በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥንቷ ኢየሩሳሌም የጠፋችው መቼ ነው?​—ክፍል ሁለት

የጥንቷ ኢየሩሳሌም የጠፋችው መቼ ነው?​—ክፍል ሁለት

የጥንቷ ኢየሩሳሌም የጠፋችው መቼ ነው?​—ክፍል ሁለት

በሸክላ ላይ የተቀረጹ ሰነዶች ምን ያሳያሉ?

ይህ ርዕስ የጥንቷ ኢየሩሳሌም መጀመሪያ የጠፋችበትን ጊዜ በተመለከተ ምሁራን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ ከሚወጡት ሁለት ተከታታይ ርዕሶች ሁለተኛው ነው። ሁለት ክፍሎች ያሉት ይህ ርዕስ፣ አንዳንድ አንባቢያንን ግራ ካጋቧቸው ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ጥልቅ ምርምር የተደረገባቸውና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መልሶችን ይዟል።

ክፍል አንድ ላይ የሚከተሉት ነጥቦች ተብራርተው ነበር፦

▪ ዓለማዊ የታሪክ ምሁራን ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ587 ዓ.ዓ. እንደሆነ ይናገራሉ።

▪ የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር ከተማዋ የጠፋችው በ607 ዓ.ዓ. እንደሆነ ይጠቁማል።

▪ ዓለማዊ የታሪክ ምሁራን ለደረሱበት መደምደሚያ መሠረት ያደረጉት የጥንት የታሪክ ምሁራንን ሥራዎችና በቶለሚ የነገሥታት ስም ዝርዝር ላይ የሚገኙ ሐሳቦችን ነው።

▪ አንዳንድ የጥንት የታሪክ ምሁራን ጽሑፎች ጉልህ ስህተቶች የሚታዩባቸው ከመሆኑም ሌላ በሸክላ ጽላቶች ላይ ሰፍረው ከሚገኙት የታሪክ መዛግብት ጋር የሚስማሙት ሁልጊዜ አይደለም። *

መጽሐፍ ቅዱስ፣ “በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ሰባው ዓመት እስኪያበቃ ድረስ” አይሁዳውያን በባቢሎን በግዞት እንደሚቆዩ ይናገራል። ታዲያ አይሁዳውያን ከግዞት ነፃ የወጡት መቼ ነበር? ‘በፋርስ ንጉሥ ቂሮስ ዘመነ መንግሥት በመጀመሪያ የግዛት ዓመት’ ላይ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 36:21, 22) አይሁዳውያን በባቢሎን ያሳለፉት የግዞት ዘመን ያበቃው፣ ቂሮስ ባቢሎንን ድል አድርጎ አይሁዳውያንን ነፃ ካወጣቸው በኋላ በ537 ዓ.ዓ. ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ዓለማዊ ታሪክ ይጠቁማል። መጽሐፍ ቅዱስ አይሁዳውያን በግዞት የቆዩት ለ70 ዓመታት እንደሆነ በግልጽ ስለሚናገር ይህ ጊዜ የጀመረው በ607 ዓ.ዓ. መሆን አለበት።

ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ምሁራን ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ587 ዓ.ዓ. እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ የግዞት ዘመኑን 50 ዓመት ብቻ ያደርገዋል። ምሁራኑ እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሱት ለምንድን ነው? ለዘመን ስሌታቸው መሠረት ያደረጉት ስለ ዳግማዊ ናቡከደነፆርና ስለ ወራሾቹ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚገልጹ ጥንታዊ የኪዩኒፎርም ሰነዶችን ስለሆነ ነው።1 ከእነዚህ ሰነዶች መካከል ብዙዎቹ የተጻፉት ኢየሩሳሌም በጠፋችበት ወቅት አሊያም በዚያ ጊዜ አካባቢ በኖሩ ሰዎች ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ587 ዓ.ዓ. ነው ለማለት ያስቻላቸው የዘመን ስሌት ምን ያህል አስተማማኝ ነው? እነዚህ ሰነዶች ምን ያሳያሉ?

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ምሁራን ብዙውን ጊዜ መሠረት የሚያደርጓቸውን ሦስት ዓይነት ሰነዶች ይኸውም (1) የባቢሎናውያን ዜና ታሪኮችን፣ (2) የንግድ ጽላቶችን እና (3) የሥነ ፈለክ ጽላቶችን እንመልከት።

የባቢሎናውያን ዜና ታሪኮች

ምንድን ናቸው? የባቢሎናውያን ዜና ታሪኮች፣ በባቢሎናውያን ታሪክ ውስጥ የተከናወኑ አበይት ክስተቶች በቅደም ተከተል የተመዘገቡባቸው ጽላቶች ናቸው።2

ምሁራን ምን ብለዋል? በኪዩኒፎርም ሰነዶች ላይ በተደረገው ምርምር ረገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ምሁር የሆኑት ሮናልድ ሳክ፣ አበይት ክስተቶችን በተመለከተ ዜና ታሪኮቹ የሚያቀርቡት ዘገባ ያልተሟላ መሆኑን ተናግረዋል። * የታሪክ ምሁራን “ምን እንደተከናወነ በትክክል ለማወቅ . . . ሁለተኛ የመረጃ ምንጮችንም” መመርመር እንደሚያስፈልጋቸው ሮናልድ ሳክ ጽፈዋል።

ሰነዶቹ ምን ያሳያሉ? በባቢሎናውያን ዜና ታሪኮች ላይ የሰፈሩት ዘገባዎች ያልተሟሉ ናቸው።3 ( ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።) እንግዲያው ‘እንዲህ ባለው ያልተሟላ ዘገባ ላይ የተመሠረተ ድምዳሜ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?’ የሚለው ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ነው።

የንግድ ጽላቶች

ምንድን ናቸው? “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” በሚባለው ዘመን የተዘጋጁት አብዛኞቹ የንግድ ጽላቶች ሕጋዊ ደረሰኞች ናቸው። ጽላቶቹ ላይ የተጻፈው ዕለት በወቅቱ የሚገዛውን ንጉሥ የግዛት ዓመት፣ ወርና ቀን የሚያመለክት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጽላት “በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደረፆር [ዳግማዊ ናቡከደነፆር በመባልም ይታወቃል] 11ኛ ዓመት፣ በኒሳን [ወር] በ27ኛው ቀን” ስለተከናወነ የንግድ ልውውጥ ዘግቧል።4

አንድ ንጉሥ ሲሞት ወይም ከሥልጣኑ ወርዶ በሌላ ንጉሥ ሲተካ የዚህ ንጉሥ የግዛት ዘመን ቀሪ ወራት የአዲሱ ንጉሥ የሽግግር ዘመን እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ። *5 በሌላ አባባል ከአንድ ንጉሥ ወደ ሌላኛው ንጉሥ ሥልጣን የሚሸጋገረው በባቢሎናውያን የዘመን አቆጣጠር በተመሳሳይ ዓመት ላይ ነው። በመሆኑም በአዲሱ ንጉሥ የሽግግር ዘመን የተዘጋጁ ጽላቶች ቀን ሊጻፍባቸው የሚገባው የቀድሞው ንጉሥ ሥልጣኑን ከለቀቀበት ወር በኋላ ካሉት ወራት ጀምሮ ነው።

ምሁራን ምን ብለዋል? ሮናልድ ሳክ “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” በሚባለው ዘመን የተዘጋጁ በርካታ የንግድ ጽላቶችን መርምረዋል። ሮናልድ ሳክ በብሪቲሽ ቤተ መዘክር ውስጥ ያሉ ገና ለኅትመት ያልበቁ አዳዲስ ሰነዶችን ከመረመሩ በኋላ ያገኙት መረጃ፣ ከዳግማዊ ናቡከደነፆር ወደ ልጁ አሜል ማርዱክ (ኢቭል ሜሮዳክ ተብሎም ይጠራል) ሥልጣን የተሸጋገረበትን ጊዜ አስመልክቶ ቀደም ሲል የተደረሰበትን ድምዳሜ “ሙሉ በሙሉ የሚያፋልስ” እንደሆነ በ1972 ጽፈው ነበር።6 ይህን ያሉት ለምንድን ነው? ዳግማዊ ናቡከደነፆር በንግሥና ዘመኑ የመጨረሻ ዓመት (43ኛው) በስድስተኛው ወር ሥልጣን ላይ እንደነበር የቀድሞዎቹ ጽላቶች እንደሚጠቁሙ ሮናልድ ሳክ ያውቁ ነበር። ይሁን እንጂ በቀጣዩ ንጉሥ ማለትም በአሜል ማርዱክ የሽግግር ዘመን የተዘጋጁትና በቅርቡ የተተረጎሙት አዳዲስ ጽላቶች ላይ የተጻፈው ቀን ጽላቶቹ ናቡከደነፆር ሥልጣን ላይ እንደነበረ በሚታሰብበት ዓመት አራተኛ እና አምስተኛ ወር ላይ እንደተጻፉ ያመለክታል።7 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የተምታታ ነገር አለ።

ሰነዶቹ ምን ያሳያሉ? ከአንድ ንጉሥ ወደ ሌላው ሥልጣን የተሸጋገረበትን ጊዜ አስመልክቶ በሰነዶቹ ላይ ሌሎችም ግራ የሚያጋቡ ነገሮች ተስተውለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰነድ ዳግማዊ ናቡከደነፆር በአሥረኛው ወር (ይኸውም አልጋ ወራሹ ሥልጣን እንደያዘ ከሚታሰብበት ጊዜ ከስድስት ወራት በኋላም) እየገዛ እንደነበረ ያመለክታል።8 በአሜል ማርዱክና በተተኪው በኔሪግሊሳር መካከል የሥልጣን ሽግግር የተደረገበትን ጊዜ አስመልክቶም ከላይ ያለው ዓይነት የተምታታ ነገር አለ።9

እነዚህ ልዩነቶች ትኩረታችንን የሚስቡት ለምንድን ነው? ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ በባቢሎናውያን ዜና ታሪኮች ላይ የሰፈሩት ዘገባዎች ያልተሟሉ መሆናቸው የታሪክ ዘገባው ቅደም ተከተሉን የጠበቀ ላይሆን እንደሚችል ይጠቁማል።10 በእነዚህ ነገሥታት መካከል የገዙ ሌሎች ነገሥታት ይኖሩ ይሆን? እንዲህ ከሆነ ደግሞ “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” በሚባለው ዘመን ላይ ተጨማሪ ዓመታት መደመር ያስፈልገናል ማለት ነው። እንግዲያው የባቢሎናውያን ዜና ታሪኮችም ሆኑ የንግድ ጽላቶች ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ587 ዓ.ዓ. እንደሆነ በእርግጠኝነት ለመናገር የሚያበቃ መሠረት አይሆኑም። *

የሥነ ፈለክ ጽላቶች

ምንድን ናቸው? ስለ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ፕላኔቶችና ከዋክብት አቀማመጥ የሚገልጽ ማብራሪያ የያዙ እንዲሁም ታሪካዊ መረጃዎችን (ለምሳሌ የአንድን ንጉሥ የግዛት ዘመን) ያካተቱ የኪዩኒፎርም ጽላቶች ናቸው። ለአብነት ያህል፣ ከታች የሚታየው የሥነ ፈለክ ጽላት በንጉሥ ሙኪን ዜሪ አንደኛ ዓመት በመጀመሪያው ወር ላይ ስለተከሰተ የጨረቃ ግርዶሽ ዘግቧል።11

ምሁራን ምን ብለዋል? ባቢሎናውያን፣ ግርዶሾች መቼ ሊከሰቱ እንደሚችሉ የሚገልጹ ትንበያዎችን የያዙ መጠነ ሰፊ ሠንጠረዦችንና ዝርዝር መግለጫዎችን አዘጋጅተው እንደነበረ ምሁራን ይስማማሉ።12

ይሁንና ባቢሎናውያን ወደኋላ በማስላት ከዚያ በፊት ግርዶሾች የታዩበትን ጊዜ ማወቅ ይችላሉ? ፕሮፌሰር ጆን ስቲል እንዲህ ብለዋል፦ “ጽላቶቹ በተዘጋጁበት ወቅት ጸሐፊዎቹ ከዚያ ቀደም ከተከሰቱት ግርዶሾች መካከል አንዳንዶቹን መገመት የቻሉት ወደኋላ በማስላት ሊሆን ይችላል።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።)13 ፕሮፌሰር ዴቪድ ብራውን ደግሞ የባቢሎናውያን የሥነ ፈለክ ጽላቶች ላይ በሰፈሩት ሠንጠረዦች ውስጥ የተካተቱት ትንበያዎች የተደረጉት ሠንጠረዦቹ ከመዘጋጀታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ እንደሆነ ያምናሉ፤ እኚህ ፕሮፌሰር ከእነዚህ ትንበያዎች አንዳንዶቹ “በ4ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እና ከዚያ በኋላ የነበሩ ጸሐፍት ወደኋላ በማስላት” የደረሱባቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል።14 ታዲያ እነዚህ ትንበያዎች ወደኋላ የተደረጉ ስሌቶች ከሆኑ በሌላ ማስረጃ እስካልተደገፉ ድረስ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ?

አንድ ግርዶሽ ባቢሎናውያን በተነበዩበት ቀን ተከስቶ ቢሆን እንኳ የጽላቱ ጸሐፊ ግርዶሹ በተከሰተበት ቀን ላይ እንደተፈጸመ አድርጎ ያቀረበው ታሪካዊ መረጃ ትክክል ነው ማለት ነው? ላይሆን ይችላል። ሮባርተስ ቫን ደር ስፔክ የተሰኙ ምሁር “ጽላቶቹን ያዘጋጁት ሰዎች ኮከብ ቆጣሪዎች እንጂ የታሪክ ምሁራን አልነበሩም” በማለት ተናግረዋል። እኚሁ ምሁር፣ በጽላቶቹ ላይ ከሰፈሩት ታሪካዊ ዘገባዎች ውስጥ ከፊሎቹ “ያን ያህል አስተማማኝ እንዳልሆኑ” የገለጹ ሲሆን እንዲህ ያለውን ታሪካዊ መረጃ ስንጠቅስ “መጠንቀቅ” እንዳለብን አሳስበዋል።15

ሰነዶቹ ምን ያሳያሉ? ቪኤቲ 4956 የተሰኘውን ጽላት እንደ ምሳሌ እንመልከት። የዚህ ጽላት የመጀመሪያ መስመር “የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነፆር 37ኛ ዓመት” ይላል።16 ከዚያ በማስከተል ከተለያዩ ከዋክብትና ኅብረ ከዋክብት አንጻር ስለ ጨረቃና ፕላኔቶች አቀማመጥ ዝርዝር መግለጫ ይዟል። በተጨማሪም በጽላቱ ላይ አንድ የጨረቃ ግርዶሽ ተጠቅሷል። ጨረቃና ፕላኔቶች በጽላቱ ላይ የተገለጸው ዓይነት አቀማመጥ የነበራቸው በ568/567 ዓ.ዓ. እንደነበረ ምሁራን ይናገራሉ፤ ይህ ደግሞ ዳግማዊ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ያጠፋበት ዓመት ይኸውም የግዛቱ 18ኛ ዓመት 587 ዓ.ዓ. ላይ እንዲውል ያደርገዋል። ይሁን እንጂ ስለ እነዚህ ሥነ ፈለካዊ ክስተቶች የሚገልጹት መረጃዎች በእርግጠኝነት የሚያመለክቱት 568/567 ዓ.ዓ. ብቻ ነው?

ከላይ የተገለጸው ጽላት፣ ሲማኑ በሚባለው የባቢሎናውያን ሦስተኛ ወር 15ኛ ቀን ላይ የጨረቃ ግርዶሽ መታየቱ በስሌት እንደተደረሰበት ይጠቅሳል። በዚህ የባቢሎናውያን ወር ማለትም በጁሊየስ የዘመን አቆጣጠር መሠረት ሐምሌ 4 ቀን 568 ዓ.ዓ. የጨረቃ ግርዶሽ ታይቶ እንደነበረ ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ ከ20 ዓመት በፊት ሐምሌ 15 ቀን 588 ዓ.ዓ. ላይም የጨረቃ ግርዶሽ ታይቶ ነበር።17

የዳግማዊ ናቡከደነፆር 37ኛ የግዛት ዓመት 588 ዓ.ዓ. ከሆነ 18ኛ ዓመቱ 607 ዓ.ዓ. ይሆናል ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ስሌት መሠረት ኢየሩሳሌም የጠፋችበት ዓመት ነው! ( ከታች ላይ ያለውን የዘመን ቅደም ተከተል ተመልከት።) ታዲያ ቪኤቲ 4956 ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ607 ዓ.ዓ. መሆኑን የሚደግፍ ተጨማሪ ማስረጃስ ያቀርብ ይሆን?

ቀደም ሲል ከተጠቀሰው ግርዶሽ በተጨማሪ ከጨረቃ አቀማመጥ ጋር በተያያዘ የታዩ 13 መረጃዎች የተመዘገቡ ሲሆን ፕላኔቶችን የሚመለከቱ 15 መረጃዎችም በጽላቱ ላይ ሰፍረዋል። እነዚህ መረጃዎች ጨረቃ ወይም ፕላኔቶች ከአንዳንድ ከዋክብት ወይም ኅብረ ከዋክብት አንጻር የነበራቸውን አቀማመጥ ይገልጻሉ።18 በተጨማሪም ፀሐይ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ እስከምትጠልቅበት ድረስ እንዲሁም ጨረቃ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ እስከምትጠልቅበት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተመዘገቡ ስምንት መረጃዎች በጽላቱ ላይ ሰፍረዋል።18ሀ

ከሌሎች የሰማይ አካላት አንጻር ጨረቃ ስላላት አቀማመጥ በእርግጠኝነት መናገር ስለሚቻል ተመራማሪዎች በቪኤቲ 4956 ላይ የተጠቀሱትን ስለ ጨረቃ አቀማመጥ የሚገልጹ 13 መረጃዎች በጥንቃቄ መርምረዋል። መረጃውን የመረመሩት በቀድሞ ዘመን በሆነ ጊዜ ላይ የሰማይ አካላት የነበሩበትን ቦታ ማመልከት በሚችል የኮምፒውተር ፕሮግራም እየታገዙ ነው።19 ታዲያ ምርምራቸው ምን አሳየ? ከጨረቃ አቀማመጥ ጋር በተያያዘ በጽላቱ ላይ ከሰፈሩት 13 መረጃዎች መካከል በ568/567 ዓ.ዓ. ከነበረው ሁኔታ ጋር የተገጣጠሙት የተወሰኑት ብቻ ሲሆኑ በ588/587 ዓ.ዓ. (ከ20 ዓመት በፊት) ከነበረው ሁኔታ ጋር ግን 13ቱም አቀማመጦች ተገጣጥመዋል።

በጽላቱ ላይ (ገጽ 26 እና 27⁠ን ተመልከት) ከሰፈሩት ስለ ጨረቃ አቀማመጥ የሚገልጹ መረጃዎች አንዱ ከ568 ዓ.ዓ. ይልቅ በ588 ዓ.ዓ. ከተከናወነው ሁኔታ ጋር ይበልጥ ይቀራረባል። ይህ ጽላት በ3ኛው መስመር ላይ፣ “በ9ኛው ዕለት ምሽት [ኒሳኑ 9]” ላይ ጨረቃ ስለነበረችበት ቦታ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ጨረቃ በዚህ ቦታ ላይ የነበረችው በ568 ዓ.ዓ. (ሥነ ፈለካዊ -567) እንደሆነ መጀመሪያ የተናገሩት ምሁራን በ568 ዓ.ዓ. ጨረቃ በዚያ ቦታ ላይ የነበረችው “ኒሳኑ 9 ሳይሆን 8” ላይ እንደነበረ አምነዋል። እነዚህ ምሁራን በጽላቱ ላይ የሰፈረው ዓመት 568 ዓ.ዓ. ነው የሚለውን ሐሳብ ለመደገፍ ሲሉ ጥንታዊው ጸሐፊ ቀኑን “8” ብሎ በመጻፍ ፈንታ በስህተት “9” ብሎ ጽፏል በማለት ተናግረዋል።20 ይሁን እንጂ በጽላቱ 3ኛ መስመር ላይ የተገለጸው የጨረቃ አቀማመጥ በትክክል የሚገጣጠመው ከኒሳኑ 9 ቀን 588 ዓ.ዓ. ጋር ነው።21

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በቪኤቲ 4956 ላይ የተገለጸው አብዛኛው ሥነ ፈለካዊ መረጃ የሚጠቁመው 588 ዓ.ዓ. የዳግማዊ ናቡከደነፆር 37ኛ የግዛት ዓመት እንደሆነ ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ607 ዓ.ዓ. መሆኑን ያረጋግጣል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው?

በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ ዓለማዊ የታሪክ ምሁራን ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ587 ዓ.ዓ. እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የሆኑት ኤርምያስና ዳንኤል፣ አይሁዳውያን በግዞት የቆዩት 70 ዓመት እንጂ 50 ዓመት እንደሆነ አልተናገሩም። (ኤርምያስ 25:1, 2, 11፤ 29:10፤ ዳንኤል 9:2) እነሱ የተናገሩት ሐሳብ ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ607 ዓ.ዓ. እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። ከላይ የተመለከትናቸው ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህ መደምደሚያ ከዓለማዊ ምንጮችም የተወሰነ ድጋፍ አለው።

ዓለማዊ ምሁራን በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ላይ በተደጋጋሚ ጥያቄ አንስተዋል። ሆኖም ተጨማሪ ማስረጃ ሲገኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክለኛነት በተደጋጋሚ ጊዜ ተረጋግጧል። * በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት የሚጥሉ ሁሉ ይህን ለማድረግ በቂ ምክንያት አላቸው። ይህ አመለካከት ሊኖራቸው የቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ፣ ከሳይንስና ከትንቢት አኳያ ትክክል ለመሆኑ ማስረጃ ስላገኙ ነው። ይህ ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ እንደሆነ የሚገልጸውን በውስጡ የሚገኘውን ሐሳብ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) አንተስ ይህን ማስረጃ ለምን አትመረምርም? እንዲህ ብታደርግ ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ልትደርስ ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.14 ማስታወሻ፦ በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት የታሪክ ምሁራን መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ607 ዓ.ዓ. እንደሆነ አያምኑም።

^ አን.18 የባቢሎን ነገሥታት “የግዛት ዘመን” የሚቆጠረው ከኒሳን ወር እስከ ኒሳን ወር ነበር። አንድ ንጉሥ የመጨረሻ “የግዛት ዘመኑን” ሳያጠናቅቅ በሚሞትበት ጊዜ አልጋ ወራሹ ሥልጣን ላይ ወጥቶ በቀሪዎቹ ወራት በመግዛት የሟቹን የግዛት ዘመን ያጠናቅቅለታል። ይህ ወቅት የአዲሱ ንጉሥ “የሽግግር ዘመን” ተብሎ ይጠራል። “የሽግግር ዘመን” የሚለው አገላለጽ አዲሱ ንጉሥ በይፋ ሥልጣን እስከሚይዝበት ጊዜ ድረስ (ይኸውም እስከ ቀጣዩ ዓመት ኒሳን ወር ድረስ) ያሉትን ወራት ያመለክታል። በመሆኑም የአዲሱ ንጉሥ “የግዛት ዘመን” እስከ ቀጣዩ ኒሳን ድረስ አይጀምርም።

^ አን.21 “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” ተብሎ በሚታመነው ዘመን በሙሉ በእያንዳንዱ ዓመት የተዘጋጁ የንግድ ጽላቶች ተገኝተዋል። እነዚህ ነገሥታት የገዙባቸው ዓመታት ከተደመሩ በኋላ “የሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” የመጨረሻ ንጉሥ ከሆነው ከናቦኒደስ አንስቶ ወደኋላ ሲሰላ ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ587 ዓ.ዓ. ነው የሚለው መደምደሚያ ላይ ይደረሳል። ይሁን እንጂ ይህ የዘመናት ስሌት ትክክል የሚሆነው እያንዳንዱ ንጉሥ ቀጣዩን ተክቶ ሥልጣን ላይ የወጣው በዚያው ዓመት ከሆነ ብቻ ነው።

^ አን.36 ይህን በተመለከተ አንዳንድ ምሳሌዎችን ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስየአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 4 እና 5 ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሰንጠረዥ]

 (መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የባቢሎናውያን ዜና ታሪኮች​—ያልተሟሉ የታሪክ ዘገባዎች

የባቢሎናውያን ዜና ታሪኮች ለ88 ዓመታት ገደማ እንደዘለቀ ከሚታመነው “ከሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” ውስጥ በዘገባቸው ላይ ያሰፈሩት የ35ቱን ዓመታት ታሪክ ብቻ ነው።

ዜና ታሪክ ያልተጻፈባቸው ዓመታት

ዜና ታሪክ የተጻፈባቸው ዓመታት

ቢኤም 21901

ቢኤም 21946

ቢኤም 35382

ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ

ፋርሳውያን

ናቦፖላሳር

ዳግማዊ ናቡከደነፆር

አሜል ማርዱክ

ናቦኒደስ

ኔሪግሊሳር

ላባሺ ማርዱክ

ቢኤም 25127

ቢኤም 22047

ቢኤም 25124

[የሥዕል ምንጭ]

BM 21901 and BM 35382: Photograph taken by courtesy of the British Museum; BM 21946: Copyright British Museum; BM 22047, 25124, 25127: © The Trustees of the British Museum

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

የሥነ ፈለክ ጽላት ቢኤም 32238

ይህ ጽላት የጨረቃ ግርዶሾች የተመዘገቡበት ነው፤ ሆኖም ጽላቱ ላይ ያለው መረጃ የተጠናቀረው የመጨረሻው ግርዶሽ ከታየ በኋላ ይኸውም በዝርዝሩ ላይ ከሰፈሩት ግርዶሾች የመጀመሪያው ከታየ ከ400 ዓመታት በኋላ ነው። ጸሐፊው ቀደም ሲል የተከሰቱትን ግርዶሾች በሙሉ ስላላያቸው የተከሰቱበትን ጊዜ ለማወቅ የሒሳብ ስሌቶችን ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል። ይህ ጸሐፊ የደረሰበትን መደምደሚያ የሚደግፉ ተጨማሪ ማስረጃዎች ካልተገኙ በቀር እሱ የሠራቸው ስሌቶች የታሪክ ቅደም ተከተልን የሚያሳይ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ላይሆኑ ይችላሉ።

[የሥዕል ምንጭ]

© The Trustees of the British Museum

[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ቪኤቲ 4956 ምን ይላል?

ይህን ጉዳይ ማንሳት ለምን አስፈለገ? በዚህ ጽላት ላይ ሦስተኛው መስመር፣ በመጀመሪያው ወር (ኒሳኑ/ኒሳን) “በ9ኛው ዕለት ምሽት” ላይ “ጨረቃ ß ቨርጂኒስ [ከተባለችው ኮከብ] ፊት ለፊት 1 ክንድ [ወይም 2 ዲግሪ] ላይ” እንደታየች ይናገራል። ይሁን እንጂ በ1915 ፖል ኖይገባው እና ኧርነስት ዋይድነ ስለ 568 ዓ.ዓ. (ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ587 ዓ.ዓ. ነው ለሚለው መደምደሚያ መሠረት የሆነው ዓመት) ሲጽፉ “ጨረቃ ከዚህ ኮከብ ፊት ለፊት አንድ ክንድ ላይ የታየችው ኒሳን 8 እንጂ ኒሳን 9 አይደለም” ብለው ነበር። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ይሁን እንጂ ኒሳን 9 ቀን 588 ዓ.ዓ. ላይ ጨረቃ ጽላቱ ውስጥ የተገለጸው ቦታ ላይ ታይታ ነበር፤ ይህም ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ607 ዓ.ዓ. መሆኑን ይጠቁማል።

መሆን ያለበት ኒሳን 9 ነው ወይስ 8?

(1) በዚህ ገጽ ላይ ባለው ፎቶግራፍ ላይ በአካድ ቋንቋ 9 ቁጥር የሚጻፍበት ምልክት በግልጽ ይታያል።

(2) ፖል ኖይገባው እና ኧርነስት ዋይድነ በኪዩኒፎርም የተጻፈውን ይህንን ጽላት በራሳቸው ቋንቋ በሚያስቀምጡበት ጊዜ “9” ቁጥርን ወደ “8” ቀይረውታል።

(3) ዋናው ጽሑፍ ላይ ያለው ቁጥር “9” እንደነበረ የገለጹት በግርጌ ማስታወሻው ላይ ብቻ ነው።

(4) በጀርመንኛ ትርጉማቸው ላይም ያሰፈሩት “8” ቁጥርን ነው።

(5) በ1988 አብርሃም ሳክስ እና ኸርማን ሀንገ በጽላቱ ላይ የሰፈረውን ጽሑፍ ሲያሳትሙ ልክ በዋናው ላይ እንደነበረው “9” ቁጥርን አስገብተዋል።

(6) ሆኖም በእንግሊዝኛው ትርጉማቸው ላይ ቁጥሩን ቀይረው “8” ያደረጉት ሲሆን በጽላቱ ላይ “9” የተባለው ‘በስህተት እንደሆነና 8 መባል እንደነበረበት’ ገልጸዋል።

[የሥዕል መግለጫ]

bpk/​Vorderasiatisches Museum, SMB/​Olaf M. Teßmer

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የጥንቷ ኢየሩሳሌም የጠፋችው መቼ ነው?​ክፍል ሁለት” ተጨማሪ መረጃ

1. ኪዩኒፎርም የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የሚጻፍበት የጽሑፍ ዓይነት ነው። አንድ ጸሐፊ እንዲህ ዓይነት ጽሑፍ የሚያዘጋጀው ሹል የሆነና ጫፉ ላይ የሽብልቅ ቅርጽ ያለው መጻፊያ እየተጠቀመ ባልደረቀ የሸክላ ጽላት ላይ የተለያዩ ምልክቶችን በመቅረጽ ነው።

2. አሲሪያን ኤንድ ባቢሎኒያን ክሮኒክልስ፣ በአልበርት ኪርክ ግሬሰን የተዘጋጀና በ1975 የታተመ፣ በ2000 እንደገና የታተመ፣ ገጽ 8

3. “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” የሚባለው ዘመን የጀመረው የከለዳውያን ሥርወ መንግሥት የባቢሎንን ግዛት ያስተዳድር በነበረበት በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነበር። የዚህ ሥርወ መንግሥት የመጀመሪያ ንጉሥ የዳግማዊ ናቡከደነፆር አባት የሆነው ናቦፖላሳር ነው። “ሁለተኛው የባቢሎን አገዛዝ” ያበቃው የመጨረሻው ንጉሥ የሆነውን ናቦኒደስን የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ በ539 ዓ.ዓ. ከሥልጣኑ ባወረደው ጊዜ ነበር።

4. ኒዎ ባቢሎኒያን ቢዝነስ ኤንድ አድሚንስትሬቲቭ ዶክዩመንትስ፣ በኤለን ዊትሊ ሙር የተዘጋጀና በ1935 የታተመ፣ ገጽ 33

5. አርከሚዲዝ፣ ቮልዩም 4 ኒው ስተዲስ ኢን ዘ ሂስትሪ ኤንድ ፊሎዞፊ ኦቭ ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ፣ “ኦብዘርቬዥንስ ኤንድ ፕሪዲክሽንስ ኦቭ ኤክሊፕስ ታይምስ ባይ ኧርሊ አስትሮኖመርስ” በጆን ስቲል የተዘጋጀና በ2000 የታተመ፣ ገጽ 36

6. አሜል ማርዱክ 562-560 ዓ.ዓ.​ኤ ስተዲ ቤዝድ ኦን ኪዩኒፎርም፣ ኦልድ ቴስታመንት፣ ግሪክ፣ ላቲን ኤንድ ረቢኒካል ሶርስስ። ዊዝ ፕሌትስ፣ በሮናልድ ሳክ የተዘጋጀና በ1972 የታተመ፣ ገጽ 3

7. ቢኤም 80920 እና ቢኤም 58872 የተባሉት ጽላቶች የተዘጋጁት በኢቭል ሜሮዳክ የሽግግር ዘመን አራተኛና አምስተኛ ወር ነው። በእነዚህ ጽላቶች ላይ ያለውን መረጃ ሮናልድ ሳክ፣ አሜል ማርዱክ 562-560 ዓ.ዓ.​ኤ ስተዲ ቤዝድ ኦን ኪዩኒፎርም፣ ኦልድ ቴስታመንት፣ ግሪክ፣ ላቲን ኤንድ ረቢኒካል ሶርስስ። ዊዝ ፕሌትስ፣ ገጽ 3, 90, 106 ላይ አሳትመውታል።

8. በብሪትሽ ቤተ መዘክር የሚገኘው ጽላት (ቢኤም 55806) ላይ የተጻፈው ቀን በ43ኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ይላል።

9. ቢኤም 75106 እና ቢኤም 61325 የተባሉት ጽላቶች የኢቭል ሜሮዳክ የግዛቱ የመጨረሻ (ሁለተኛ) ዓመት ተብሎ በሚታሰበው ወቅት ሰባተኛና አሥረኛ ወር የተዘጋጁ ናቸው። ሆኖም ቢኤም 75489 የተባለው ጽላት የተጻፈው በኢቭል ሜሮዳክ አልጋ ወራሽ ማለትም በኔሪግሊሳር የሽግግር ዘመን ሁለተኛ ወር ነው።​—ካታሎግ ኦቭ ዘ ባቢሎንያን ታብሌትስ ኢን ዘ ብሪትሽ ሙዚየም፣ ጥራዝ 8 (ታብሌትስ ፍሮም ሲፓር 3) በኧርል ሊችቲ፣ ፊንከልስታይን እና ክሪስቶፈር ዎከር የተዘጋጀና በ1988 የታተመ፣ ገጽ 25, 35

ካታሎግ ኦቭ ዘ ባቢሎንያን ታብሌትስ ኢን ዘ ብሪትሽ ሙዚየም፣ ጥራዝ 7 (ታብሌትስ ፍሮም ሲፓር 2) በኧርል ሊችቲ እና በአልበርት ኪርክ ግሬሰን የተዘጋጀና በ1987 የታተመ፣ ገጽ 36

ኔሪግሊሳር​ኪንግ ኦቭ ባቢሎን፣ በሮናልድ ሳክ የተዘጋጀና በ1994 የታተመ፣ ገጽ 232። በጽላቱ ላይ ያለው ወር አጃሩ (ሁለተኛ ወር) ነው።

10. የኔሪግሊሳርን ምሳሌ እንመልከት። ስለ እሱ የተዘጋጀ የንጉሣዊ ቤተሰብ ጽሑፍ ይህ ሰው “የባቢሎን ንጉሥ” የሆነው “የቤል ሹም ኢሽኩን ልጅ” እንደሆነ ይገልጻል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ሌላ ጽሑፍ ደግሞ ቤል ሹም ኢሽኩንን “ጠቢቡ ልዑል” ይለዋል። “ልዑል” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ሩቡ ሲሆን ይህ የማዕረግ ስም “ንጉሥ፣ ገዥ” የሚል ትርጉምም አለው። በኔሪግሊሳርና ከእሱ በፊት እንደነበረ በሚታሰበው በአሜል ማርዱክ የግዛት ዘመን መካከል የተምታታ ነገር እንዳለ በግልጽ ስለሚታይ “የባቢሎን ንጉሥ” የተባለው ቤል ሹም ኢሽኩን በሁለቱ ነገሥታት መካከል ባለው ጊዜ ገዝቶ ይሆን? ፕሮፌሰር ሬይመንድ ዶኸርቲ “ኔርግሊሳር የነገሥታት ዘር እንደሆነ የሚያሳየው መረጃ አሌ የሚባል አይደለም” በማለት ተናግረዋል።​—ናቦኒደስ ኤንድ ቤልሻዛር​ኤ ስተዲ ኦቭ ዘ ክሎዚንግ ኢቨንትስ ኦቭ ዘ ኒዎ ባቢሎኒያን ኢምፓየር፣ በሬይመንድ ዶኸርቲ የተዘጋጀና በ1929 የታተመ፣ ገጽ 61

11. አስትሮኖሚካል ዳየሪስ ኤንድ ሪሌትድ ቴክስትስ ፍሮም ባቢሎኒያ፣ ጥራዝ 5፣ አርታኢ ኸርማን ሃንገ፣ በ2001 የታተመ፣ ገጽ 2, 3

12. ጆርናል ኦቭ ኪዩኒፎርም ስተዲስ፣ ጥራዝ 2 ቁ. 4, 1948 “ኤ ክላሲፊኬሽን ኦቭ ዘ ባቢሎኒያን አስትሮኖሚካል ታብሌትስ ኦቭ ዘ ሰሉሲድ ፒሬድ” በአብርሃም ሳክስ የተዘጋጀ፣ ገጽ 282, 283

13. አስትሮኖሚካል ዳየሪስ ኤንድ ሪሌትድ ቴክስትስ ፍሮም ባቢሎኒያ፣ ጥራዝ 5 ገጽ 391

14. ሜሶፖታሚያን ፕላኔተሪ አስትሮኖሚ አስትሮሎጂ፣ በዴቪድ ብራውን የተዘጋጀና በ2000 የታተመ፣ ገጽ 164, 201, 202

15. ቢብሊዮቴካ ኦሪየንታሊስ፣ ጥራዝ 50 ቁ. 1, 2 ጃኑዋሪ-ማርት፣ 1993 “ዚ አስትሮኖሚካል ዳየሪስ አዝ ኤ ሶርስ ፎር ኧኪመኒድ ኤንድ ሰሉሲድ ሂስትሪ” በሮባርተስ ቫን ደር ስፔክ የተዘጋጀ፣ ገጽ 94, 102

16. አስትሮኖሚካል ዳየሪስ ኤንድ ሪሌትድ ቴክስትስ ፍሮም ባቢሎኒያ፣ ጥራዝ 1 በአብርሃም ሳክስ የተዘጋጀ፣ መጽሐፉን አጠናቅቀው የአርትኦት ሥራውን ያከናወኑት ኸርማን ሃንገ፣ በ1988 የታተመ፣ ገጽ 47

17. ባቢሎኒያን ኤክሊፕስ ኦብዘርቬሽንስ ፍሮም 750 ቢሲ ቱ 1 ቢሲ፣ በፒተር ሂዩበር እና በሳልቮ ደ ሜስ የተዘጋጀና በ2004 የታተመ ገጽ 186። ቪኤቲ 4956 እንደሚገልጸው ይህ ግርዶሽ የታየው በባቢሎናውያን ሦስተኛ ወር 15ኛ ቀን ሲሆን ይህም ሲማኑ የተባለው ወር የጀመረው 15 ቀን ቀደም ብሎ እንደሆነ ይጠቁማል። ግርዶሹ የታየው በጁሊየስ የዘመን አቆጣጠር ሐምሌ 15 ቀን 588 ዓ.ዓ. ከሆነ የሲማኑ የመጀመሪያ ዕለት ሰኔ 30/ሐምሌ 1 ቀን 588 ዓ.ዓ ይሆናል። እንግዲያው የባቢሎናውያን የመጀመሪያ ወር የሆነው ኒሳኑ (የአዲሱ ዓመት መባቻ) የጀመረው ከሁለት ወር በፊት ማለትም ግንቦት 2/3 ይሆናል። እንደ ወትሮው ቢሆን ግርዶሹ የታየበት ዓመት ሚያዝያ 3/4 መጀመር ነበረበት፤ ሆኖም ቪኤቲ 4956 በ6ኛው መስመር ላይ እንደሚገልጸው ካለፈው ዓመት አሥራ ሁለተኛ ወር (አዳሩ ከሚባለው የመጨረሻው ወር) በኋላ ተጨማሪ ወር ታክሏል። (ጽላቱ “XIIወር [13ኛ ወር] 8ኛ ቀን” ይላል።) በዚህም የተነሳ አዲሱ ዓመት እስከ ግንቦት 2/3 አልጀመረም። ስለዚህ በ588 የታየው ግርዶሽ በጽላቱ ላይ ካለው ሐሳብ ጋር ይስማማል።

18. ቤርሽቴ ኡበር ዲ ፈርሃንድለንገን ዴር ከርኒግሊሽ። ዜግሴሽን ግዜልሻፍት ዴር ቪስንሻፍተን ጹ ላይፕዚግ (ሪፖርትስ ሪጋርዲንግ ዘ ዲስከሽንስ ኦቭ ዘ ሮያል ሳክሶኒያን ሶሳይቲ ኦቭ ሳይንስስ አት ላይፕዚግ)፤ ጥራዝ 67፤ ግንቦት 1 ቀን 1915፤ “አይን አስትሮኖሚሸር ቤኦባክቱንግስቴክት አውስ ዴም 37። ያሬ ኔቡኬድኔጻርስ II” (አን አስትሮኖሚካል ኦብዘርቨርስ ቴክስት ኦቭ ዘ 37ዝ ይር ናቡከድናዘር II) በሚለው ርዕስ ሥር፤ በፖል ኖይገባው እና በኧርነስት ዋይድነ የተዘጋጀ፣ ከገጽ 67-76 እንደሚለው ጨረቃ ከአንድ ኮከብ ወይም ከኅብረ ከዋክብት አንጻር የታየችበትን ቦታ የሚያብራሩ 13 መረጃዎች አሉ። በተጨማሪም ፕላኔቶችን የሚመለከቱ 15 መረጃዎች በጽላቱ ላይ ሰፍረዋል። (ከገጽ 72-76) ጨረቃን የሚያመለክተው የኪዩኒፎርም ምልክት ግልጽና የማያሻማ ቢሆንም የፕላኔቶቹን ስምና የታዩበትን ቦታ ከሚጠቁሙት ምልክቶች አንዳንዶቹ አሻሚ ናቸው። (ሜሶፖታሚያን ፕላኔተሪ አስትሮኖሚ​አስትሮሎጂ፣ በዴቪድ ብራውን የተዘጋጀና በ2000 የታተመ፣ ከገጽ 53-57) በዚህም ምክንያት ስለ ፕላኔቶቹ አቀማመጥ የቀረቡትን መረጃዎች በተመለከተ ግምታዊ ሐሳቦች ሊሰነዘሩና የተለያየ ፍቺ ሊሰጥ ይችላል። የጨረቃን እንቅስቃሴ በቀላሉ ማወቅ ስለሚቻል፣ በቪኤቲ 4956 ላይ የተጠቀሱትንና ከጨረቃ ጋር ተያይዘው የተገለጹትን ሌሎች የሰማይ አካላት አቀማመጥ ማወቅ እንዲሁም የታዩበትን ቀን በተወሰነ መጠን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።

18ሀ. እነዚህ መረጃዎች (“ሉናር ስሪስ”) ለምሳሌ በወሩ የመጀመሪያ ቀን እንዲሁም በወሩ ውስጥ በሌሎች ሁለት ቀናት ፀሐይ ከጠለቀችበት ጀምሮ ጨረቃ እስከምትጠልቅበት ያለውን የጊዜ ርዝመት ያመለክታሉ። ምሁራን በተለያዩ ቀናት ላይ ያስተዋሉትን የጊዜ ርዝመት (ለምሳሌ ፀሐይ ከጠለቀችበት ጀምሮ ጨረቃ እስከምትጠልቅበት ያለውን ጊዜ) በመጠቀም እነዚያን ቀናት በቀን መቁጠሪያ ላይ ከሚገኙት ቀናት ጋር አዛምደዋቸዋል። (“ዚ ኧርሊየስት ዴተብል ኦብዘርቬሽን ኦቭ ዚ አውሮራ ቦሪያሊስ፣” በሪቻርድ ስቴፈንሰን እና ዴቪድ ዊሊስ የተዘጋጀ፣ አንደር ዋን ስካይ​አስትሮኖሚ ኤንድ ማቲማቲክስ ኢን ዚ ኤንሸንት ኒር ኢስት ከሚለው መጽሐፍ፣ አርታእያን ጆን ስቲል እና አኔት ኢምሃውሰን፣ በ2002 የታተመ፣ ከገጽ 420-428) የጥንቶቹ ባለሙያዎች ይህን ጊዜ ለመለካት እንደ ሰዓት የሚያገለግል መሣሪያ ያስፈልጋቸው ነበር። ሆኖም እንዲህ ዓይነቶቹ መለኪያዎች አስተማማኝ አልነበሩም። (አርከሚዲዝ፣ ቮልዩም 4 ኒው ስተዲስ ኢን ዘ ሂስትሪ ኤንድ ፊሎዞፊ ኦቭ ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ፣ “ኦብዘርቬዥንስ ኤንድ ፕሪዲክሽንስ ኦቭ ኤክሊፕስ ታይምስ ባይ ኧርሊ አስትሮኖመርስ” በጆን ስቲል የተዘጋጀና በ2000 የታተመ፣ ገጽ 65, 66) በሌላ በኩል ግን ጨረቃ ከሌሎች የሰማይ አካላት አንጻር የታየችበትን ቦታ በእርግጠኝነት ማስላት ይቻል ነበር።

19. ይህ ምርምር የተደረገው TheSky6™ የተባለ የሥነ ፈለክ የኮምፒውተር ፕሮግራም በመጠቀም ነው። በተጨማሪም ካርት ዱ ሲየል/ስካይ ቻርትስ (ሲዲሲ) የተባለውን ብዙ ነገር ያካተተ የኮምፒውተር ፕሮግራም እና የዩናይትድ ስቴትስ ናቫል ኦብዘርቫቶሪ ያዘጋጀውን ቀን መቀየሪያ ተጠቅመዋል። የፕላኔቶችን አቀማመጥ የሚያሳዩት ብዙዎቹ የኪዩኒፎርም ምልክቶች አሻሚ ከመሆናቸውም ሌላ የተለያየ ግምታዊ ፍቺ ሊሰጣቸው ይችላል፤ በመሆኑም ምሁራን በጽላቱ ላይ የተጠቆመውን ዓመት ለማስላት የፕላኔቶችን አቀማመጥ አልተጠቀሙም።

20. ቤርሽቴ ኡበር ዲ ፈርሃንድለንገን ዴር ከርኒግሊሽ። ዜግሴሽን ግዜልሻፍት ዴር ቪስንሻፍተን ጹ ላይፕዚግ (ሪፖርትስ ሪጋርዲንግ ዘ ዲስከሽንስ ኦቭ ዘ ሮያል ሳክሶኒያን ሶሳይቲ ኦቭ ሳይንስስ አት ላይፕዚግ)፤ ጥራዝ 67፤ ግንቦት 1 ቀን 1915፤ “አይን አስትሮኖሚሸር ቤኦባክቱንግስቴክት አውስ ዴም 37። ያሬ ኔቡኬድኔጻርስ II (-567/66)” (አን አስትሮኖሚካል ኦብዘርቨርስ ቴክስት ኦቭ ዘ 37ዝ ይር ናቡከድናዘር II) በፖል ኖይገባው እና በኧርነስት ዋይድነ የተዘጋጀ፣ ገጽ 41

21. ቪኤቲ 4956 በሦስተኛው መስመር ላይ “ጨረቃ ß ቨርጂኒስ [ከተባለችው ኮከብ] ፊት ለፊት 1 ክንድ [ወይም 2 ዲግሪ] ላይ ታይታለች” ይላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ምርምር እንደሚገልጸው በኒሳኑ 9 ጨረቃዋ ß ቨርጂኒስ ከተባለችው ኮከብ ፊት ለፊት 2°04ʹ ላይ እንዲሁም ከኮከቡ ሥር 0° ላይ ነበረች። ጽላቱ ላይ የሰፈረውና በኒሳኑ 9 የታየው የጨረቃ አቀማመጥ በትክክል ተገጣጥሟል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

 (መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቪኤቲ 4956 ኢየሩሳሌም የጠፋችው በየትኛው ዓመት እንደሆነ ያመለክታል?​—በ587 ዓ.ዓ. ወይስ በ607 ዓ.ዓ.?

◼ ይህ ጽላት በዳግማዊ ናቡከደነፆር 37ኛ የግዛት ዓመት ስለታዩት ሥነ ፈለካዊ ክስተቶች ይገልጻል።

◼ ዳግማዊ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ያጠፋት በ18ኛው የግዛት ዘመኑ ነው።​—ኤርምያስ 32:1

የናቡከደነፆር 37ኛ የግዛት ዓመት 568 ዓ.ዓ. ከነበረ ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ587 ዓ.ዓ. ይሆናል።

610 ዓ.ዓ.

600

590

580

570

560

የናቡከደነፆር 37ኛ የግዛት ዓመት 588 ዓ.ዓ. ከነበረ ደግሞ ኢየሩሳሌም የጠፋችው የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር በሚያመለክተው ዓመት ይኸውም በ607 ዓ.ዓ. ይሆናል።

◼ ቪኤቲ 4956 ላይ ያለው መረጃ ይበልጥ የሚያደላው ወደ 607 ዓ.ዓ. ነው።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Photograph taken by courtesy of the British Museum