በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደ ዮፍታሔ ልጅ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ

እንደ ዮፍታሔ ልጅ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ

እንደ ዮፍታሔ ልጅ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ

ጆአና ሶንስ እንደተናገረችው

በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ እንደ ዮፍታሔ ልጅ የመሆን ታላቅ ጉጉት አደረብኝ። ፍላጎቴ ምን እንደነበርና ከጊዜ በኋላ እንደ እሷ መሆን የቻልኩት እንዴት እንደሆነ እስቲ ላጫውታችሁ።

በ1956 የይሖዋ ምሥክሮች በቦምቤይ (ሙምባይ)፣ ሕንድ ባደረጉት ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘሁ ሲሆን ይህ ስብሰባ ሕይወቴን ለወጠው። ስለ ዮፍታሔ ልጅ የቀረበ አንድ ንግግር ልቤን በጥልቅ ነካው።

የዮፍታሔ ልጅ ምናልባትም ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለች ሳታገባ ለመኖር እንደተስማማች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንብባችሁ ይሆናል። ይህን በማድረጓ አባቷ ስእለቱን መፈጸም ችሏል። እሷም ዕድሜዋን ሙሉ በይሖዋ ቤት ማለትም በመገናኛ ድንኳኑ ነጠላ ሆና አገልግላለች።​—መሳፍንት 11:28-40

እኔም እንደ እሷ ለመሆን በጣም ጓጓሁ! ይሁንና ምኞቴን እንዳላሳካ እንቅፋት የሚሆንብኝ ከባድ ፈተና ነበረ፤ በወቅቱ በሕንድ ባሕል ሳያገቡ መኖር ጨርሶ ያልተለመደ ነገር ነበር።

የቤተሰባችን ሕይወት

ወላጆቼ ቤንጃሚን እና ማርሴሊና ሶንስ ከወለዷቸው ስድስት ልጆች መካከል አምስተኛዋ ስሆን የምንኖረው በሕንድ ምዕራባዊ ዳርቻ በምትገኝ ዩዱፒ የተባለች ከተማ ነበር። የአፍ መፍቻ ቋንቋችን ቱሉ ነው፤ በዚህ ቋንቋ ሁለት ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ይጠቀማሉ። ይሁንና በዩዱፒ እንደሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉ ትምህርት የተማርነው ካናዳ በተባለው ቋንቋ ነበር።

በዚህ አካባቢ፣ አግብቶ ልጆች መውለድ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር ነው። በልጅነቴ “ነጠላነት፣” “ብቸኝነት” እና “የቤተሰብ ናፍቆት” የሚሉት ቃላት በቱሉ ቋንቋ ሲነገሩ ሰምቼ አላውቅም። በባሕላችን ውስጥ እነዚህ ሁኔታዎች የነበሩ አይመስልም። ለምሳሌ ያህል፣ እኛ የምንኖረው ከአያቶቻችን፣ ከአጎትና ከአክስቶቻችን እንዲሁም ከአሥራ ሁለት ልጆቻቸው ጋር ነበር።

በባሕላችን ልጆች የእናት ቤተሰብ አባል እንደሆኑ ተደርጎ ይታሰባል። የዘር ሐረግ የሚቆጠረው በእናት በኩል ሲሆን ውርስ ሲከፋፈል ሴት ልጆች በርከት ያለውን ድርሻ ይወስዳሉ። በአንዳንድ የቱሉ ማኅበረሰቦች አንዲት ሴት ካገባችም በኋላ ባሏን ይዛ እናቷ ቤት መኖሯን ትቀጥላለች።

ቤተሰባችን የሕዝበ ክርስትና አባል በመሆኑ በአንዳንድ ነገሮች ከማኅበረሰቡ የተለየን ነበርን። ሁልጊዜ ምሽት ላይ አያቴ፣ ቤተሰቡን ሰብስቦ በመጸለይና በቱሉ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ጮክ ብሎ በማንበብ የአምልኮ ሥርዓት ያካሂድ ነበር። አያቴ ያረጀውን መጽሐፍ ቅዱሱን ለማንበብ ሲያወጣ ውድ ሀብት የተከማቸበትን ሣጥን የሚከፍት ያህል ነበር። ይህን ጊዜ በጉጉት እንጠብቀው ነበር! በመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ወቅት የሰማሁት “ይሖዋ እረኛዬ ነው። የሚጎድልብኝ አንዳች ነገር የለም” የሚለው በ⁠መዝሙር 23:1 (NW) ላይ የሚገኘው ጥቅስ ጥያቄ ይፈጥርብኝ ነበር። ‘እዚህ ላይ ይሖዋ የተባለው ማን ነው? እረኛ የተባለውስ ለምንድን ነው?’ የሚሉት ጥያቄዎች በአእምሮዬ ይመላለሱ ነበር።

