በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ዕድሜዬን ሙሉ የብርታት ምንጭ የሆነኝ ልማድ

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ዕድሜዬን ሙሉ የብርታት ምንጭ የሆነኝ ልማድ

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ዕድሜዬን ሙሉ የብርታት ምንጭ የሆነኝ ልማድ

ሞርሶ ለርዎ እንደተናገረው

“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።” ይህንን ሐሳብ ያነበብኩት ክፍሌ ውስጥ ተደብቄ ነበር። መደበቅ ያስፈለገኝ ለምንድን ነው? አምላክ የለሽ የሆነው አባቴ የማነብበውን መጽሐፍ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስን እንደማይቀበለው አውቅ ነበር።

ከዚያ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን አንብቤ ስለማላውቅ በዘፍጥረት መጽሐፍ መግቢያ ላይ ያለው ይህ ሐሳብ ለእኔ ፈጽሞ እንግዳ ነበር። በተፈጥሮ ሕግጋት ላይ የሚታየው ሥርዓት ሁልጊዜ ያስደንቀኛል፤ ይህን ጥቅስ ሳነብ ‘እንዲህ ያለ የሚያስገርም ሥርዓት ሊኖራቸው የቻለው ለካስ ለዚህ ነው!’ ብዬ አሰብኩ። በማነበው ነገር በጣም ስለተመሰጥኩ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት የጀመርኩ እስከ አሥር ሰዓት ድረስ ሳነብ ቆየሁ። ዕድሜዬን ሙሉ አብሮኝ የኖረው የአምላክን ቃል የማንበብ ልማድ የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በሕይወቴ ሁሉ የብርታት ምንጭ የሆነልኝ እንዴት እንደሆነ እስቲ ልንገራችሁ።

“በየዕለቱ ማንበብ ይኖርብሃል”

በሰሜን ፈረንሳይ በምትገኝ ቬርሜል የተባለች የድንጋይ ከሰል የሚመረትባት መንደር ውስጥ በ1926 ተወለድኩ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የድንጋይ ከሰል በአገሪቱ ውስጥ በጣም ተፈላጊ ነበር። እኔም የከሰል ማዕድን ማውጫ ሠራተኛ በመሆኔ ከውትድርና አገልግሎት ነፃ ነበርኩ። ያም ሆኖ ሕይወቴን ለማሻሻል ስለፈለግኩ የሬዲዮና የኤሌክትሪክ ሙያ መማር ጀመርኩ፤ በተፈጥሮ ሕግጋት ላይ ስለሚታየው ሥርዓት ያወቅሁት በዚህ ጊዜ ነበር። የ21 ዓመት ወጣት ሳለሁ አንድ የክፍል ጓደኛዬ መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠኝና “ሊነበብ የሚገባው መጽሐፍ ነው” አለኝ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት በዚያ ወቅት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን አንብቤ ስጨርስ ይህ መጽሐፍ ለሰው ዘር የተገለጠ የአምላክ ቃል እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ቻልኩ።

ጎረቤቶቼም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንደሚያስደስታቸው ስላሰብኩ ስምንት መጽሐፍ ቅዱሶችን ወሰድኩ። የሚገርመው ግን ጎረቤቶቼ ያፌዙብኝ ከመሆኑም ሌላ ተቃወሙኝ። አጉል እምነት ያላቸው ዘመዶቼ “ይሄን መጽሐፍ አንዴ ማንበብ ከጀመርክ በየዕለቱ ማንበብ ይኖርብሃል!” አሉኝ። እኔም እነሱ እንዳሉት ያደረግሁ ሲሆን በዚህ ደግሞ ፈጽሞ ተቆጭቼ አላውቅም። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ዕድሜዬን ሙሉ አብሮኝ የኖረ ልማድ ሆነ።

አንዳንድ ጎረቤቶቼ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ያለኝን ፍላጎት ስላስተዋሉ ከይሖዋ ምሥክሮች የተቀበሏቸውን ጽሑፎች ሰጡኝ። አንድ ዓለም፣ አንድ አገዛዝ * (ሥዕሉ ላይ በፈረንሳይኛ የሚታየው) እንደተባለው ያሉ ቡክሌቶች መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ዘር ብቸኛው ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን የሚናገረው ለምን እንደሆነ አብራሩልኝ። (ማቴ. 6:10) ይህን ተስፋ ለሌሎች ለመናገር ከምንጊዜውም በላይ ቆርጬ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ስሰጣቸው መጀመሪያ ከተቀበሉኝ ሰዎች መካከል አንዱ የልጅነት ጓደኛዬ የሆነው ኖኤል ነው። ቀናተኛ ካቶሊክ የሆነው ኖኤል፣ ቄስ ለመሆን እየተማረ ካለ ሰው ጋር እንድንገናኝ ዝግጅት አደረገ። በመጀመሪያ ላይ ፍርሃት ተሰምቶኝ ነበር፤ ሆኖም አምላክ ጣዖታትን ለአምልኮ መጠቀምንና ቀሳውስትን በሃይማኖታዊ የማዕረግ ስሞች መጥራትን እንደሚያወግዝ መዝሙር 115:4-8⁠ን እና ማቴዎስ 23:9, 10⁠ን ሳነብ ተገንዝቤ ነበር። ይህን ማወቄ አዲሱን እምነቴን ለማስረዳት ድፍረት እንዲኖረኝ ረዳኝ። ከውይይቱ በኋላ ኖኤል እውነትን የተቀበለ ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ ታማኝ የይሖዋ ምሥክር ነው።

ለእህቴም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ነገርኳት። ባለቤቷ ከመናፍስታዊ ሥራዎች ጋር የተያያዙ መጻሕፍት ስለነበሩት አጋንንት ያስቸግሩት ነበር። መጀመሪያ ላይ ሁኔታው ከአቅሜ በላይ እንደሆነ ቢሰማኝም እንደ ዕብራውያን 1:14 ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የይሖዋ መላእክት እንደሚረዱኝ እንድተማመን አደረጉኝ። የእህቴ ባል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ሲያደርግና ከመናፍስታዊ ሥራዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ሲያስወግድ ከአጋንንት ተጽዕኖ ነፃ መሆን ቻለ። እሱም ሆነ እህቴ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።

በ1947 አርተር ኤምዮት የተባለ አሜሪካዊ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤቴ መጣ። በዚህ በጣም የተደሰትኩ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች የት እንደሚሰበሰቡ ጠየቅኩት። ካለሁበት አካባቢ 10 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በሊየቨ አንድ ቡድን እንዳለ ነገረኝ። በዚያ ወቅት ብስክሌት እንኳ መግዛት አስቸጋሪ ስለነበር ለበርካታ ወራት በስብሰባ ላይ ለመገኘት በእግሬ እጓዝ ነበር። በወቅቱ ፈረንሳይ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ከታገደ ስምንት ዓመት ሆኖት ነበር። በመላው አገሪቱ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች 2,380 ብቻ ሲሆኑ አብዛኞቹ ከፖላንድ የመጡ ነበሩ። መስከረም 1, 1947 በፈረንሳይ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በድጋሚ ሕጋዊ እውቅና አገኙ። በመሆኑም በቪላ ጊቤር፣ ፓሪስ ቅርንጫፍ ቢሮ እንደገና ተከፈተ። በፈረንሳይ አንድም የዘወትር አቅኚ ስላልነበረ የታኅሣሥ 1947 የኢንፎርማንት እትም (አሁን የመንግሥት አገልግሎታችን የሚባለው) ወንድሞችና እህቶች የዘወትር አቅኚዎች ሆነው በየወሩ 150 ሰዓት እንዲያገለግሉ የሚያበረታታ ሐሳብ ይዞ ወጣ። (በ1949 የዘወትር አቅኚዎች የሰዓት ግብ ወደ 100 ሰዓት ዝቅ አለ።) በ⁠ዮሐንስ 17:17 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ‘የአምላክ ቃል እውነት ነው’ ከሚለው ሐሳብ ጋር በመስማማት በ1948 ተጠመቅሁ፤ ከዚያም ታኅሣሥ 1949 አቅኚ ሆንኩ።

ከእስር ቤት ስወጣ እንደገና በዳንከርክ ተመደብኩ

የመጀመሪያው ምድቤ በደቡባዊ ፈረንሳይ በምትገኘው በአዠ ነበር፤ ሆኖም በዚያ ብዙም አልቆየሁም። በድንጋይ ከሰል ማውጫ ውስጥ መሥራቴን ስላቆምኩ ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅብኝ ነበር። እኔ ግን ሠራዊቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ስላልሆንኩ ወኅኒ ወረድኩ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኖረኝ ባይፈቀድልኝም ከመዝሙር መጽሐፍ ላይ የተወሰኑ ገጾችን ማግኘት ችዬ ነበር። ይህንን ማንበቤም አበረታቶኛል። ከእስር ቤት ስለቀቅ አንድ ውሳኔ ተደቀነብኝ፦ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን አቁሜ የራሴን ኑሮ ብመሠርት ይሻል ይሆን? ብዬ አሰብኩ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ያነበብኩት ነገር በዚህ ጊዜም ውሳኔ ለማድረግ ረድቶኛል። በ⁠ፊልጵስዩስ 4:11-13 ላይ በሚገኘው ሐሳብ ላይ አሰላሰልኩ፤ ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ” ብሎ ነበር። ስለዚህ በአቅኚነት ለመቀጠል ወሰንኩ። በ1950 አዲስ ምድብ ተሰጠኝ፤ ከዚህ በፊት ባገለገልኩበት በዳንከርክ እንድሰብክ ተመደብኩ።

እዚያ ስደርስ ምንም ነገር አልነበረኝም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከተማዋ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባት ማረፊያ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ከዚህ ቀደም እሰብክላቸው ወደነበሩ አንድ ቤተሰብ ሄድኩ፤ ሚስትየዋ ስታየኝ እንዲህ አለችኝ፦ “ሚስተር ለርዎ፣ ከእስር በመፈታትህ በጣም ደስ ብሎኛል! ባለቤቴ፣ እንደ አንተ ያሉ ብዙ ሰዎች ቢኖሩ ኖሮ ጦርነት ፈጽሞ እንደማይነሳ ይናገራል።” እነዚህ ባልና ሚስት የእንግዳ ማረፊያ ስለነበራቸው ጎብኚዎች የሚመጡበት ወቅት እስከሚደርስ ድረስ እዚያ እንድቆይ ፈቀዱልኝ። የአርተር ኤምዮት ወንድም የሆነው ኤቨንዝ በዚያኑ ዕለት ሥራ ሰጠኝ። * ኤቨንዝ በወደቡ ላይ ተርጓሚ ሆኖ የሚሠራ ሲሆን ሌሊት ላይ መርከብ የሚጠብቅ ሰው ይፈልግ ነበር። ከመርከቡ ምክትል መሪዎች አንዱን አስተዋወቀኝ። እስር ቤት ስለቆየሁ በጣም ከሲታ ሆኜ ነበር። ኤቨንዝ የከሳሁት ለምን እንደሆነ ለምክትል መሪው ሲነግረው ሰውየው ከማቀዝቀዣው ውስጥ ምግብ ወስጄ እንድበላ ጋበዘኝ። በመሆኑም በአንድ ቀን ውስጥ ማረፊያ፣ ሥራና ምግብ አገኘሁ! ይህም በ⁠ማቴዎስ 6:25-33 ላይ በሚገኘው ኢየሱስ በተናገረው ሐሳብ ላይ ያለኝን እምነት ይበልጥ አጠናክሮልኛል።

ጎብኚዎች የሚመጡበት ወቅት ሲደርስ እኔና በአቅኚነት አብሮኝ የሚያገለግለው ሲሞን አፖሊናርስኪ ሌላ ማረፊያ ቦታ ማግኘት ነበረብን፤ ያም ሆኖ በአገልግሎት ምድባችን ለመቆየት ቆርጠን ነበር። በአንድ ያረጀ የፈረስ ጋጣ ውስጥ ማረፊያ ያገኘን ሲሆን በዚያም በሣር ፍራሽ ላይ እንተኛለን። ቀኑን ሙሉ በአገልግሎት እናሳልፍ ነበር። የምናርፍበትን ጋጣ ለሰጠን ሰው የመሠከርንለት ሲሆን እሱም እውነትን ተቀበለ። ሌሎች በርካታ ሰዎችም እውነትን ተቀበሉ። ብዙም ሳይቆይ በአካባቢው በሚታተመው ጋዜጣ ላይ ‘የይሖዋ ምሥክሮች ከተማዋን ስላጥለቀለቋት’ የዳንከርክ ነዋሪዎች እንዲጠነቀቁ የሚያሳስብ ርዕስ ወጣ። የሚገርመው ከእኔና ከሲሞን ሌላ በዚያች ከተማ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ! በአስቸጋሪ ጊዜያት በክርስቲያናዊ ተስፋችን ላይ ማሰላሰላችንና ይሖዋ እንዴት እንደተንከባከበን ማሰባችን አበረታቶናል። በ1952 ሌላ ቦታ ስመደብ በዳንከርክ 30 አዘውታሪ አስፋፊዎች ነበሩ።

አዲስ ኃላፊነቶችን ለመቀበል ተበረታታሁ

በአሚየን ከተማ የተወሰነ ጊዜ ካገለገልኩ በኋላ ከፓሪስ ወጣ ብሎ በሚገኘው በቡሎን ቢያንኩር ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የነበሩኝ ሲሆን ከጊዜ በኋላ አንዳንዶቹ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈልና በሚስዮናዊነት ማገልገል ችለዋል። ከእነዚህ መካከል ጊ ማቢላ የተባለ አንድ ወጣት ይገኝበታል፤ ይህ ወጣት እውነትን የተቀበለ ሲሆን ከጊዜ በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካች ቆይቶ ደግሞ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆነ። ቆየት ብሎም ከፓሪስ ወጣ ብሎ በሚገኘው በሉቪዬ አሁን ያለው ቤቴል ሲሠራ የማተሚያውን ግንባታ በበላይነት የመከታተል መብት አገኘ። በአገልግሎት ላይ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ጊዜያት ከሰዎች ጋር መወያየቴ የአምላክ ቃል በአእምሮዬ ይበልጥ እንዲቀረጽ አድርጓል፤ ይህም ደስተኛ እንድሆንና የማስተማር ችሎታዬን እንዳሻሽል ረድቶኛል።

በ1953 ደግሞ ያልጠበቅሁት ኃላፊነት ተሰጠኝ፤ በአልሳስ ሎሬን የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። ይህ አካባቢ ከ1871 እስከ 1945 ባሉት ዓመታት ውስጥ ሁለት ጊዜ በጀርመን አገዛዝ ሥር ነበር። በመሆኑም ጀርመንኛ መማር ነበረብኝ። የወረዳ ሥራ ስጀምር መኪና፣ ቴሌቪዥን ወይም የጽሕፈት መኪና በዚያ አካባቢ ያን ያህል የተለመዱ ነገሮች አልነበሩም፤ እንዲሁም ሬዲዮ ወይም ኮምፒውተር አልነበረም። ያም ቢሆን ግን ሕይወቴ ደስታ የራቀው ወይም የባሕታዊ ዓይነት ነበር ማለት አይደለም። እንዲያውም በጣም አስደሳች ጊዜ አሳልፌያለሁ። በዛሬው ጊዜም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓይናችን አጥርቶ የሚያይ’ እንዲሆን የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ካደረግን ልባችን እንዲከፋፈል የሚያደርጉ ነገሮች አይኖሩም።—ማቴ. 6:19-22

በ1955 በፓሪስ የተደረገውን “ድል አድራጊው መንግሥት” የተባለ ትልቅ ስብሰባ ፈጽሞ አልረሳውም። በዚህ ስብሰባ ላይ ኢሬን ኮላንስኪ ከተባለች እህት ጋር ተገናኘሁ፤ ኢሬን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመረችው ከእኔ አንድ ዓመት ቀደም ብላ ነው። የፖላንድ ተወላጅ የሆኑት ወላጆቿ ለረጅም ዓመታት ይሖዋን ያገለገሉ ቀናተኛ ክርስቲያኖች ናቸው። ፈረንሳይ ውስጥ እውነትን የመሠከረላቸው አዶልፍ ቪቤር ነበር። የወንድም ራስል አትክልተኛ የነበረው ይህ ወንድም ምሥራቹን ለመስበክ ወደ አውሮፓ መጥቶ ነበር። በ1956 ከኢሬን ጋር ተጋባንና በወረዳ ሥራ አብረን ማገልገል ጀመርን። ኢሬን በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ከፍተኛ ድጋፍ አድርጋልኛለች!

ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ ሌላ ያልጠበቅኩት ኃላፊነት ተሰጠኝ፤ ይኸውም የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ይሁንና ብቃት ያላቸው ወንድሞች እጥረት ስለነበር የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ የተወሰኑ ጉባኤዎችን መጎብኘቴን ቀጥዬ ነበር። በዚያ ወቅት ሥራ በጣም ይበዛብኝ ነበር! በወር 100 ሰዓት ከማገልገል በተጨማሪ በየሳምንቱ ንግግሮችን እሰጥ፣ ሦስት የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖችን እጎበኝ፣ የጉባኤ መዝገቦችን እመረምርና ሪፖርቶችን አጠናቅር ነበር። ታዲያ የአምላክን ቃል ለማንበብ ጊዜ ማግኘት የምችለው እንዴት ነበር? የታየኝ አንድ መፍትሔ ብቻ ነው፤ ከአንድ አሮጌ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰኑ ገጾችን ቀድጄ ይዣቸው እዞር ነበር። ከአንድ ሰው ጋር ቀጠሮ ኖሮኝ ግለሰቡ እስኪመጣ በምጠብቅበት ጊዜ እነዚህን ገጾች አነባለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ የማሳልፋቸው እነዚያ ወቅቶች በመንፈሳዊ የሚያድሱኝ ከመሆኑም ሌላ በተመደብኩበት አገልግሎት ለመቀጠል ያደረግሁትን ውሳኔ አጠናክረውልኛል።

በ1967 እኔና ኢሬን በቡሎን ቢያንኩር የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ አባላት እንድንሆን ተጋበዝን። በዚያም በአገልግሎት ክፍል ውስጥ መሥራት ጀመርኩ፤ ይህ ከሆነ ከ40 ዓመታት በላይ ያለፉ ቢሆንም ዛሬም በዚያው ክፍል ውስጥ እያገለገልኩ ነው። በሥራዬ ላይ በጣም የሚያስደስተኝ ነገር ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ነው። የአምላክን ቃል በመቆፈር “ለምሥራቹ ስሟገት” እንዴት ደስ እንደሚለኝ መገመት ትችላላችሁ! (ፊልጵ. 1:7) ከዚህም በተጨማሪ ከቁርስ በፊት በምናደርገው የማለዳ አምልኮ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶችን መምራት ያስደስተኛል። በ1976 የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኜ ተሾምኩ።

ከሁሉ የላቀ ሕይወት

በሕይወቴ ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ያሳለፍኩ ቢሆንም ከሁሉ ይበልጥ የከበደኝ በአሁኑ ወቅት እኔና ኢሬን በዕድሜ መግፋትና በጤና እክሎች ምክንያት የምንፈልገውን ያህል መሥራት አለመቻላችን ነው። ያም ቢሆን የአምላክን ቃል አብረን ማንበባችንና ማጥናታችን ተስፋችን እውን ሆኖ እንዲታየን አድርጎልናል። ወደ ጉባኤያችን ክልል በአውቶቡስ በመጓዝ ይህንን ተስፋ ለሌሎች መስበክ ያስደስተናል። ሁለታችን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍናቸው ዓመታት አንድ ላይ ሲደመሩ ከ120 ዓመት ይበልጣሉ፤ አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት የሚፈልጉ ሁሉ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉ እናበረታታለን። ንጉሥ ዳዊት መዝሙር 37:25⁠ን ሲጽፍ ‘አርጅቶ’ ነበር፤ እኔም እንደ እሱ “ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም” ማለት እችላለሁ።

በሕይወቴ ሙሉ ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት አበረታቶኛል። ዘመዶቼ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ሕይወቴን ሙሉ አብሮኝ የሚኖር ልማድ መሆን እንዳለበት ከ60 ዓመታት በፊት ነግረውኝ ነበር። በእርግጥም የተናገሩት ተፈጽሟል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ፈጽሞ የማልቆጭበት የዕለት ተዕለት ልማድ ሆኖልኛል!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 በ1944 የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።

^ አን.14 ስለ ወንድም ኤቨንዝ ኤምዮት ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የጥር 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 22 እና 23⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ሲሞን

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጀመሪያ ያገኘሁት ዓይነት መጽሐፍ ቅዱስ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ ሳገለግል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሠርጋችን ዕለት

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ኢሬን የአምላክን ቃል ማንበብና ማጥናት ያስደስተናል