በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

1 ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም​—ይህ እውነት ነው?

1 ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም​—ይህ እውነት ነው?

1 ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም​—ይህ እውነት ነው?

እንዲህ ሲባል ሰምተህ ይሆናል፦ “አምላክ ነገሮችን የሚያከናውነው ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ነው።”

“አብን መረዳት አዳጋች ነው፤ ወልድን መረዳት አዳጋች ነው፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን መረዳት አዳጋች ነው።”​—የአትናቴዎስ ድንጋጌ፣ ይህ በርካታ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ስለ ሥላሴ የሚያስተምሩት ትምህርት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? ኢየሱስ ‘ብቸኛ ስለሆነው እውነተኛ አምላክ እውቀት መቅሰማቸውን የሚቀጥሉ’ ሰዎች በረከት እንደሚያገኙ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) ይሁንና አምላክ ሚስጥር ከሆነ ስለ እሱ እውቀት መቅሰም የምንችለው እንዴት ነው? አምላክ ሰው ሁሉ እንዲያውቀው ይፈልጋል እንጂ ማንነቱን አይሰውርም።​—ኤርምያስ 31:34

እርግጥ ነው፣ መቼም ቢሆን ስለ አምላክ ሁሉንም ነገር ማወቅ አንችልም። ይህ ደግሞ የሚጠበቅ ነገር ነው፤ ምክንያቱም የእሱ አስተሳሰብና መንገድ ከእኛ በእጅጉ የላቀ ነው።​—መክብብ 3:11፤ ኢሳይያስ 55:8, 9

እውነቱን ማወቅህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው? አምላክ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ሚስጥር ከሆነ እሱን ለማወቅ ጥረት ማድረግ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አምላክ እሱን በሚገባ እንድናውቀው ብቻ ሳይሆን ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርትም ይረዳናል። እንዲያውም ታማኝ የነበረውን አብርሃምን “ወዳጄ” ብሎ ጠርቶታል፤ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ደግሞ “እግዚአብሔር ለሚታዘዙት ሁሉ ወዳጃቸው ነው” በማለት ጽፏል።​—ኢሳይያስ 41:8፤ መዝሙር 25:14 የ1980 ትርጉም

ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ፈጽሞ የማይቻል ነገር እንደሆነ ይሰማሃል? እንደዚያ ይሰማህ ይሆናል፤ ሆኖም በ⁠ሐዋርያት ሥራ 17:27 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ልብ በል፦ “[አምላክ] ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም።” እንዲህ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? እሱን በሚገባ ማወቅ እንድንችል የሚረዳንን ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላሰፈረልን ነው። *

አምላክ ስሙ ይሖዋ እንደሆነ ነግሮናል። (ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም) ስሙ የሚወክለውን አካል ማወቅ እንድንችል ለሰው ልጆች ያደረጋቸው ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገቡ አድርጓል። ከዚህም በላይ ለሰዎች ያለውን ስሜት ገልጿል። አምላክ ‘ሩኅሩኅ፣ ቸር፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ’ ነው። (ዘፀአት 34:6) እኛ የምናደርገው ነገር ሊያስደስተው ወይም ሊያሳዝነው ይችላል። ለምሳሌ የጥንቱ የእስራኤል ብሔር በእሱ ላይ ባመፀ ጊዜ ‘አዝኗል’፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች በጥበብ ጎዳና በመመላለስ እሱን ሲታዘዙት ይደሰታል።​—መዝሙር 78:40፤ ምሳሌ 27:11

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ምን እንደሚል ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ተመልከት።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ የሚስጥረ ሥላሴ ክፍል ከሆነ እንዴት እሱን ማወቅ ይቻላል?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

The Trinity c.1500, Flemish School, (16th century) / H. Shickman Gallery, New York, USA / The Bridgeman Art Library International