በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእሳት ተራራ ጥላ ሥር መኖር

በእሳት ተራራ ጥላ ሥር መኖር

ከኮንጎ (ኪንሻሳ) የተላከ ደብዳቤ

በእሳት ተራራ ጥላ ሥር መኖር

ፀሐይዋ በጎማ ከተማ ላይ ብርሃኗን ስትፈነጥቅ ሰማዩ በሮዝና በብርቱካን ቀለም ያሸበርቃል። ሲያዩት የሚያስደምመው የኒራጎንጎ ተራራ በየቀኑ ከፊታችን ጉብ እንዳለ ነው፤ ኒራጎንጎ በዓለማችን ላይ በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዱ የሚችሉ እሳተ ገሞራዎች ከሚገኝባቸው ተራራዎች አንዱ ነው። ክፍት ከሆነው አፉ ምንጊዜም ጭስ እየተትጎለጎለ ይወጣል። ቀኑ ሲጨልም፣ ጭሱ የቀለጠውን ድንጋይ ቀለም በማንጸባረቅ ቀይ መልክ ይይዛል።

ተራራው በስዋሂሊ ቋንቋ ሙሊማ ያ ሞቶ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጉሙም የእሳት ተራራ ማለት ነው። በኒራጎንጎ ተራራ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ከፍተኛ ፍንዳታ የተከሰተው በ2002 ነበር። በዚያን ወቅት በጎማ ከተማ የሚኖሩ በርካታ ጎረቤቶቻችንና ጓደኞቻችን ሀብት ንብረታቸውን በሙሉ አጥተዋል። እኔና ባለቤቴ በምንሰብክባቸው በአቅራቢያችን በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የምንጓዘው በእሳተ ገሞራ ቀልጦ በወጣ ድንጋይ በተሸፈነ አባጣ ጎርባጣ መንገድ ላይ ነው፤ በዚህ ጊዜ ‘በጨረቃ ላይ መራመድስ ምን ይመስል ይሆን?’ የሚል ሐሳብ ወደ አእምሮዬ ይመጣል። የአካባቢው ነዋሪዎች እሳተ ገሞራው ካስገኘው ጠንካራ ድንጋይ ፍጹም ተቃራኒ ናቸው። የምንሰብክላቸውን ምሥራች የሚቀበል ገር ልብ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ግልጽና ደስተኛ ሰዎች ናቸው። ይህ ሁኔታ በእሳት ተራራ ጥላ ሥር ማገልገልን አስደሳች ያደርገዋል።

ቅዳሜ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ በውስጤ ደስ የሚል ስሜት ተፈጥሮ ነበር። እኔና ባለቤቴ ሊጠይቁን ከመጡት ጓደኞቻችንና እንደ እኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ከሆኑት ሚስዮናውያን ጋር ከከተማዋ በስተምዕራብ ጫፍ ላይ በሚገኘው፣ በሙጉንጋ የስደተኞች ካምፕ ቀኑን ሙሉ ስንሰብክ እንውላለን። አብዛኞቹ የካምፑ ነዋሪዎች፣ በሚኖሩበት ከተማ ላይ ከተሰነዘረው ከባድ ጥቃት ሸሽተው የመጡ ናቸው።

በትልቁ መኪናችን ላይ በፈረንሳይኛ፣ በኪስዋሂሊና በኪንያርዋንዳ የተዘጋጁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ጫንን። ከዚያም ጉዞ ጀመርን። ሴክ ተብሎ በሚጠራው መንገድ ላይ እየተንገጫገጭን በመጓዝ ላይ ሳለን በከተማዋ ውስጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሞቅ ብሎ ተመለከትን። ወጣት ወንዶች ቹኩዱስ (በእጅ የሚሠራ፣ ዕቃ ለማጓጓዝ የሚያገለግል ጎማ ያለው የእንጨት ተሽከርካሪ) ላይ ብዙ ዕቃ ጭነው እየገፉ ይጓዛሉ። ደማቅ ቀለም ያለው ቀሚስ የለበሱ ሴቶች ጭንቅላታቸው ላይ ትልቅ ዕቃ ተሸክመው የመንገዱን ዳር ዳር ይዘው ሲሄዱ ማየት ትኩረት ይስባል። ታክሲዎች ሰዎችን ወደ ሥራና ወደ ገበያ ቦታ ለማድረስ ያለ ፋታ ይነጉዳሉ። ጥቁር ቡኒ ቀለም የተቀቡና ለማሳመር ተብሎ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ከእንጨት የተሠሩ ቤቶች ራቅ ራቅ ብለው አካባቢው ላይ ይታያሉ።

በንዶሾ ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ደረስን፤ በዚያም በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ወደ ካምፑ አብረውን ለመሄድ ከመጡ የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘን። በመካከላቸው ወጣቶች፣ መበለቶች፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች እንዲሁም የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ሰዎች መኖራቸውን ስመለከት ስሜቴ በጥልቅ ተነካ። አብዛኞቹ ይህ ነው የማይባል መከራ ያሳለፉ ናቸው፤ ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል በመምረጣቸው ሕይወታቸው ተሻሽሏል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ በልባቸው ውስጥ ይንቦገቦጋል፤ ይህንንም ለሌሎች ለማካፈል ጓጉተዋል። ለምናገኛቸው ሰዎች የምናነብላቸውን የሚያበረታቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በተመለከተ አንዳንድ ሐሳቦች እንድናገኝ አጭር ስብሰባ ካደረግን በኋላ 130 የምንሆን ክርስቲያኖች ቆመው ወደነበሩት አምስት ሚኒባሶችና አንድ ትልቅ መኪና አመራን።

ከ30 ደቂቃ ገደማ በኋላ ካምፑ ደረስን። በእሳተ ገሞራ ቀልጦ የወጣው ድንጋይ በሸፈነው ሜዳ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትንንሽ ነጭ ድንኳኖች ተተክለዋል። በካምፑ መሃል መደዳውን የተደረደሩ ንጹሕ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶችና ነዋሪዎቹ በጋራ የሚጠቀሙባቸው ልብስ ማጠቢያ ቦታዎች አሉ። ልብስ የሚያጥቡ፣ ምግብ የሚያበስሉ፣ ባቄላ የሚፈለፍሉ እንዲሁም የድንኳናቸውን ደጃፍ የሚጠርጉ ሰዎች በየቦታው ይታያሉ።

የካምፑ የተወሰነ ክፍል ተቆጣጣሪ ከሆኑት ከፓፓ ዣክ ጋር ተገናኘን። እኚህ ሰው በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ልጆቻቸውን ማሳደግ ያለባቸው እንዴት እንደሆነ ያሳስባቸው ነበር። ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ስንሰጣቸው በደስታ የፈነደቁ ከመሆኑም ሌላ መጽሐፉን እንደሚያነቡትና በአካባቢው ያሉ ሰዎችን በትንሽ በትንሽ ቡድን እያሰባሰቡ ያገኙትን እውቀት እንደሚያካፍሏቸው ነገሩን።

ትንሽ አለፍ እንዳልን ማማ ቢያትሪስ ከሚባሉ ሴት ጋር ተገናኘን። እሳቸውም አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ጠየቁን። ሴትየዋ አምላክ እየቀጣቸው እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። ባለቤታቸው በጦርነቱ ወቅት ተገድለዋል፤ ካምፑ ውስጥ የምትኖረው ሴት ልጃቸው ሕፃን ልጇን ለማሳደግ የምትፍጨረጨር ነጠላ ወላጅ ነች፤ ወንዱ ልጃቸው ደግሞ ከተወሰኑ ወራት በፊት ታፍኖ ተወስዷል። የት እንደደረሰ እንኳ የሚያውቁት ነገር የለም።

ማማ ቢያትሪስ ያሳለፉት አሳዛኝ ታሪክ ኢዮብ ያ ሁሉ መርዶ ሲነገረው ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል እንዳስብ አደረገኝ። ለመከራ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ነገርናቸው፤ እንዲሁም የደረሰባቸው መከራ ከአምላክ የመጣ ቅጣት አለመሆኑን አስረዳናቸው። (ኢዮብ 34:10-12፤ ያዕቆብ 1:14, 15) በተጨማሪም አምላክ በቅርቡ በመንግሥቱ አማካኝነት በምድር ላይ የሚያመጣቸውን ለውጦች ገለጽንላቸው። በዚህ ጊዜ ፊታቸው በደስታ ፈካ፤ ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናታቸውንና አምላክ እንዲረዳቸው መጸለያቸውን ለመቀጠል መወሰናቸውን ነገሩን።

በቡድኑ ውስጥ የነበረው ሰው ሁሉ በዕለቱ ባከናወነው ሥራ የተደሰተ ከመሆኑም ሌላ ሁላችንም ላገኘናቸው ሰዎች ተስፋና ማበረታቻ ለመስጠት ባደረግነው ጥረት የይሖዋ ድጋፍ እንዳልተለየን ተሰማን። ካምፑን ለቅቀን ስንወጣ በዚያ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች የያዟቸውን ትራክቶች፣ መጽሔቶችና መጻሕፍት እያውለበለቡ ተሰናበቱን።

ወደ ቤት ለመመለስ ያደረግነው ጉዞ ማሰላሰል የምንችልበት አጋጣሚ ሰጥቶናል። ይህን የመሰለ ልዩ ቀን በማሳለፌ ልቤ በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልቷል። ፓፓ ዣክ ላይ የታየውን የአድናቆት መንፈስ፣ ማማ ቢያትሪስ ዓይኖች ላይ ይነበብ የነበረውን የእፎይታ ስሜት እንዲሁም በፈገግታ ብቻ ሐሳባቸውን የገለጹልኝ አንዲት አረጋዊ ሴት እንዴት አጥብቀው እንደጨበጡኝ አልረሳውም። ማስተዋል የታከለባቸው ጥያቄዎችን ያነሱትና ከዕድሜያቸው በላይ በሳል መሆናቸውን ያሳዩት ወጣቶች ወደ አእምሮዬ መጡ። ለመገመት እንኳ የሚከብድ መከራ ቢያሳልፉም ፈገግታና ሳቅ ያልተለያቸው እነዚህ ሰዎች ባላቸው ውስጣዊ ጥንካሬ በአድናቆት ተዋጥኩ።

በዚህ አገር፣ ሌሎች በርካታ ግለሰቦች መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች እፎይታ ለማስገኘት ልባዊ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ። በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ሰዎች ለችግሮቻቸው ሥር ነቀል መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ ማሳወቅ መቻል ትልቅ መብት ነው። በዓለም ላይ ከዚህ በኋላ በማይደገመውና ሰዎች መንፈሳዊ እፎይታ እንዲያገኙ ለማድረግ በሚካሄደው ታላቅ ሥራ መሳተፍ በመቻሌ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል።