በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድርሻዬ ይሖዋ ነው

ድርሻዬ ይሖዋ ነው

ድርሻዬ ይሖዋ ነው

“በእስራኤላውያን መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ።”​—ዘኍ. 18:20

1, 2. (ሀ) በተስፋይቱ ምድር ውስጥ ርስት ከማግኘት ጋር በተያያዘ ለሌዋውያን የተደረገው ዝግጅት ምን ነበር? (ለ) ይሖዋ ለሌዋውያን ምን ዋስትና ሰጥቷቸው ነበር?

እስራኤላውያን አብዛኛውን የተስፋይቱን ምድር ድል አድርገው ከተቆጣጠሩ በኋላ ኢያሱ ምድሪቱን በዕጣ መደልደል ጀመረ። ይህን ሥራ ያከናወነው ከሊቀ ካህናቱ ከአልዓዛርና ከነገድ አለቆች ጋር ሆኖ ነበር። (ዘኍ. 34:13-29) ሌዋውያን ግን እንደ ሌሎቹ ነገዶች ርስት አልተሰጣቸውም። (ኢያሱ 14:1-5) የሌዊ ነገድ በተስፋይቱ ምድር ርስት ወይም ድርሻ ያልተሰጠው ለምን ነበር? ይህ ነገድ ርስት ያልተሰጠው ተረስቶ ይሆን?

2 ይሖዋ ለሌዋውያን የተናገረው ነገር ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። ይሖዋ፣ ለሌዊ ነገድ “በእስራኤላውያን መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ” ማለቱ ሌዋውያንን ችላ እንዳላላቸው ያሳያል። (ዘኍ. 18:20) ‘ድርሻህ ነኝ’ የሚለው አባባል እንዴት ያለ አስተማማኝ ዋስትና ነው! ይሖዋ አንተን እንዲህ ቢልህ ምን ይሰማሃል? በቅድሚያ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ‘ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ እንዲህ ያለ ማረጋገጫ ለማግኘት ብቁ ነኝ?’ የሚል ጥያቄ ይሆናል። ምናልባትም ‘በእርግጥ ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ለሚኖር ፍጽምና የጎደለው ክርስቲያን ድርሻው ሊሆን ይችላል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። እነዚህ ጥያቄዎች አንተንም ሆነ የምትወዳቸውን ሰዎች ይመለከታሉ። እንግዲያው አምላክ የተናገረው ይህ ሐሳብ ምን ትርጉም እንዳለው እስቲ እንመልከት። ይህን ማድረጋችን ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ድርሻቸው የሚሆነው እንዴት እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። ደግሞም ተስፋህ ወደ ሰማይ መሄድም ይሁን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለአንተም ድርሻህ ሊሆንልህ ይችላል።

ይሖዋ ሌዋውያኑን ይንከባከባቸው ነበር

3. አምላክ፣ ሌዋውያን እሱን እንዲያገለግሉት የመረጠበት ምክንያት ምንድን ነው?

3 ይሖዋ ሕጉን ለእስራኤላውያን ከመስጠቱ በፊት የቤተሰብ ራሶች ለቤተሰባቸው እንደ ካህናት ሆነው ያገለግሉ ነበር። አምላክ ሕጉን ለእስራኤላውያን በሰጣቸው ወቅት ሙሉ ጊዜያቸውን ካህናት ሆነው የሚያገለግሉና እነሱን የሚረዱ ሰዎችን ከሌዊ ነገድ መረጠ። ይህ ዝግጅት እንዲደረግ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው? አምላክ የግብፃውያንን የበኩር ልጆች ባጠፋበት ጊዜ የእስራኤላውያንን የበኩር ልጆች ቀድሷቸው ይኸውም ለእሱ የተለዩና ንብረቱ እንዲሆኑ አድርጓቸው ነበር። ከዚያ በኋላ አምላክ “በኵር ሆኖ በሚወለደው ሁሉ ምትክ ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን [ለመውሰድ]” ወሰነ። ሕዝቡ ሲቆጠር፣ ወንዶች የሆኑት የእስራኤላውያን የበኩር ልጆች ከሌዋውያን ስለበለጡ ልዩነቱን ለማካካስ በተረፉት የበኩር ልጆች ልክ ቤዛ ተከፈለ። (ዘኍ. 3:11-13, 41, 46, 47) በዚህ መንገድ ሌዋውያን የእስራኤልን አምላክ የማገልገል መብት ሊኖራቸው ቻለ።

4, 5. (ሀ) አምላክ ለሌዋውያን ድርሻቸው ይሆናል ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) አምላክ ለሌዋውያን የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ የሚያሟላላቸው እንዴት ነበር?

4 ይህ ኃላፊነት ለሌዋውያኑ ምን ትርጉም ነበረው? ይሖዋ ድርሻቸው እንደሚሆን ነግሯቸዋል፤ ይህም ሲባል በተስፋይቱ ምድር ርስት ከመቀበል ይልቅ በዋጋ ሊተመን የማይችል የአገልግሎት መብት በአደራ ተሰጥቷቸዋል ማለት ነው። ርስታቸው “ለእግዚአብሔር የሚሰጡት የክህነት አገልግሎት” ነበር። (ኢያሱ 18:7) በ⁠ዘኍልቍ 18:20 ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ይህ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ለችግር የሚዳርጋቸው አልነበረም። (ዘኍልቍ 18:19, 21, 24ን አንብብ።) ይሖዋ “ለሚሠሩት ሥራ ደመወዝ እንዲሆናቸው ከእስራኤል የሚወጣውን ዐሥራት ሁሉ ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ” ብሏል። እስራኤላውያን ከምርታቸው እንዲሁም ከቤት እንስሶቻቸው ካገኙት ጭማሪ ላይ 10 በመቶውን ለሌዋውያን እንዲሰጡ ታዝዘው ነበር። ሌዋውያኑም በተራቸው ካገኙት ነገር መካከል “ምርጥ” የሆነውን ለካህናቱ ዐሥራት ይሰጡ ነበር። * (ዘኍ. 18:25-29) በተጨማሪም የእስራኤል ልጆች ወደ ይሖዋ የአምልኮ ስፍራ ይዘው የሚመጡት ‘የተቀደሰ ቍርባን ሁሉ’ ለካህናቱ ይሰጣቸው ነበር። በመሆኑም ካህናቱ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጣቸው የሚተማመኑበት በቂ ምክንያት ነበራቸው።

5 በሙሴ ሕግ ሥር ሁለተኛ አሥራት የማውጣት ዝግጅትም የነበረ ይመስላል፤ ይህ አሥራት በየዓመቱ በሚከበሩት የተቀደሱ ጉባኤዎች ወቅት እያንዳንዱ ቤተሰብ እንዲመገበውና እንዲደሰትበት ተብሎ የሚቀመጥ ነበር። (ዘዳ. 14:22-27) ይህን አሥራት ለሌላ ዓላማም ይጠቀሙበት ነበር፤ እስራኤላውያን በየሰባት ዓመቱ ሰንበት የሚያከብሩ ሲሆን በእነዚህ ሰባት ዓመታት ውስጥ በየሦስተኛውና በየስድስተኛው ዓመት ማብቂያ ላይ አሥራቱን ለድሆችና ለሌዋውያን እንዲሆን በከተማይቱ መግቢያ ላይ ያከማቹት ነበር። ከዚህ አሥራት ከሚጠቀሙት መካከል ሌዋውያን የተጠቀሱት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሌዋውያን በእስራኤል ውስጥ ‘የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት አልነበራቸውም።’​—ዘዳ. 14:28, 29

6. ሌዋውያን በእስራኤል ውስጥ ርስት ካልተሰጣቸው የት ይኖራሉ?

6 ይሁንና ‘ሌዋውያን ርስት ካልተሰጣቸው የት ይኖራሉ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አምላክ የሚኖሩበትን ቦታ አዘጋጅቶላቸው ነበር። ይሖዋ 48 ከተሞችንና በከተሞቹ ዙሪያ ያለውን የግጦሽ መሬት ሰጥቷቸዋል። ይህም ስድስቱን የመማጸኛ ከተሞች ይጨምራል። (ዘኍ. 35:6-8) በመሆኑም ሌዋውያኑ በአምላክ መቅደስ ውስጥ በማያገለግሉበት ጊዜ የሚኖሩበት ቦታ ነበራቸው። ይሖዋ እሱን ለማገልገል ራሳቸውን ላቀረቡት ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አትረፍርፎ ሰጥቷቸዋል። ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ሌዋውያኑ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት ፈቃደኛ እንደሆነና አቅሙም እንዳለው በመተማመን ድርሻቸው ይሖዋ መሆኑን ማሳየት ይችሉ ነበር።

7. ሌዋውያን፣ ይሖዋ ድርሻቸው እንዲሆን ምን ማድረግ ነበረባቸው?

7 የሙሴ ሕግ፣ አንድ እስራኤላዊ አሥራት ባያወጣ ቅጣት እንደሚጣልበት አይገልጽም። ሕዝቡ አሥራት ማውጣትን ችላ በሚልበት ጊዜ ካህናቱና ሌዋውያኑ ይቸገሩ ነበር። በነህምያ ዘመን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞ ነበር። በመሆኑም ሌዋውያኑ አገልግሎታቸውን ትተው በእርሻቸው ላይ ለመሥራት ተገደዱ። (ነህምያ 13:10ን አንብብ።) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሌዋውያኑ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማግኘታቸው የተመካው በብሔሩ መንፈሳዊ አቋም ላይ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ካህናቱና ሌዋውያኑ ራሳቸው በይሖዋና ይሖዋ እነሱን ለመንከባከብ ባደረገው ዝግጅት ላይ እምነት ሊኖራቸው ይገባ ነበር።

በግለሰብ ደረጃ ይሖዋን ድርሻቸው ያደረጉ ሌዋውያን

8. ሌዋዊው አሳፍ ምን አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞት እንደነበር ግለጽ።

8 ይሖዋ በቡድን ደረጃ ለሌዋውያን ድርሻቸው ነበር። አንዳንድ ሌዋውያን ለአምላክ ያደሩ መሆናቸውንና በእሱ እንደሚተማመኑ ለመግለጽ ይሖዋ ‘ዕድል ፈንታቸው’ ወይም ድርሻቸው እንደሆነ ይናገሩ ነበር። (ሰቆ. 3:24) ከእነዚህ ሌዋውያን መካከል አንዱ ዘማሪና ሙዚቃ አቀናባሪ ነበር። ይህ ሌዋዊ አሳፍ ተብሎ የተጠራ ቢሆንም በንጉሥ ዳዊት ዘመን የመዘምራን አለቃ የነበረው አሳፍ የተባለው ሌዋዊ ወገንም ሊሆን ይችላል። (1 ዜና 6:31-43) በ⁠መዝሙር 73 ላይ አሳፍ (ወይም ከዘሮቹ አንዱ ሊሆን ይችላል) ክፉዎች ተመችቷቸው ሲኖሩ በማየቱ ግራ እንደተጋባና በእነሱ እንደቀና ገልጿል። እንዲያውም “ለካ ልቤን ንጹሕ ያደረግሁት በከንቱ ነው፤ እጄንም በየዋህነት የታጠብሁት በከንቱ ኖሮአል!” እስከ ማለት ደርሶ ነበር። አሳፍ ለአገልግሎት መብቱ የነበረው አድናቆት የቀነሰ ይመስላል፤ ይሖዋ ድርሻው መሆኑን ዘንግቶ ነበር። “ወደ አምላክ መቅደስ [እስኪገባ]” ድረስ መንፈሳዊ አቋሙ ተናግቶ ነበር።​—መዝ. 73:2, 3, 12, 13, 17

9, 10. አሳፍ አምላክን “የዘላለም ዕድል ፈንታዬ” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው?

9 አሳፍ ወደ አምላክ መቅደስ ሲገባ ነገሮችን ከአምላክ አመለካከት አንጻር ማየት ጀመረ። አንተም በአንድ ወቅት ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆናል። ለመንፈሳዊ መብቶችህ ያለህ አድናቆት በተወሰነ መጠን የቀነሰበትና በሌሉህ ቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮርክበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ይሁንና የአምላክን ቃል ስታጠና እንዲሁም ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ስትሄድ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት አዳበርክ። አሳፍ፣ ክፉዎች መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን ማስተዋል ቻለ። በተጨማሪም ስላገኛቸው መልካም ነገሮች ማሰብ የጀመረ ሲሆን ይሖዋ ቀኝ እጁን ይዞ እንደሚመራው ተገነዘበ። በመሆኑም አሳፍ “በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ? በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም” በማለት ለይሖዋ መናገር ችሏል። (መዝ. 73:23, 25) ከዚያም አምላክ ዕድል ፈንታው ወይም ድርሻው እንደሆነ ተናገረ። (መዝሙር 73:26ን አንብብ።) መዝሙራዊው ‘ሥጋውና ልቡ ሊደክሙ ቢችሉም’ አምላክ ‘የዘላለም ዕድል ፈንታው’ እንደሆነ ገልጿል። ይሖዋ እንደ ወዳጁ ቆጥሮ እንደሚያስታውሰው እርግጠኛ ነበር። በታማኝነት ያቀረበውን አገልግሎት አምላክ ፈጽሞ አይረሳውም። (መክ. 7:1) ይህ አሳፍን ምንኛ አጽናንቶት ይሆን! “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ ጌታ እግዚአብሔርን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ” በማለት ዘምሯል።​—መዝ. 73:28

10 አሳፍ፣ አምላክ ድርሻው እንደሆነ ሲናገር ሌዋዊ መሆኑ የሚያስገኝለትን ቁሳዊ ጥቅም ብቻ መጥቀሱ አልነበረም። ይህን ሲል በዋነኝነት ስለ አገልግሎት መብቱና ሉዓላዊ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ጋር ስለመሠረተው ወዳጅነት መግለጹ ነበር። (ያዕ. 2:21-23) መዝሙራዊው ይህን ወዳጅነት ላለማጣት ከፈለገ በይሖዋ ላይ ያለው እምነት እንዳይጠፋ መጠንቀቅ ነበረበት። አሳፍ በአምላክ መመሪያ መሠረት የሚኖር ከሆነ ደስተኛ ሕይወት መምራት እንደሚችል ሊተማመን ይገባ ነበር። አንተም በተመሳሳይ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ መተማመን ትችላለህ።

11. ኤርምያስ ምን ዓይነት ጥያቄ ተፈጥሮበት ነበር? መልስ ያገኘውስ እንዴት ነው?

11 ይሖዋ ዕድል ፈንታው እንደሆነ የተናገረው ሌላው ሌዋዊ ደግሞ ነቢዩ ኤርምያስ ነው። ኤርምያስ ይህን ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ኤርምያስ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ በምትገኘውና የሌዋውያን ከተማ በሆነችው በዓናቶት ይኖር ነበር። (ኤር. 1:1) በአንድ ወቅት ኤርምያስ፣ ጻድቃን እየተሠቃዩ ክፉዎች የሚበለጽጉት ለምን እንደሆነ ግራ ገብቶት ነበር። (ኤር. 12:1) በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የተፈጸመውን ሁኔታ ከተመለከተ በኋላ ቅር የተሰኘበትን ‘ጉዳይ’ ለአምላክ መናገር እንዳለበት ተሰማው። እርግጥ ነው፣ ይህ ነቢይ ይሖዋ ጻድቅ መሆኑን ያውቃል። ኤርምያስ ከላይ ያለውን ጥያቄ ካነሳ በኋላ ይሖዋ በመንፈሱ መሪነት በዚህ ነቢይ በኩል ያስነገራቸው ትንቢቶችና እነዚህን ትንቢቶች የፈጸመበት መንገድ ነቢዩ ላነሳው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ሰጥቶታል። አምላክ ካስነገራቸው ትንቢቶች ጋር በሚስማማ መልኩ የይሖዋን መመሪያ የታዘዙ ሰዎች ‘ነፍሳቸውን ያተረፉ’ ሲሆን ባለጸጋ የሆኑት ክፉዎች ግን ማስጠንቀቂያውን ችላ በማለታቸው ጠፍተዋል።​—ኤር. 21:9

12, 13. (ሀ) ኤርምያስ፣ ይሖዋ “ዕድል ፈንታዬ ነው” እንዲል ያነሳሳው ምንድን ነው? ምን ዓይነት አመለካከትስ ነበረው? (ለ) የእስራኤል ነገዶች በሙሉ ይሖዋን ተስፋ ማድረግ የነበረባቸው ለምንድን ነው?

12 ከጊዜ በኋላ ኤርምያስ የወደመችውን የትውልድ አገሩን ሲመለከት በጨለማ ውስጥ እንደሚኖር ሆኖ ተሰምቶት ነበር። ነቢዩ፣ ይሖዋ “ከሞቱ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው” ሰዎች እንዳደረገው ተሰምቶታል። (ሰቆ. 1:1, 16፤ 3:6) ኤርምያስ፣ ዓመፀኛውን ሕዝብ በሰማይ ወደሚገኘው አምላኩ እንዲመለስ ቢያስጠነቅቅም የሕዝቡ ክፋት በጣም ስለበዛ አምላክ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ እንዲጠፉ ፈቀደ። ኤርምያስ ያጠፋው ነገር ባይኖርም በተከሰተው ነገር በጣም አዘነ። ነቢዩ በሐዘን ተውጦ በነበረበት ወቅት አምላክ መሐሪ መሆኑን በማስታወስ ጨርሶ ‘እንዳልጠፉ’ ገልጿል። በእርግጥም የይሖዋ ምሕረት ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው! ነቢዩ፣ ይሖዋ “ዕድል ፈንታዬ ነው” ያለው በዚህ ጊዜ ነበር። ኤርምያስ የይሖዋ ነቢይ ሆኖ ማገልገሉን የቀጠለ ሲሆን ይህም ታላቅ መብት ነው።​—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:22-24ን አንብብ።

13 እስራኤላውያን ለ70 ዓመታት የራሳቸው አገር አይኖራቸውም። ምድራቸው ባድማ ይሆናል። (ኤር. 25:11) ይሁንና ኤርምያስ፣ ይሖዋ “ዕድል ፈንታዬ ነው” ማለቱ አምላክ ምሕረት እንደሚያሳይ ያለውን እምነት የሚጠቁም ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ ‘ተስፋ ለማድረግ’ ምክንያት ሆኖታል። የእስራኤል ነገዶች በሙሉ ርስታቸውን ስላጡ የነቢዩን ዓይነት አመለካከት ማዳበር ይኸውም በይሖዋ ተስፋ ማድረግ ነበረባቸው። ብቸኛ ተስፋቸው ይሖዋ ነበር። ከ70 ዓመታት በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን በዚያም እሱን የማገልገል መብት አግኝተዋል።​—2 ዜና 36:20-23

ሌሎችም ይሖዋን ድርሻቸው ሊያደርጉት ይችላሉ

14, 15. ከሌዋውያን በተጨማሪ ይሖዋን ድርሻው ያደረገው ማን ነው? ለምንስ?

14 አሳፍም ሆነ ኤርምያስ ሌዋውያን ነበሩ፤ ይሁንና ይሖዋን የማገልገል መብት ማግኘት የሚችሉት ሌዋውያን ብቻ ነበሩ ማለት ነው? አይደለም! ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ታጭቶ በነበረበት ወቅት አምላክን “በሕያዋንም ምድር ዕድል ፈንታዬ ነህ” ብሎት ነበር። (መዝሙር 142:1, 5ን አንብብ።) ዳዊት ይህን መዝሙር ያቀናበረው በቤተ መንግሥት ሌላው ቀርቶ በቤት ውስጥ እንኳ ሆኖ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ከጠላቶቹ ሸሽቶ በዋሻ ውስጥ ነበር። ዳዊት ቢያንስ በሁለት ወቅቶች በዋሻዎች (በዓዶላም አቅራቢያና በዐይንጋዲ ምድረ በዳ) ተደብቆ ነበር። መዝሙር 142⁠ን ያቀናበረው ከእነዚህ ዋሻዎች መካከል በአንዱ ውስጥ ሆኖ ሊሆን ይችላል።

15 ዳዊት መዝሙሩን የጻፈው በዋሻ ውስጥ ከሆነ እንዲህ ያደረገው ሕይወቱን ለማጥፋት የሚፈልገው ንጉሥ ሳኦል ያሳድደው ስለነበር ነው። በዚህ ጊዜ ዳዊት ሰዎች በቀላሉ ሊደርሱበት በማይችሉት ዋሻ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር። (1 ሳሙ. 22:1, 4) ዳዊት ሩቅ በሆነው በዚህ አካባቢ በነበረበት ወቅት ከጎኑ ሆኖ ‘አይዞህ’ የሚለው ወዳጅ እንደሌለው ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። (መዝ. 142:4) ዳዊት ወደ አምላክ የጮኸው በዚህ ጊዜ ነበር።

16, 17. (ሀ) ዳዊት ረዳት የለሽ እንደሆነ እንዲሰማው ያደረጉት ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ዳዊት እርዳታ ለማግኘት ወደ ማን ዘወር ማለት ይችል ነበር?

