በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አጽናፈ ዓለም የሚተዳደርበትን ሕግ ያወጣው ማን ነው?

አጽናፈ ዓለም የሚተዳደርበትን ሕግ ያወጣው ማን ነው?

አጽናፈ ዓለም የሚተዳደርበትን ሕግ ያወጣው ማን ነው?

“ሰማያት በምን ዐይነት ሕግ እንደሚተዳደሩ ታውቃለህ?” (ኢዮብ 38:33 የ1980 ትርጉም) አምላክ በመከራ ውስጥ ለነበረው ለኢዮብ እንዲህ ያለ ጥያቄ ያቀረበለት የሰው ልጆች ያላቸው እውቀት ወሰን ከሌለው የፈጣሪ ጥበብ ጋር ሲወዳደር ምን ያህል ኢምንት እንደሆነ እንዲገነዘብ ለመርዳት አስቦ ነው። አንተስ ይህ ንጽጽር ትክክል እንደሆነ ይሰማሃል?

የሰው ልጆች የሰማይ አካላት ስለሚተዳደሩበት ሕግ ብዙ ነገሮችን ማወቅ ቢችሉም አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች ገና ብዙ የሚቀራቸው ነገር እንዳለ ያምናሉ። በየጊዜው የሚደረስባቸው አዳዲስ ግኝቶች በመኖራቸው የተነሳ ሳይንቲስቶች በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለውን ሥርዓት አስመልክቶ ያወጧቸውን ንድፈ ሐሳቦች በድጋሚ ለማጤን ተገድደዋል። ከአጽናፈ ዓለም አሠራር ጋር በተያያዘ ሰዎች የደረሱባቸው አዳዲስ ግኝቶች አምላክ ለኢዮብ ያቀረበው ጥያቄ ጊዜ ያለፈበት እንዲሆን አድርገውት ይሆን? ወይስ እነዚህ ግኝቶች ሰማያት የሚተዳደሩባቸውን ሕግጋት ያወጣው ይሖዋ እንደሆነ ለማረጋገጥ አስችለዋል?

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ለመሰሉ ጥያቄዎች መልስ እንድናገኝ የሚረዱ ትኩረት የሚስቡ ሐሳቦችን ይዟል። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ አይደለም። ያም ሆኖ በከዋክብት ስለተሞሉት ሰማያት የሚናገረው ሐሳብ በሚያስደንቅ ሁኔታ ትክክለኛ ነው፤ እንዲሁም በአብዛኛው ማለት ይቻላል ሰዎች እነዚህ ሐሳቦች እውነት መሆናቸውን የደረሱበት በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ነው።

ከአጽናፈ ዓለም ጋር በተያያዘ በድሮ ዘመን የነበሩ አመለካከቶች

በድሮ ዘመን የነበሩ አንዳንድ አመለካከቶችን ለማየት እንድንችል እስቲ ወደ አራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መለስ እንበል፤ በዚህ ጊዜ ብሉይ ኪዳን የሚባለው የዕብራይስጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ተጽፎ ካለቀ አንድ መቶ ዓመት ሆኖት ነበር። በዚያ ወቅት አርስቶትል የተባለው ግሪካዊ ፈላስፋ በዘመኑ ለነበሩት ታላላቅ ምሑራን ስለ ሰማይ አካላት ያስተምር ነበር። ዛሬም ቢሆን ይህ ሰው በምድር ላይ ከኖሩትና ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ከቻሉት ታላላቅ ሳይንቲስቶች ጎራ ይመደባል። (  በገጽ 25 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚገልጸው ከሆነ “በታሪክ ውስጥ በትክክል ሳይንቲስት ተብሎ ሊጠራ የሚችለው የመጀመሪያው ሰው አርስቶትል ነው። . . . ለሳይንቲስቶች በሙሉ ባለውለታቸው ነው።”

አርስቶትል አጽናፈ ዓለምን የሚያሳይ ሞዴል በጥንቃቄ አዘጋጅቶ ነበር። አርስቶትል ባዘጋጀው ንድፍ መሠረት ምድር የአጽናፈ ዓለም እምብርት ስትሆን ከምድር በላይ አንዱ ሌላውን በመክበብ የተነባበሩ ከ50 የሚበልጡ እንደ መስታወት ያሉ ክበቦች አሉ። ከዋክብት በመጨረሻው ክበብ ላይ ተጣብቀው የሚገኙ ሲሆን ፕላኔቶች ደግሞ ለምድር ቅርብ በሆኑት ክበቦች ላይ ተጣብቀዋል። እንደ አርስቶትል አመለካከት ከሆነ ከምድር በላይ ያለው ማንኛውም ነገር ዘላለማዊና የማይለዋወጥ ነው። እነዚህ ጽንሰ ሐሳቦች በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ ተረት መስለው ይታዩን ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ለ2000 ዓመታት ገደማ በሳይንስ ሊቃውንት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ችለዋል።

የአርስቶትል ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል? በጊዜ ሂደት ትክክለኛ መሆኑ የተረጋገጠው የትኛው ትምህርት ነው? እስቲ አጽናፈ ዓለም የሚተዳደርባቸውን ሕግጋት አስመልክቶ ሦስት ጥያቄዎችን እንመርምር። የጥያቄዎቹን መልስ ማወቃችን የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት በሆነውና ሕግ በማውጣት “የሰማያትን ሥርዐት” በዘረጋው አካል ላይ እምነት ለማሳደር ይረዳናል።​—ኢዮብ 38:33

1. አጽናፈ ዓለም ምንም ለውጥ አያደርግም?

አርስቶትል በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ክበቦች ምንም ዓይነት ለውጥ የማይታይባቸው እንደሆኑ አድርጎ ያስብ ነበር። እንደ አርስቶትል አስተሳሰብ ከሆነ ከዋክብትን የያዘው ክበብም ሆነ ሌሎቹ ክበቦች እየሰፉም ሆነ እያነሱ መሄድ አይችሉም።

በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? እንዲህ የመሰለ ግምታዊ ሐሳብ ይሰነዝራል? በፍጹም! የአምላክ ቃል በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ቀጥተኛ መግለጫ የለም። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የሚከተለውን አስገራሚ መግለጫ ልብ በል፦ “እርሱ ከምድር ክበብ በላይ በዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ ሕዝቦቿም እንደ አንበጣ ናቸው። ሰማያትን እንደ ድባብ [“ስስ ጨርቅ፣” NW] ይዘረጋቸዋል፤ እንደ መኖሪያ ድንኳንም ይተክላቸዋል።”​—ኢሳይያስ 40:22 *

ታዲያ ዛሬ ይበልጥ ትክክል ሆኖ የተገኘው የአርስቶትል ሐሳብ ነው ወይስ የመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫ? ዘመናዊው የጠፈር ጥናት አጽናፈ ዓለምን በተመለከተ ምን ይላል? በ20ኛው መቶ ዘመን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች አጽናፈ ዓለም ባለበት የሚቀጥል ሳይሆን እየተለጠጠ የሚሄድ መሆኑን ሲያውቁ በጣም ተደንቀዋል። እንዲያውም ጋላክሲዎች በከፍተኛ ፍጥነት አንዳቸው ከሌላው በመሸሽ ላይ ያሉ ይመስላል። አጽናፈ ዓለም እየሰፋ እንደሚሄድ የገመቱ ሳይንቲስቶች አልነበሩም፤ ካሉም በጣም ጥቂት ቢሆኑ ነው። በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የኮስሞሎጂ ባለሙያዎች አጽናፈ ዓለም መጀመሪያ ላይ አነስተኛና ጥቅጥቅ ያለ እንደነበረ እንዲሁም ከዚያን ጊዜ አንስቶ አለማቋረጥ እየሰፋ እንደመጣ ያምናሉ። በሌላ አባባል አርስቶትል አጽናፈ ዓለምን አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ የተሳሳተ መሆኑን ሳይንስ አረጋግጧል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጠው መግለጫስ ምን ማለት ይቻላል? ነቢዩ ኢሳይያስ ራሱን ቀና አድርጎ በከዋክብት ያሸበረቀውን ሰማይ ሲመለከት ሁኔታውን ከተዘረጋ ድንኳን ጋር ማመሳሰሉ ምንም አያስገርምም። * እንዲያውም ኢሳይያስ ፍኖተ ሐሊብ የተባለው ጋላክሲ “ስስ ጨርቅ” እንደሚመስል ሳያስተውል አልቀረም።

ከዚህም በላይ ኢሳይያስ የተጠቀመበት መግለጫ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችን እንድንስለው የሚያደርግ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች ከጠንካራ ጨርቅ የተሠራና ተጠቅልሎ የተቀመጠን ድንኳን ሲፈቱ፣ በእንጨት ሲወጥሩ እናም ትንሽ የሚመስለው ጨርቅ ተዘርግቶ ትልቅ ቤት ሲሆን በአእምሯችን ማሰብ እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ነጋዴ ስስ ጨርቅ ሊገዛ ለመጣ ሰው ትንሽ የሚመስል አንድ ጣቃ አንስቶ እየተረተረ ሲያሳየው በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንችላለን። በሁለቱም ሁኔታ እንዳየነው ከሆነ ተጠቅልሎ ሲቀመጥ ትንሽ ይመስል የነበረው ነገር ሲዘረጋ ትልቅ ሆኗል።

እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን በአእምሯችን እንድንስለው በሚያደርግ መንገድ ስለ ድንኳንና ስለ ስስ ጨርቅ የተናገረው አጽናፈ ዓለም እየሰፋ መሄዱን ለማመልከት ነው ማለታችን አይደለም። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አጽናፈ ዓለም የሚሰጠው መግለጫ ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር የሚጣጣም መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም? ኢሳይያስ የኖረው አርስቶትል ከኖረበት ዘመን ሦስት መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ እንዲሁም ሳይንስ በዚህ ጉዳይ ላይ አሳማኝ ማስረጃ ከማቅረቡ በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ነው። ያም ቢሆን ይህ ተራ ዕብራዊ ነቢይ የጻፈው መግለጫ አርስቶትል እንዳዘጋጀው ድንቅ ሞዴል ማሻሻያ ወይም ማስተካከያ ማድረግ አላስፈለገውም።

2. የሰማይ አካላት ቦታቸውን እንዲጠብቁ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?

አርስቶትል አጽናፈ ዓለም በተለያዩ ነገሮች የታጨቀ እንደሆነ አድርጎ ያስብ ነበር። ምድርና የምድር ከባቢ አየር ከአራት ነገሮች ማለትም ከአፈር፣ ከውኃ፣ ከአየርና ከእሳት የተሠሩ እንደሆኑ ያምን ነበር። ከምድር ውጪ ያለው አጽናፈ ዓለም እንደ መስታወት ባሉ ክበቦች የተሞላ ሲሆን እያንዳንዱ ክበብ ደግሞ እሱ ኢተር ብሎ ከጠራው ዘላለማዊ የሆነ ንጥረ ነገር የተሠራ ነው። እንደ እሱ አመለካከት ከሆነ የሰማይ አካላት የሚገኙት በዓይን በማይታዩት ክበቦች ላይ ተጣብቀው ነው። ይህ የአርስቶትል አመለካከት በአብዛኞቹ የሳይንስ ሊቃውንት ዘንድ ለረጅም ዘመናት ተቀባይነት አግኝቶ ቆይቷል፤ ምክንያቱም አንድ አካል አንድ ነገር ላይ ካላረፈ ወይም ካልተጣበቀ ይወድቃል ከሚለው በወቅቱ ከነበረው መሠረታዊ እምነት ጋር ይጣጣም ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ይላል? የአምላክ ቃል ኢዮብ የተባለ አንድ ታማኝ ሰው ይሖዋን አስመልክቶ እንዲህ ማለቱን ይናገራል፦ “ምድርንም እንዲያው በባዶው ላይ አንጠለጠላት።” (ኢዮብ 26:7) እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ለአርስቶትል ፈጽሞ ሊዋጥለት እንደማይችል ምንም ጥርጥር የለውም።

በ17ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ማለትም ከኢዮብ ዘመን 3000 ዓመት በኋላም እንኳ አጽናፈ ዓለም በሆነ ነገር የተሞላ እንደሆነ የሚገልጸው ንድፈ ሐሳብ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፤ በእርግጥ በዚህ ወቅት የነበሩት ሰዎች ያምኑ የነበረው አጽናፈ ዓለም እንደ መስታወት ባሉ ክበቦች ሳይሆን ፈሳሽ በሆነ ነገር እንደተሞላ አድርገው ነው። ይሁንና የፊዚክስ ሊቅ የነበረው ሰር አይዛክ ኒውተን በዚሁ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ሐሳብ አቀረበ። የሰማይ አካላት እርስ በርሳቸው እንዲሳሳቡ የሚያደርጋቸው የስበት ኃይል መሆኑን ተናገረ። በመሆኑም ኒውተን ምድርም ሆነች ሌሎች የሰማይ አካላት ምንም ነገር በሌለው ሕዋ ላይ ማለትም በሰው ዓይን ሲታይ “ባዶ” በሚመስል ስፍራ ተንጠልጥለዋል ወደሚለው አመለካከት አንድ እርምጃ ቀረብ ብሎ ነበር።

ኒውተን የስበት ኃይልን አስመልክቶ ያቀረበው ንድፈ ሐሳብ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። የሳይንስ ሊቃውንት ከዋክብትና ሌሎች የሰማይ አካላት በሆነ ነገር ላይ ሳይቀመጡ ወይም ሳይጣበቁ እንዲሁ ተንጠልጥለዋል የሚለውን ሐሳብ ለመቀበል ከብዷቸው ነበር። ‘ግዙፏ ምድራችንም ሆነች ሌሎቹ የሰማይ አካላት እንዴት እንዲሁ በሕዋ ላይ ሊንጠለጠሉ ይችላሉ?’ የሚለው ጥያቄ ለብዙዎቹ እንቆቅልሽ ነበር። አንዳንዶች ይህ ሐሳብ ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ እንደ ሆነ አድርገው አስበው ነበር። ምክንያቱም ከአርስቶትል ዘመን አንስቶ የነበሩት አብዛኞቹ የሳይንስ ሊቃውንት ሕዋ በሆነ ነገር የተሞላ መሆን አለበት ብለው ያምኑ ነበር።

እርግጥ ነው፣ ምድር ከምሕዋሯ ዝንፍ ሳትል ፀሐይን እንድትዞር የሚያደርጋት በዓይን የማይታየው ነገር ምን እንደሆነ ኢዮብ የሚያውቀው ነገር የለም። ታዲያ ፕላኔታችን “እንዲያው በባዶው ላይ” ተንጠልጥላለች ብሎ እንዲናገር ያነሳሳው ምንድን ነው?

ከዚህም በላይ ምድርን ደግፎ የያዛት ምንም ነገር የለም የሚለው ሐሳብ ‘ታዲያ ምድርም ሆነች ሌሎቹ የሰማይ አካላት ቦታ ቦታቸውን ጠብቀው እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችላቸው ነገር ምንድን ነው?’ የሚል ሌላ ጥያቄ ያስነሳል። በአንድ ወቅት አምላክ ለኢዮብ የተናገረውን የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ልብ በል፦ “ፐልያዲስ የተባሉትን ከዋክብት በአንድነት ማሰር ትችላለህን? ኦርዮን የተባሉትንስ ከዋክብት የተያያዙበትን ገመድ መበጠስ ትችላለህን?” (ኢዮብ 38:31 የ1980 ትርጉም) ኢዮብ በሕይወት በኖረባቸው ረጅም ዓመታት ውስጥ ምሽት ላይ የሚወጡትንና ምንጊዜም ተመሳሳይ አቀማመጥ ያላቸውን እነዚህን ኅብረ ከዋክብት ይመለከት ነበር። እንደነዚህ ያሉ የከዋክብት ስብስቦች ጉልህ ለውጥ ሊታይባቸው የሚችለው በአሥር ሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ነው። ይሁንና እነዚህ ኅብረ ከዋክብት ከዓመት እስከ ዓመት አቀማመጣቸውን የማይቀይሩት ለምንድን ነው? እነዚህ ከዋክብትም ሆኑ ሌሎቹ የሰማይ አካላት ቦታቸውን እንዳይለቁ ጠፍሮ የያዛቸው ማሰሪያ ምንድን ነው? ኢዮብ ስለ እነዚህ ነገሮች ማሰቡ በአድናቆት ስሜት እንዲዋጥ አድርጎት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።

ከዋክብት በአጽናፈ ዓለም ውስጥ በሚገኙ ክበቦች ላይ የተጣበቁ ቢሆኑ ኖሮ እንዲህ ያለው ማሰሪያ አያስፈልግም ነበር። ሳይንቲስቶች የሰማይ አካላት በጨለማ በተዋጠው ሕዋ ውስጥ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት ሲንቀሳቀሱ እንዳይነጣጠሉ አንድ ላይ ያስተሳሰራቸው በዓይን የማይታይ “ገመድ” ወይም ማሰሪያ መኖሩን ያወቁት በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ነው። አይዛክ ኒውተንና ከእሱ በኋላ የኖረው አልበርት አንስታይን በዚህ መስክ የደረሱባቸው አዳዲስ ግኝቶች ዝነኛ አድርገዋቸዋል። እርግጥ ነው፣ አምላክ የሰማይ አካላት እርስ በርሳቸው እንዲተሳሰሩ ለማድረግ ስለሚጠቀምበት ኃይል ኢዮብ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ሆኖም በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ሐሳብ በጊዜ ሂደት ሲፈተሽ ምሑሩ አርስቶትል ካቀረበው ሐሳብ ይበልጥ ትክክለኛ ሆኖ ተገኝቷል። የሰማይ አካላት የሚመሩበትን ሕግ ካወጣው አካል በስተቀር እንዲህ ያለ ጥልቅ ማስተዋል ማን ሊኖረው ይችላል?

3. የሰማይ አካላት ጠፊ ነገሮች ናቸው ወይስ ዘላለማዊ?

አርስቶትል በሰማይ አካላትና በምድር መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ ያምን ነበር። እሱ እንደሚለው ከሆነ ምድር የምትለዋወጥ፣ የምትጠፋና እየመነመነች የምትሄድ ሲሆን በከዋክብት የተሞላው ሰማይ የተሠራበት ኢተር ብሎ የጠራው ንጥረ ነገር ግን ለውጥ የማያደርግና ዘላለማዊ ነው። አርስቶትል በሞዴሉ ላይ የገለጻቸው እንደ መስታወት ያሉ ክበቦችና በክበቦቹ ላይ የተጣበቁት የሰማይ አካላት ሊለዋወጡ፣ ሊያረጁ ወይም ከሕልውና ውጪ ሊሆኑ እንደማይችሉ ያምን ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስስ ስለዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላል? መዝሙር 102:25-27 እንዲህ ይላል፦ “አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፤ እነርሱም ወዲያ ይጣላሉ። አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።”

ከአርስቶትል ዘመን ሁለት ምዕተ ዓመታት ያህል አስቀድሞ የኖረው ይህ መዝሙራዊ ከዋክብት ዘላለማዊ እንደሆኑ፣ ምድር ግን ጠፊ ነገር እንደሆነች በመግለጽ በመካከላቸው ልዩነት እንዳለ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ሁለቱንም ማለትም ሰማይን እና ምድርን ከይሖዋ አምላክ ጋር አነጻጽሯቸዋል፤ እነዚህን ነገሮች የፈጠረው ኃያል መንፈሳዊ አካል የሆነው ይሖዋ ነው። * ይህ መዝሙር በምድር ላይ የሚገኝ ማንኛውም ነገር ሊጠፋ እንደሚችል ሁሉ ከዋክብትም ጠፊ ነገሮች እንደሆኑ ይጠቁማል። ታዲያ ዘመናዊው ሳይንስ ምን ነገር አረጋግጧል?

የሥነ ምድር ሳይንስ ምድር ልትጠፋ እንደምትችል ስለሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ የአርስቶትልን ሐሳብ ይደግፋል። እንዲያውም የምድር ዐለቶች አለማቋረጥ በመሸርሸራቸው ሳቢያ መንምነው እየጠፉ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በእሳተ ገሞራና በሌሎች ሥነ ምድራዊ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት አዳዲስ ዐለቶች እየተፈጠሩ ነው።

ይሁንና ስለ ከዋክብትስ ምን ማለት ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በተፈጥሯቸው ጠፊ ነገሮች ናቸው? ወይስ አርስቶትል እንዳስተማረው ዘላለማዊ? በ16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የአውሮፓ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች አንድ ኮከብ በአስደናቂ ሁኔታ ሲፈነዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመለከቱ ከዋክብት ዘላለማዊ ናቸው የሚለውን የአርስቶትልን አመለካከት መጠራጠር ጀመሩ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሳይንቲስቶች ከዋክብት እንዲህ ባለ ኃይለኛና ቅጽበታዊ ፍንዳታ አማካኝነት ወይም ቀስ በቀስ ተቃጥለው ሌላው ቀርቶ ሟሽሸው እንደሚጠፉ ማስተዋል ችለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች በከዋክብት ፍንዳታ ሳቢያ በተፈጠረ የጋዝ ዳመና ውስጥ አዳዲስ ከዋክብት ሲፈጠሩ ተመልክተዋል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ የሰማይ አካላትን ከሚያረጅና በሌላ ከሚተካ ልብስ ጋር ማመሳሰሉ ትክክል ነው። * በጥንት ዘመን የኖረው ይህ መዝሙራዊ ከዘመናዊ የሳይንስ ግኝት ጋር የሚስማማ ሐሳብ መጻፍ መቻሉ በጣም የሚያስገርም ነው!

ያም ሆኖ ‘ታዲያ ምድር ወይም በከዋክብት የተሞላው አጽናፈ ዓለም ሙሉ በሙሉ ከሕልውና ውጪ የሚሆንበት ወይም በሌላ የሚተካበት ጊዜ እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ምድርም ሆነ አጽናፈ ዓለም ለዘላለም እንደሚኖሩ ነው። (መዝ 104:5፤ 119:90) እንዲህ ሊሆን የቻለው ግን እነዚህ ፍጥረታት በራሳቸው ዘላለማዊ ስለሆኑ ሳይሆን እነሱን የፈጠረው አምላክ ለዘላለም እንደሚያኖራቸው ቃል ስለገባ ነው። (መዝ 148:4-6) እርግጥ አምላክ ይህን የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ አልተናገረም፤ ይሁንና የሁሉ ነገር ፈጣሪ የሆነው አምላክ አጽናፈ ዓለምን ለዘላለም ለማኖር የሚያስችል ኃይል ይኖረዋል ብሎ ማመን ምክንያታዊ አይሆንም? አንድ በሙያው የተካነ መሐንዲስ ለራሱና ለቤተሰቡ የገነባውን መኖሪያ ቤት በየጊዜው እንደሚያድስ ሁሉ ይሖዋም አጽናፈ ዓለም ለዘላለም እየታደሰ እንዲኖር ማድረግ አያቅተውም።

ግርማና ክብር ሊቀበል የሚገባው ማን ነው?

ሰማያት ከሚመሩባቸው ሕግጋት መካከል የተወሰኑትን ማየታችን የዚህ ጥያቄ መልስ ፍንትው ብሎ እንዲታየን አድርጓል። ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ከዋክብት በተንጣለለው ሕዋ ላይ ያስቀመጣቸው፣ በስበት ኃይል አማካኝነት ቦታቸውን እንዳይለቁ አስሮ የያዛቸውና ማለቂያ በሌለው ዑደት አማካኝነት ለዘላለም እየታደሱ እንዲኖሩ ያደረጋቸው ማን እንደሆነ መመርመራችን በአድናቆት ስሜት እንድንዋጥ አላደረገንም?

እንዲህ ያለ የአድናቆት ስሜት እንዲያድርብን የሚያደርገውን ምክንያት ኢሳይያስ 40:26 ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው።” ከዋክብት እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮች ባቀፈ ሠራዊት መመሰላቸው ተገቢ ነው። አንድ የጦር ሠራዊት አዛዥ ከሌለው ትርምስምሱ እንደሚወጣና ሥርዓት አልበኝነት እንደሚነግሥ ምንም ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም ፕላኔቶች፣ ከዋክብትና ጋላክሲዎች ይሖዋ የሰጣቸው ሕግ ባይኖራቸው ኖሮ ትርምስምሳቸው ይወጣል እንጂ መስመራቸውን ጠብቀው በሥርዓት አይንቀሳቀሱም ነበር። በተቃራኒው ደግሞ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ወታደሮችን ያቀፈ ሠራዊት የሚመራን አንድ አዛዥ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር፤ ይህ አዛዥ የሠራዊቱን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱን ወታደር ስም፣ የሚገኝበትን ቦታና ያለበትን ሁኔታ ጠንቅቆ የሚያውቅ ቢሆን በአድናቆት ስሜት እንድትዋጥ አያደርግህም?

ሰማያት ስለሚተዳደሩበት ሕግ መጠነኛ ግንዛቤ ማግኘታችን አዛዣቸው ወሰን የሌለው ጥበብና እውቀት እንዳለው እንድንረዳ ያስችለናል። እንዲህ ያሉ ሕግጋትን ሊያወጣ እንዲሁም ሳይንቲስቶች ስለ እነዚህ ሕግጋት ከመረዳታቸው በመቶ እንዲያውም በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ሰዎች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ትክክለኛ ነገር እንዲጽፉ ሊያደርግ የሚችል ከዚህ አዛዥ ሌላ ማን ሊኖር ይችላል? በመሆኑም ለይሖዋ ‘ግርማና ክብር’ የምንሰጥበት በቂ ምክንያት እንዳለን ምንም ጥርጥር የለውም።​—ራእይ 4:11

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.11 መጽሐፍ ቅዱስ ምድርን ክበብ ብሎ መጥራቱ የሚያስደንቅ ነው፤ ክበብ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ድቡልቡል ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። አርስቶትልና ሌሎች ጥንታዊ የግሪክ ሊቃውንት ምድር ድቡልቡል እንደሆነች ያስቡ ነበር፤ ይሁን እንጂ ምድር ድቡልቡል ናት የሚለው ሐሳብ በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላም እንኳ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ነበር።

^ አን.13 ይህ ዓይነቱ ዘይቤያዊ አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ተሠርቶበታል።​—ኢዮብ 9:8፤ መዝሙር 104:2፤ ኢሳይያስ 42:5፤ 44:24፤ 51:13፤ ዘካርያስ 12:1

^ አን.27 ይሖዋ ሁሉንም ነገሮች ወደ ሕልውና ለማምጣት መንፈሳዊ አካል የሆነውን አንድያ ልጁን “ዋና ሠራተኛ” አድርጎ በመጠቀሙ መዝሙራዊው የተናገረው ሐሳብ ለወልድም ሊሠራ ይችላል።​—ምሳሌ 8:30, 31፤ ቆላስይስ 1:15-17፤ ዕብራውያን 1:10

^ አን.29 በ19ኛው መቶ ዘመን የኖረው ዊልያም ቶምሰን (ሎርድ ኬልቪን በመባልም ይታወቃል) የተባለ ሳይንቲስት ማንኛውም ነገር በጊዜ ሂደት እየፈራረሰ የሚሄደው ለምን እንደሆነ የሚገልጸውን ሁለተኛውን የተርሞዳይናሚክስ ሕግ አገኘ። ይህን ሕግ ለማግኘት ከረዱት ነገሮች መካከል አንዱ በመዝሙር 102:25-27 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ በጥንቃቄ ማጥናቱ ነበር።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ሰው

 “አርስቶትል በጥንት ዘመን ከኖሩት ሁሉ ተወዳዳሪ የሌለው ፈላስፋና ሳይንቲስት ነበር።” ይህን ያለው ዘ 100​ኤ ራንኪንግ ኦቭ ዘ ሞስት ኢንፍሉኤንሸል ፐርሰንስ ኢን ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ ነው። በዘመኑ ካሉት ሰዎች ለየት ብሎ ለሚታየው ለዚህ ግለሰብ እንዲህ ያለ አስተያየት የተሰጠበትን ምክንያት መረዳት አዳጋች አይሆንም። አርስቶትል (ከ384 እስከ 322 ዓ.ዓ.) የዝነኛው ፈላስፋ የፕላቶ ተማሪ ነበር፤ በኋላ ላይ ደግሞ አርስቶትል ታላቁ እስክንድርን በልጅነቱ አስተምሮታል። የጥንት መዛግብት እንደሚያሳዩት ከሆነ አርስቶትል ካዘጋጃቸው በርካታ ጽሑፎች ውስጥ 170 የሚያህሉ መጻሕፍት የሚገኙበት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 47ቱ ዛሬም ድረስ አሉ። ሥነ ፈለክን፣ ባዮሎጂን፣ ኬሚስትሪን፣ ዙዎሎጂን፣ ፊዚክስን፣ ሥነ ምድርንና ሥነ ልቦናን የሚመለከቱ በርካታ ጽሑፎችን አዘጋጅቷል። ሕይወት ስላላቸው ነገሮች አንዳንድ ዝርዝር መረጃዎችን የጻፈ ሲሆን ሌሎች ሰዎች ስለ እነዚህ ነገሮች ጥናት አድርገው ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ የደረሱት ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ነበር። “አርስቶትል ከእሱ በኋላ የኖሩት ምዕራባውያን በሚከተሏቸው አስተሳሰቦች ላይ በሙሉ ይህ ነው የማይባል ተጽዕኖ አሳድሯል” በማለት ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ ይናገራል። አክሎም “ለአርስቶትል የተሰጠው አድናቆት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ በመካከለኛ ዘመን መገባደጃ ላይ ወደ መመለክ ደረጃ ደርሶ ነበር” ብሏል።

[የሥዕሉ ምንጭ]

Royal Astronomical Society / Photo Researchers, Inc.

From the book A General History for Colleges and High Schools, 1900

[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስበት ኃይል የሰማይ አካላት ቦታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ያደርጋል

[የሥዕሉ ምንጭ]

NASA and The Hubble Heritage Team (AURA/STScl)

[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፐልያዲስ የተባሉት ኅብረ ከዋክብት

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ከዋክብት በፍንዳታ አማካኝነት ሕልውናቸው ያከትማል

[የሥዕሉ ምንጭ]

ESA/Hubble

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳዲስ ከዋክብት የሚፈጠሩበት ቦታ

[የሥዕሉ ምንጭ]

J. Hester and P. Scowen (AZ State Univ.), NASA

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Peter Arnold, Inc./Alamy