ከዓይኖቼ ላይ “ቅርፊት” የወደቀ ያህል ሆኖ ተሰማኝ

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተከሰተው የኢኮኖሚ ችግር የተነሳ ቤተሰባችን 900 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ቦምቤይ ተዛወረ። በዚያ እያለን በ1945 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች አባቴን ያነጋገሩት ሲሆን በካናዳ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ያለው ቡክሌት ሰጡት። የደረቀ መሬት ዝናብ ሲያገኝ ምጥጥ እንደሚያደርገው ሁሉ አባቴም በቡክሌቱ ላይ ያለውን መልእክት በጉጉት ያነበበው ከመሆኑም ሌላ ያገኘውን እውቀት የካናዳ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ማካፈል ጀመረ። ከጊዜ በኋላ፣ በቦምቤይ መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ የሚያጠናው ትንሽ ቡድን አድጎ በ1950ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በካናዳ ቋንቋ የሚመራ የመጀመሪያው ጉባኤ ለመሆን በቃ።

ወላጆቻችን ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችና ውጤታማ አስተማሪዎች እንድንሆን አሠልጥነውናል። በየቀኑ አብረውን ለመጸለይና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጊዜ ይመድቡ ነበር። (ዘዳግም 6:6, 7፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:14-16) አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱስ እያነበብኩ እያለ ከዓይኖቼ ላይ ቅርፊት የወደቀ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። (የሐዋርያት ሥራ 9:18) ይሖዋ በእረኛ የተመሰለው፣ አምላኪዎቹን ስለሚመራና ስለሚመግባቸው እንዲሁም ጥበቃ ስለሚያደርግላቸው መሆኑን ተገነዘብኩ።​—መዝሙር 23:1-6፤ 83:18 NW

ይሖዋ እጄን ይዞ መርቶኛል

በ1956 በቦምቤይ ከተደረገው የማይረሳ የአውራጃ ስብሰባ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቅሁ። ከስድስት ወር በኋላ፣ ፕራባካር የተባለውን ታላቅ ወንድሜን ምሳሌ በመከተል የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆንኩ። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለሰዎች የማካፈል ጉጉት የነበረኝ ቢሆንም ስለማምንበት ነገር ለመናገር ስሞክር ምላሴ ይተሳሰር ነበር። ስናገር የምንተባተብ ከመሆኑም ሌላ ድምፄ መንቀጥቀጥ ይጀምራል። ‘ይህን ሥራ መሥራት የምችለው በይሖዋ እርዳታ ብቻ ነው!’ ብዬ አስብ ነበር።

ይሖዋም ሆመርና ሩት መኬይ በተባሉ ካናዳውያን የሆኑ ሚስዮናውያን አማካኝነት ይህን ችግሬን ማሸነፍ እንድችል ረዳኝ፤ እነዚህ ባልና ሚስት በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በይሖዋ ምሥክሮች የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት በ1947 ሠልጥነዋል። አገልግሎቴን ሀ ብዬ ስጀምር እነዚህ ሚስዮናውያን እጄን ይዘው የመምራት ያህል በአገልግሎቴ ረድተውኛል። ሩት ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል የምንጠቀምባቸውን መግቢያዎች ሁልጊዜ ታዘጋጀኛለች። እኔን ለማረጋጋት ምን ማድረግ እንዳለባት ታውቅ ነበር። የሚንቀጠቀጠውን እጄን ያዝ በማድረግ “አይዞሽ፣ እስቲ የሚቀጥለውን ቤት እንሞክር” ትለኛለች። የሚያበረታታው የድምፅዋ ቃና ድፍረት እንዳገኝ ይረዳኝ ነበር።

አንድ ቀን፣ ኤልዛቤት ቻክራናራያን የተባለች በዕድሜ የምትበልጠኝና መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ረገድ ተሞክሮ ያካበተች እህት አብራኝ እንደምታገለግል ተነገረኝ። መጀመሪያ ላይ ‘በዕድሜ ይህን ያህል ከምትበልጠኝ እህት ጋር አብሬ የምኖረው እንዴት ነው?’ የሚል ስሜት አድሮብኝ ነበር። ይሁንና የሚያስፈልገኝ ልክ እንደ እሷ ዓይነት ሰው መሆኑን እያደር ተገነዘብኩ።

“ፈጽሞ ብቻችንን አይደለንም”

የመጀመሪያ ምድባችን ከቦምቤይ በስተምሥራቅ 400 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው አውራንጋባድ የተባለች ታሪካዊ ከተማ ነበረ። ብዙም ሳይቆይ፣ አንድ ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች በሚኖሩባት በዚህች ከተማ ውስጥ ያለነው የይሖዋ ምሥክሮች ሁለታችን ብቻ እንደሆንን ተገነዘብን። በዚያ ላይ ደግሞ መራቲ የተባለውን በከተማዋ ውስጥ በዋነኝነት የሚነገረውን ቋንቋ መማር ነበረብኝ።

አንዳንድ ጊዜ በብቸኝነት ስሜት ስለምዋጥ እናት እንደሌለው ልጅ ስቅስቅ ብዬ አለቅሳለሁ። ይሁንና ኤልዛቤት እንደ እናት ሆና ታበረታታኝ ነበር። “አልፎ አልፎ ብቸኝነት ቢሰማንም ፈጽሞ ብቻችንን አይደለንም” ትለኛለች። “ከጓደኞችሽና ከቤተሰቦችሽ ብትርቂም ይሖዋ ምንጊዜም ከአንቺ ጋር ነው። እሱን ወዳጅሽ ካደረግሽው የብቸኝነት ስሜትሽ ድራሹ ይጠፋል።” የሰጠችኝን ምክር አሁንም ቢሆን ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ።

የትራንስፖርት ገንዘባችን እየተሟጠጠ ሲሄድ በሞቃትም ሆነ በቅዝቃዜ ወቅት መንገዱ አቧራም ይሁን ጭቃ በየዕለቱ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ድረስ በእግራችን እንጓዝ ነበር። በሞቃቱ ወቅት ብዙውን ጊዜ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስ ሙቀት ይኖራል። ኃይለኛ ዝናብ በሚኖርበት ወቅት ደግሞ አንዳንድ አካባቢዎች ለብዙ ወራት ይጨቀዩ ነበር። ከአየሩ ጠባይ ይበልጥ ተፈታታኝ የነበረው ግን ባሕሉ በሰዎች አመለካከት ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ ነው።

በአካባቢው ባሕል መሠረት ሴቶች ከዘመዶቻቸው ጋር ካልሆነ በቀር በአደባባይ ከወንዶች ጋር አያወሩም፤ ሴቶች ወንዶችን ማስተማራቸውም ቢሆን ያልተለመደ ነገር ነው። በመሆኑም ሰዎች ያፌዙብንና ያንገላቱን ነበር። በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ በሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ የምንገኘው ሁለታችን ብቻ ነበርን። ከጊዜ በኋላ ግን ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በስብሰባ ላይ መገኘት ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ አነስተኛ ቡድን ተመሠረተ። እንዲያውም አንዳንዶቹ በአገልግሎት አብረውን ይካፈሉ ነበር።

“ችሎታሽን ማዳበርሽን ቀጥይ”

በአውራንጋባድ ሁለት ዓመት ተኩል ካገለገልን በኋላ እንደገና በቦምቤይ ተመደብን። ኤልዛቤት በስብከቱ ሥራ መካፈሏን የቀጠለች ሲሆን እኔ ደግሞ አባቴን በትርጉም ሥራ እንዳግዝ ተጠየቅሁ፤ በዚያን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ወደ ካናዳ ቋንቋ የሚተረጉመው አባቴ ብቻ ነበር። አባቴ በጉባኤ ውስጥ በርካታ ኃላፊነቶች ስለነበሩት እኔ በመምጣቴ ደስ አለው።

በ1966 ወላጆቼ በዩዱፒ ወደሚገኘው የቀድሞ መኖሪያችን ለመመለስ ወሰኑ። አባባ ቦምቤይን ለቅቆ ሲሄድ እንዲህ አለኝ፦ “ልጄ፣ ችሎታሽን ማዳበርሽን ቀጥይ። ግልጽና ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ ተርጉሚ። ከልክ በላይ በራስሽ አትተማመኚ፤ ምንጊዜም ትሑት ሁኚ። እንዲሁም በይሖዋ ታመኚ።” አባቴ የሰጠኝ የመጨረሻ ምክር ይሄ ነበር፤ ወላጆቼ ወደ ዩዱፒ ከተመለሱ ብዙም ሳይቆይ አባቴ በሞት አንቀላፋ። ዛሬም ቢሆን በትርጉም ሥራዬ ላይ የአባቴን ምክር በተግባር ለማዋል ጥረት አደርጋለሁ።

“ቤተሰብ መመሥረት አትፈልጊም?”

በሕንድ ባሕል ውስጥ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ገና ወጣት እያሉ የትዳር ጓደኛ የሚያመጡላቸው ሲሆን ልጆች እንዲወልዱም ያበረታቷቸዋል። በዚህም ምክንያት ብዙ ጊዜ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ይቀርቡልኛል፦ “ቤተሰብ መመሥረት አትፈልጊም? ስታረጂ ማን ይጦርሻል? ብቸኝነት አይሰማሽም?”

እንዲህ ዓይነት አስተያየቶች ሲደጋገሙብኝ አንዳንድ ጊዜ ጭንቅ ይለኛል። ከሰዎች ጋር ስሆን ስሜቴን አውጥቼ ባልናገርም ብቻዬን የመሆን አጋጣሚ ሳገኝ ለይሖዋ የልቤን ግልጥልጥ አድርጌ እነግረዋለሁ። ይሖዋ፣ ነጠላ በመሆኔ የጎደለኝ ነገር እንዳለ አድርጎ እንደማይመለከተኝ ማወቄ ያጽናናኛል። ልቤ ሳይከፋፈል ይሖዋን ለማገልገል ያደረግሁትን ውሳኔ ለማጠናከር ስል ስለ ዮፍታሔ ልጅ እንዲሁም ስለ ኢየሱስ አስባለሁ፤ ሁለቱም ሳያገቡ በመኖር የአምላክን ፈቃድ በመፈጸሙ ሥራ ተጠምደው ነበር።​—ዮሐንስ 4:34

ከይሖዋ ያገኘሁት ስጦታ

እኔና ኤልዛቤት ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት የቅርብ ጓደኛሞች ሆነን ኖረናል። ኤልዛቤት በ2005 በ98 ዓመቷ አረፈች። በዕድሜዋ መገባደጃ አካባቢ ዓይኗ ስለደከመ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ባትችልም በቀኑ ውስጥ አብዛኛውን ሰዓት ለአምላክ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ታሳልፍ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ክፍሏ ውስጥ ሆና ስታወራ ከአንድ ሰው ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት የምታደርግ ይመስላል፤ እሷ ግን ከይሖዋ ጋር በጸሎት እየተነጋገረች ነው። ይሖዋ ለእሷ እውን የነበረ ሲሆን ይህም በአኗኗሯ በግልጽ ይታያል። እኔም ልክ እንደ ዮፍታሔ ሴት ልጅ በአምላክ አገልግሎት ለመጽናት ቁልፉ ይህ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ይሖዋ፣ ወጣት በነበርኩበት ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙኝ የምታሠለጥነኝ ብሎም የምታበረታታኝ በዕድሜ የምትበልጠኝ የጎለመሰች እህት ስለሰጠኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ።​—መክብብ 4:9, 10

ልክ እንደ ዮፍታሔ ልጅ በነጠላነት ይሖዋን በማገልገሌ ምንኛ ተባርኬያለሁ! ሳላገባ መኖሬና የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተሌ ‘ልቤ ሳይከፈል ዘወትር ጌታን ለማገልገል’ እንዲሁም አስደሳችና የሚክስ ሕይወት ለመምራት አስችሎኛል።​—1 ቆሮንቶስ 7:35

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አባቴ በ1950ዎቹ ዓመታት በቦምቤይ የሕዝብ ንግግር ሲያቀርብ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከመሞቷ ትንሽ ቀደም ብሎ ከኤልዛቤት ጋር

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1960 በቦምቤይ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ስናስተዋውቅ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በትርጉም ቢሯችን ውስጥ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር