በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

5 አምላክ በቅንነት የሚቀርብ አምልኮን ሁሉ ይቀበላል​—ይህ እውነት ነው?

5 አምላክ በቅንነት የሚቀርብ አምልኮን ሁሉ ይቀበላል​—ይህ እውነት ነው?

5 አምላክ በቅንነት የሚቀርብ አምልኮን ሁሉ ይቀበላል​—ይህ እውነት ነው?

እንዲህ ሲባል ሰምተህ ይሆናል፦ “ወደ አንድ ቦታ መድረስ የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች ወይም ጎዳናዎች እንዳሉ ሁሉ ወደ አምላክ የሚያደርሱም ብዙ መንገዶች አሉ። እያንዳንዱ ሰው ወደ አምላክ መድረስ የሚችልበትን የራሱን መንገድ መፈለግ ይኖርበታል።”

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? ማስመሰልንና ግብዝነትን በማስወገድ አምልኳችንን በቅን ልብ ተነሳስተን ማከናወን ይኖርብናል። ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች አምላክ የተዋቸው ለምን እንደሆነ እንዲህ በማለት ነግሯቸዋል፦ “ኢሳይያስ፣ ግብዞች ስለሆናችሁት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፦ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው።’” (ማርቆስ 7:6) ይሁንና አምልኳችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በቅን ልቦና የቀረበ መሆኑ ብቻውን በቂ አይደለም።

ኢየሱስ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮቻቸው በሚያቀርቡት አምልኮ ላይ የሚንጸባረቀውን መሠረታዊ ችግር በማጋለጥ ይህን ሐቅ ግልጽ አድርጓል። ኢየሱስ፣ “የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው” የሚለው ሐሳብ በእነሱ ላይ ተፈጻሚነት እንዳለው ተናግሯል። (ማርቆስ 7:7) ከአምላክ መሥፈርቶች ይልቅ ሃይማኖታዊ ወጋቸውን ያስቀድሙ ስለነበር አምልኳቸው “ከንቱ” ወይም የማይረባ ሊሆን ችሏል።

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አምላክ የሚያደርሱ ተቀባይነት ያላቸው በርካታ መንገዶች አሉ የሚለውን ሐሳብ አይደግፍም፤ ከዚህ ይልቅ መንገዱ አንድ ብቻ እንደሆነ ያስተምራል። ማቴዎስ 7:13, 14 እንዲህ ይላል፦ “በጠባቡ በር ግቡ፣ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅና ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው። ወደ ሕይወት የሚያስገባው በር ግን ጠባብ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።”

እውነቱን ማወቅህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው? ማራቶን ለመሮጥ ለበርካታ ወራት ዝግጅት ስታደርግ ቆይተሃል እንበል። ከዚያም ሩጫውን በአንደኝነት አጠናቀቅክ፤ ሆኖም ከውድድሩ ደንቦች መካከል አንዱን ባለማወቅ በመጣስህ ሽልማቱን እንደማታገኝ ቢነገርህ ምን ይሰማሃል? ልፋትህ ሁሉ መና እንደቀረ ሊሰማህ ይችላል። ለአምላክ ከምናቀርበው አምልኮ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ነገር ሊከሰት ይችላል?

ሐዋርያው ጳውሎስ አምልኳችንን ከአትሌቲክስ ውድድር ጋር በማነጻጸር እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በውድድር የሚካፈል ሰውም ቢሆን የውድድሩን ደንብ ጠብቆ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አይሸለምም።” (2 ጢሞቴዎስ 2:5) የአምላክን ሞገስ የምናገኘው ‘ደንቡን’ ጠብቀን ይኸውም እሱ በሚፈልገው መንገድ ካመለክነው ብቻ ነው። አንድ ሯጭ የፈለገበት ቦታ ሮጦ የውድድሩ አሸናፊ ለመባል ተስፋ እንደማያደርግ ሁሉ እኛም ወደ አምላክ መድረስ የምንችልበትን የራሳችንን መንገድ የመምረጥ መብት የለንም።

አምላክን ማስደሰት እንድንችል አምልኳችን ስለ እሱ ከሚነገሩ ውሸቶች የጸዳ መሆን አለበት። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት [ያመልኩታል]” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:23) ወደ አምላክ የሚያደርሰው ትክክለኛ መንገድ የቱ እንደሆነ የሚነግረን ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።​—ዮሐንስ 17:17 *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 አምላክ የሚቀበለውን አምልኮ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 15 ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሁሉም ሃይማኖቶች፣ ሰዎች አምላክን እሱ በሚፈልገው መንገድ እንዲያመልኩት ያስተምራሉ?