16 ዳዊት መዝሙር 142⁠ን ባቀናበረበት ጊዜ በሊቀ ካህናቱ በአቢሜሌክ ላይ የደረሰውን አስከፊ ነገር ሳይሰማ አልቀረም፤ አቢሜሌክ ዳዊት ከሳኦል እየሸሸ መሆኑን ስላላወቀ ረድቶት ነበር። ንጉሥ ሳኦል በቅናት ተነሳስቶ አቢሜሌክንና ቤተሰቡን አስገደላቸው። (1 ሳሙ. 22:11, 18, 19) ዳዊት ለእነዚህ ሰዎች ሞት ራሱን ተጠያቂ አድርጎ ነበር። እርዳታ የሰጠውን ካህን እሱ ራሱ እንደገደለው ሆኖ ተሰምቶታል። አንተ በዳዊት ቦታ ብትሆን ኖሮ ለካህናቱ ሞት ተጠያቂ እንደሆንክ ይሰማህ ነበር? ዳዊት ያለበት ጭንቀት እንዳይበቃው ደግሞ ሳኦል ያሳድደው ነበር፤ በመሆኑም ምንም እረፍት አልነበረውም።

17 ብዙም ሳይቆይ፣ ዳዊትን ንጉሥ እንዲሆን የቀባው ነቢዩ ሳሙኤል ሞተ። (1 ሳሙ. 25:1) ይህም ዳዊት ረዳት እንደሌለው ይበልጥ እንዲሰማው አድርጎት ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ዳዊት እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ማለት እንደሚችል ያውቅ ነበር። ዳዊት የሌዋውያኑ ዓይነት የአገልግሎት መብት አልነበረውም፤ ሆኖም ለሌላ ዓይነት አገልግሎት ይኸውም ከጊዜ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ንጉሥ እንዲሆን ተቀብቶ ነበር። (1 ሳሙ. 16:1, 13) በመሆኑም ዳዊት ልቡን ለይሖዋ ያፈሰሰ ከመሆኑም ሌላ ቀደም ሲል ያደርግ እንደነበረው መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ብሏል። አንተም በይሖዋ አገልግሎት በትጋት በምትካፈልበት ጊዜ ይሖዋን ድርሻህና መጠጊያህ ልታደርገው ትችላለህ፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ይኖርብሃል።

18. በዚህ ርዕስ ላይ የተመለከትናቸው ሰዎች ይሖዋን ድርሻቸው እንዳደረጉት ያሳዩት እንዴት ነው?

18 በዚህ ርዕስ ላይ የተመለከትናቸው ሰዎች በይሖዋ አገልግሎት ኃላፊነት በመቀበል እሱን ድርሻቸው አድርገውት ነበር። አምላክን በሚያገለግሉበት ጊዜ እሱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላላቸው እምነት ነበራቸው። ሌዋውያንም ሆኑ ከሌሎቹ የእስራኤል ነገዶች የመጡ እንደ ዳዊት ያሉ ሰዎች አምላክን ድርሻቸው ማድረግ ይችሉ ነበር። አንተስ በተመሳሳይ ይሖዋን ድርሻህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ይህን ጥያቄ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ካህናቱ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች እንዴት እንደሚያገኙ ለማወቅ የታኅሣሥ 1, 1991 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 29-30 እንዲሁም ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 684⁠ን ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ይሖዋ ለሌዋውያን ድርሻቸው የነበረው እንዴት ነው?

• አሳፍ፣ ኤርምያስና ዳዊት ይሖዋ ድርሻቸው እንደሆነ ያሳዩት እንዴት ነበር?

• አምላክ ድርሻህ እንዲሆን የትኛውን ባሕርይ ማዳበር አለብህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሌዋውያን ርስት አልተሰጣቸውም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክን የማገልገል ታላቅ መብት ስለነበራቸው ድርሻቸው ይሖዋ ነበር

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ ድርሻቸው የነበረው እንዴት ነው?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሳፍ ምንጊዜም ይሖዋን ድርሻው እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው?