በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መልሱን ማወቅ ለውጥ ያመጣል?

መልሱን ማወቅ ለውጥ ያመጣል?

መልሱን ማወቅ ለውጥ ያመጣል?

“የወንድ ጓደኛ መያዝ የጀመርኩት በአሥር ዓመቴ ነበር። መጀመሪያ አካባቢ እጅ ለእጅ እንያያዝ እንዲሁም እንሳሳም ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን እርስ በርስ መደባበስና የፆታ ስሜታችንን የሚያረኩ የተለያዩ ድርጊቶችን መፈጸሙን ተያያዝነው። አሥራ አምስት ዓመት ሲሞላኝ ሥራ ያዝኩ፤ ከሥራ ባልደረቦቼ መካከል የፆታ ግንኙነት እንድንፈጽም የጠየቁኝ ወንዶች ነበሩ። እኔም ደፋር ለመሆንና እነሱ የሚያደርጉትን ሁሉ ለማድረግ ፈለግሁ። በሥራ ባልደረቦቼ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ያለኝ ጉጉት ርካሽ በሆኑ የፆታ ድርጊቶች ወደ መካፈል መራኝ።”​—ሣራ፣ * አውስትራሊያ

ሣራ ያደገችው ሃይማኖተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ እንደሆነ ቢነገርህ ታምናለህ? ወላጆቿ የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንድትከተል ሊረዷት ሞክረው ነበር። እሷ ግን በሌላ አቅጣጫ መሄድን መረጠች።

ብዙዎች የሣራ ምርጫ ትክክል እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት የሚሰጠው ሐሳብ በጣም ኋላ ቀር እንደሆነ ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ አንድ ሰው ሃይማኖተኛ ቢሆንም በፆታ ረገድ ልቅ የሆነ ሕይወት መምራቱ ምንም ችግር እንደሌለው ያምናሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት የሚሰጠውን ሐሳብ ማወቅህና በዚያ መመራትህ ለውጥ ያመጣል? መጽሐፍ ቅዱስ “በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ” እንደሆነና ‘ለማስተማር እንደሚጠቅም’ በውስጡ ከሰፈረው ሐሳብ መረዳት እንችላለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) የሰው ልጆችን የፈጠራቸው አምላክ እንደሆነና መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ መሪነት እንዳስጻፈው የምታምን ከሆነ ይህ መጽሐፍ የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ የሚሰጠውን ሐሳብ ማወቅህ እንደሚጠቅምህ ጥርጥር የለውም።

የሚያሳዝነው ነገር ብዙዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ምን እንደሚያስተምር ግራ ገብቷቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት እንደሚያስተምሩ የሚናገሩ የሃይማኖት መሪዎች በዚህ ረገድ የተለያየ አቋም ያራምዳሉ። እንዲያውም ይህ ጉዳይ በተለያዩ ዋና ዋና አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ መከፋፈል እንዲፈጠር አድርጓል።

አንተስ በዚህ ጉዳይ ላይ በሌሎች ሐሳብ ከመመራት ይልቅ ለምን ጥቂት ደቂቃዎች ወስደህ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል አትመረምርም? ቀጣዩ ርዕስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ከሚሰጠው ትምህርት ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ለሚነሱ አሥር ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡት መልሶች ግልጽና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ከእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች የመጨረሻው ደግሞ በዚህ ረገድ የምንመርጠው አካሄድ ለውጥ የሚያመጣው ለምን እንደሆነ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ስሟ ተቀይሯል።