰዎች የሚመሩትን ሕይወት “ትርጉም የለሽና ባዶ” የሚያደርግባቸው ሌላም ምክንያት አለ። ይህ ምንድን ነው? ሕይወት እጅግ አጭር መሆኑ ነው። ታላላቅ ነገሮችን የማከናወን ስጦታ የተሰጣቸው የሰው ልጆች ሕይወታቸው አጭር የመሆኑ ጉዳይ ለብዙ ሰዎች እንቆቅልሽ ነው። በሁላችንም ፊት የተደቀነውን መራራ እውነታ ይኸውም በሰው ልጆች ላይ እየደረሱ ካሉት አሳዛኝ ሁኔታዎች ብናመልጥ እንኳ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ሞት ሁሉንም ነገር የሚያሳጣን የመሆኑን ሐቅ መረዳት አዳጋች ሆኖባቸዋል።​—መክብብ 3:19, 20

ሕይወት በዚህ መልኩ ይቀጥላል?

የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰለሞን ይህን ሁኔታ ጠቅለል ባለ መንገድ ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። በዛሬው ጊዜ ያለነው ሰዎች እንደምናደርገው ሁሉ በእሱ ዘመን የነበሩ ሰዎችም ያላቸውን ተሰጥኦና ችሎታ ተጠቅመው በመትከል፣ በማልማት፣ በመገንባትና ቤተሰቦቻቸውን በመንከባከብ ረገድ ምን ያህል ጠንክረው ይሠሩ እንደነበረ ተመልክቷል። ከዚያም ‘የዚህ ሁሉ ልፋት ጥቅሙ ምንድን ነው?’ የሚል አንድምታ ያለው ጥያቄ አንስቷል። በመጨረሻም ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ሁሉ “ባዶ፣ ነፋስንም እንደ ማሳደድ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።​—መክብብ 2:17 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል

ይሁን እንጂ ንጉሥ ሰለሞን የሰው ልጆች የሚያደርጓቸው ነገሮች በሙሉ ምንጊዜም “ባዶ፣ ነፋስንም እንደ ማሳደድ” ሆነው እንደሚቀሩ ያምን ነበር? በጭራሽ። ከዚህ ይልቅ ይህን ሐሳብ የተናገረው ፍጽምና በሌለው በዚህ ዓለም ውስጥ ሕይወት ምን መልክ እንዳለው እውነታውን ለመግለጽ ነበር። ሆኖም በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ነገሮች ምንጊዜም በዚህ መልኩ እንደማይቀጥሉ እርግጠኛ እንድትሆን ያደርግሃል።

ታዲያ አንተ ይህ እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? መልሱ ለማወቅ፣ እባክህ የሚቀጥሉትን ሁለት ርዕሶች አንብብ። እነዚህ ርዕሶች ሕይወትን ይህን ያህል ትርጉም የለሽ እንዲመስል ያደረገው ምን እንደሆነ፣ ይህ ሁኔታ እንዴት መፍትሔ እንደሚያገኝ እንዲሁም በዛሬው ጊዜም እንኳ ሕይወትህ እውነተኛ ትርጉም እንዲኖረው ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንድትገነዘብ ሊረዱህ ይችላሉ።