በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁን አስተምሩ

በንቃት መከታተል የሚያስፈልገን መቼ ነው?

በንቃት መከታተል የሚያስፈልገን መቼ ነው?

ትምህርት ቤት በምትሆንበት ጊዜ በንቃት መከታተል አስፈላጊ እንደሆነ ታውቃለህ። በትምህርት ሰዓት እንቅልፍ የሚወስዳቸው ብዙ ልጆች አሉ፤ አንተ ግን መማር የምትፈልግ ከሆነ በንቃት መከታተል ይኖርብሃል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በሚሰጥበት ስብሰባ ላይ ትገኝ ይሆናል።

በንቃት ለመከታተል ምን ሊረዳህ የሚችል ይመስልሃል?​ * ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ ማታ በጊዜ መተኛት ነው። ከምሳ በኋላ ትንሽ መተኛትህም ሊጠቅምህ ይችላል። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ ንግግር ሲሰጥ በጣም ስለመሸ አንድ ወጣት እንቅልፍ ወሰደው፤ ይህ ወጣት ካጋጠመው ሁኔታ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስህን አውጣና የሐዋርያት ሥራ 20:7-12 ምን እንደሚል ተመልከት።

ጳውሎስ የወደብ ከተማ በሆነችው በጥሮአስ የሚገኘውን ጉባኤ እየጎበኘ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ጳውሎስ “በማግስቱ” በመርከብ ለመሄድ ተዘጋጅቶ እንደነበር ይገልጻል። በመሆኑም ‘ንግግሩን እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አስረዘመ።’ ታሪኩ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ጳውሎስ ንግግሩን ባስረዘመ ጊዜ መስኮት ላይ ተቀምጦ የነበረ አውጤኪስ የሚባል አንድ ወጣት ከባድ እንቅልፍ ያዘው።” ከዚያስ ምን ሆነ?​

አውጤኪስ “ከሁለተኛ ፎቅ” መስኮት ላይ ወደቀ። ጳውሎስና አብረውት የነበሩት ሰዎች ደረጃውን በፍጥነት ወረዱ። አጠገቡ ሲደርሱ መሬት ላይ ተዘርሮ አገኙት፤ አውጤኪስ ሞቷል! ሰዎቹ ምን ያህል እንዳዘኑ መገመት ትችላለህ?​— መጽሐፍ ቅዱስ ጳውሎስ አውጤኪስን እንዳቀፈው ይናገራል። ከዚያም ጳውሎስ ‘አይዟችሁ፣ ልጁ ደኅና ነው!’ በማለት በደስታ ተናገረ። አምላክ አውጤኪስን ከሞት አስነስቶታል!

በአውጤኪስ ላይ የደረሰው ሁኔታ ስለ አምላክ ምን ያስተምረናል?​— አንደኛ ነገር፣ በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ ልጆችን ጨምሮ የሞቱ ሰዎችን በሙሉ ከሞት ማስነሳት ይችላል። ይሖዋ ከወላጆችህ የበለጠ ስለ አንተ ያውቃል እንዲሁም ይወድሃል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ትንንሽ ልጆችን በማቀፍና በመባረክ አባቱ ልጆችን እንደሚወድ አሳይቷል። በተጨማሪም የ12 ዓመቷን ልጅ ጨምሮ ሌሎች ወጣቶችን ከሞት አስነስቷል።

በሰማይ የሚኖረው አባትህ እንደሚወድህ በማወቅህ ምን ይሰማሃል?​— አዎ፣ ይህን ማወቃችን እኛም ይሖዋን እንድንወደውና እሱ የሚነግረንን እንድንታዘዝ ያነሳሳናል። አምላክን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?​— አንዱ መንገድ እንደምንወደው መናገር ነው። ኢየሱስ ‘እኔ አብን እወደዋለሁ’ ብሏል። ይሁንና ኢየሱስ አምላክን እንደሚወድ ከመናገር ያለፈ ነገር አድርጓል። በሚያደርገው ነገር አባቱን እንደሚወድ አሳይቷል።

ኢየሱስ አምላክን ይታዘዝ ነበር። ‘ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን አደርጋለሁ’ ብሏል። እኛም ይሖዋንና ልጁን ኢየሱስን ለማስደሰት ስንል አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ በንቃት ለመከታተል የቻልነውን ያህል ጥረት እናድርግ።

ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ

^ አን.4 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።