በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ አንድን ዘር ከሌላው አስበልጦ ይመለከታል?

አምላክ አንድን ዘር ከሌላው አስበልጦ ይመለከታል?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

አምላክ አንድን ዘር ከሌላው አስበልጦ ይመለከታል?

▪ በፍጹም! አምላክ እንዲህ አያደርግም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ እንደማያዳላ . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት” እንዳለው በግልጽ ይናገራል።​—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

በዚህ ረገድ አምላክ ያለው አስተሳሰብ ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ካላቸው አስተሳሰብ እጅግ የላቀ ነው። ብዙ ሰዎች አንድ ዘር (ብዙውን ጊዜ የራሳቸው ዘር) ከሌላው እንደሚበልጥ ይሰማቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ የተዛባ አስተሳሰብ የቻርልስ ዳርዊንን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው፤ ዳርዊን እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “ወደፊት በሆነ ወቅት ላይ . . . የሠለጠነው የሰው ዘር ኋላ ቀሩን የሰው ዘር ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ከምድረ ገጽ በማስወገድ የእሱን ቦታ እንደሚይዝ ምንም ጥርጥር የለውም።” እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ወገኖች በብዙ ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸው የሚያሳዝን ነው።

ሰዎች የራሳቸው ዘር ከፍ ያለ እንደሆነ እንዲሰማቸው የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት ይኖር ይሆን? ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ዘሮች በተፈጥሯቸው ከሌሎች ዘሮች የተሻሉ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ሳይንሳዊ ማስረጃ ተገኝቷል? የዘረ መል ጥናት ባለሙያና የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ብራያን ሳይክስ እንዲህ ብለዋል፦ “የአንድን ሰው ጂን መሠረት በማድረግ ግለሰቡ ከዚህ ጎሳ ወይም ከዚህ ዘር ይመደባል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። . . . ብዙ ጊዜ ሰዎች፣ የግሪክ ዲ ኤን ኤ ወይም የጣሊያን ጂን የሚባል ነገር ይኖር እንደሆነ ይጠይቁኛል፤ ይሁንና እንዲህ የሚባል ነገር የለም። . . . እኛ የሰው ዘሮች ምንም ዓይነት ልዩነት የለንም ማለት ይቻላል።”

እንዲህ ያሉት የምርምር ውጤቶች ቅዱሳን መጻሕፍት ከሚናገሩት ሐሳብ ጋር ይስማማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ አንድ ወንድና አንዲት ሴት እንደፈጠረና የሰው ዘር በሙሉ የተገኙት ከእነዚህ ባልና ሚስት እንደሆነ ያስተምራል። (ዘፍጥረት 3:20፤ የሐዋርያት ሥራ 17:26) በመሆኑም በምድር ላይ ያሉት የሰው ልጆች በሙሉ በአምላክ ዘንድ የሚታዩት ልክ እንደ አንድ ዘር ነው።

አንድ ሰው ያለው የቆዳ ቀለም ወይም የፊት ገጽታ ምንም ይሁን ምን በይሖዋ ዘንድ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምሳሌያዊ ልባችን ማለትም ለውስጣዊ ማንነታችን ነው። እንዲህ ብሏል፦ “እኔ የምፈርደው ሰዎች እንደሚፈርዱት አይደለም፤ ሰው ውጫዊ መልክን ያያል፣ እኔ ግን ውስጣዊ ልብን አያለሁ።” (1 ሳሙኤል 16:7 የ1980 ትርጉም) ይህንን ሐቅ መገንዘባችን ትልቅ ማጽናኛ ይሆነናል። እንዴት?

ዘራችን ምንም ይሁን ምን ብዙዎቻችን በተወሰነ መጠንም ቢሆን ባለን ቁመና ደስተኞች አይደለንም፤ ያም ሆኖ ቁመናችንን ለመቀየር ያለን አቅም በጣም ውስን ነው። ይሁንና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ይኸውም ውስጣዊ ስሜታችንንና በልባችን የምናስባቸውን ነገሮች ማስተካከል እንችላለን። (ቆላስይስ 3:9-11) ራሳችንን በሐቀኝነት ስንመረምር የእኛን ዘር በትንሹም ቢሆን ከሌላው ዘር ከፍ አድርገን አሊያም ዝቅ አድርገን የመመልከት ዝንባሌ እንዳለን እንገነዘብ ይሆናል። ሁለቱም ዝንባሌዎች ቢሆኑ ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚጣጣሙ ባለመሆናቸው እንዲህ ያሉ ስሜቶችን ከልባችን ውስጥ ነቅለን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባናል።​—መዝሙር 139:23, 24

ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ይሖዋ በሚያይበት መንገድ ለማየት ጥረት የምናደርግ ከሆነ የይሖዋ ድጋፍ እንደማይለየን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ።” (2 ዜና መዋዕል 16:9) ዘራችን ምንም ይሁን ምን ይህ ጥቅስ በእኛም ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል።