በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ሕጎች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

የአምላክ ሕጎች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

ከአምላክ ቃል ተማር

የአምላክ ሕጎች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

ይህ ርዕሰ ትምህርት በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን የሚያነሳ ሲሆን መልሶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችልም ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ቢወያዩ ደስ ይላቸዋል።

1. አምላክን መታዘዝ ያለብን ለምንድን ነው?

አምላክ ፈጣሪያችን ስለሆነ እሱን መታዘዝ ተገቢ ነው። ኢየሱስም እንኳ አምላክን ምንጊዜም ይታዘዝ ነበር። (ዮሐንስ 6:38፤ ራእይ 4:11) የአምላክ ሕጎች ለእሱ ያለንን ፍቅር ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚ ይሰጡናል።​—1 ዮሐንስ 5:3ን አንብብ።

የይሖዋ አምላክ ሕጎች በሙሉ ይጠቅሙናል። እነዚህ ሕጎች፣ በአሁኑ ጊዜ ከሁሉ የሚሻለው የሕይወት መንገድ የቱ እንደሆነ የሚያስተምሩን ከመሆኑም በላይ ወደፊት ደግሞ ዘላለማዊ በረከቶችን ማጨድ የምንችልበትን መንገድ ያሳዩናል።​—መዝሙር 19:7, 11ን እና ኢሳይያስ 48:17, 18ን አንብብ።

2. የአምላክ ሕጎች ከጤናችን አንጻር የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

አምላክ ከስካር እንድንርቅ ያወጣው ሕግ ከአደጋና ለሞት ከሚዳርጉ በሽታዎች ይጠብቀናል። ከልክ በላይ መጠጣት ለሱስ የሚዳርግ ከመሆኑም ሌላ የሞኝነት ድርጊት ወደመፈጸም ያመራል። (ምሳሌ 23:20, 29, 30) ይሖዋ የአልኮል መጠጥ እንድንጠጣ የፈቀደልን ቢሆንም ይህን በልክ ማድረግ አለብን።​—መዝሙር 104:15ን እና 1 ቆሮንቶስ 6:10ን አንብብ።

ይሖዋ ከቅናት፣ ከግልፍተኝነት እንዲሁም ጎጂ ከሆኑ ሌሎች ባሕርያት እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል። ምክሩን የምንሰማ ከሆነ የዚያኑ ያህል ጤንነታችን ይጠበቃል።​—ምሳሌ 14:30ን እና ምሳሌ 22:24, 25ን አንብብ።

3. የአምላክ ሕጎች ጥበቃ የሚያደርጉልን እንዴት ነው?

የአምላክ ሕግ ከጋብቻ ውጭ የሚደረግን የፆታ ግንኙነት ይከለክላል። (ዕብራውያን 13:4) ይህንን ሕግ የሚታዘዙ የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርስ የሚተማመኑ ከመሆኑም ሌላ ልጆቻቸው በተሻለ ሁኔታ እንዲያድጉ አጋጣሚ ይፈጥራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ የፆታ ግንኙነት አብዛኛውን ጊዜ ለበሽታ የሚዳርግ ከመሆኑም በላይ ፍቺ፣ የስሜት ቀውስና ግጭት ያስከትላል፤ እንዲሁም ልጆች በነጠላ ወላጅ ብቻ ለማደግ እንዲገደዱ ያደርጋል።​—ምሳሌ 5:1-9ን አንብብ።

ከጋብቻ ውጭ የፆታ ግንኙነት እንድንፈጽም ከሚፈትኑ ሁኔታዎች በመራቅ ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት ጠብቀን መኖር እችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎችን ከመጉዳት እንቆጠባለን።​—1 ተሰሎንቄ 4:3-6ን አንብብ።

4. ለሕይወት አክብሮት ማሳየታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ከአምላክ ላገኘነው የሕይወት ስጦታ አክብሮት ያላቸው ሰዎች ከማጨስና ሕይወትን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ሌሎች ሱሶች ሲርቁ የተሻለ ጤና ይኖራቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) አምላክ በማህፀን ውስጥ ያለን ፅንስ ሕይወት እንኳ ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (ዘፀአት 21:22, 23) በመሆኑም አንድን ፅንስ ሆነ ብለን መግደል የለብንም። በተጨማሪም አምላክ ለሕይወት ያለው ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች በሥራ ቦታቸውም ሆነ በመኖሪያቸው አሊያም ደግሞ መኪና በሚያሽከረክሩበት ወቅት አደጋ ላለማድረስ ይጠነቀቃሉ። (ዘዳግም 22:8) እንዲሁም ሕይወት የአምላክ ስጦታ ስለሆነ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አይካፈሉም።​—መዝሙር 36:9ን አንብብ።

5. ደም ቅዱስ መሆኑን ማወቃችን ጥቅም የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

አምላክ፣ ደም ሕይወትን ወይም የአንድን ፍጡር ነፍስ እንደሚወክል ስለገለጸ ደም ቅዱስ ነው። (ዘፍጥረት 9:3, 4) የአምላክ ሕግ ደምና ሕይወት የተያያዙ ነገሮች እንደሆኑ ይናገራል፤ ይህ ደግሞ እኛን ይጠቅመናል። እንዴት? የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት እንድንችል ያደርገናል።​—ዘሌዋውያን 17:11-13ን እና ዕብራውያን 9:22ን አንብብ።

ኢየሱስ ፍጹም በመሆኑ የእሱ ደም ከማንም የላቀ ዋጋ ነበረው። ኢየሱስ ሕይወቱን የሚወክለውን ነገር ማለትም ደሙን በአምላክ ፊት አቅርቧል። (ዕብራውያን 9:12) የፈሰሰው ደሙ ደግሞ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን በር ከፍቶልናል።​—ማቴዎስ 26:28ን እና ዮሐንስ 3:16ን አንብብ።

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 12 እና 13 ተመልከት።