በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ​—“ሰላም የሚሰጠው አምላክ”

ይሖዋ​—“ሰላም የሚሰጠው አምላክ”

ይሖዋ​—“ሰላም የሚሰጠው አምላክ”

“ሰላም የሚሰጠው አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።”​—ሮም 15:33

1, 2. በ⁠ዘፍጥረት ምዕራፍ 32 እና 33 ላይ ምን ውጥረት የሰፈነበት ሁኔታ ተገልጿል? ውጤቱስ ምን ነበር?

ታሪኩ የተፈጸመው ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ባለው በያቦቅ ሸለቆ አጠገብ በምትገኘው በጵኒኤል አቅራቢያ ነው። ዔሳው መንትያ ወንድሙ የሆነው ያዕቆብ ወደ አገሩ እየተመለሰ መሆኑን ሰምቷል። ዔሳው የብኩርና መብቱን ለወንድሙ ከሸጠለት 20 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ያዕቆብ ‘ወንድሜ ቂም ይዞ ይገድለኝ ይሆናል’ የሚል ስጋት አድሮበታል። ዔሳው ለበርካታ ዓመታት ተለይቶት ወደቆየው ወንድሙ 400 ሰዎችን አስከትሎ እየገሠገሠ ነው። ያዕቆብ፣ የዔሳው ሁኔታ ስላስፈራው ከ550 በላይ እንስሳትን በመላክ ስጦታ አዥጎደጎደለት። እያንዳንዱን መንጋ የሚነዱት የያዕቆብ አገልጋዮች፣ ዔሳው ጋ ሲደርሱ እንስሳቱ ከወንድሙ የተላኩ ስጦታዎች መሆናቸውን ይነግሩት ነበር።

2 በመጨረሻም ወንድማማቾቹ ተገናኙ! ያዕቆብ ራሱን እንደ ምንም አደፋፍሮ ወደ ዔሳው የሄደ ሲሆን በዚህ ወቅት ወንድሙን አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሰባት ጊዜ እጅ ነሳው። ያዕቆብ የወንድሙን ልብ ለማራራት ሲል ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን እርምጃ ወስዷል፤ ይኸውም ከዔሳው እጅ እንዲያስጥለው ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። ታዲያ ይሖዋ ጸሎቱን ሰምቶት ይሆን? አዎ፣ ሰምቶታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ዔሳው . . . ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጦ ሄዶ ዐቀፈው፤ በዐንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ሳመው።”​—ዘፍ. 32:11-20፤ 33:1-4

3. ስለ ያዕቆብና ስለ ዔሳው ከሚናገረው ዘገባ ምን እንማራለን?

3 ስለ ያዕቆብና ስለ ዔሳው የሚገልጸው ዘገባ፣ ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ያለንን ሰላም ሊያደፈርሱ የሚችሉ ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅት ለችግሩ እልባት ለማስገኘት ከልብ ተነሳስተን ጥረት ማድረግና አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ያስተምረናል። ያዕቆብ ከዔሳው ጋር ሰላም ለመፍጠር ጥረት አድርጓል፤ ይህን ያደረገው ግን ወንድሙን ስለበደለና ይቅርታ መጠየቅ ስለነበረበት አይደለም። እንዲያውም ብኩርናውን በምስር ወጥ በመለወጥ መብቱን ያቃለለው ዔሳው ነበር። (ዘፍ. 25:31-34፤ ዕብ. 12:16) ያም ቢሆን ያዕቆብ ከዔሳው ጋር ሲገናኝ ያደረገው ነገር ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ያለን ሰላም እንዳይደፈርስ ስንል የቻልነውን ሁሉ ጥረት ማድረግ እንዳለብን የሚጠቁም ነው። በተጨማሪም ይህ ዘገባ ሰላም ለመፍጠር ጸሎት የታከለበት ጥረት ስናደርግ እውነተኛው አምላክ እንደሚባርከን ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰላም ፈጣሪዎች እንድንሆን የሚረዱን ሌሎች በርካታ ምሳሌዎችን ይዟል።

ልንከተለው የሚገባ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ

4. አምላክ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ምን ዝግጅት አድርጓል?

4 ሰላምን በመፍጠር ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ “ሰላም የሚሰጠው አምላክ” የተባለው ይሖዋ ነው። (ሮም 15:33) ይሖዋ ከእሱ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ለማድረግ ሲል ምን ያህል መሥዋዕትነት እንደከፈለ አስብ። የአዳምና የሔዋን ዘሮች በመሆናችን ኃጢአት ስለወረስን ‘ኃጢአት የሚከፍለውን ደሞዝ’ መቀበል አለብን። (ሮም 6:23) ያም ሆኖ ይሖዋ በታላቅ ፍቅሩ ተነሳስቶ መዳን የምናገኝበትን መንገድ አዘጋጅቷል፤ ይህንንም ያደረገው በሰማይ የነበረው የሚወደው ልጁ ፍጹም ሰው ሆኖ በምድር ላይ እንዲወለድ በማድረግ ነው። ልጁም ታዛዥ ሆኖ ወደ ምድር የመጣ ከመሆኑም ሌላ በአምላክ ጠላቶች እጅ ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል። (ዮሐ. 10:17, 18) እውነተኛው አምላክ የሚወደውን ልጁን ከሞት ያስነሳው ሲሆን እሱም የፈሰሰው ደሙን ዋጋ ለአባቱ አቅርቧል፤ ይህ መሥዋዕት ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ከዘላለማዊ ሞት የሚዋጅ ቤዛ ሆኗል።​—ዕብራውያን 9:14, 24ን አንብብ።

5, 6. የፈሰሰው የኢየሱስ ደም በአምላክና ኃጢአተኛ በሆኑት የሰው ልጆች መካከል ያለውን የሻከረ ግንኙነት ለማደስ የሚያስችለው እንዴት ነው?

5 የአምላክ ልጅ ያቀረበው ቤዛዊ መሥዋዕት በአምላክና ኃጢአተኛ በሆኑት የሰው ልጆች መካከል ያለውን የሻከረ ግንኙነት ለማደስ የሚያስችለው እንዴት ነው? ኢሳይያስ 53:5 “በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን” ይላል። በዚህም ምክንያት ታዛዥ የሰው ልጆች የአምላክ ጠላቶች እንደሆኑ ተደርገው ከመቆጠር ይልቅ ከእሱ ጋር ሰላማዊ ወዳጅነት መመሥረት ይችላሉ። “[ኢየሱስ] ቤዛውን በመክፈል በደሙ አማካኝነት ነፃ እንድንወጣ ማለትም ለበደላችን ይቅርታ እንድናገኝ አድርጎናል።”​—ኤፌ. 1:7

6 መጽሐፍ ቅዱስ “ሙላት ሁሉ [በክርስቶስ] ውስጥ እንዲኖር አምላክ መልካም ሆኖ [አግኝቶታል]” ይላል። ይህ የሆነው ክርስቶስ የአምላክ ዓላማ እንዲፈጸም በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና ስለሚጫወት ነው። የይሖዋ ዓላማ ምንድን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ “ባፈሰሰው ደም አማካኝነት ሰላም በመፍጠር ሌሎቹን ነገሮች ሁሉ . . . ከራሱ ጋር እንደገና ለማስታረቅ” ነው። አምላክ ከራሱ ጋር የሚያስታርቃቸውና ‘ሌሎቹ ነገሮች ሁሉ’ የተባሉት ‘በምድርም ሆነ በሰማያት ያሉት ነገሮች’ ናቸው። እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው?​—ቆላስይስ 1:19, 20ን አንብብ።

7. ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የመሠረቱት ‘በሰማያት ያሉት ነገሮች’ እና ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ ምንድን ናቸው?

7 የቤዛው ዝግጅት፣ እንደ አምላክ ልጆች ተቆጥረው ‘ጻድቃን ተብለው የተጠሩት’ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ከአምላክ ጋር ሰላም’ እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል። (ሮም 5:1ን አንብብ።) እነዚህ ክርስቲያኖች ሰማያዊ ተስፋ ስላላቸው፣ ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው ስለሚገዙ’ እንዲሁም ለአምላካችን ካህናት ሆነው ስለሚያገለግሉ ‘በሰማያት ያሉት ነገሮች’ ተብለው ተጠርተዋል። (ራእይ 5:10) ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ የተባሉት ደግሞ ንስሐ የገቡ የሰው ልጆች ሲሆኑ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።​—መዝ. 37:29

8. ይሖዋ፣ የሰው ዘር ከእሱ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረው ሲል ምን ያህል መሥዋዕትነት እንደከፈለ ማሰላሰልህ ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል?

8 ጳውሎስ ይሖዋ ላደረገው ለዚህ ዝግጅት ልባዊ ምስጋናውን ሲገልጽ በኤፌሶን ለነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲህ ብሎ ጽፏል፦ “ምሕረቱ ብዙ የሆነው አምላክ . . . በበደላችን ሙታን በነበርንበት ጊዜም እንኳ ሕያዋን አድርጎ ከክርስቶስ ጋር አንድ አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው።” (ኤፌ. 2:4, 5) ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ይሁን በምድር ላይ መኖር አምላክ ላሳየን ምሕረትና ጸጋ ባለዕዳዎች ነን። ይሖዋ፣ የሰው ዘር ከእሱ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲል ምን ያህል መሥዋዕትነት እንደከፈለ ስናስብ ልባችን በአመስጋኝነት ስሜት ይሞላል። የጉባኤውን ሰላምና አንድነት የሚያደፈርሱ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን አምላክ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን ሰላም ፈጣሪዎች እንድንሆን ሊያነሳሳን አይገባም?

አብርሃምና ይስሐቅ ከተዉት ምሳሌ መማር

9, 10. በአብርሃምና በሎጥ እረኞች መካከል አለመግባባት በተፈጠረ ጊዜ አብርሃም ሰላም ፈጣሪ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነበር?

9 መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃምን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “‘አብርሃም በይሖዋ አመነ፤ እንደ ጽድቅም ተቆጠረለት’ . . . እሱም ‘የይሖዋ ወዳጅ’ ለመባል በቃ።” (ያዕ. 2:23) አብርሃም እምነት እንዳለው ካሳየባቸው መንገዶች አንዱ ሰላም ወዳድ መሆኑ ነው። ለምሳሌ የአብርሃም በጎች፣ ፍየሎችና ከብቶች እየበዙ ሲሄዱ በእሱ እረኞችና በወንድሙ ልጅ በሎጥ እረኞች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር። (ዘፍ. 12:5፤ 13:7) ቀላሉ መፍትሔ አብርሃምና ሎጥ መለያየታቸው ነበር። አብርሃም ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዴት ይፈታው ይሆን? አብርሃም ሎጥን በዕድሜ ስለሚበልጠውና ከአምላክ ጋር ልዩ ወዳጅነት ስላለው ብቻ የፈለገውን ከማድረግ ይልቅ እውነተኛ ሰላም ፈጣሪ መሆኑን አሳይቷል።

10 አብርሃም የወንድሙን ልጅ እንዲህ አለው፦ “እኛ ወንድማማቾች ነንና በአንተና በእኔ ወይም በእረኞቻችን መካከል ጠብ ሊኖር አይገባም።” አክሎም እንዲህ ብሎታል፦ “ይኸው እንደምታየው አገሩ ሰፊ ነው፤ ብንለያይ ይሻላል። አንተ ግራውን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተ ቀኙን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ግራ አመራለሁ።” ሎጥ እጅግ ለም የሆነውን ምድር መረጠ፤ አብርሃም ግን በዚህ ቂም አልያዘበትም። (ዘፍ. 13:8-11) ከጊዜ በኋላ አብርሃም፣ ወራሪዎች ሎጥን እንደማረኩት ሲሰማ የወንድሙን ልጅ ከጠላት እጅ ከማስጣል ወደኋላ አላለም።​—ዘፍ. 14:14-16

11. አብርሃም ፍልስጥኤማውያን ከሆኑት ጎረቤቶቹ ጋር በሰላም ለመኖር ምን አድርጓል?

11 አብርሃም በከነዓን ምድር በነበረበት ወቅት ፍልስጥኤማውያን ከሆኑ ጎረቤቶቹ ጋር በሰላም ለመኖር ምን እንዳደረገም እንመልከት። ፍልስጥኤማውያኑ፣ የአብርሃም አገልጋዮች በቤርሳቤህ የቆፈሩትን የውኃ ጉድጓድ ‘ነጥቀዋቸው’ ነበር። አራት ነገሥታትን አሸንፎ የወንድሙን ልጅ ከምርኮ ያስመለሰው አብርሃም ለዚህ ድርጊት ምን ምላሽ ይሰጥ ይሆን? አብርሃም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ግብግብ ፈጥሮ የውኃ ጉድጓዱን ለማስመለስ ከመሞከር ይልቅ ነገሩን በዝምታ ለማለፍ መረጠ። ከጊዜ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ንጉሥ የሰላም ቃል ኪዳን ለማድረግ ወደ አብርሃም መጣ። ንጉሡ፣ ልጆቹን በደግነት እንዲይዝለት አብርሃምን ቃል አስገባው፤ አብርሃም ስለተወሰደበት የውኃ ጉድጓድ ቅሬታውን የገለጸው ከዚህ በኋላ ነበር። ንጉሡ ጉዳዩን ሲሰማ በጣም ያዘነ ሲሆን የውኃ ጉድጓዱን ለአብርሃም መለሰለት። አብርሃምም በፍልስጥኤማውያን ምድር በሰላም በእንግድነት መኖሩን ቀጠለ።​—ዘፍ. 21:22-31, 34

12, 13. (ሀ) ይስሐቅ የአባቱን ምሳሌ የተከተለው እንዴት ነው? (ለ) ይስሐቅ ሰላም ወዳድ በመሆኑ ይሖዋ የባረከው እንዴት ነው?

12 የአብርሃም ልጅ ይስሐቅም እንደ አባቱ ሰላም ወዳድ መሆኑን አሳይቷል። ይህንንም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ከነበረው ግንኙነት መመልከት ይቻላል። ይስሐቅ በሚኖርበት ከብኤርላሃይሮኢ በስተሰሜን በሚገኘው ደረቅ በሆነው የኔጌብ ምድር ረሃብ በመከሰቱ ቤተሰቡን ይዞ በፍልስጥኤማውያን ክልል ውስጥ ወደሚገኘውና ይበልጥ ለም ወደሆነው የጌራራ ምድር ሄደ። በዚያም ይሖዋ የተትረፈረፈ ምርት በመስጠትና ከብቶቹ እንዲበዙለት በማድረግ ይስሐቅን ባረከው። በዚህም የተነሳ ፍልስጥኤማውያን ተመቀኙት። ፍልስጥኤማውያኑ፣ ይስሐቅም እንደ አባቱ ባለጠጋ እንዲሆን ስላልፈለጉ የአብርሃም አገልጋዮች የቆፈሯቸውን የውኃ ጉድጓዶች ደፈኗቸው። በመጨረሻም የፍልስጥኤማውያን ንጉሥ ይስሐቅን “አገራችንን ልቀቅልን” አለው። ሰላም ወዳድ የሆነው ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሄደ።​—ዘፍ. 24:62፤ 26:1, 12-17

13 ይስሐቅ ከአካባቢው ርቆ ከሰፈረ በኋላ እረኞቹ ሌላ የውኃ ጉድጓድ ቆፈሩ። በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እረኞች የውኃ ጉድጓዱ የእነሱ እንደሆነ ተናገሩ። ይስሐቅም ልክ እንደ አባቱ እንደ አብርሃም በውኃ ጉድጓዱ የተነሳ ግጭት ውስጥ አልገባም። ከዚህ ይልቅ ይስሐቅ አገልጋዮቹ ሌላ የውኃ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ አደረገ። ፍልስጥኤማውያኑ ግን አሁንም ጉድጓዱ የእነሱ እንደሆነ ገለጹ። ይስሐቅ ብዙ ጓዝ የነበረው ቢሆንም ሰላም ለመፍጠር ሲል ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ሰፈረ። እዚያም አገልጋዮቹ የውኃ ጉድጓድ የቆፈሩ ሲሆን ይስሐቅ ጉድጓዱን ርኆቦት ብሎ ሰየመው። ከጊዜ በኋላ፣ ይበልጥ ለም ወደሆነው ወደ ቤርሳቤህ ምድር ሄደ፤ በዚያም ይሖዋ የባረከው ከመሆኑም ሌላ “ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው።​—ዘፍ. 26:17-25

14. የፍልስጥኤማውያን ንጉሥ የሰላም ቃል ኪዳን ለማድረግ በመጣ ጊዜ ይስሐቅ ሰላም ፈጣሪ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

14 ይስሐቅ መብቱን ለማስከበር ሲል ከፍልስጥኤማውያን ጋር ውጊያ በመግጠም አገልጋዮቹ የቆፈሯቸውን የውኃ ጉድጓዶች በሙሉ መውሰድ ይችል እንደነበር ጥርጥር የለውም። ከጊዜ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ንጉሥና ባለሥልጣናቱ ወደ ቤርሳቤህ መምጣታቸውና ከእሱ ጋር የሰላም ቃል ኪዳን ለመግባት ጥያቄ ማቅረባቸው ይህን ያረጋግጣል፤ በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያኑ ይስሐቅን “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር መሆኑን በግልጽ ተረድተናል” አሉት። ይስሐቅ ውጊያ ከመግጠም ይልቅ ለሰላም ሲል የሚኖርበትን ቦታ በተደጋጋሚ ጊዜያት ለቅቆ ለመሄድ ፈቃደኛ ነበር። በዚህም ወቅት ቢሆን ይስሐቅ ሰላም ፈጣሪ መሆኑን አስመሥክሯል። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ይስሐቅም [እንግዶቹን] ድግስ ደግሶ፣ አበላቸው፤ አጠጣቸው። በማግስቱም በማለዳ ተነሥተው፣ በመካከላቸው መሐላ ፈጸሙ። ይስሐቅም አሰናበታቸው፤ እነርሱም በሰላም ሄዱ።”​—ዘፍ. 26:26-31

ያዕቆብ አብልጦ የሚወደው ልጁ ከተወው ምሳሌ መማር

15. የዮሴፍ ወንድሞች በሰላም ሊያናግሩት ያልቻሉት ለምን ነበር?

15 የይስሐቅ ልጅ የሆነው ያዕቆብ “ጭምት” ወይም ነቀፋ የሌለበት ሰው ነበር። (ዘፍ. 25:27) በመግቢያችን ላይ እንዳየነው ያዕቆብ ከወንድሙ ከዔሳው ጋር ሰላም ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ያዕቆብ፣ ሰላም ወዳድ የሆነው አባቱ ይስሐቅ ከተወው ምሳሌ እንደተጠቀመ ምንም ጥርጥር የለውም። ስለ ያዕቆብ ልጆችስ ምን ማለት ይቻላል? ያዕቆብ ከ12 ወንዶች ልጆቹ መካከል አብልጦ የሚወደው ዮሴፍን ነበር። ዮሴፍ ለአባቱ ከልብ የሚያስብ ታዛዥና ሰው አክባሪ ልጅ ነበር። (ዘፍ. 37:2, 14) ይሁንና የዮሴፍ ታላላቅ ወንድሞች በጣም ይቀኑበት ስለነበር በሰላም ሊያናግሩት አልቻሉም። በመሆኑም ዮሴፍን ለባርነት በመሸጥ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት የፈጸሙ ከመሆኑም ሌላ አውሬ እንደበላው አድርገው በመናገር አባታቸውን አታለሉት።​—ዘፍ. 37:4, 28, 31-33

16, 17. ዮሴፍ ከወንድሞቹ ጋር በተያያዘ ሰላም ወዳድ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

16 ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ነበረ። ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ከፈርዖን ቀጥሎ ያለውን ሥልጣን በመያዝ የግብፅ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነ። የዮሴፍ ወንድሞች ታላቅ ረሃብ ተከስቶ ወደ ግብፅ በሄዱበት ጊዜ ዮሴፍ የባለሥልጣን ልብሱን ለብሶ ሲያዩት ሊለዩት አልቻሉም። (ዘፍ. 42:5-7) በዚህ ጊዜ ዮሴፍ፣ ወንድሞቹ በእሱና በአባቱ ላይ ለፈጸሙት የጭካኔ ድርጊት አጸፋውን መመለስ ይችል ነበር! እሱ ግን ወንድሞቹን ከመበቀል ይልቅ ከእነሱ ጋር ሰላም ፈጥሯል። ዮሴፍ፣ ወንድሞቹ በድርጊታቸው መጸጸታቸውን በግልጽ ሲመለከት ማንነቱን የገለጠላቸው ሲሆን እንዲህ አላቸው፦ “አሁንም [እኔን] በመሸጣችሁ አትቈጩ፤ በራሳችሁም ዐትዘኑ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወት ለማዳን ሲል ከእናንተ አስቀድሞ እኔን ወደዚህ ልኮኛል።” ከዚያም ወንድሞቹን አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ።​—ዘፍ. 45:1, 5, 15

17 የዮሴፍ ወንድሞች አባታቸው ያዕቆብ ከሞተ በኋላ ዮሴፍ እንዳይበቀላቸው ስጋት አድሮባቸው ነበር። ይህን ስጋታቸውን ሲነግሩት ዮሴፍ “አለቀሰ።” ከዚያም “አትፍሩ፤ ለእናንተና ለልጆቻችሁ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አደርግላችኋለሁ” አላቸው። ሰላም ወዳድ የሆነው ዮሴፍ ወንድሞቹን ያጽናናቸው ከመሆኑም በላይ “በደግ ቃል አናገራቸው።”​—ዘፍ. 50:15-21

“ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል”

18, 19. (ሀ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የተገለጹትን ሰላም ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ምሳሌ በመመርመርህ ምን ጥቅም አግኝተሃል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ምን እንመለከታለን?

18 ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።” (ሮም 15:4) ከሁሉ የላቀውን የይሖዋን ምሳሌ ብቻ ሳይሆን በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሰፈረውን የአብርሃምን፣ የይስሐቅን፣ የያዕቆብንና የዮሴፍን ምሳሌ በመመርመራችን ምን ጥቅም አግኝተናል?

19 ይሖዋ በእሱና ኃጢአተኛ በሆኑት የሰው ልጆች መካከል ያለውን የሻከረ ግንኙነት ለማደስ ሲል በወሰደው እርምጃ ላይ ማሰላሰላችን እኛም ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ሰላማዊ ለመሆን የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ አያነሳሳንም? የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብና የዮሴፍ ምሳሌ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ዘገባዎች ይሖዋ ሰላም ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን እንደሚባርክ ይጠቁማሉ። ጳውሎስ ይሖዋን “ሰላም የሚሰጠው አምላክ” ብሎ መጥራቱ ምንም አያስገርምም። (ሮም 15:33⁠ን እና 16:20ን አንብብ።) በሰላም ለመኖር ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ጳውሎስ ያጎላው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ሰላም ፈጣሪዎች መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• ያዕቆብ ከዔሳው ጋር ሊገናኝ ሲል ሰላም ለመፍጠር ጥረት ያደረገው በምን መንገድ ነበር?

• ይሖዋ የሰው ዘር ከእሱ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲል የወሰደው እርምጃ ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል?

• አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ዮሴፍ ሰላም ፈጣሪ በመሆን ረገድ ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ያዕቆብ ከዔሳው ጋር ሰላም ለመፍጠር ሲል የወሰደው ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ምን ነበር?