በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

2 አምላክ ስለ እኛ አያስብም​—ይህ እውነት ነው?

2 አምላክ ስለ እኛ አያስብም​—ይህ እውነት ነው?

2 አምላክ ስለ እኛ አያስብም​—ይህ እውነት ነው?

እንዲህ ሲባል ሰምተህ ይሆናል፦ “አምላክ በእርግጥ ስለ ሰው ልጆች የሚያስብ ቢሆን ኖሮ በዓለም ላይ የሚታየውን ክፋትና መከራ ያስወግድ ነበር። በጥቅሉ ስለ ሰው ልጆች ያስባል ቢባል እንኳ እኔ ስላለሁበት ሁኔታ ያስባል ማለት ይከብደኛል።”

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? ይሖዋ አምላክ የክፋት መንስኤ አይደለም። (ያዕቆብ 1:13) ምንም እንኳ ክፋትን በፈለገው ጊዜ ማስወገድ ቢችልም በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ የተነሱ መልስ የሚያሻቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች እልባት እንዲያገኙ ለማስቻል ሲል ብልሹ የሆነው ኅብረተሰብ ለጊዜውም ቢሆን እንዲቀጥል ፈቅዷል። ለሰው ልጆች ጥቅም ብሎ እርምጃ የሚወስድበትና የእሱን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረኝ ያሉ ሰዎች ያስከተሏቸውን ችግሮች በሙሉ የሚያስወግድበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም።​—ዘፍጥረት 3:1-6፤ ኢሳይያስ 65:17 *

አምላክ ለሰው ዘር በሙሉ የሚያስብ ከመሆኑም አልፎ በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዳችን ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠን አሳይቷል። ስለ ራሳችን የማናውቃቸውን ጥቃቅን ነገሮች እንኳ እንደሚያስተውል ማቴዎስ 10:29-31 ላይ ያለው ሐሳብ ያሳያል፦ “ሁለት ድንቢጦች የሚሸጡት አነስተኛ ዋጋ ባላት ሳንቲም አይደለም? ሆኖም ከእነሱ አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም። የእናንተ ግን የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል። ስለዚህ አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።”

እውነቱን ማወቅህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው? በጥቅሉ ሲታይ ክፉ ከሆኑ ወይም አሳቢነት ከሚጎድላቸው ሰዎች ጋር መቀራረብ እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። አምላክ ለእኛ ግድ የለውም የሚለው ውሸት፣ ብዙ ሰዎች ከናካቴው ስለ እሱ የማወቅ ፍላጎት እንዳይኖራቸው ወይም ምርጫ ሲያጡ ብቻ ወደ እሱ ዞር እንዲሉ ያደረጋቸው መሆኑ ምንም አያስገርምም። ይሖዋ አምላክ በእርግጥ ስለ አንተ እንደሚያስብ ማወቅህ ስለ እሱ ይበልጥ ለመማርና ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ሊያነሳሳህ ይችላል።

ለምሳሌ ያህል፣ ወደ አምላክ ብትጸልይም እንኳ ‘ጸሎቴን ሰምቶኝ ይሆን? ደግሞስ ይመልስልኝ ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። “ጸሎትን የምትሰማ” ተብሎ የተገለጸው አምላክ በቅን ልብ ተነሳስተው ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሁሉ ይህን የግንኙነት መስመር ምንጊዜም ክፍት እንደሚያደርግላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ዋስትና ይሰጠናል።​—መዝሙር 65:2

አምላክ ያቀረበልንን ግብዣ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።” (1 ጴጥሮስ 5:7) አዎ፣ አምላክ በአስቸጋሪ ጊዜም እንኳ እንደሚያስብልን መተማመን እንችላለን፤ ምክንያቱም ቃሉ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” ይላል።​—መዝሙር 34:18

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ የማያስብልን ከሆነ ወደ እሱ እንድንጸልይ ለምን ይጋብዘናል?