በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአምላክ ሕዝብ ጥብቅና ቆማለች

ለአምላክ ሕዝብ ጥብቅና ቆማለች

በእምነታቸው ምሰሏቸው

ለአምላክ ሕዝብ ጥብቅና ቆማለች

አስቴር በሱሳ ቤተ መንግሥት ወደሚገኘው ውስጠኛ አደባባይ እየተቃረበች ስትመጣ ራሷን ለማረጋጋት ሞከረች። ሁኔታው ቀላል አልነበረም። በበረዶ በተሸፈኑት የዛግሮስ ተራሮች አጠገብ በጣም ግዙፍ በሆኑ ዐለቶች ላይ የተገነባውና ጥርት ያለ ውኃ ካለው የቾአስፔስ ወንዝ ትይዩ የሚገኘው ይህ ቤተ መንግሥት ክንፍ ያላቸው ኮርማዎች እንዲሁም የቀስተኞችና የአንበሶች ምስል በተቀረጸበት በልዩ ልዩ ቀለማት ባሸበረቀ የሸክላ ግንብ የተሠራ ነው፤ ከዚህም ሌላ ከድንጋይ የተሠሩ ጌጠኛ ዓምዶችና ግዙፍ የሆኑ ሐውልቶች አሉት። ቤተ መንግሥቱ የተገነባበት መንገድ፣ ራሱን “ታላቅ ንጉሥ” ብሎ የሚጠራውና አስቴር ልታነጋግረው የመጣችው ሰው ያለውን ታላቅ ኃይል ሁሉም ሰው እንዲገነዘብ ለማድረግ የታቀደ ነው። የሚገርመው ነገር ይህ ሰው ባሏም ነው።

ባሏ? የትኛዋም ታማኝ አይሁዳዊ ወጣት እንደ ጠረክሲስ ያለ ሰው አገባለሁ የሚል ሐሳብ ፈጽሞ ወደ አእምሮዋ ሊመጣ አይችልም! * ጠረክሲስ እንደ አብርሃም ያሉ ግለሰቦችን አርዓያ አድርጎ የሚመለከት አልነበረም፤ አብርሃም ሚስቱ ሣራ የነገረችውን እንዲሰማ አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ በትሕትና የተቀበለ ሰው ነበር። (ዘፍጥረት 21:12) ይህ ንጉሥ ግን የአስቴር አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋም ሆነ ስለ ሕጎቹ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። ይሁንና ጠረክሲስ፣ አስቴር አሁን ልታደርገው ያሰበችውን ነገር የሚከለክለውን ሕግ ጨምሮ የፋርስን ሕግ በሚገባ ያውቃል። ሕጉ ምን ይላል? ማንኛውም ሰው የፋርስ ንጉሥ ሳይጠራው ወደ እሱ ከገባ በሞት እንዲቀጣ ሕጉ ያዝዛል። አስቴር ንጉሡ ፊት እንድትቀርብ ባትጠራም የመጣው ይምጣ ብላ እሱ ዘንድ ልትገባ ነው። አስቴር፣ ንጉሡ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ሊያያት ወደሚችልበት ወደ ውስጠኛው አደባባይ እየተቃረበች ስትመጣ ወደ ሞት እያመራች እንደሆነ ሳይሰማት አልቀረም።​—አስቴር 4:11፤ 5:1

አስቴር ሕይወቷን አደጋ ላይ መጣል ያስፈለጋት ለምንድን ነው? ይህች ግሩም ሴት ካሳየችው እምነት ምን እንማራለን? በቅድሚያ አስቴር በቀላሉ የማይገኘውን የፋርስ ንግሥት የመሆን አጋጣሚ ማግኘት የቻለችው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

‘እጅግ የተዋበች’

አስቴር አባትና እናቷ የሞቱባት ልጅ ነበረች። ስለ ወላጆቿ የምናውቀው ነገር ቢኖር ሀደሳ የሚል ስም እንዳወጡላት ብቻ ነው፤ ሀደሳ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ባርሰነት” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ይህ ተክል ማራኪ የሆነ ነጭ አበባ ያወጣል። የአስቴር ወላጆች ሲሞቱ ከዘመዶቿ መካከል መርዶክዮስ የተባለ ደግ ሰው የልጅቷ ሁኔታ አሳዝኖት ነበር። አስቴር፣ ለመርዶክዮስ የአጎቱ ልጅ ስትሆን መርዶክዮስም በዕድሜ በጣም ይበልጣታል። አስቴርን ወደ ቤቱ ከወሰዳት በኋላ እንደ ገዛ ልጁ አድርጎ አሳደጋት።​—አስቴር 2:5-7, 15

