በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን ድርሻህ አድርገኸዋል?

ይሖዋን ድርሻህ አድርገኸዋል?

ይሖዋን ድርሻህ አድርገኸዋል?

“ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋችሁን ቀጥሉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።”​—ማቴ. 6:33

1, 2. (ሀ) በ⁠ገላትያ 6:16 ላይ ‘የአምላክ እስራኤል’ የተባሉት እነማን ናቸው? (ለ) በ⁠ማቴዎስ 19:28 ላይ የተጠቀሱት “አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” እነማንን ያመለክታሉ?

እስራኤል የሚለውን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስታነብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ከጊዜ በኋላ ስሙ ተለውጦ እስራኤል የተባለው የይስሐቅ ልጅ ያዕቆብ ትዝ ይልሃል? ወይስ የእሱ ዝርያዎች የሆኑትን የጥንቶቹን እስራኤላውያን ታስታውሳለህ? አሊያም ደግሞ መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ታስብ ይሆን? እስራኤል የሚለው ስም በምሳሌያዊ መንገድ ሲጠቀስ ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው ‘የአምላክን እስራኤል’ ይኸውም በሰማይ ነገሥታትና ካህናት እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡትን 144,000 ሰዎች ነው። (ገላ. 6:16፤ ራእይ 7:4፤ 21:12) በሌላ በኩል ግን በ⁠ማቴዎስ 19:28 ላይ ስለ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች በሚገልጸው ሐሳብ ላይ ይህ ቃል ለየት ባለ መንገድ ተሠርቶበታል።

2 ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በዳግም ፍጥረት የሰው ልጅ፣ ክብር በተላበሰው ዙፋኑ ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ እኔን የተከተላችሁኝ እናንተም በአሥራ ሁለት ዙፋኖች ላይ ተቀምጣችሁ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።” በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጹት “አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች” የኢየሱስ ቅቡዓን ደቀ መዛሙርት የሚፈርዱላቸውንና ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ያመለክታሉ። እነዚህ ሰዎች 144,000ዎቹ ከሚያከናውኑት የክህነት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ይሆናሉ።

3, 4. ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን ምን ግሩም ምሳሌ ትተዋል?

3 በጥንት ዘመን ይኖሩ እንደነበሩት ካህናትና ሌዋውያን ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉት ቅቡዓንም አገልግሎታቸውን እንደ ታላቅ መብት ይቆጥሩታል። (ዘኍ. 18:20) ቅቡዓኑ በምድር ላይ ርስት ወይም ውርስ እንደሚሰጣቸው አይጠብቁም። ከዚህ ይልቅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማይ ነገሥታትና ካህናት የመሆን ተስፋ አላቸው። በሰማይ ያሉት ቅቡዓን ስላሉበት ሁኔታ የሚገልጸው በ⁠ራእይ 4:10, 11 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እንደሚጠቁመው ቅቡዓኑ በተመደቡበት ቦታ ሆነው ይሖዋን ማገልገላቸውን ይቀጥላሉ።​—ሕዝ. 44:28

4 በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ድርሻቸው ይሖዋ እንደሆነ በአኗኗራቸው ያሳያሉ። አምላክን የማገልገል መብታቸውን እጅግ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያምኑ ከመሆኑም በላይ ኢየሱስን ያለማቋረጥ ይከተሉታል፤ በዚህ መንገድ ‘መጠራታቸውንና መመረጣቸውን አስተማማኝ ለማድረግ’ ይጥራሉ። (2 ጴጥ. 1:10) እነዚህ ቅቡዓን በግለሰብ ደረጃ ያሉበት ሁኔታ ይለያያል፤ ችሎታቸውም ቢሆን ተመሳሳይ አይደለም። ሆኖም ያለባቸውን የአቅም ገደብ እንደ ሰበብ አድርገው በማቅረብ በአምላክ አገልግሎት መጠነኛ ተሳትፎ በማድረግ ብቻ አይወሰኑም። ይልቁንም አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ሁሉ በማድረግ ለአምላክ አገልግሎት ቅድሚያውን ይሰጣሉ። ቅቡዓኑ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ላላቸው ሰዎች ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ።

5. ሁሉም ክርስቲያኖች ይሖዋን ድርሻቸው ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህስ አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

5 ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ይሁን በምድር ላይ መኖር ‘ራሳችንን መካድ እንዲሁም የራሳችንን የመከራ እንጨት ተሸክመን ክርስቶስን ያለማቋረጥ መከተል’ ይኖርብናል። (ማቴ. 16:24) ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋን የሚያመልኩ ከመሆኑም ሌላ ክርስቶስን ያለማቋረጥ እየተከተሉት ነው። ብዙ ነገሮችን ማከናወን እንደሚችሉ እያወቁ ትንሽ ነገር በመሥራት ብቻ ረክተው አይቀመጡም። በርካቶች ሕይወታቸውን ቀላል በማድረግ አቅኚ ሆነው ለማገልገል ተነሳስተዋል። ሌሎች በየዓመቱ ለተወሰኑ ወራት ረዳት አቅኚ መሆን ችለዋል። በአቅኚነት ማገልገል ያልቻሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ደግሞ በአገልግሎቱ በትጋት ይካፈላሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ከሆነችውና በኢየሱስ ራስ ላይ ሽቶ ካፈሰሰችው ከማርያም ጋር ይመሳሰላሉ። ኢየሱስ “እሷ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች። . . . የምትችለውን አድርጋለች” ብሏል። (ማር. 14:6-8) ሰይጣን በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ ስለምንኖር የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንደምናስበው ቀላል ላይሆን ይችላል። ያም ሆኖ ከፍተኛ ተጋድሎ የምናደርግ ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ እንታመናለን። እስቲ ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን አራት መንገዶች እንመልከት።

ከሁሉ አስቀድሞ የአምላክን መንግሥት መፈለግ

6. (ሀ) ብዙዎች ዕድል ፈንታቸው ይህችው ሕይወት ብቻ እንደሆነች የሚያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) የዳዊት ዓይነት አመለካከት ማዳበራችን የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?

6 ኢየሱስ ተከታዮቹን ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ እንዲፈልጉ አስተምሯቸዋል። በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎች “ዕድል ፈንታቸው ይህችው ሕይወት ብቻ [ስለሆነች]” የግል ጥቅማቸውን ማስቀደም ይቀናቸዋል። (መዝሙር 17:1, 13-15ን አንብብ።) ብዙዎች በሕይወታቸው ውስጥ ለፈጣሪያቸው ጨርሶ ቦታ አይሰጡም፤ ከዚህ ይልቅ በዋነኝነት ትኩረት የሚያደርጉት የተመቻቸ ሕይወት በመኖር፣ ቤተሰብ በመመሥረትና ለልጆቻቸው ጥሪት በማስቀረት ላይ ነው። ዕድል ፈንታቸው ይህችው ሕይወት ብቻ ናት። በሌላ በኩል ግን ዳዊት በዋነኝነት ያሳስበው የነበረው በይሖዋ ዘንድ “መልካም ስም” ማትረፉ ነበር፤ ቆየት ብሎም ልጁ ሰለሞን ሁላችንም እንዲህ እንድናደርግ አበረታቶናል። (መክ. 7:1) ልክ እንደ አሳፍ፣ ዳዊትም በሕይወቱ ውስጥ የራሱን ፍላጎት ከማስቀደም ይበልጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ከይሖዋ ጋር ያለው ወዳጅነት መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። አካሄዱን ከአምላክ ጋር በማድረጉ ደስተኛ ነበር። በጊዜያችንም በርካታ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ከሰብዓዊ ሥራቸው አስቀድመዋል።

7. አንድ ወንድም የአምላክን መንግሥት በማስቀደሙ ምን በረከት አግኝቷል?

7 በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የሚኖረውን ዣን ክሎድን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ሲሆን በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። በሚኖርበት አካባቢ ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ አብዛኞቹ ሰዎች ከሥራቸው ላለመፈናቀል ሲሉ የማያደርጉት ነገር የለም። አንድ ቀን የመሥሪያ ቤቱ የምርት ክፍል ኃላፊ፣ ዣን ክሎድን ምሽት ላይ ከ12:30 ጀምሮ ሥራ እንዲገባ እንዲሁም በሳምንቱ ውስጥ ሰባቱንም ቀን እንዲሠራ አዘዘው። ዣን ክሎድ፣ ለኃላፊው የቤተሰቡን ቁሳዊ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ፍላጎትም የማሟላት ኃላፊነት እንዳለበት ሊያስረዳው ሞከረ። ከዚህም በተጨማሪ ጉባኤውን የመርዳት ኃላፊነት እንዳለበት ገለጸለት። ኃላፊው ምን ምላሽ ሰጠው? እንዲህ አለው፦ “ዕድለኛ ሆነህ ሥራ ካገኘህ ሚስትህን፣ ልጆችህን፣ ያሉብህን ችግሮችና ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ከአእምሮህ ማውጣት ይኖርብሃል። መላ ሕይወትህን ለሥራህ መስጠት አለብህ፤ ከሥራህ በስተቀር ሁሉንም ነገር መርሳት ይኖርብሃል። ምርጫው የአንተ ነው፦ ሃይማኖትህ ይሻልሃል ወይስ ሥራህ?” አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ዣን ክሎድ ሥራውን ቢያጣ አምላክ እንደሚንከባከበው ያውቅ ነበር። በአምላክ አገልግሎት ብዙ የሚሠራው ነገር የሚኖረው ከመሆኑም ሌላ የቤተሰቡን ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት እንዲችል ይሖዋ ይረዳዋል። ይህን ስለተገነዘበ ሌላ ጊዜ እንደሚያደርገው ሁሉ በሳምንቱ መሃል በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኘ። ከዚያም በሥራው መቀጠል መቻሉን እርግጠኛ ባይሆንም ወደ ሥራ ለመሄድ መዘገጃጀት ጀመረ። በዚህ ጊዜ ስልክ ተደወለለትና ኃላፊው ከሥራ እንደተባረረ ተነገረው። ወንድማችን ግን ከሥራ ገበታው አልተፈናቀለም።

8, 9. ይሖዋን ድርሻችን በማድረግ ረገድ የካህናቱንና የሌዋውያኑን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

8 አንዳንዶች ሥራቸውን የማጣት አደጋ ሲደቀንባቸው ‘ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን የማሟላት ኃላፊነቴን እንዴት መወጣት እችላለሁ?’ ብለው ያስቡ ይሆናል። (1 ጢሞ. 5:8) እንዲህ የመሰለ ሁኔታ አጋጥሞህ ቢያውቅም ባያውቅም አምላክን ድርሻህ የምታደርግና እሱን የማገልገል መብትህን እጅግ ከፍ አድርገህ የምትመለከት ከሆነ ይሖዋ እንደማያሳፍርህ ከራስህ ተሞክሮ ሳትገነዘብ አትቀርም። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥት መፈለጋቸውን እንዲቀጥሉ በነገራቸው ጊዜ ‘እነዚህ ነገሮች ሁሉ’ ይኸውም ምግብ፣ መጠጥ፣ ልብስና የመሳሰሉት ነገሮች “ይሰጧችኋል” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል።​—ማቴ. 6:33

9 በተስፋይቱ ምድር ርስት ያልተሰጣቸውን ሌዋውያንን አስብ። በዋነኝነት የሚያሳስቧቸው ከንጹሕ አምልኮ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ስለነበሩ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በተመለከተ በይሖዋ መታመን ነበረባቸው፤ እሱ “ድርሻህ . . . እኔ ነኝ” ብሏቸው ነበር። (ዘኍ. 18:20) ካህናትና ሌዋውያን ያደርጉት እንደነበረው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባናገለግልም ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን በመተማመን የእነሱን ዓይነት አመለካከት ማዳበር እንችላለን። ወደ መጨረሻው ዘመን ማብቂያ ይበልጥ በቀረብን መጠን አምላክ የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን መተማመናችን ይበልጥ አስፈላጊ ነው።​—ራእይ 13:17

ከሁሉ አስቀድሞ የአምላክን ጽድቅ መፈለግ

10, 11. አንዳንዶች ከሰብዓዊ ሥራ ጋር በተያያዘ በይሖዋ የታመኑት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

10 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን . . . ጽድቅ መፈለጋችሁን ቀጥሉ” በማለትም አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 6:33) ይህ ሲባል ትክክል ወይም ስህተት ስለሆኑት ነገሮች ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ከሰብዓዊ መሥፈርቶች ማስቀደም ማለት ነው። (ኢሳይያስ 55:8, 9ን አንብብ።) ብዙዎች ክርስቲያኖች ከመሆናቸው በፊት ትንባሆ በማምረትና የትንባሆ ምርቶችን በመሸጥ ወይም ሌሎችን ለውትድርና በማሠልጠን አሊያም የጦር መሣሪያዎችን በማምረትና በመሸጥ ይተዳደሩ እንደነበር ታውቅ ይሆናል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ እውነትን ሲያውቁ ሥራቸውን በመለወጥ ለጥምቀት ብቁ ሆነዋል።​—ኢሳ. 2:4፤ 2 ቆሮ. 7:1፤ ገላ. 5:14

11 አንድሩ በዚህ ረገድ ምሳሌ ይሆነናል። አንድሩና ባለቤቱ ስለ ይሖዋ ሲያውቁ እሱን ለማገልገል ወሰኑ። አንድሩ ሥራውን በጣም ይወደው የነበረ ቢሆንም ሥራውን ለቀቀ። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? ይሠራበት የነበረው ድርጅት ከውትድርና ጋር የተያያዘ ሲሆን አንድሩ ደግሞ የአምላክን ጽድቅ ለማስቀደም ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። አንድሩ ሥራውን በለቀቀበት ጊዜ ሁለት ልጆች የነበሩት ከመሆኑም ሌላ የገቢ ምንጭ አልነበረውም፤ ያለው ገንዘብም ቢሆን ከጥቂት ወራት በላይ ሊያኖራቸው የሚችል አልነበረም። ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ምንም ዓይነት ‘ውርስ’ ያለው አይመስልም ነበር። አንድሩ በአምላክ በመታመን ሥራ መፈለግ ጀመረ። እሱና ቤተሰቡ ያሳለፉትን ጊዜ መለስ ብለው ሲያስቡት የይሖዋ እጅ አጭር እንዳልነበረ አፋቸውን ሞልተው መናገር ይችላሉ። (ኢሳ. 59:1) አንድሩና ባለቤቱ አኗኗራቸውን ቀላል በማድረግ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል እንኳ ችለዋል። አንድሩ እንዲህ ብሏል፦ “ከገንዘብ፣ ከቤት፣ ከጤና እንዲሁም ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ የተጨነቅንባቸው ወቅቶች ነበሩ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን አልተለየንም። . . . ይሖዋን ማገልገል የሰው ልጆች ሊያከናውኗቸው ከሚገቡ ሥራዎች ሁሉ እጅግ የላቀና የሚክስ ስለመሆኑ ምንም ጥያቄ እንደሌለው በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን።” *​—መክ. 12:13

12. የአምላክን መሥፈርቶች ለማስቀደም የትኛውን ባሕርይ ማዳበር ያስፈልጋል? አንተ የምታውቀው ተሞክሮ ካለ ተናገር።

12 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያክል እምነት ካላችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም።” (ማቴ. 17:20) አንተስ የአምላክን መሥፈርቶች ማስቀደም ችግር የሚያስከትልብህ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ታደርጋለህ? ይህን ማድረግ መቻልህን እርግጠኛ ካልሆንክ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖችን አነጋግራቸው። ተሞክሯቸውን መስማትህ በመንፈሳዊ እንደሚያበረታታህ ጥርጥር የለውም።

የይሖዋን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ማድነቅ

13. በይሖዋ አገልግሎት በትጋት ስንካፈል ከመንፈሳዊ ዝግጅቶች ጋር በተያያዘ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

13 ይሖዋን የማገልገል መብትህን ከፍ አድርገህ የምትመለከተው ከሆነ ይሖዋ ለሌዋውያኑ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች እንደሰጣቸው ሁሉ ለአንተም ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎቶችህን እንደሚያሟላልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዳዊት በዋሻ ውስጥ የነበረ ቢሆንም አምላክ የሚያስፈልገውን እንደሚያሟላለት ይተማመን ነበር። እኛም አንድ ችግር አጋጥሞን መውጫ ቀዳዳ እንደሌለን በሚሰማን ጊዜም እንኳ በይሖዋ መታመን እንችላለን። አሳፍ ይረብሸው የነበረው ነገር ምን እንደሆነ ማስተዋል የቻለው “ወደ አምላክ መቅደስ” በመጣ ጊዜ እንደሆነ አስታውስ። (መዝ. 73:17) እኛም በተመሳሳይ አምላክ፣ መንፈሳዊ ማዕድ እንድናገኝ ካደረገው ዝግጅት መጠቀም ይኖርብናል። እንዲህ ስናደርግ ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን አምላክን የማገልገል መብታችንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው እናሳያለን። በዚህ መንገድ ይሖዋ ድርሻችን እንዲሆን እናደርጋለን።

14, 15. ከአንዳንድ ጥቅሶች ጋር በተያያዘ መንፈሳዊ ብርሃን ሲበራ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ለምንስ?

14 የመንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ የሆነው ይሖዋ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ‘የአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ ላይ ብርሃን በሚፈነጥቅበት ጊዜ ምን ይሰማሃል? (1 ቆሮ. 2:10-13) ኢየሱስ ተከታዮቹን “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁና ደሙን ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም” ባላቸው ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠው ምላሽ ጥሩ ትምህርት ይዞልናል። በርካታ ደቀ መዛሙርት ይህን ሐሳብ ቃል በቃል በመረዳት “ይህ የሚሰቀጥጥ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ። በመሆኑም “ትተውት ወደነበረው ነገር ተመለሱ።” ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት ተናገረ።​—ዮሐ. 6:53, 60, 66, 68

15 ኢየሱስ ሥጋውን ስለ መብላትና ደሙን ስለ መጠጣት የተናገረውን ሐሳብ ጴጥሮስ ሙሉ በሙሉ አልተረዳውም። ያም ሆኖ ይህ ሐዋርያ፣ አምላክ መንፈሳዊ ብርሃን እንደሚፈነጥቅለት እምነት ነበረው። ከአንዳንድ ጥቅሶች ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መንፈሳዊ ብርሃን ሲበራ ማስተካከያው እንዲደረግ ምክንያት የሆኑትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥቦች ለመረዳት ጥረት ታደርጋለህ? (ምሳሌ 4:18) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የቤርያ ክርስቲያኖች “በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀብለዋል።” (ሥራ 17:11) እነዚህን ክርስቲያኖች መምሰልህ ይሖዋን የማገልገልና እሱን ድርሻህ የማድረግ መብትህን ይበልጥ እንድታደንቅ ያደርግሃል።

በጌታ ብቻ ማግባት

16. በ⁠1 ቆሮንቶስ 7:39 ላይ ከሚገኘው ትእዛዝ ጋር በተያያዘ አምላክ ድርሻችን መሆኑን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ክርስቲያኖች ለአምላክ ዓላማ ቅድሚያ እንደሚሰጡ የሚያሳዩበት ሌላው መንገድ ደግሞ “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ የሚያዝዘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ነው። (1 ቆሮ. 7:39) ብዙዎች ይህን መለኮታዊ መመሪያ ከመጣስ ይልቅ ነጠላ ሆነው ለመኖር መርጠዋል። ይሖዋም እንዲህ ያሉትን ክርስቲያኖች በደግነት ይንከባከባቸዋል። ዳዊት ብቸኝነት በተሰማውና አይዞህ ባይ ባጣበት ጊዜ ምን አደረገ? “መንፈሴ በውስጤ ሲዝል” “ብሶቴን [በአምላክ ፊት] አፈስሳለሁ፤ ችግሬንም በፊቱ እናገራለሁ” ብሏል። (መዝ. 142:1-3) ለበርካታ ዓመታት ነጠላ ሆኖ አምላክን በታማኝነት ያገለገለው ነቢዩ ኤርምያስም ተመሳሳይ ስሜት ሳያድርበት አልቀረም። ከኤርምያስ ምሳሌ ለመጠቀም በኤርምያስ በኩል የተላለፈልን የአምላክ ቃል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8⁠ን መመልከት ትችላለህ።

17. ነጠላ የሆነች አንዲት እህት አልፎ አልፎ የሚሰማትን የብቸኝነት ስሜት ለመቋቋም የረዳት ምንድን ነው?

17 በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ነጠላ ሆኜ የመኖር ዓላማ የለኝም። የሚሆነኝን ሰው ሳገኝ ለማግባት ዝግጁ ነኝ። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነችው እናቴ ለትዳር የጠየቀኝን ማንኛውንም ሰው እንዳገባ ትገፋፋኝ ነበር። ትዳሬ ባይሰምር ኃላፊነቱን እሷ ትወስድ እንደሆነ ጠየቅኳት። ከጊዜ በኋላ ግን ጥሩ ሥራ እንዳለኝ፣ ራሴን ችዬ እንደምኖርና ደስተኛ እንደሆንኩ አስተዋለች። ከዚያ በኋላ እንዳገባ መጎትጎቷን አቆመች።” እርግጥ ነው፣ ይህች እህት አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነት ይሰማታል። “በዚህ ጊዜ ይበልጥ በይሖዋ ለመተማመን ጥረት አደርጋለሁ። እሱም ፈጽሞ አልተወኝም” በማለት ተናግራለች። በይሖዋ እንድትተማመን የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ጸሎት፣ አምላክ እውን እንዲሆንልኝና ፈጽሞ ብቻዬን እንዳልሆንኩ እንዲሰማኝ ይረዳኛል። የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ ጸሎቴን ይሰማል፤ ታዲያ አምላክ እንደሚያከብረኝ ቢሰማኝና ደስተኛ ብሆን ምን ያስገርማል?” ይህች እህት “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ [እንደሚያስገኝ]” በመተማመን እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ከሌሎች ምንም ሳልጠብቅ እነሱን ለመርዳት እጥራለሁ። ‘ይህን ሰው ለመርዳት ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ብዬ ሳስብ ውስጣዊ ደስታ አገኛለሁ።” (ሥራ 20:35) በእርግጥም ይህች እህት ይሖዋን ድርሻዋ ያደረገችው ሲሆን እሱን የማገልገል መብት በማግኘቷ ደስተኛ ናት።

18. ይሖዋ ድርሻው እንድትሆን ሊያደርግህ ይችላል ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

18 ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ አምላክ ድርሻህ እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ። እንዲህ ስታደርግ ደስተኛ ከሆኑት ሕዝቦቹ መካከል አንዱ ትሆናለህ። (2 ቆሮ. 6:16, 17) ይህም ባለፉት ዘመናት እንደነበሩት የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ የይሖዋ ድርሻ ለመሆን ያስችልሃል። (ዘዳግም 32:9, 10ን አንብብ።) እስራኤላውያን ከሌሎች ብሔራት ተለይተው የአምላክ ድርሻ እንደሆኑ ሁሉ ይሖዋ አንተንም የራሱ ንብረት እንደሆንክ አድርጎ ሊቆጥርህና በፍቅር ሊንከባከብህ ይችላል።​—መዝ. 17:8

[የግርጌ ማስታወሻ]

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ከሁሉ አስቀድመህ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ በመፈለግ ይሖዋን ድርሻህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

• ለመንፈሳዊ ምግብ አድናቆት በማሳየት ይሖዋን ድርሻህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

• አምላክ፣ በጌታ ብቻ እንድናገባ የሰጠንን ትእዛዝ በመጠበቅ ይሖዋን ድርሻህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአምላክ አገልግሎት ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ይሖዋ ድርሻችን ይሆናል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤርምያስ የሚያበረታታ ምሳሌ ትቶልናል