በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቀረጥ መክፈል ይኖርብሃል?

ቀረጥ መክፈል ይኖርብሃል?

ቀረጥ መክፈል ይኖርብሃል?

ብዙዎች ቀረጥ መክፈል አያስደስታቸውም። በርካታ ሰዎች የሚከፍሉት ቀረጥ በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንደማይውል፣ ወደ ግለሰቦች ኪስ እንደሚገባ አሊያም እንደሚጭበረበር ይሰማቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ ቀረጥ ከመክፈል የሚቆጠቡት ገንዘቡ ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ ከሥነ ምግባር አኳያ ሲታይ አግባብ እንዳልሆነ ስለሚሰማቸው ነው። በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኝ አንድ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ቀረጥ ላለመክፈል የወሰኑት ለምን እንደሆነ ሲገልጹ “ልጆቻችን ለሚገደሉበት ጥይት ገንዘብ አንከፍልም” በማለት ተናግረዋል።

እንዲህ ዓይነት አመለካከቶች ያልተለመዱ ወይም አዲስ አይደሉም። የሂንዱ መሪ የነበሩት ሞሃንደስ ጋንዲ ሕሊናቸው ቀረጥ እንዳይከፍሉ የሚከለክላቸው ለምን እንደሆነ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “በወታደራዊ መንገድ የተዋቀረን መንግሥት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚደግፍ ሰው በኃጢአቱ ተካፋይ ይሆናል። በዕድሜ የገፋም ሆነ ወጣት፣ እያንዳንዱ ሰው ቀረጥ በመክፈል የመንግሥት ሕልውና እንዲቀጥል አስተዋጽኦ ስለሚያበረክት የኃጢአቱ ተባባሪ ይሆናል።”

በተመሳሳይም በ19ኛው መቶ ዘመን የኖረው ሄንሪ ዴቪድ ቶሮ የተባለ ፈላስፋ፣ ጦርነትን ለመደገፍ የሚውለውን ቀረጥ ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆነው ከሥነ ምግባር አኳያ የራሱ የሆነ አቋም ስላለው እንደሆነ ገልጿል። እንዲህ ሲል ጠይቋል፦ “አንድ ዜጋ ሕሊናው የሚነግረውን ሰምቶ ሊያደርገው የሚገባውን ውሳኔ አንድ ሕግ አውጪ እንዲወስንለት መፍቀድ ይኖርበታል? ታዲያ እያንዳንዱ ሰው ሕሊና ያለው መሆኑ ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው?”

ይህ ጉዳይ ክርስቲያኖችን ያሳስባቸዋል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች በሁሉም ረገድ ንጹሕ ሕሊና መያዝ እንዳለባቸው በግልጽ ያስተምራል። (2 ጢሞቴዎስ 1:3) በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ መንግሥታት ቀረጥ የመሰብሰብ ሥልጣን እንዳላቸውም ይናገራል። እንዲህ ይላል፦ “ነፍስ ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት [ለሰብዓዊ መንግሥታት] ይገዛ፤ ምክንያቱም ሥልጣን ሁሉ የሚገኘው ከአምላክ ነው፤ ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ሥልጣናቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው። ስለዚህ ቁጣውን በመፍራት ብቻ ሳይሆን ስለ ሕሊናችሁ ስትሉም መገዛታችሁ አስፈላጊ ነው። ቀረጥ የምትከፍሉትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም እነሱ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚያከናውኑ የአምላክ አገልጋዮች ናቸው፤ የዘወትር ተግባራቸውም ይኸው ነው። ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ፤ ቀረጥ ለሚጠይቅ ቀረጥ . . . ስጡ።”​—ሮም 13:1, 5-7

በመሆኑም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች መንግሥት ከሚሰበስበው ቀረጥ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለወታደራዊ ዓላማ የሚውል ቢሆንም ቀረጥ በወቅቱ በመክፈል ይታወቁ ነበር። በዛሬው ጊዜ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮችም እንዲሁ ያደርጋሉ። * ታዲያ እርስ በርሱ የሚጋጭ የሚመስለውን ይህን ጉዳይ ማስታረቅ የሚቻለው እንዴት ነው? አንድ ክርስቲያን ቀረጥ የመክፈል ጉዳይ ሲነሳ ሕሊናውን ቸል ማለት ይኖርበታል?

ቀረጥና ሕሊና

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እንዲከፍሉ ከተጣለባቸው ቀረጥ ውስጥ የተወሰነው ገንዘብ ለውትድርና ዓላማ እንደሚውል የታወቀ ነበር። ጋንዲ እና ቶሮ ቀረጥ ከመክፈል እንዲቆጠቡ ያደረጋቸው ከሕሊና ጋር ተያያዥነት ያለው ይህ ወሳኝ ጉዳይ ነበር።

ክርስቲያኖች በ⁠ሮም ምዕራፍ 13 ላይ ያለውን መመሪያ የታዘዙት ከቅጣት ለማምለጥ ብለው ብቻ ሳይሆን ‘ስለ ሕሊናቸው ሲሉም’ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። (ሮም 13:5) አዎ፣ አንድ ክርስቲያን የሚከፍለው ቀረጥ እሱ በግሉ ለማይደግፈው ዓላማ የሚውል ቢሆንም እንኳ ቀረጥ እንዲከፍል ሕሊናው ያስገድደዋል። እርስ በርሱ የሚጣረስ የሚመስለውን ይህን ሐሳብ ለመረዳት ስለ ሕሊናችን ማለትም ተግባራችን ትክክል ወይም ስህተት መሆን አለመሆኑን ስለሚነግረን ውስጣዊ ድምፅ አንድ ሐቅ መገንዘብ አለብን።

ቶሮ እንደተረዳው ሁሉም ሰው በውስጡ እንዲህ ያለ ድምፅ አለው፤ ሆኖም ይህ ድምፅ ሁልጊዜ እምነት የሚጣልበት ይሆናል ማለት አይደለም። አምላክን ማስደሰት እንድንችል ሕሊናችን ከእሱ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር መስማማት ይኖርበታል። የአምላክ ሐሳብ ከእኛ ሐሳብ እጅግ የላቀ በመሆኑ አስተሳሰባችንን ወይም አመለካከታችንን ከእሱ አስተሳሰብና አመለካከት ጋር ለማስማማት ዘወትር ማስተካከያ ማድረግ ይኖርብናል። (መዝሙር 19:7) እንግዲያው አምላክ ስለ ሰብዓዊ መንግሥታት ያለውን አመለካከት ለመረዳት ጥረት ማድረግ አለብን። ታዲያ የአምላክ አመለካከት ምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሰብዓዊ መንግሥታትን “ሕዝባዊ አገልግሎት የሚያከናውኑ የአምላክ አገልጋዮች” በማለት እንደጠራቸው እንመለከታለን። (ሮም 13:6) ይህ ምን ማለት ነው? ባለሥልጣናት ሥርዓት እንዲከበር ያደርጋሉ እንዲሁም ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ አገልግሎት ይሰጣሉ ማለት ነው። ምግባረ ብልሹ ናቸው የሚባሉ መንግሥታትም እንኳ አብዛኛውን ጊዜ እንደ ፖስታ አገልግሎት፣ ትምህርትና እሳት አደጋ መከላከልን የመሳሰሉ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ከመሆኑም ሌላ ሕግ እንዲከበር ያደርጋሉ። አምላክ እነዚህ ሰብዓዊ ባለሥልጣናት ያሉባቸውን ጉድለቶች ጠንቅቆ የሚያውቅ ቢሆንም ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ ፈቅዶላቸዋል፤ እንዲሁም ለአምላክ ዝግጅት ካለን አክብሮት የተነሳ ይኸውም እንዲህ ያሉ መንግሥታት የሰው ልጆችን እንዲገዙ ስለፈቀደ ቀረጥ እንድንከፍል አዝዞናል።

ይሁን እንጂ አምላክ ሰብዓዊ መንግሥታት እንዲገዙ የፈቀደው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው። ሁሉንም መንግሥታት በሰማይ በሚገኘው መንግሥቱ የመተካት እንዲሁም ሰብዓዊ አገዛዝ ባለፉት ዘመናት ሁሉ በሰው ልጆች ላይ ያስከተለውን ጉዳት በሙሉ የማስተካከል ዓላማ አለው። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን አምላክ፣ ክርስቲያኖች ቀረጥ አንከፍልም በማለትም ሆነ በሌላ መንገድ በሕዝባዊ ዓመፅ እንዲካፈሉ ፈቃድ አልሰጣቸውም።

የምትከፍለው ቀረጥ ለጦርነት ዓላማ እንደሚውል እያወቅህ ገንዘብ መስጠትህ ልክ እንደ ጋንዲ ኃጢአት እንደሆነ የሚሰማህ ከሆነስ? ከፍ ወዳለ ቦታ መውጣታችን አንድን አካባቢ በተሻለ ሁኔታ ለማየት እንደሚያስችለን ሁሉ፣ የአምላክ አስተሳሰብ ከእኛ አስተሳሰብ ምን ያህል የላቀ እንደሆነ በማሰላሰል አመለካከታችንን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ለማስማማት አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ እንችላለን። አምላክ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል፦ “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው።”​—ኢሳይያስ 55:8, 9

ሥልጣናቸው ገደብ የለሽ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ቀረጥ ስለ መክፈል የሚያስተምረው ትምህርት ሰብዓዊ መንግሥታት በተገዢዎቻቸው ላይ ገደብ የለሽ ሥልጣን እንዳላቸው የሚያሳይ አይደለም። ኢየሱስ፣ አምላክ ለእነዚህ መንግሥታት የሰጣቸው ሥልጣን ገደብ እንዳለው አስተምሯል። ኢየሱስ በዚያን ጊዜ ይገዛ ለነበረው ለሮም መንግሥት ቀረጥ መክፈል ከአምላክ አመለካከት አንጻር ተገቢ መሆን አለመሆኑን በተጠየቀ ጊዜ “የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ” የሚል ትልቅ ትርጉም ያዘለ መልስ ሰጥቷል።​—ማርቆስ 12:13-17

‘በቄሳር’ የተመሰሉት መንግሥታት ሳንቲሞችን ያዘጋጃሉ እንዲሁም የብር ኖቶችን ያትማሉ፤ በተጨማሪም ለገንዘቡ ዋጋ ይተምኑለታል። በመሆኑም በአምላክ አመለካከት እነዚህ መንግሥታት፣ ሰዎች ቀረጥ በመክፈል ይህን ገንዘብ እንዲመልሱላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው። ያም ሆኖ “የአምላክ የሆነው” ነገር ማለትም ሕይወታችንና የምናቀርበው አምልኮ እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት ያለው አንድም ሰብዓዊ ተቋም ሊኖር እንደማይችል ኢየሱስ ገልጿል። ሰብዓዊ ሕጎች ወይም ደንቦች ከአምላክ ሕጎች ጋር በሚጋጩበት ጊዜ ክርስቲያኖች ‘ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያቸው አድርገው ይታዘዛሉ።’​—የሐዋርያት ሥራ 5:29

በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች ከሚከፍሉት ቀረጥ መካከል የተወሰነው ለምን ዓላማ እንደሚውል ማወቃቸው ይረብሻቸው ይሆናል፤ ያም ሆኖ መንግሥታትን በመቃወም ወይም ቀረጥ ከመክፈል በመቆጠብ መንግሥት በሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ ጣልቃ ለመግባትም ሆነ ተጽዕኖ ለማሳደር አይሞክሩም። ይህ ዓይነቱ አድራጎት፣ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ላለው ችግር መፍትሔ የሚያመጣው አምላክ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እንደማናምን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ክርስቲያኖች “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” ብሎ በተናገረው በኢየሱስ አገዛዝ አማካኝነት አምላክ በሰው ልጆች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ በትዕግሥት ይጠባበቃሉ።​—ዮሐንስ 18:36

የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት መከተል የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

መጽሐፍ ቅዱስ ቀረጥ መክፈልን በተመለከተ የሚያስተምረውን ትምህርት በመከተል በርካታ ጥቅሞችን ማግኘት ትችላለህ። ሕግ የሚተላለፉ ሰዎች ከሚደርስባቸው ቅጣት ማምለጥ የምትችል ከመሆኑም ሌላ ‘እያዛለሁ’ ከሚለው ስጋት ትገላገላለህ። (ሮም 13:3-5) ከሁሉም በላይ ደግሞ በአምላክ ዘንድ ንጹሕ ሕሊና የሚኖርህ ሲሆን ሕግ አክባሪ በመሆንህ ለእሱ ክብር ታመጣለህ። ቀረጥ ከማይከፍሉ ወይም ከሚያጭበረብሩ ሰዎች አንጻር የተወሰነ ገንዘብ የምታጣ ቢሆንም አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚንከባከባቸው በገባው ተስፋ ላይ እምነት ማሳደር ትችላለህ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የሆነው ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም።”​—መዝሙር 37:25

በመጨረሻም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ቀረጥ እንድትከፍል የሚሰጥህን ትእዛዝ መረዳትህና ተግባራዊ ማድረግህ የአእምሮ ሰላም ያስገኝልሃል። ለቤት ኪራይ የከፈልከውን ገንዘብ አከራዩ ጥቅም ላይ ያዋለበትን መንገድ በተመለከተ አንተ በሕግ እንደማትጠየቅ ሁሉ አንተ በከፈልከው ቀረጥ መንግሥት ለሚያደርገው ነገር አምላክ ተጠያቂ አያደርግህም። ስቴልቪዮ የተባለ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከመማሩ በፊት ለበርካታ ዓመታት በደቡብ አውሮፓ ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ሲታገል ቆይቶ ነበር። ያደርግ የነበረውን ጥረት ለምን እንደተወ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሰው በዓለም ላይ ፍትሕ፣ ሰላምና የወንድማማች አንድነት ማምጣት እንደማይችል አምኜ መቀበል ነበረብኝ። በዓይነቱ የተለየና የተሻለ ኅብረተሰብ እንዲመጣ ማድረግ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።”

እንደ ስቴልቪዮ ሁሉ አንተም በታማኝነት ‘የአምላክ የሆነውን ነገር ለአምላክ መልሰህ’ የምትሰጥ ከሆነ እንዲህ ያለ ተስፋ ይኖርሃል። አምላክ በመላው ምድር ላይ ጽድቅ የሰፈነበት አገዛዝ በማምጣት የሰው ልጆች አገዛዝ ያስከተለውን ጉዳት ሲሽር እንዲሁም በምድር ላይ የሚታየውን ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲያስወግድ የማየት አጋጣሚ ታገኛለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 የይሖዋ ምሥክሮች ቀረጥ በመክፈል ረገድ ምን ስም እንዳተረፉ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የኅዳር 1, 2002 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 12 አንቀጽ 15⁠ን እና የግንቦት 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16 አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የአምላክ ሐሳብ ከእኛ ሐሳብ እጅግ የላቀ በመሆኑ አመለካከታችንን ከእሱ አመለካከት ጋር ለማስማማት ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገናል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ክርስቲያኖች በታዛዥነት ቀረጥ በመክፈል በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዘው ይኖራሉ፤ እንዲሁም አምላክ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላላቸው ያላቸውን እምነት በተግባር ያሳያሉ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

“የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ”

[የሥዕሉ ምንጭ]

Copyright British Museum