ግዞተኛ አይሁዳውያን የሆኑት መርዶክዮስና አስቴር የሚኖሩት በፋርስ መዲና ነበር፤ በዚህች ከተማ ሲኖሩ በሃይማኖታቸውና የሙሴን ሕግ ለመከተል በሚያደርጉት ጥረት የተነሳ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሳይጠሉ አይቀሩም። ይሁንና መርዶክዮስ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሕዝቡን ከችግር ስላዳነውና ወደፊትም ሕዝቡን ስለሚያድነው ይሖዋ ስለተባለው መሐሪ አምላክ ለአስቴር ባስተማራት መጠን እርስ በርስ ይበልጥ እንደሚቀራረቡ ምንም ጥያቄ የለውም። (ዘሌዋውያን 26:44, 45) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በአስቴርና በመርዶክዮስ መካከል በፍቅርና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ዝምድና ነበር።

መርዶክዮስ በሱሳ በሚገኘው ቤተ መንግሥት ውስጥ አንድ ዓይነት ኃላፊነት የነበረው ሲሆን ሥራው ከሌሎቹ የንጉሡ አገልጋዮች ጋር በቤተ መንግሥቱ በር ላይ ዘወትር መቀመጥን የሚጠይቅ ሳይሆን አይቀርም። (አስቴር 2:19, 21፤ 3:3) አስቴር የልጅነት ዕድሜዋን እንዴት እንዳሳለፈች የምናውቀው ነገር ባይኖርም በዕድሜ ለሚበልጣት ለመርዶክዮስ የሚያስፈልገውን ትሠራለት እንዲሁም መኖሪያ ቤቱን ጥሩ አድርጋ ትይዝለት እንደነበር ብንናገር ስህተት አይሆንብንም፤ ቤታቸው የሚገኘው ከንጉሡ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ካለው ወንዝ ማዶ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት ሰፈር ሳይሆን አይቀርም። ምናልባትም አስቴር ወርቅና ብር አንጥረኞች እንዲሁም ሌሎች ዕቃዎችን የሚሸጡ ነጋዴዎች ለገበያ ያቀረቧቸውን ነገሮች ለማየት በሱሳ ወዳለው የገበያ ቦታ መሄድ ያስደስታት ይሆናል። እነዚህን የቅንጦት ዕቃዎች እንደ ተራ ነገር የምታይበት ጊዜ እንደሚመጣ ልትገምት እንኳ አትችልም። አዎ፣ ወደፊት ምን እንደሚጠብቃት የምታውቀው አንዳች ነገር አልነበረም።

ንግሥናዋን ያጣች ሴት

አንድ ቀን የሱሳ ከተማ በንጉሡ ቤት ውስጥ ስለተፈጠረው አስደንጋጭ ሁኔታ በሚገልጽ ወሬ ታመሰች። ጠረክሲስ ለመኳንንቱ ባደረገው ድል ያለ ግብዣ ላይ ምግብና የወይን ጠጅ በገፍ እንዲቀርብ አድርጓል፤ ከዚያም ንጉሡ ውብ የሆነችው ንግሥት አስጢን (በወቅቱ ለብቻዋ ለሴቶቹ ግብዣ አዘጋጅታ ነበር) በግብዣው ላይ እንድትገኝ አስጠራት። አስጢን ግን ለመሄድ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። እንደተዋረደ የተሰማውና በቁጣ የገነፈለው ንጉሥ፣ አስጢን እንዴት መቀጣት እንዳለባት ከአማካሪዎቹ ጋር ተነጋገረ። ውጤቱስ ምን ሆነ? አስጢን ከንግሥትነቷ ተሻረች። በመሆኑም ንጉሡ አዲስ ንግሥት መምረጥ እንዲችል አገልጋዮቹ በመላ አገሪቱ እየተዘዋወሩ ቆንጆ ልጃገረዶችን መፈለግ ጀመሩ።​—አስቴር 1:1 እስከ 2:4

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ መርዶክዮስ አስቴርን ሲመለከት ምን ያህል እንደሚደሰት በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንችላለን፤ ትንሿ አስቴር እያደገች እንዲሁም ውበቷ ይበልጥ እየወጣ ሲሄድ መርዶክዮስ በአንድ በኩል ኩራት እንደሚሰማው በሌላ በኩል ደግሞ ሁኔታዋ እንደሚያሳስበው መገመት አያዳግትም። ዘገባው “ይህች ልጃገረድ በተክለ ሰውነቷም ሆነ በመልኳ እጅግ ውብ ነበረች” ይላል። (አስቴር 2:7) አካላዊ ቁንጅና በራሱ ጥሩ ነገር ነው፤ ይሁንና ጥበብና ትሕትና ሊታከልበት ይገባል። ካልሆነ ግን እብሪት፣ ኩራትና በልብ ውስጥ ያሉ ሌሎች መጥፎ ባሕርያት እንዲያቆጠቁጡ ሊያደርግ ይችላል። (ምሳሌ 11:22) ይህ አባባል እውነት መሆኑን የሚያሳይ ነገር አጋጥሞህ ያውቃል? የአስቴር መጨረሻስ ምን ይመስል ይሆን? ውበቷ የኋላ ኋላ ይጠቅማታል ወይስ ይጎዳታል? ይህ ጊዜ የሚያሳየው ነገር ይሆናል።

አስቴር የንጉሡ አገልጋዮች ዓይን ውስጥ ገባች። አስቴርን ከመርዶክዮስ ነጥለው በመውሰድ ከሰበሰቧቸው ሌሎች ወጣት ሴቶች ጋር አድርገው ከወንዙ ማዶ ወዳለው ታላቅ ቤተ መንግሥት አመጧት። (አስቴር 2:8) አስቴርና መርዶክዮስ የአባትና የልጅ ዓይነት ቅርርብ ስለነበራቸው መለያየቱ ለሁለቱም በጣም ከብዷቸው መሆን አለበት። መርዶክዮስ፣ ያሳደጋት ልጅ የማያምን ሰው (ንጉሥም እንኳ ቢሆን) እንድታገባ አይፈልግም ነበር፤ ሆኖም ሁኔታዎች ከእሱ ቁጥጥር ውጭ ነበሩ። አስቴር ከመወሰዷ በፊት መርዶክዮስ የሰጣትን ምክር በትኩረት አዳምጣ መሆን አለበት! በሱሳ ወደሚገኘው ቤተ መንግሥት ስትወሰድ በአእምሮዋ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች ሳይጉላሉ አይቀሩም። ከፊቷ ምን ዓይነት ሕይወት ይጠብቃት ይሆን?

“በሚያዩዋት ሁሉ ዘንድ ሞገስ አገኘች”

አስቴር ለእሷ ፍጹም አዲስና እንግዳ የሆነ ዓለም ውስጥ ገባች። ከመላው የፋርስ ግዛት ከተሰበሰቡ “ብዙ ልጃገረዶች” መካከል አንዷ ነበረች። የእነዚህ ወጣቶች ባሕል፣ ቋንቋና አስተሳሰብ በእጅጉ የተለያየ ነው። ወጣቶቹ፣ ሄጌ ለተባለ ባለሥልጣን በኃላፊነት የተሰጡ ሲሆን አንድ ዓመት የሚፈጅና ጥሩ መዓዛ ባላቸው ዘይቶች መታሸትን የሚያካትት መጠነ ሰፊ የመዋቢያ ዝግጅት ተደርጎላቸዋል። (አስቴር 2:8, 12) በዚያ ያለው ሁኔታና አኗኗር ወጣቶቹ ሴቶች ከመጠን በላይ ስለ መልካቸው እንዲያስቡ እንዲሁም በመካከላቸው የኩራትና የፉክክር መንፈስ እንዲፈጠር ሳያደርግ አይቀርም። ይህ ሁኔታ በአስቴር ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆን?

በምድር ላይ የመርዶክዮስን ያህል ለአስቴር የሚጨነቅ ሰው የለም። መርዶክዮስ ሴቶቹ ወደሚኖሩበት ቤት የቻለውን ያህል በመቅረብ በየዕለቱ ስለ አስቴር ሁኔታ ለማወቅ ይጥር እንደነበር ዘገባው ይገልጻል። (አስቴር 2:11) ምናልባትም በዚህ ቤት ውስጥ በሚኖሩ ተባባሪ የሆኑ አገልጋዮች አማካኝነት ስለ እሷ የሚደርሰው ትንሽ ትንሽ ወሬ የአባትነት ኩራት እንዲሰማው አድርጎት መሆን አለበት። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

ሄጌ በአስቴር ሁኔታ እጅግ ከመደነቁ የተነሳ ለእሷ ሰባት ሴት አገልጋዮችንና በሴቶቹ ቤት ውስጥ ከሁሉ የተሻለውን ክፍል በመስጠት ታላቅ ፍቅራዊ ደግነት አሳያት። ደግሞም ዘገባው “አስቴር በሚያዩዋት ሁሉ ዘንድ ሞገስ አገኘች” ይላል። (አስቴር 2:9, 15) እንዲህ በአድናቆት እንዲዋጡ ያደረጋቸው ቁንጅናዋ ብቻ ነበር? አይደለም፤ አስቴርን ተወዳጅ ያደረጓት ሌሎች ነገሮችም አሉ።

ለምሳሌ ያህል፣ “መርዶክዮስ እንዳትናገር አዞአት ስለ ነበር፣ አስቴር የየት አገር ሰውና የእነማን ወገን እንደ ሆነች አልገለጸችም” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። (አስቴር 2:10) መርዶክዮስ አስቴር አይሁዳዊ መሆኗን እንዳትናገር አሳስቧት ነበር፤ እንዲህ ያደረገው የፋርስ ንጉሣውያን ቤተሰብ ለእሱ ወገኖች ከፍተኛ ጭፍን ጥላቻ እንዳላቸው በማስተዋሉ ሳይሆን አይቀርም። አስቴር በአካል ከእሱ ብትርቅም እንኳ እንደ ቀድሞው ሁሉ አሁንም በጥበብ እንደምትመላለስና ታዛዥ እንደሆነች ማወቁ ምንኛ አስደስቶት ይሆን!

በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች ወላጆቻቸውንም ሆነ አሳዳጊዎቻቸውን ማስደሰት ይችላሉ። መጥፎ ሥነ ምግባር የሚከተሉ፣ ፌዘኛ ወይም ዓመፀኛ የሆኑ ልጆች የሚያሳድሩባቸውን ጎጂ ተጽዕኖዎች ወላጆቻቸው በሌሉበት ጊዜም እንኳ መቋቋምና የሚያምኑባቸውን ትክክለኛ መሥፈርቶች አጥብቀው መከተል ይችላሉ። እንደ አስቴር ሁሉ እነዚህ ወጣቶችም እንዲህ ዓይነት አቋም መያዛቸው በሰማይ የሚኖረውን የአባታቸውን ልብ ያስደስታል።​—ምሳሌ 27:11

አስቴር ወደ ንጉሡ የምትወሰድበት ጊዜ ሲደርስ ራሷን ይበልጥ ለማስዋብ ያስፈልገኛል ብላ የምታስበውን ማንኛውንም ነገር የመጠየቅ ነፃነት ተሰጥቷት ነበር። እሷ ግን ሄጌ ከነገራትና ከተሰጧት ነገሮች ውጪ ምንም ባለመጠየቅ ያላት እንደሚበቃት አሳይታለች። (አስቴር 2:15) የንጉሡን ልብ ለመማረክ ውበት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ተገንዝባ ይሆናል፤ ልክን የማወቅና የትሕትና መንፈስ በቤተ መንግሥት ውስጥ እንደ ልብ የማይገኝ ብርቅ ነገር ነው። ታዲያ እንዲህ ዓይነት አመለካከት መያዟ ትክክል ነበር?

ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ንጉሡ ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይበልጥ አስቴርን ወደዳት፤ ከሌሎቹ ደናግልም ሁሉ ይልቅ በእርሱ ዘንድ ሞገስንና መወደድን አገኘች። ስለዚህ የእቴጌነት ዘውድ በራሷ ላይ ጫነላት፤ በአስጢንም ፈንታ ንግሥት አደረጋት።” (አስቴር 2:17) ትሑት የሆነችው ይህች አይሁዳዊት ወጣት በሕይወቷ ውስጥ ካጋጠማት ለውጥ ጋር ራሷን ማስማማት ከባድ እንደሚሆንባት ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም አዲሷ ንግሥት ለመሆን ይኸውም በወቅቱ በምድር ላይ ካሉት ነገሥታት መካከል ኃያል የነበረው ንጉሥ ሚስት ለመባል በቅታለች! ንግሥት መሆኗ በኩራት እንድትወጠርና እንድትታበይ አድርጓት ይሆን?

በፍጹም! አስቴር እንደ አባት ሆኖ ላሳደጋት ለመርዶክዮስ ታዛዥነት ማሳየቷን ቀጥላለች። ከአይሁዳውያን ጋር ያላትን ዝምድና ሚስጥር አድርጋ ይዛው ነበር። በተጨማሪም መርዶክዮስ፣ ጠረክሲስን ለመግደል የተጠነሰሰውን ሴራ ባወቀ ጊዜ አስቴር ንጉሡን እንድታስጠነቅቅ የነገራትን መልእክት በታዛዥነት አድርሳለች፤ በዚህም የተነሳ የሰዎቹ ሴራ ሊጨናገፍ ችሏል። (አስቴር 2:20-23) የትሕትናና የታዛዥነት መንፈስ በማሳየት በአምላክ ላይ የነበራትን እምነት ጠብቃ መቀጠል ችላለች። በዛሬው ጊዜ ታዛዥነት ያን ያህል ትልቅ ግምት የሚሰጠው ባሕርይ አይደለም፤ ይልቁንም እምቢተኝነትና ዓመፀኝነት የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል። ይሁንና እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ልክ እንደ አስቴር ታዛዥነትን ከፍ አድርገው ይመለከታሉ።

የአስቴር እምነት ተፈተነ

ሐማ የሚባል አንድ ሰው በጠረክሲስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ እያገኘ መጣ። ንጉሡ ለሐማ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ በመስጠት ዋነኛ አማካሪውና በግዛቱ ውስጥ ሁለተኛ ሰው አድርጎ ሾመው። ከዚህም በላይ ንጉሡ፣ ሰዎች ለዚህ ባለሥልጣን እንዲሰግዱለት ትእዛዝ አስተላለፈ። (አስቴር 3:1-4) ይህ ሕግ በመርዶክዮስ ላይ ችግር የሚፈጥር ነበር። ንጉሡን መታዘዝ እንዳለበት ያምናል፤ ይሁንና ይህን ለማድረግ ሲል የአምላክን ሕግ መጣስ እንደሌለበትም ያውቃል። ሐማ “አጋጋዊ” መሆኑ መረሳት የሌለበት ነገር ነው። ይህ ሲባል ሐማ የአጋግ ዝርያ ነው ማለት ነው፤ አጋግ ደግሞ የአምላክ ነቢይ የነበረው ሳሙኤል የገደለው የአማሌቃውያን ንጉሥ ነበር። (1 ሳሙኤል 15:33) አማሌቃውያን እጅግ ክፉ ከመሆናቸው የተነሳ የይሖዋና የእስራኤላውያን ጠላቶች ሆነው ነበር። አማሌቃውያን በብሔር ደረጃ አምላክ ጥፋት የወሰነባቸው ሕዝቦች ነበሩ። * (ዘዳግም 25:19) ታዲያ አንድ ታማኝ አይሁዳዊ በቤተ መንግሥት ውስጥ ሥልጣን ላለው አንድ አማሌቃዊ እንዴት ሊሰግድ ይችላል? መርዶክዮስ ይህን ሊያደርግ አይችልም። ደግሞም ከአቋሙ ፍንክች አላለም። ዛሬም ቢሆን አምላክን በታማኝነት የሚያገለግሉ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” የሚለውን መመሪያ በጥብቅ ለመከተል ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል።​—የሐዋርያት ሥራ 5:29

ይህ ሁኔታ ሐማን እጅግ አስቆጣው። ይሁንና መርዶክዮስን ማስገደል ብቻ በቂ መስሎ አልታየውም። የመርዶክዮስን ወገኖች በሙሉ ለመደምሰስ ቆርጦ ተነሳ! ሐማ ስለ አይሁዳውያን ለንጉሡ መጥፎ ወሬ በመንገር አሳጣቸው። ምናምንቴ እንደሆኑ በመቁጠር ስማቸውን እንኳ ሳይጠቅስ በሕዝቡ መካከል “ተሠራጭቶና ተበታትኖ የሚኖር አንድ ሕዝብ” እንዳለ ነገረው። ይባስ ብሎም ንጉሡ ያወጣቸውን ሕጎች እንደማያከብሩ ተናገረ፤ ይህም እነዚህ ሰዎች ስጋት የሚፈጥሩ ዓመፀኞች ናቸው የሚል አንድምታ አለው። ሐማ፣ በግዛቱ ውስጥ የሚገኙትን አይሁዳውያን በሙሉ ለማስገደል የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማስገባት ሐሳብ አቀረበ። * ጠረክሲስ፣ ሐማ ማንኛውንም ትእዛዝ ማውጣትና ትእዛዙን በማኅተም ማጽደቅ እንዲችል የራሱን የቀለበት ማኅተም ሰጠው።​—አስቴር 3:5-10

ከዚያም መልእክተኞች በአይሁድ ሕዝብ ላይ የተላለፈውን የሞት ፍርድ በመላው የፋርስ ግዛት በአራቱም ማዕዘን ለማድረስ በከፍተኛ ፍጥነት በፈረስ ገሰገሱ። ይህ አዋጅ ከፋርስ ርቃ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ሲሰማ በነዋሪዎቹ ላይ ምን ስሜት ፈጥሮ ሊሆን እንደሚችል ገምት፤ በወቅቱ ኢየሩሳሌም የመከላከያ ቅጥር ያልነበራት ሲሆን ከባቢሎን ግዞት የተመለሱ አይሁዳውያን ቀሪዎች ከተማዋን መልሰው ለመገንባት እየተፍጨረጨሩ ነበር። መርዶክዮስ ይህን አስደንጋጭ ዜና ሲሰማ በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩት እንዲሁም በሱሳ ስለሚገኙት ወዳጅ ዘመዶቹ አስቦ ሊሆን ይችላል። በጭንቀት የተዋጠው መርዶክዮስ ልብሱን ቀደደ፤ ከዚያም ማቅ ለብሶና በራሱ ላይ ዐመድ ነስንሶ በከተማዋ መካከል ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸ። ሐማ ግን እሱ ባመጣው ጦስ የተነሳ በሱሳ የሚገኙ በርካታ አይሁዳውያንና ወዳጆቻቸው የተሰማቸው ድንጋጤ ምንም ግድ ሳይሰጠው ከንጉሡ ጋር የወይን ጠጅ ለመጠጣት ተቀመጠ።​—አስቴር 3:12 እስከ 4:1

መርዶክዮስ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት ተሰማው። ግን ምን ማድረግ ይችላል? አስቴር፣ መርዶክዮስ ያጋጠመውን ጭንቀት ስትሰማ ልብስ ላከችለት፤ እሱ ግን ሊጽናና አልቻለም። አምላኩ ይሖዋ፣ የሚወዳት አስቴር ከእሱ ተነጥላ እንድትወሰድና የአንድ አረማዊ ገዥ ሚስት እንድትሆን የፈቀደው ለምን እንደሆነ ለረጅም ጊዜ ሲያሳስበው ቆይቶ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን ፍንጭ ሳያገኝ አይቀርም። መርዶክዮስ፣ አስቴር ወደ ንጉሡ ገብታ “ስለ ሕዝቧ” ጥብቅና እንድትቆም የሚማጸን መልእክት ላከባት።​—አስቴር 4:4-8

አስቴር መልእክቱ ሲደርሳት በድንጋጤ ክው ብላ መሆን አለበት። ይህ አጋጣሚ እምነቷን በእጅጉ የሚፈትን ነበር። ለመርዶክዮስ ከላከችው ምላሽ መረዳት እንደሚቻለው አስቴር በጣም ፈርታ ነበር። የንጉሡ ሕግ ምን እንደሚል አስታወሰችው። ማንም ሰው ሳይጠራ ንጉሡ ፊት ቀረበ ማለት ሕይወቱን አጣ ማለት ነው። እንዲህ ዓይነት ጥፋት የፈጸመ ሰው በሕይወት መትረፍ የሚችለው ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ከዘረጋለት ብቻ ነው። አስጢን ንጉሡ ፊት እንድትቀርብ ስትጠራ ይህን ለማድረግ አሻፈረኝ በማለቷ ከደረሰባት ዕጣ አንጻር አስቴር ንጉሡ ርኅራኄ ያሳየኛል ብላ የምትጠብቅበት አንዳች ምክንያት ይኖራል? ላለፉት 30 ቀናት ንጉሡ ወደ እሱ እንድትገባ እንዳልጠራት ለመርዶክዮስ ነገረችው! የማይጨበጥ አመል ያለው ይህ ንጉሥ ለረጅም ጊዜ ሳይጠራት የቀረ ከመሆኑ አንጻር በእሱ ዘንድ ያላትን ተወዳጅነት እንዳጣች ብታስብ የሚያስገርም አይሆንም። *​—አስቴር 4:9-11

መርዶክዮስ፣ አስቴር ያላትን እምነት ለማጎልበት ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጣት። እርምጃ ሳትወስድ ብትቀር አይሁዳውያን ከሌላ ምንጭ መዳን እንደሚያገኙ በእርግጠኝነት ነገራት። ሆኖም ስደቱ እንዲህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ጊዜ አስቴር እንዴት በሕይወት እተርፋለሁ ብላ ልትጠብቅ ትችላለች? በዚህ ጊዜ መርዶክዮስ በይሖዋ ላይ ከፍተኛ እምነት እንዳለው አሳይቷል፤ ምክንያቱም ይሖዋ ሕዝቡ ተጠራርገው እንዲጠፉም ሆነ የገባው ቃል ሳይፈጸም እንዲቀር ፈጽሞ አይፈቅድም። (ኢያሱ 23:14) ከዚያም መርዶክዮስ ለአስቴር “አንቺ ንግሥት ለመሆን የበቃሽው ለዚህ ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” የሚል ጥያቄ አቀረበላት። (አስቴር 4:12-14) መርዶክዮስ ሙሉ በሙሉ እምነቱን የጣለው በአምላኩ በይሖዋ ላይ ነበር። እኛስ እንዲህ ዓይነት እምነት አለን?​—ምሳሌ 3:5, 6

የሞትን ፍርሃት ያሸነፈ እምነት

አስቴር ቁርጧን የምታውቅበት ሰዓት ደርሷል። የአገሯ ሰዎች ለሦስት ቀን አብረዋት እንዲጾሙ እንዲያደርግ መርዶክዮስን ጠይቃው ነበር፤ በመልእክቷ መደምደሚያ ላይ “ከጠፋሁም ልጥፋ” በማለት እምነትና ድፍረት የሚንጸባረቅበት የማያወላውል ሐሳብ የተናገረች ሲሆን ይህ አባባል እስከ ዛሬ ድረስ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል። (አስቴር 4:15-17) በእነዚህ ሦስት ቀናት ከመቼውም ይልቅ ልባዊ ጸሎት አቅርባ መሆን አለበት። በመጨረሻም ወሳኙ ሰዓት ደረሰ። የክብር ልብሷን መልበስን ጨምሮ ንጉሡ ሲያያት ደስ እንዲሰኝባት ስትል የምትችለውን ነገር ሁሉ አደረገች። ከዚያም እሱ ወዳለበት አቀናች።

በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው አስቴር ንጉሡ ወደሚገኝበት አደባባይ ሄደች። የተሰማት ጭንቀትና ደጋግማ ታቀርብ የነበረው ጸሎት አእምሮዋንና ልቧን ተቆጣጥሮት እንደነበር መገመት አያዳግተንም። ከዚያም ጠረክሲስን ዙፋኑ ላይ ሆኖ ማየት ወደምትችልበት ወደ ውስጠኛው አደባባይ ገባች። ጥቅልል ያለው ፀጉሩ ዙሪያውን የከበበውንና በአራት ማዕዘን ቅርጽ በተከረከመው ጢሙ የተሸፈነውን ፊቱን ለማንበብ ሳትሞክር አትቀርም። ንጉሡ እስኪያያት ጥቂት መጠበቅ አስፈልጓት ከነበረ ይህ ጊዜ በጣም ረዝሞባት ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ጊዜው አለፈና ባሏ ተመለከታት። ሁኔታው ያልጠበቀው ነገር እንደሆነበት ምንም ጥርጥር የለውም፤ ሆኖም ፊቱን ፈታ አደረገ። ከዚያም የወርቅ ዘንጉን ዘረጋላት!​—አስቴር 5:1, 2

አስቴር የመጣችበትን ጉዳይ እንድትናገር ተፈቀደላት። ለአምላኳም ሆነ ለሕዝቧ ጥብቅና በመቆም እምነት በማሳየት ረገድ እስከ ዛሬ ድረስ ላሉ የአምላክ አገልጋዮች ግሩም ምሳሌ ትታለች። ይሁንና ይህ የተልእኮዋ መጀመሪያ ብቻ ነው። አስቴር፣ የንጉሡ የቅርብ አማካሪ የሆነው ሐማ መሠሪ ሰው መሆኑን ለባሏ ልታሳምነው የምትችለው እንዴት ነው? ሕዝቧን ለማዳን ምን ማድረግ ትችላለች? እነዚህ ጥያቄዎች ወደፊት በሚወጣ ርዕስ ላይ ይብራራሉ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ቀዳማዊ ጠረክሲስ በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መጀመሪያ ላይ የፋርስን ግዛት ያስተዳድር የነበረ ንጉሥ ነው።

^ አን.24 ከአማሌቃውያን መካከል “የቀሩት” በንጉሥ ሕዝቅያስ የግዛት ዘመን ተደምስሰው ስለነበር ሐማ በሕይወት ተርፈው ከነበሩት ጥቂት አማሌቃውያን ውስጥ አንዱ መሆን አለበት።​—1 ዜና መዋዕል 4:43

^ አን.25 ሐማ ቃል የገባው 10,000 መክሊት ብር ለመክፈል ነበር፤ ይህ ገንዘብ በዛሬው ጊዜ ባለው የዋጋ ተመን ቢሰላ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ይሆናል። ንጉሡ በእርግጥ ቀዳማዊ ጠረክሲስ ከሆነ ሐማ ያቀረበው ገንዘብ እጅግ አጓጉቶት ሊሆን ይችላል። ጠረክሲስ ከግሪኮች ጋር ባደረገው አውዳሚ ጦርነት ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ ተዳርጎ ነበር፤ ይህን ጦርነት ያደረገው አስቴርን ከማግባቱ በፊት ሳይሆን አይቀርም።

^ አን.28 ቀዳማዊ ጠረክሲስ ስሜቱ በቅጽበት የሚለዋወጥ ግልፍተኛ ሰው በመሆኑ ይታወቃል። ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶተስ፣ ጠረክሲስ ከግሪክ ጋር ስላደረገው ጦርነት በጻፈው ታሪክ ላይ ስለ ንጉሡ ባሕርይ የሚገልጹ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጠቅሷል። ንጉሡ በሄሌስፖንት ወሽመጥ ላይ ድልድይ እንዲሠራ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። ድልድዩን ማዕበል ባፈረሰው ጊዜ ጠረክሲስ መሃንዲሶቹ አንገታቸው እንዲቀላ ያዘዘ ከመሆኑም ሌላ ከፍ ባለ ድምፅ እርግማን በሚታወጅበት ጊዜ አገልጋዮቹ ውኃውን በመግረፍ ሄሌስፖንትን “እንዲቀጡ” መመሪያ ሰጥቷል። ከዚህ ዘመቻ ጋር በተያያዘ ባለጸጋ የሆነ አንድ ሰው ልጁ ከውትድርና ግዳጅ ነፃ እንዲሆን በለመነው ጊዜ ጠረክሲስ ልጁ ለሁለት እንዲቆረጥ ያዘዘ ከመሆኑም ሌላ አስከሬኑን ሌሎች እንዲያዩት በማድረግ መቀጣጫ እንዲሆን አድርጓል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መርዶክዮስ ባሳደጋት ልጅ ለመኩራት በቂ ምክንያት አለው

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስቴር ከአካላዊ ውበት ይበልጥ ትሕትና እና ጥበብ እንደሚበልጡ ታውቅ ነበር

[በገጽ 22 እና 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስቴር የአምላክን ሕዝቦች ለመታደግ ሕይወቷን አደጋ ላይ ጥላለች