በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

4 አምላክ ያዳላል​—ይህ እውነት ነው?

4 አምላክ ያዳላል​—ይህ እውነት ነው?

4 አምላክ ያዳላል​—ይህ እውነት ነው?

እንዲህ ሲባል ሰምተህ ይሆናል፦ “አምላክ ዓለምን ሙሉ በሙሉ ስለሚቆጣጠር ያለ እሱ ፈቃድ የሚሆን አንዳች ነገር የለም። በዓለም ላይ ተንሰራፍቶ ለሚታየው አድልዎ፣ ኢፍትሐዊነትና ጭቆና ተጠያቂው እሱ ነው።”

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? በዓለም ላይ ለሚታየው የፍትሕ መጓደል ተጠያቂው አምላክ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው።”​—ዘዳግም 32:4

አምላክ ለሰዎች ሁሉ ደግነት ያሳያል፤ ሌላው ቀርቶ የሚገባቸው አይደሉም ተብለው ለሚታሰቡ ሰዎችም ጭምር ደግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ “እሱ በክፉና በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣል፤ ጻድቅ በሆኑና ጻድቅ ባልሆኑ ሰዎች ላይም ዝናብ ያዘንባል።” (ማቴዎስ 5:45) የተለያየ ዘርና ባሕል ያላቸውን ሰዎች በእኩል ዓይን ያያል፤ የዚህን እውነተኝነት የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ማየት እንችላለን፦ “አምላክ [አያዳላም] . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”

ታዲያ የፍትሕ መጓደል መንስኤው ምንድን ነው? በርካታ ሰዎች የአምላክን የፍትሕ መንገድ ከመከተል ይልቅ ተገቢ ያልሆነ ነገር ለማድረግ መርጠዋል። (ዘዳግም 32:5) በተጨማሪም አምላክ፣ ጠላቱ የሆነው ዲያብሎስ ዓለምን እንዲቆጣጠር መፍቀዱን መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። * (1 ዮሐንስ 5:19) ይሁን እንጂ አምላክ ፍትሕ የጎደለው አገዛዝ እንዲቀጥል የፈቀደበት ጊዜ በቅርቡ ያበቃል። ደግሞም “የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ” የሚያስችለውን መንገድ ቀይሷል።​—1 ዮሐንስ 3:8

እውነቱን ማወቅህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው? ማብቂያ የሌላቸው ስለሚመስሉ የሙስና፣ የጭቆና እና የፍትሕ መጓደል ድርጊቶች ስትሰማ ግራ ትጋባ ይሆናል። የችግሩን መንስኤ ማወቅህ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ይህን ያህል አስከፊ የሆነውና የሰው ልጅ አቅሙ የፈቀደለትን ሁሉ ጥረት ቢያደርግም ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ የሄዱት ለምን እንደሆነ እንድትገነዘብ ያስችልሃል። (መዝሙር 146:3) ለጊዜው ብቻ መፍትሔ በሚያስገኙ ነገሮች ላይ ጊዜና ጉልበት ከማባከን ይልቅ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት በማሳደር የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አስተማማኝ ተስፋ ሊኖርህ ይችላል።​—ራእይ 21:3, 4

ኢፍትሐዊነት እንዲነግሥ ምክንያት የሆነውን ዋነኛ መንስኤ መረዳታችን በተለይ መከራ በእኛ ላይ በሚደርስበት ጊዜ ይጠቅመናል። አግባብ ያልሆነ ነገር ሲፈጸምብን የአምላክ አገልጋይ እንደነበረው እንደ ዕንባቆም “ሕግ ላልቶአል፤ ፍትሕ ድል አይነሣም” በማለት ብሶታችንን እናሰማ ይሆናል። (ዕንባቆም 1:4) ዕንባቆም እንዲህ በማለቱ አምላክ አልወቀሰውም። እንዲያውም አምላክ ሁኔታዎችን የሚያስተካክልበት ጊዜ እንደቀጠረ በመግለጽ አገልጋዩን ያጽናናው ከመሆኑም ሌላ ችግር እያለም እንዴት ደስተኛ ሆኖ መኖር እንደሚችል በመንገር ረድቶታል። (ዕንባቆም 2:2-4፤ 3:17, 18) አንተም ብትሆን አምላክ ኢፍትሐዊነትን እንደሚያስወግድ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት ማሳደርህ ፍትሕ በጎደለው ዓለም ውስጥ ተረጋግተህና የአእምሮ ሰላምህን ጠብቀህ እንድትኖር ይረዳሃል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ዲያብሎስ የመጣው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ በምድር ላይ ለሚታየው መከራና ፍትሕ የጎደለው ድርጊት በእርግጥ ተጠያቂ ነው?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]

© Sven Torfinn/Panos Pictures