በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከወንድ ልጅህ ጋር ያለህ ጓደኝነት እንዲቀጥል ምን ማድረግ ትችላለህ?

ከወንድ ልጅህ ጋር ያለህ ጓደኝነት እንዲቀጥል ምን ማድረግ ትችላለህ?

ከወንድ ልጅህ ጋር ያለህ ጓደኝነት እንዲቀጥል ምን ማድረግ ትችላለህ?

“አባዬ፣ ይህን ሁሉ እንዴት አወቅህ?” ልጅህ እንዲህ ብሎ ጠይቆህ ያውቃል? በወቅቱ በልጅህ ጥያቄ ከመገረምም አልፈህ የአባትነት ኩራት ተሰምቶህ ይሆናል። ከዚህም ባሻገር ልጅህ የሰጠኸውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ጥቅም ሲያገኝ ብትመለከት ደግሞ ልብህ ይበልጥ በሐሴት እንደሚሞላ ጥርጥር የለውም። *​—ምሳሌ 23:15, 24

ልጅህ እያደገ ሲሄድ ለአንተ ያለው አድናቆት አሁንም እንደቀድሞው ነው? ወይስ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ለአንተ የሚሰጠው ግምት እየቀነሰ መጥቷል? ልጅህ ወደ አዋቂነት ሲሸጋገር በመካከላችሁ ያለው ጓደኝነት እየጠነከረ እንዲሄድ ምን ማድረግ ትችላለህ? እስቲ መጀመሪያ አባቶች የሚያጋጥሟቸውን የተለመዱ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንመልከት።

ሦስት ተፈታታኝ ሁኔታዎች

1. ጊዜ ማጣት፦ በበርካታ አገሮች ውስጥ ቤተሰቦች ከሚተዳደሩበት ገቢ አብዛኛውን የሚያመጡት አባቶች ናቸው። ብዙውን ጊዜ ደግሞ ሥራቸው ረዘም ያለ ሰዓት ከቤት ውጭ እንዲያሳልፉ ያስገድዳቸዋል። እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች፣ አባቶች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ በጣም ትንሽ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በቅርቡ በፈረንሳይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው በዚያ የሚኖሩ አባቶች በቀን ውስጥ ልጆቻቸውን በመንከባከብ የሚያሳልፉት ጊዜ በአማካይ ከ12 ደቂቃ ያነሰ ነው።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ከልጅህ ጋር ምን ያህል ጊዜ ታሳልፋለህ? በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከልጅህ ጋር በየዕለቱ ምን ያህል ጊዜ እንደምታሳልፍ በወረቀት ላይ ለማስፈር ሞክር። ውጤቱን ስታየው ትገረም ይሆናል።

2. ጥሩ አርዓያ ማጣት፦ አንዳንድ ወንዶች፣ ልጆች እያሉ ከአባቶቻቸው ጋር ያን ያህል የቀረበ ግንኙነት አልነበራቸውም። በፈረንሳይ የሚኖረው ዣን መሪ “ከአባቴ ጋር አንቀራረብም ነበር” ብሏል። ታዲያ ይህ ምን ተጽዕኖ አሳድሮበታል? ዣን መሪ እንዲህ ብሏል፦ “ፈጽሞ ያልጠበቅኳቸውን ችግሮች ፈጥሯል። ለምሳሌ ከልጆቼ ጋር ትርጉም ያለው ውይይት ማድረግ ይከብደኛል።” አንዳንዶች ደግሞ አባቶቻቸውን በደንብ ቢያውቋቸውም እንኳ ከእነሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት አልነበራቸውም። የ43 ዓመቱ ፊሊፕ እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ እንደሚወደኝ ለእኔ መንገር ይከብደው ነበር። በዚህም የተነሳ እኔም ለልጄ ያለኝን ፍቅር ለመግለጽ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጠይቆብኛል።”

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ከአባትህ ጋር የነበረህ ግንኙነት ልጅህን በምትይዝበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ እንዳለ ይሰማሃል? የአባትህን ጥሩም ሆነ መጥፎ ልማዶች እንደምታንጸባርቅ አስተውለሃል? ከሆነ እንዴት?

3. ሚዛናዊ የሆነ ምክር አለማግኘት፦ በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ አባቶች ልጆቻቸውን በማሳደግ ረገድ ብዙም ድርሻ ሊኖራቸው እንደማይገባ ይታሰባል። በምዕራብ አውሮፓ ያደገው ሉካ “ባደግሁበት አካባቢ ሰዎች፣ ልጆችን መንከባከብ የሚስት ኃላፊነት እንደሆነ ይሰማቸዋል” ብሏል። በሌሎች ባሕሎች ውስጥ ደግሞ አባቶች ጥብቅ ሆነው ልጆቻቸውን ሥርዓት ከማስያዝ ውጪ በቤት ውስጥ ሌላ ሚና እንዲጫወቱ አይጠበቅባቸውም። ዦርዥ ያደገው በአፍሪካ ውስጥ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “በእኛ ባሕል አባቶች ከልጆቻቸው ጋር አይጫወቱም፤ ምክንያቱም እንዲህ ካደረጉ ልጆቹ አባቶቻቸውን አያከብሯቸውም ተብሎ ይታሰባል። በዚህም የተነሳ ከልጄ ጋር መጫወት ሁልጊዜ ያስቸግረኛል።”

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ አንተ በምትኖርበት አካባቢ አባቶች ምን ሚና እንዲጫወቱ ይጠበቅባቸዋል? ልጆችን መንከባከብ የሴቶች ሥራ እንደሆነ ይነገራቸዋል? በአካባቢህ አባቶች ለወንዶች ልጆቻቸው ፍቅራቸውን እንዲገልጹ ይበረታታሉ ወይስ እንዲህ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ይታሰባል?

ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙህ ከሆነ ከልጅህ ጋር በመቀራረብ ረገድ እንዲሳካልህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ከዚህ በታች የቀረቡትን ነጥቦች ልብ በል።

ልጅህ ትንሽ እያለ ጀምር

ወንዶች ልጆች ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ አባታቸውን የመምሰል ፍላጎት ያላቸው ይመስላል። በመሆኑም ልጅህ ትንሽ እያለ ይህን ፍላጎቱን ለመኮትኮት ጥረት አድርግ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ደግሞስ ከእሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የምትችለው መቼ ነው?

በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ልጅህ በየዕለቱ በምታከናውናቸው ሥራዎች አብሮህ እንዲካፈል አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ በቤት ውስጥ በምታከናውናቸው ሥራዎች እንዲረዳህ ልታደርግ ትችላለህ። ቤት የምትጠርግ ከሆነ ለልጅህም ትንሽ መጥረጊያ ስጠው፤ ወይም ደግሞ አትክልቶችን የምትኮተኩት ከሆነ አነስ ያለ መኮትኮቻ ይዞ እንዲያግዝህ አድርግ። ልጅህ አባቱን መምሰል ስለሚፈልግ ከአንተ ጋር መሥራት እንደሚያስደስተው ጥርጥር የለውም! እርግጥ አብራችሁ ስትሠሩ ሥራውን ለማጠናቀቅ የበለጠ ጊዜ ሊወስድባችሁ ይችላል፤ ሆኖም እንዲህ ማድረጋችሁ በመካከላችሁ ያለውን ወዳጅነት የሚያጠናክረው ከመሆኑም ሌላ ልጅህ ጥሩ የሥራ ባሕል እንዲኖረው ታሠለጥነዋለህ። ከረጅም ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ፣ አባቶች በዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ልጆቻቸውንም እንዲያሳትፏቸው እንዲሁም አጋጣሚውን ከእነሱ ጋር ለማውራትና እነሱን ለማሠልጠን እንዲጠቀሙበት አበረታቷቸው ነበር። (ዘዳግም 6:6-9) ይህ ምክር ዛሬም ቢሆን ይሠራል።

ከልጅህ ጋር አብረህ ከመሥራት በተጨማሪ ከእሱ ጋር ለመጫወትም ጊዜ መድብ። አብራችሁ መጫወታችሁ ከመዝናናት ያለፈ ተግባር ያከናውናል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ አባቶች ከልጆቻቸው ጋር መጫወታቸው ልጆቹ አዳዲስ ነገሮችን ለማድረግ እንዲደፍሩና ልበ ሙሉ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።

አባትና ልጅ አብረው መጫወታቸው ከዚህም የበለጠ ጥቅም አለው። ሚሼል ፊዝ የተባሉት ተመራማሪ “አንድ ልጅ ከአባቱ ጋር ይበልጥ የሚያወራው አብረው ሲጫወቱ ነው” ብለዋል። በዚህ ወቅት አንድ አባት ለልጁ ያለውን ፍቅር በቃልም ሆነ በድርጊት መግለጽ ይችላል። ይህን ሲያደርግ ልጁም እንዴት ፍቅሩን መግለጽ እንደሚችል ይማራል። በጀርመን የሚኖረው አንድሬ እንዲህ ብሏል፦ “ልጄ ትንሽ እያለ ብዙውን ጊዜ አብረን እንጫወት ነበር፤ እቅፍ አደርገው የነበረ ሲሆን እሱም በምላሹ ለእኔ ያለውን ፍቅር መግለጽ ተምሯል።”

አንድ አባት ከልጁ ጋር ያለውን ቅርበት ማጠናከር የሚችልበት ሌላው አጋጣሚ ደግሞ ማታ ላይ ልጁ ከመተኛቱ በፊት ያለው ጊዜ ነው። ለልጅህ አዘውትረህ ታሪኮችን አንብብለት፤ እንዲሁም ስላስደሰቱት ነገሮችና ስለ ውሎው ሲነግርህ አዳምጠው። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ልጅህ እያደገ ሲሄድም ከአንተ ጋር ማውራት ቀላል ይሆንለታል።

ሁለታችሁንም በሚያስደስቱ ነገሮች መካፈላችሁን ቀጥሉ

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ወንዶች ልጆች ከአባቶቻቸው ጋር ማውራት የማይፈልጉ ይመስሉ ይሆናል። ልጅህ ጥያቄ ስታቀርብለት የሚሸሽ ቢመስልህም ከአንተ ጋር ምንም ነገር ማውራት እንደማይፈልግ አድርገህ አታስብ። ከልጅህ ጋር የምታወራበትን መንገድ ለእሱ እንደሚመቸው ብትቀያይር የልቡን አውጥቶ ለመናገር ሊነሳሳ ይችላል።

በፈረንሳይ የሚኖረው ዣክ አንዳንድ ጊዜ ከልጁ ከዤሮም ጋር ማውራት አስቸጋሪ ይሆንበታል። ሆኖም ልጁ እንዲያወራ ከማስገደድ ይልቅ የሚጠቀምበትን ዘዴ በመለወጥ አብሮት እግር ኳስ መጫወት ጀመረ። ዣክ እንዲህ ብሏል፦ “ከተጫወትን በኋላ ሣሩ ላይ አረፍ እንላለን። ብዙውን ጊዜ ልጄ በዚህ ወቅት የልቡን አውጥቶ ይነግረኛል። አብረን መሆናችንና ብቻችንን ጊዜ ማሳለፍ መቻላችን በመካከላችን ልዩ የሆነ ትስስር እንዲፈጠር እንዳደረገ ይሰማኛል።”

ልጅህ ስፖርት ባይወድስ? አንድሬ ከልጁ ጋር ከዋክብትን በመመልከት ያሳልፉ ስለነበረው ጊዜ ጥሩ ትዝታ አለው። እንዲህ ብሏል፦ “ማታ ማታ ወንበራችንን አውጥተን ቀዝቃዛውን አየር እየሳብን ደጅ የምንቀመጥ ሲሆን የሚሞቅ ልብስ እንደርብና ሻያችንን እየጠጣን ሰማዩን እንመለከታለን። በዚህ ወቅት ከዋክብትን ስለፈጠረው አካል እናወራለን። ስለ ግል ጉዳዮቻችንም እንጨዋወታለን። የማናወራው ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል።”​—ኢሳይያስ 40:25, 26

ልጅህ ከሚወዳቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ባይጥሙህስ? እንዲህ ከሆነ ምርጫዎችህን መሥዋዕት ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። (ፊልጵስዩስ 2:4) በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ኢየን እንዲህ ይላል፦ “እኔ ስፖርት በጣም እወዳለሁ። ልጄ ቮን ግን ይበልጥ የሚወደው አውሮፕላንና ኮምፒውተር ነው። በመሆኑም እኔም እነዚህን ነገሮች ለመውደድ ጥረት ማድረግ ጀመርኩ፤ ልጄን በአየር ላይ ትርዒት ወደሚታይባቸው ቦታዎች እወስደው ነበር፤ እንዲሁም አውሮፕላን ለማብረር የሚያስችል የኮምፒውተር ጨዋታ አብረን እንጫወት ነበር። በእነዚህ አስደሳች እንቅስቃሴዎች አብረን በመካፈላችን ቮን ከእኔ ጋር ይበልጥ በነፃነት ማውራት እንደቻለ ይሰማኛል።”

በራስ የመተማመን ስሜቱ እንዲጎለብት እርዳው

“አባዬ፣ እየኝ፣ እየኝ . . . ።” ልጅህ ትንሽ እያለ አንድ ነገር ማድረግ ሲችል እንዲህ ብሎህ ያውቃል? አሁን ልጅህ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሊሆን ይችላል፤ ታዲያ ልክ እንደ ድሮው “ጎሽ የኔ ልጅ!” ብለህ አድናቆትህን እንድትገልጽለት ለማድረግ ይሞክራል? ምናልባት እንዲህ አያደርግ ይሆናል። ሆኖም ሲያድግ ለራሱ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረው ከፈለግህ በአሁኑ ወቅት ለእሱ ያለህን አድናቆት መግለጽህ አስፈላጊ ነው።

ይሖዋ አምላክ ከአንደኛው ልጁ ጋር በተያያዘ የተወውን ምሳሌ እስቲ እንመልከት። ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ውስጥ አንድ ልዩ ምዕራፍ ሊጀምር ሲል አምላክ “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ለእሱ ያለውን ፍቅር በይፋ ገልጿል። (ማቴዎስ 3:17፤ 5:48) እውነት ነው፣ ልጅህን የማስተማርና የመገሠጽ ኃላፊነት አለብህ። (ኤፌሶን 6:4) ይሁንና በዚህ ብቻ ሳትወሰን ልጅህ አንድ ጥሩ ነገር ሲያደርግ ወይም ሲናገር አድናቆትህን ትገልጽለታለህ?

አንዳንድ ወንዶች አድናቆታቸውንና ፍቅራቸውን መግለጽ ይከብዳቸዋል። ምናልባትም ልጆች ሳሉ ወላጆቻቸው ከመልካም ሥራቸው ይልቅ በስህተቶቻቸው ላይ ያተኩሩ ይሆናል። አንተም ያደግኸው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ከሆነ ልጅህ በራስ የመተማመን ስሜቱ እንዲጎለብት ለመርዳት የታሰበበት ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሉካ፣ 15 ዓመት ከሆነው ማኑዌል ከተባለው ልጁ ጋር አዘውትሮ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ያከናውናል። ሉካ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ማኑዌል አንድን ሥራ ራሱ እንዲጀምርና እርዳታ ከፈለገ እንዲጠራኝ እነግረዋለሁ። ብዙውን ጊዜ ሥራውን ብቻውን ያከናውነዋል። ውጤታማ መሆኑ እርካታ የሚሰጠው ከመሆኑም ሌላ በራስ የመተማመን ስሜቱን ያጎለብትለታል። በሥራው ሲሳካለት አድናቆቴን እገልጽለታለሁ። ሥራው ያሰበውን ያህል ባይሳካለትም እንኳ ያደረገውን ጥረት እንደማደንቅ እነግረዋለሁ።”

የልጅህን በራስ የመተማመን ስሜት ማጎልበት የምትችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ በሕይወቱ ውስጥ ትልልቅ ግቦች ላይ እንዲደርስ መርዳት ነው። ሆኖም ልጅህ አንተ ባሰብከው ፍጥነት ግቦቹ ላይ ባይደርስስ? ወይም ደግሞ ግቦቹ መጥፎ ባይሆኑም እንኳ አንተ ከምትመኝለት ግቦች የተለዩ ቢሆኑስ? እንዲህ ከሆነ ከእሱ ስለምትጠብቀው ነገር መለስ ብለህ ማሰብ ይኖርብሃል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዣክ እንዲህ ብሏል፦ “ልጄ ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች እንዲያወጣ እረዳዋለሁ። ሆኖም እኔ የምፈልጋቸውን ሳይሆን እሱ የሚፈልጋቸውን ግቦች እንዲያወጣ ለመርዳት እጥራለሁ። ከዚያም ግቦቹ ላይ ለመድረስ በሚያደርገው ጥረት በራሱ ፍጥነት እንደሚጓዝ ላለመዘንጋት እሞክራለሁ።” ልጅህ ሐሳቡን ሲገልጽልህ የምታዳምጠው፣ ጠንካራ ጎኖቹን አንስተህ አድናቆትህን የምትገልጽለት እንዲሁም ድክመቶቹን እንዲያሸንፍ የምታበረታታው ከሆነ ግቦቹ ላይ እንዲደርስ ልትረዳው ትችላለህ።

እርግጥ ነው፣ በመካከላችሁ አለመግባባት ሊፈጠርና ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ። ሆኖም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ልጅህ ከአንተ ጋር ያለው ጓደኝነት እንዲቀጥል መፈለጉ የማይቀር ነው። ደግሞስ ስኬታማ እንዲሆን ከሚረዳው ሰው ጋር ያለውን ወዳጅነት ጠብቆ ማቆየት የማይፈልግ ማን አለ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ይህ ርዕስ አባቶች ከወንዶች ልጆቻቸው ጋር ባላቸው ለየት ያለ ቅርርብ ላይ ያተኮረ ቢሆንም ነጥቦቹ አባቶች ከሴቶች ልጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድም ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ።