በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

ባለትዳሮች መንፈሳዊነታችሁን ለማሳደግ በጋራ ጥረት አድርጉ

ባለትዳሮች መንፈሳዊነታችሁን ለማሳደግ በጋራ ጥረት አድርጉ

ፍሬድሪክ *“እኔና ባለቤቴ እንደተጋባን አካባቢ፣ መጽሐፍ ቅዱስን አብረን ማጥናት አለብን የሚል አቋም ነበረኝ። በጥናታችን ወቅት ባለቤቴ በትኩረት እንድትከታተል ለማድረግ ቆርጬ ነበር። ሊያን ግን አርፋ መቀመጥ አይሆንላትም። ጥያቄ ስጠይቃት ደግሞ የምትሰጠኝ መልስ ‘አዎ’ ወይም ‘አይ’ የሚል ብቻ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያለብን በዚህ መንገድ እንዳልሆነ ይሰማኝ ነበር።”

ሊያን፦ “ፍሬድሪክን ሳገባ 18 ዓመቴ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን አብረን እናጠና ነበር፤ ሆኖም ፍሬድሪክ እያንዳንዱን የጥናት ወቅት ስህተቶቼን በሙሉ ለመጠቆምና ጥሩ ሚስት ለመሆን ማሻሻል የሚኖርብኝን ነጥቦች ለማጉላት ይጠቀምበት ነበር። ይህም በጣም ተስፋ ያስቆረጠኝ ከመሆኑም ሌላ ስሜቴን ጎድቶት ነበር!”

የፍሬድሪክና የሊያን ችግር ምን ይመስልሃል? ሐሳባቸው ጥሩ ነበር። ሁለቱም አምላክን ይወዳሉ። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ ማጥናት አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበዋል። ይሁንና አንድነት እንዲኖራቸው ሊያደርጋቸው የሚገባው ነገር በመካከላቸው ልዩነት ፈጥሯል። አብረው ያጠኑ የነበረ ቢሆንም መንፈሳዊነታቸውን ለማሳደግ በጋራ ጥረት እያደረጉ አልነበረም።

መንፈሳዊነት ሲባል ምን ማለት ነው? ባለትዳሮች መንፈሳዊነታቸውን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው? ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ? እነዚህንስ ሁኔታዎች እንዴት ሊወጧቸው ይችላሉ?

መንፈሳዊነት ሲባል ምን ማለት ነው?

‘መንፈሳዊነት’ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት አንድ ሰው ስለ ሕይወት ያለውን አመለካከት ለመግለጽ ነው። (ይሁዳ 18, 19) ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስ መንፈሳዊ በሆነና ሥጋዊ በሆነ ሰው መካከል ያለውን የአመለካከት ልዩነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ጳውሎስ፣ ሥጋዊ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ስለ ራሳቸው እንደሚያስቡ ተናግሯል። በአምላክ መሥፈርቶች ከመመራት ይልቅ ለራሳቸው ትክክል የመሰላቸውን ነገር ያደርጋሉ።​—1 ቆሮንቶስ 2:14፤ ገላትያ 5:19, 20

በአንጻሩ ግን መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ለአምላክ መሥፈርቶች የላቀ ቦታ ይሰጣሉ። ይሖዋ አምላክን እንደ ወዳጃቸው አድርገው የሚያዩት ከመሆኑም ሌላ እሱን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። (ኤፌሶን 5:1) በመሆኑም ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ አፍቃሪዎች፣ ደጎችና ገሮች ናቸው። (ዘፀአት 34:6) አምላክን መታዘዝ ቀላል በማይሆንበት ጊዜም እንኳ ይህን ያደርጋሉ። (መዝሙር 15:1, 4) በካናዳ የሚኖረውና በትዳር ውስጥ 35 ዓመታት ያሳለፈው ዳረን “ለእኔ እንደሚገባኝ ከሆነ መንፈሳዊ ሰው ምንጊዜም ቢሆን ንግግሩና ድርጊቱ ከአምላክ ጋር ያለውን ወዳጅነት እንዴት እንደሚነካው ያስባል” ብሏል። ባለቤቱ ጄን ደግሞ አክላ “መንፈሳዊ ሴት የምትባለው የአምላክን መንፈስ ፍሬ በየዕለቱ በሕይወቷ ውስጥ ለማንጸባረቅ የምትጥር እንደሆነች ይሰማኛል” በማለት ተናግራለች።​—ገላትያ 5:22, 23

እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው መንፈሳዊ አመለካከት ለማዳበር የግድ ትዳር መመሥረት የለበትም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው ስለ አምላክ የመማርና እሱን የመምሰል ኃላፊነት እንዳለበት ይናገራል።​—የሐዋርያት ሥራ 17:26, 27

መንፈሳዊነታችሁን ለማሳደግ በጋራ ጥረት ማድረግ የሚኖርባችሁ ለምንድን ነው?

አንድ ባልና ሚስት መንፈሳዊነታቸውን ለማሳደግ በጋራ ጥረት ማድረግ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ሁለት አትክልተኞች የጋራ ንብረታቸው በሆነ ቦታ ላይ አትክልት መትከል ፈለጉ እንበል። ሆኖም እነዚህ ሰዎች አትክልቶቹን ለመትከል ያሰቡበት ወቅት ይለያያል። እንዲሁም አንዱ አትክልተኛ ማዳበሪያ ለመጠቀም የሚፈልግ ሲሆን ሌላኛው ግን አትክልቶቹ በጭራሽ ማዳበሪያ እንደማያስፈልጋቸው ይሰማዋል። አንደኛው የአትክልት ስፍራውን ለመንከባከብ ሌት ተቀን ሲለፋ ሌላኛው ምንም ሳይሠራ እጆቹን አጣጥፎ ቁጭ ይላል። እንዲህ ባለው ሁኔታ የአትክልት ቦታው የተወሰነ ምርት ሊያስገኝ ይችል ይሆናል፤ ያም ቢሆን ግን የሚገኘው ምርት ሁለቱም አትክልተኞች ምን መሥራት እንዳለባቸው ተስማምተው ግባቸው ላይ ለመድረስ በጋራ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ የሚገኘውን ያህል አይሆንም።

ባልና ሚስት እንደነዚህ አትክልተኞች ናቸው። እርግጥ ነው፣ አንደኛው ወገን ብቻ መንፈሳዊነቱን ቢያሳድግ ግንኙነታቸው ሊሻሻል ይችል ይሆናል። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ይሁን እንጂ ሁለቱም የአምላክን መመሪያዎች በሕይወታቸው ውስጥ በተግባር ቢያውሉና ለእሱ በሚያቀርቡት አገልግሎት አንዳቸው ሌላውን ለመደገፍ ብርቱ ጥረት ቢያደርጉ ውጤቱ ምንኛ ያማረ ይሆናል! ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል” ብሏል። እንዲህ ያለው ለምንድን ነው? “ለሥራቸው መልካም ውጤት ስለሚያገኙ” ነው። “አንዱ ቢወድቅ፣ ባልንጀራው ደግፎ ያነሣዋል።”​—መክብብ 4:9, 10

እናንተም ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር መንፈሳዊነታችሁን ለማሳደግ ትጓጉ ይሆናል። ይሁን እንጂ አትክልት እንደ መንከባከብ ሁሉ መንፈሳዊነትን በማሳደግ ረገድም ፍላጎት ብቻውን ፍሬ አያስገኝም። ሊያጋጥሟችሁ የሚችሉ ሁለት ተፈታታኝ ሁኔታዎችንና እነዚህን ለመወጣት የምትችሉባቸውን መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ተፈታታኝ ሁኔታ 1፦ ጊዜ ማግኘት አልቻልንም።

ካገባች ብዙም ያልቆየችው ሱ እንዲህ ብላለች፦ “ከምሽቱ 1:00 ላይ ከሥራ ስወጣ ባለቤቴ መጥቶ ይወስደኛል። ቤት ስንደርስ የቤቱ ሥራ ተከምሮ ይጠብቀናል። ሰውነታችን በጣም ስለሚዝል እረፍት ማድረግ እንዳለብን ይሰማናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አእምሯችን ስለ አምላክ ማጥናት እንዳለብን ይነግረናል። ሆኖም ይህን ማድረግ ከባድ ትግል ነው።”

የመፍትሔ ሐሳብ፦ ከሁኔታዎች ጋር ራሳችሁን ለማስማማትና እርስ በርስ ለመተባበር ጥረት አድርጉ። ሱ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ማለዳ ለመነሳትና ወደ ሥራ ከመሄዳችን በፊት የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አብረን ለማንበብ እንዲሁም ባነበብነው ላይ ለመወያየት ወሰንን። ከዚህም በተጨማሪ አብረን ጊዜ ማሳለፍ እንድንችል ባለቤቴ አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ያግዘኛል።” እንዲህ ዓይነት የተለየ ጥረት ማድረጋቸው ምን ጥቅም አስገኝቶላቸዋል? የሱ ባል የሆነው ኤድ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ሱ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ አዘውትረን ስንወያይ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተሻለ መንገድ መፍታት እንደቻልንና እንደ ድሮው ብዙም እንደማንጨነቅ አስተውያለሁ።”

ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ከመወያየት በተጨማሪ በየዕለቱ አብራችሁ መጸለያችሁ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረጋችሁ የሚጠቅማችሁ እንዴት ነው? በትዳር ዓለም 16 ዓመት ያሳለፈው ራየን እንዲህ ብሏል፦ “ከተወሰነ ጊዜ በፊት እኔና ባለቤቴ በትዳራችን ውስጥ በጣም ከባድ ችግር አጋጥሞን ነበር። ይሁንና ሁልጊዜ ከመተኛታችን በፊት አብረን ለመጸለይ ጊዜ የመደብን ሲሆን የሚያሳስቡንን ነገሮች ለአምላክ እንነግረው ነበር። አብረን መጸለያችን ችግሮቻችንን ለመፍታትና በትዳራችን ውስጥ ያጣነውን ደስታ መልሰን ለማግኘት እንዳስቻለን ይሰማኛል።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በእያንዳንዱ ቀን ምሽት ላይ አምላክን እንድታመሰግኑ የሚያነሳሷችሁን በትዳራችሁ ውስጥ ያጋጠሟችሁን መልካም ነገሮች የምትወያዩባቸው ጥቂት ደቂቃዎች መድቡ። በተጨማሪም ያጋጠሟችሁን ፈታኝ ሁኔታዎች በተለይም የአምላክን እርዳታ የሚሹ ጉዳዮችን አንስታችሁ ተነጋገሩ። ሆኖም ጥንቃቄ ልታደርጉበት የሚገባ ነገር አለ፦ ይህን አጋጣሚ የትዳር ጓደኛችሁን ስህተቶች ለመለቃቀም አትጠቀሙበት። ከዚህ ይልቅ አብራችሁ ስትጸልዩ ሁለታችሁም ልትሠሩባቸው የሚገቡ ነጥቦችን ብቻ ጥቀሱ። ከዚያም ከጸሎታችሁ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰዱ።

ተፈታታኝ ሁኔታ 2፦ ችሎታችን ይለያያል።

ቶኒ “ቁጭ ብዬ ማንበብ ፈጽሞ አይሆንልኝም” ብሏል። ባለቤቱ ናታሊ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ማንበብ በጣም የምወድ ሲሆን ስላወቅሁት ነገር መወያየትም ያስደስተኛል። አንዳንድ ጊዜ ከቶኒ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገሮች አንስተን ስንወያይ እኔ እንደምበልጠው የሚሰማው ይመስለኛል።”

የመፍትሔ ሐሳብ፦ አንዳችሁ ሌላውን የምትደግፉ እንጂ እርስ በርስ የምትፎካከሩ ወይም በሌላው ላይ የምትፈርዱ አትሁኑ። የትዳር ጓደኛችሁ ያሉትን መልካም ጎኖች እንደምታደንቁ ንገሩት እንዲሁም አበረታቱት። ቶኒ እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ለማውራት ያላት ጉጉት አንዳንድ ጊዜ ከአቅሜ በላይ ይሆንብኛል። በመሆኑም ከዚህ ቀደም ከእሷ ጋር ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ማውራት ይከብደኝ ነበር። ይሁንና ናታሊ በጣም ታበረታታኛለች። አሁን አሁን ስለ መንፈሳዊ ነገሮች አዘውትረን እንወያያለን፤ እኔም ይህን ማድረግ ምንም እንደማያስፈራ ተገንዝቤያለሁ። እንዲያውም ከእሷ ጋር ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት ያስደስተኛል። እንዲህ ማድረጋችን በመካከላችን የመፈራራት ስሜት እንዳይኖርና ሰላማዊ ግንኙነት እንዲሰፍን አድርጓል።”

በርካታ ባለትዳሮች በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስን አብረው ለማንበብና ለማጥናት ቋሚ ጊዜ መመደባቸው የተሻለ ትዳር እንዲኖራቸው እንደረዳቸው አስተውለዋል። ሆኖም ጥንቃቄ ልታደርጉበት የሚገባ ነገር አለ፦ ያገኛችሁትን ምክር የትዳር ጓደኛችሁ እንዴት ተግባራዊ ሊያደርገው እንደሚገባ ሳይሆን ራሳችሁ እንዴት ተግባራዊ እንደምታደርጉት ተናገሩ። (ገላትያ 6:4) ከትዳራችሁ ጋር የተያያዙ ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮችን በጥናታችሁ ወቅት ሳይሆን በሌላ ጊዜ ተነጋገሩባቸው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ከቤተሰብህ ጋር ማዕድ ላይ ተቀምጠህ እያለ ያመረቀዘ ቁስል መጠራረግ ትጀምራለህ? እንደማታደርገው የታወቀ ነው። እንዲህ ብታደርግ የሁሉም ሰው የምግብ ፍላጎት ይዘጋል። ኢየሱስ ስለ አምላክ ፈቃድ መማርንና ፈቃዱን ማድረግን ምግብ ከመብላት ጋር አመሳስሎታል። (ማቴዎስ 4:4፤ ዮሐንስ 4:34) መጽሐፍ ቅዱስ በተገለጠ ቁጥር ስሜታችሁ የቆሰለበትን ጉዳይ የምታነሱ ከሆነ የትዳር ጓደኛችሁ መንፈሳዊ ምግብ የመመገብ ፍላጎቱ ሊዘጋ ይችላል። እውነት ነው፣ በችግሮቻችሁ ላይ መወያየት አለባችሁ። ይሁንና እነዚህን ጉዳዮች ጊዜ መድባችሁ በሌላ ወቅት መወያየታችሁ የተሻለ ይሆናል።​—ምሳሌ 10:19፤ 15:23

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የትዳር ጓደኛችሁ ካሉት ባሕርያት መካከል የምታደንቋቸውን ሁለት ወይም ሦስት ባሕርያት ጻፉ። ከዚያም ከእነዚህ ባሕርያት ጋር የተያያዘ መንፈሳዊ ውይይት በምታደርጉበት ጊዜ የትዳር ጓደኛችሁ እነዚህን ባሕርያት የሚያንጸባርቅበትን መንገድ ምን ያህል እንደምታደንቁ ንገሩት።

የዘራችሁትን ታጭዳላችሁ

መንፈሳዊነታችሁን ለማሳደግ በጋራ ጥረት የምታደርጉ ከሆነ ይበልጥ ሰላማዊና አስደሳች ትዳር ይኖራችኋል። የአምላክ ቃል “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጣል።​—ገላትያ 6:7

በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ፍሬድሪክና ሊያን የዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እውነተኝነት በሕይወታቸው ተመልክተዋል። አሁን በትዳር ዓለም 45 ዓመታት ያሳለፉ ሲሆን መንፈሳዊነታቸውን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ መልሶ እንደሚክስ ተገንዝበዋል። ፍሬድሪክ “ባለቤቴ ሐሳቧን ስለማትገልጽልኝ እወቅሳት ነበር” ብሏል። “ይሁን እንጂ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እኔም ጥረት ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።” ሊያንም እንዲህ ብላለች፦ “አስቸጋሪ የሆኑትን ጊዜያት ለማለፍ የረዳን ሁለታችንም ለይሖዋ አምላክ ያለን ፍቅር ነው። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን የምናጠና ከመሆኑም ሌላ አብረን እንጸልይ ነበር። ፍሬድሪክ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማንጸባረቅ ጥረት እያደረገ እንዳለ ስመለከት እሱን መውደድ ይበልጥ ቀላል ሆኖልኛል።”

^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦

  • ከባለቤቴ ጋር አብረን የጸለይነው መቼ ነው?

  • ባለቤቴ ከእኔ ጋር ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ለመወያየት ፈቃደኛ እንድትሆን/እንዲሆን ምን ማድረግ እችላለሁ?